የአንድ አገር ውስጥ የሥራ አጥ ቁጥር እያሻቀበ መሄድ ለመንግሥት ትልቅ ፈተና እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ።በሌላ መልኩ ደግሞ ይህን የሥራ አጥ ቁጥር ሥራ ለማስያዝ መንግሥት የሚያመጣቸው አዳዲስ አሠራሮች እና ዘዴዎች ወይም እቅዶች ለመንግሥትነቱ ዕድሜ አስተማማኝ ዋስትና ትኬት መቁረጫ ተደርገውም ይወሰዳሉ።በአገራችን ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የሥራ ዕድል ለመፍጠር የተሰሩ ሥራዎች ቢኖሩም ሰፊውን ሥራ አጥ ባለ ሥራ የማድረጉ ጉዳይ አለመሳካት መንግሥትን የፈተነና ሥርዓት እስከመቀየር የተገዳደረ ጉዳይ ጭምር ነው፡፡
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 11 ሚሊዮን ሥራ ፈላጊ ወጣቶች የሚገኙ ሲሆን በየዓመቱ ከ2 እስከ 3 ሚሊዮን የሚጠጉ ወጣቶች ሥራ ፈላጊውን የዕድሜ ክልል ይቀላቀላሉ። በመሆኑም መንግሥት ይህን ሥራ አጥ ቁጥር ትርጉም ባለው መልኩና በዘላቂነት ሥራ ለማስያዝ የተለያዩ እቅዶችን ይፋ አድርጓል።በዚህም በመጪው 2012 ዓ.ም ብቻ ሊፈጠር ከታሰበው 3 ሚሊዮን ሥራ ውስጥ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በጊዜያዊነት እና 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ደግሞ በቋሚነት ይገኝበታል።ለዚህም ስኬታማነት የሥራ ዕድል የሚፈጥር የሠራተኛ እና ኢንቨስትመንት ኮሚቴ ተቋቁሟል።በኮሚቴው ስርም ሦስት ዓይነት ንዑሳን ኮሚቴዎች ተቋቁመዋል።በዚህ ኮሚቴ ውስጥ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች እና የከተማ አስተዳደሮች መካተታቸው ለጉዳዩ የተሰጠውን ክብደት ያመላከተ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በአዲሱ ዓመት የሚፈጠሩ ሥራዎችን በስም ሳይቀር በመዘርዘር ለምክር ቤቱ ሪፖርት እንደሚያቀርቡ ቃል ገብተዋል።ለዚህ ዓላማ የሚውል 3 ቢሊዮን ብር ድጋፍ ከውጭ መገኘቱም ታውቋል።በመሆኑም የ2012 በጀት ዓመት ዕድገት የሚለካው ሰውን ሥራ በማስያዝ ነው ሲሉ የገለፁበት መልዕክት ለዘርፉ ለሥራ ዕድል ፈጠራ የተሰጠውን ትኩረት ያመላከተ ነበር።«ዘላቂ እና አስተማማኝ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ደግሞ የግሉ ዘርፍ ያለውን አቅም አሟጠን እንጠቀማለን» ብለዋል፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
የግል ባለሀብቱ በሥራ ዕድል ፈጠራ የሚሰማራበት እና እንዲሳተፍ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች ውስጥ ቱሪዝም፣ የማዕድን ዘርፍ እና የግብርና ዘርፎች በዋናነት ይጠቀሳሉ።በእነዚህ አብይ ዘርፎች ውስጥ ሊፈጠር የታሰበው የሥራ ዕድል በጥቅሉ ሦስት ሚሊዮን ሲሆን አብሮ ሊታሰቡ የሚገባቸው ትላልቅ ጉዳዮችን በትኩረት መስራት ለታለመው ዓላማ መሳካት ትልቅ ሚና አላቸው።
የአገሪቱ የሰላም ሁኔታ በተለይ ደግሞ ሙስናና የተንዛዙ የቢሮክራሲ አሠራሮች በፍጥነት ሊስተካከሉ የሚገባቸው ጉዳዮች ናቸው።የግል ባለሀብቱ በሚሰማራበት የሥራ መስክ ስኬታማ መሆን አለመሆኑ ሰላም ትልቅ ዋጋ አለው።በተለይ ደግሞ በቱሪዝም ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ቱሪስቱ በደረሰበት ቦታ ሁሉ ሰላም ካጋጠመው በድንኳንም አድሮ ስኬታማ እንቅስቃሴ ያደርጋል። በማዕድን ዘርፉም ቢሆን እንደ ቱሪዝም ዘርፉ ሰላም መስፈኑ የቅድሚያ ቅድሚያ ሊሆን ይገባል፡፡
ባለሀብቱ ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ከሚያስችለው ቁልፍ ድጋፍ ውስጥ የተመቻቸ የብድር አቅርቦት፣ ማን በምን ዘርፍ ላይ ቢሰማራ ራሱን ጠቅሞ ሰፊ የሥራ ዕድል ይፈጠራል በሚለው ላይ በቂ መረጃ ማቅረብ፤ ምቹ የገበያ ትስስር ማመቻቸት እና ተቋማዊ አሠራርን ግልፅነት ባለው መልኩ ማስተካከል እና ሌሎች ተያያዥ ሥራዎችን በመስራት ለባለሀብቱ ምቹ ሁኔታ መፍጠር የመንግሥት ቁልፍ የቤት ሥራ መሆኑ ሊታሰብበት ይገባል፤ ለተቋቋመው ኮሚቴም ሆነ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች መለኪያቸው ሆኖ መወሰድ ይገባዋል።
ከተመረጡ ዘርፎች ጋር በተያያዘ መታየት የሚገባቸው በተለይ በጥናት ሊመለሱ የሚገባቸው ጉዳዮች ውስጥ ዋና ዋናዎቹን መጠቆም ይበጃል። እያንዳንዱ የሥራ ዘርፍ ለምሳሌ አይሲቲ እና የማዕድን ዘርፉ ብዙ የገንዘብ ሀብት የሚጠይቅ ሆኖ ሳለ ሊፈጥር የሚችለው የሥራ ዕድል ግን ምን ያህል ነው የሚለው በሚገባ መልስ ሊያገኝ ይገባል።ይህ ከሀብት አጠቃቀምና ከሥራ ዕድል ፈጠራ ምጣኔ አኳያ በግልፅ ጥናት ላይ ተመስርቶ ምላሽ ሊሰጠው ግድ ይላል፤ ይህም የመንግሥት የቤት ሥራ ይሆናል፡፡
በመጪው አዲስ ዓመት ሦስት ሚሊዮን የሥራ ዕድል በአንድ ጊዜ ለመፍጠር መታቀዱ ይበል የሚያስብል ጉዳይ ነው።ይሁን እንጂ ይህን ያህል ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ወደ ኢኮኖሚው የሚለቀቀው ከፍተኛ የገንዘብ መጠን ገበያ ውስጥ በሚገባበት ወቅት ግለት ፈጥሮ የዋጋ ግሽበት እንዳያስከትል በትኩረት ክትትል ሊደረግበት ይገባል፡፡
በአጠቃላይ በሥራ ዕድል ፈጠራው መስክ የተያዘው የተቀደሰ እቅድ በተለይ ደግሞ ባለሀብቱን በስፋት የማሳተፍ እና አቅምን አሟጦ የመጠቀም ሁኔታ ለአገራዊ እድገቱም ጭምር ትልቅ አስተዋፅኦ አለው።ይህን ለማሳካት ደግሞ የግሉ ዘርፍና መንግሥት በቅርበት የሚሰሩበትን አዲስ የግንኙነት ሥርዓት መዘርጋት አለበት። በተለይ የግል ባለሀብቱ ማነቆ ሆነው የቆዩ ሙስና፣ ቢሮክራሲው እና የኢንቨስተሮች አጋዥ ማጣት ችግሮችን በዘላቂነት እና በተደራጀ መልኩ በመፍታት የሥራ ዕድል ፈጠራውን በማሳካት አገሪቱን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ማሸጋገር ይገባል።በዚህም ታሪካዊ ተልዕኮ መንግሥትና ባለሀብቱ የሚፈተኑበት ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን ነሀሴ 9/2011