የዓለም ዕድገት መሠረቱ ዕውቀት እንደሆነ አይጠረጠርም። የእውቀት መገኛ ማዕዱ ደግሞ ትምህርት ነው። ትምህርት በመደበኛና በኢመደበኛ መንገድ የሚቀሰም፤ የሚጠራቀምና መልሶ ጥቅም ላይ የሚውል መንፈሳዊ ሀብት ነው። ይህ ሀብት ግለሰባዊ ይሁን እንጂ በአንድ በኩል ራስን ሲያበለፅግ በሌላ በኩል ከራሥ ተርፎ ለሌሎችና ለአገርም ይካፈላል።
የአንድ ሀገር መደበኛ ትምህርት ሥርዓተ ትምህርት ተቀርፆለት፤ የመማሪያ ቦታ ተወስኖለት፤ መማሪያና ማስተማሪያ ተዘጋጅቶለት በዘርፍና በየትምህርት ዓይነቱ ዕውቀት በቀሰሙና ለማስተማር በሰለጠኑ ባለሙያዎች የሚሰጥ ነው። የእኛም ሀገር ሁኔታ ከዚህ የተለየ አይደለም። የመደበኛ ትምህርት የሚሰጥባቸው መንገዶችም እንደተማሪዎቹ ሁኔታ፤ አቅምና ፍላጎት ተመስርተው የሚመቻቹ ወይም በአስገዳጅ ሁኔታ የሚተገበሩ ናቸው።
በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ የትምህርት አሰጣጥ ደረጃ የአንደኛ፤ የሁለተኛ እና የከፍተኛ ተብሎ በሦስት እርከኖች የተከፈለ ነው። በነዚህ ደረጃዎች ማጠቃለያና ወደሚቀጥለው ደረጃ የመጨረሻ ክፍል ሲደረስ ደግሞ አገር አቀፍ ፈተናዎች ይዘጋጃሉ። እያንዳንዱ ተማሪ ባለበት ደረጃ የመጨረሻ ክፍል ውስጥ የሚገኝ፤ ማለትም በአንደኛ ደረጃ የስምንተኛ፤ በሁለተኛ ደረጃ አስረኛ ክፍል፤ በከፍተኛ ትምህርት መሰናዶ አስራ ሁለተኛ ክፍል የደረሰ ተማሪ ተገቢውን አገር አቀፍ ፈተና የመፈተን ግዴታ አለበት።
አሁን አሁን ይኸ በአሠራር ብቻ ተወስኖ የቀረ ይመስላል። በመዲናዋም ሆነ በአገሪቱ ሁሉም አካባቢዎቸ ለአገር አቀፍ ፈተና የሚቀመጡ ተማሪዎች የሚያስጨንቋቸው በክፍል ውስጥ ከሸፈኗቸው የትምህርት ዓይነቶች የሚወጡ መመዘኛ ጥያቄዎች አይደሉም። ይልቁንም፤ የሚያሳስባቸው በስም ቅደም ተከተል አብረዋቸው የሚቀመጡና የሚያስኮርጇቸው ተማሪዎች ማንነት፤ አሊያም ህሊናውን ሸጦ፤ የሙያውን ክብር አዋርዶ መልስ የሚሠራላቸው “መምህር” መኖር ያለመኖሩ ጉዳይ ብቻ ነው።
በሌላ በኩል “እየሠሩ ይማሩ፤ እየተማሩ ይሥሩ” በሚል ይትባሀል በተለያዩ ምክንያቶች ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ ሥራ የተሰማሩ ዜጎች ራሳቸውን በዕውቀት አንፀው የጎደላቸውን እንዲሞሉ ሲባል ባሉበት ቦታ ሆነው የሚማሩባቸው የርቀት ትምህርትና ከሥራ ሰዓት ውጭ በአቅራቢያ በሚገኙ መደበኛ ተቋማት የሚሰጡ የማታ የትምህርት መርሐ ግብሮች በትክክል ዕውቀት ተጠምተው፤ ግን ደግሞ የመማር ዕድል ላጡ ዜጎች አይነተኛ መጠቀሚያ መንገዶች ሆነዋል።
በአንፃሩ፤ ጊዜአቸውን በአላስፈላጊ ቦታ ማሳለፍ የሰለቻቸው፤ ወይም እኩዮቻቸው ሲያደርጉ ተመልክተው “ከማን አንሼ” የተሰማቸው፤ አሊያም የሥራ ቆይታ እድሜአቸውን በወረቀት መደገፍና ክፍያቸውን ማሳደግ የሚፈልጉ፤ ግን ለትምህርቱ አቅምም ፍላጎትም የሌላቸው አያሌዎች ያለአግባብ በዚህ መስመር ተጠቃሚዎቸ ናቸው።
እንደነዚህ ዓይነቶቹ የርቀት ትምህርት ወይም የማታ ክፍለ ጊዜ ተማሪዎች ቀድሞም ዓላማቸው ክፍልና ጊዜ ቆጥሮ ወረቀት የማግኘት፤ ባገኙት ሰርተፊኬት፤ ዲፕሎማ ወይም ዲግሪ የሥራ ዕድልና እድገት፤ እንዲሁም ተያያዥ ጥቅም ማፍራት እንጂ ዕውቀት መገብየት አይደለምና ትኩረታቸውም በመማሩ ላይ ሳይሆን በመጨረሱና ወረቀት በመያዙ ላይ ይሆናል።
ይህንን ለማሳካትና ለመጨረስ ደግሞ ከሚያስተምራቸው መምህር ይልቅ ጥያቄ የሚሰጣቸውን ወይም መልስ የሚሠራላቸውን ሲመርጡ፤ አንዳንዴም በጥቅም ሲደልሉ ይስተዋላሉ። ከዚሁ ባልራቀ መንገድ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተመርቆ የሙያውን ክብርና ግዴታ ሳይረዳ በመምህርነት የተቀላቀለ አንዳንዱ ዋልጌም የነዚህ አካላት ሰለባ ይሆንና በክፍል ዕውቀት ብሎ ላስተማረው ትምህርት መመዘኛ ያዘጋጀውን ፈተና ለጥቅም አሳልፎ ይሰጣል።
ይህ ሀቅ በሙሉም ባይሆን ያገራችን ትምህርት ይዘትና ጥራት እያሽቆለቆለ ከመጣባቸው፤ ያወቀ ሳይሆን ወረቀት ያለው ወደክብርና ዝና ከሚወጣባቸው መንገዶች አንዱና ዋነኛው ነው ማለት ይቻላል። እናም ይህ የሆነ ለታ አገር ወደአዘቅት ወደቀች። የትምህርት ጥራት አሽቆልቁሎ በከፍተኛ ጥረትና ትግል ይገኝ የነበረው የኮሌጅ ዲፕሎማና የዩኒቨርሲቲ ዲግሪ እንደሸቀጥ በየመደብሩና በየ“ተቋሙ” መቸብቸብ ያዘ።
ትውልዱም ሁሉ ባይሆን፤ ወረቀት ገዝቶ ወይም የጥናት ወረቀት አሠርቶ በአቋራጭ ዲፕሎማና ዲግሪ ለማግኘት ጓጓ። በተግባርም አሳየው ከዚህም ጋር ተያይዞ ምግባርና ሞራል እንጦሮጦስ ወረዱ።
ለዚህ ነው በአሁኑ ወቅት በየመሥሪያ ቤቱ ማስታወቂያ ሰሌዳ ላይና በየመገናኛ ብዙሃኑ ስለተሳሳተ ወይም ያለአግባብ ስለተያዘ የትምህርት ማስረጃና እርሱን ተጠቅሞ ሥራና ዕድገት ስለማግኘት ማውራት የተዘወተረው፤ እንዲህ ያደረጉ በራሳቸው ወይም በሚያውቋቸው እንዲጋለጡ የሚወተወተው። ከዚህ በላይ እንደ ሀገር የሚያሸማቅቅ፤ አንገት የሚያስደፋ አሳፋሪ ጉዳይ የለም። እንዲህ ያለ ለራስ የዋሸ አዕምሮ ለአገር የሚፈይደው አንዳች ነገር ይኖራል ብሎ መናገር የዋህነት ነው። መገመትም አይቻልም። እናም ከወዲሁ ሃይ ሊባል ይገባል።
በመሆኑም፤ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አንስቶ በየደረጃው የሚገኙ ትምህርት ቤቶችና የትምህርቱ ሥራ የሚመለከታቸው አካላት በመደበኛ፤ በርቀትና በማታ ክፍለ ጊዜ የሚሰጡ መርሐ ግብሮች በእውነት በታለመላቸው አቅጣጫ፤ በተቀረፀላቸው አሠራር እየተተገበሩ ስለመሆናቸው ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
በየደረጃው የተመደቡና በተለያየ የትምህርት ዓይነት ተመርቀው በሙያው የሚያገለግሉ መምህራንም፤ አንድም ራሳቸው የሙያውን ክብር ከሚያረክስ ሥራ እንዲታቀቡ፤ እልፍ ሲልም በዚህ ሥራ ላይ ተሰማርተው በይፋም ይሁን በድብቅ የመምህርነትን ሙያና ክብር የሚያንኳስሱ ባልደረቦቻቸውን ፈተና ከመሸጥ፤ የፈተና መልስ ከመስጠትና የሌሎችን ፈተና ከመሥራት አሳፋሪ ድርጊት እንዲቆጠቡ ማስተማር ይጠበቅባቸዋል።
በአጠቃላይ በየደረጃው ባሉ የትምህርት ተቋማትና የመማር ማስተማር መርሐ ግብሮች ውስጥ በአግባቡ ተምሮ፤ አስፈላጊውን ጊዜ ሸፍኖ፤ ተፈትኖና በራሱ ጥረት የችሎታውን ውጤት የሚያመጣ፤ በጎደለው ለመሙላት የሚጥርና በሥነ ምግባር ታንፆ ለህሊናው የሚያድር ዜጋ ለመፍጠር ሁሉም የድርሻውን መወጣት ይገባዋል።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 10/2011