ሰሞኑን ወደ መገናኛ አካባቢ የሚወስደኝ ጉዳይ ነበረኝ፡፡ መገናኛ… ቦሌ ክፍለ ከተማ ግርጌ የተለመደ ገበያ ጦፏል፡፡ የዘመን መለወጫ መቃረብን አስመልክቶ ሕዝቤ ለሸመታ ነቅሎ ሳይወጣ አልቀረም::
ልባሽ ጨርቅ (በተለምዶ አጠራር – ሰልቫጅ) እንደ ጉድ ይቸበቸባል፡፡ (ነጋዴዎችም ዘና ብለው የሚሰሩት የከተማ አስተዳደሩ ባመቻቸላቸው ቦታ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡) ይህን በኮንትሮባንድ የገባ ልባሽ ጨርቅ መሸጥም ሆነ መግዛት በሕግ እንደሚያስጠይቅ እንኳንስ ነዋሪው የከተማው አስተዳደርም ጭምር ስለማወቁ እንጃ፡፡
ከዚህ ሥፍራ በቅርብ ርቀት የሚገኘው የገቢዎች ሚኒስቴርም ደጃፉ ላይ እየሆነ ያለውን ነገር ልብ ያለው አይመስልም፡፡ ንግዱ የጦፈው በመገናኛ አካባቢ ብቻ አይደለም፤ በሲኤምሲ፣ በአራት ኪሎ፣ በስድስት ኪሎ፣ በሽሮሜዳ፣ በኮልፌ፣ በአውቶቡስ ተራ፣ በመርካቶ፣ በቂርቆስ፣ በቄራ፣ በለገሃር፣ በሳሪስ … በድፍን የአዲ ስአበባ ጥጋጥግ ነው፡፡
በክልሎችም ከዚህ የተለየ ነገር የለም፡፡ ምን ይህ ብቻ፤ መርካቶን ጨምሮ በከተማዋ ውስጥ ባሉ ትላልቅ የንግድ ማዕከላት ሕጋዊ ነጋዴዎች ከሚሸጡት ዋጋ ባነሰ፤ በኮንትሮባንድ የገቡ እቃዎችን መገበያየት ነውርነቱ ከቀረ ብዙ ዓመታት ነጉደዋል፡፡ የሚገርመው ሕጋዊ ነጋዴዎችና ሕገወጦቹ (ኮንትሮባንድ ነጋዴዎች) አንዳንዴ ሱቆቻቸውን ጎን ለጎን ጭምር ማግኘት እምብዛም እንግዳ ነገር አለመሆኑ ነው፡፡
መንግሥት ግን መሀል ከተማ ላይ በግላጭ፣ በአደባባይ ከሚቸረችረው የኮንትሮባንድ ሸቀጥ ይልቅ የጠረፍ ኬላዎች ላይ የሙጢኝ ያለበት ሚስጢር አልገለጥ ብሏል፡፡ ነገሩ ችግሩን ከምንጩ እናድርቀው ቢመስልም ስኬቱ ግን መራቁ ዘንድሮም ለሰሚው ግራ ሆኗል፡፡ እናም የቁጥጥር ሥራው ከዓመት ዓመት አመርቂ ውጤት አለማሳየቱ የተቀደደ በርሜልን እንደ መሙላት መመሰል ይቻላል፡፡
ምክትል ጠ/ሚኒስትር ደመቀ መኮንንና የገቢዎች ሚኒስትሯ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ኮንትሮባንድና ሕገ ወጥ ንግድ አሁንም ትልቅ ፈተና መሆናቸውን ሰሞኑን በአንድ መድረክ ላይ ሲናገሩ የበርሜሉ ሽንቁር ቀዳዳ እየሰፋ መምጣቱን በቀጥታ መጠቆማቸው ነበር፡፡ በእርግጥም የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ከገቢ ባሻገር የሉአላዊነት ጉዳይ እየሆነ መምጣቱንና ችግሩን ለመቅረፍ በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላትን ቅንጅትና ቁርጠኛ ውሳኔ የሚጠይቅ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለውን ሁለንተናዊ ለውጥ ቀጣይ ለማድረግ መንግሥት በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ቢገኝም ኮንትሮባንድና ሕገወጥ ንግድ አሁንም ትልቅ ፈተና መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ሲናገሩ፤ የገቢዎች ሚኒስትሯ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው በ2011 ዓ.ም የሥራ ዘመን ኮንትሮባንድና ሕገ-ወጥ ንግድን ለመከላከል በርካታ ሥራዎች የተሠሩ ቢሆንም አሁንም ችግሩ እንዳልተቀረፈ አምነዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኮንትሮባንድ የሚያስከትለውን ኋላቀርነትና ብልሹ አሰራርን ለመታገል እስከ ቀበሌ መዋቅር ያለን አመራሮች የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡ለዚህም ግልፅ በሆነ ሥርዓት የሚመራ መዋቅር ሊኖር እንደሚገባ መናገራቸው ተሰምቷል፡፡
ጥቂት ነጥቦች ስለኮንትሮባንድ ምንነት
“ኮንትሮባንድ” የሚለው ቃል የተከለከሉ ነገሮችን ይዞ መገኘት ወይም መግዛትን የሚያመለክት ነው፡፡ የቃሉ ትርጉም የአንድን ሀገር ሕግ በሚቃረን መልኩ ዕቃዎችን ከማስወጣትና ማስገባት ጋር እንዲሁም የተከለከሉ ነገሮችን ከማምረትና ባለቤት ከመሆን ጋር በቀጥታ ይገናኛል፡፡
ከጉምሩክ ሕግጋት አኳያም ሲታይ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የጉምሩክ ሕጎችን በመተላለፍ የተከለከሉ፣ ገደብ የተደረገባቸውን ወይንም የንግድ መጠን ያላቸውን የጉምሩክ ሥነሥርዓት ያልተፈጸመባቸውን ዕቃዎች በድብቅ ወይንም ከሕጋዊ መተላለፊያ መስመሩ ውጪ ወደአገር ማስገባት፣ ከሀገር ማስወጣት ወይንም በሕጋዊ መንገድ የወጡ ዕቃዎችን ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ መልሶ ማስገባት የኮንትሮባንድ ወንጀል ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን ማጓጓዝ፣ ማከማቸት፣ መያዝ፣ ለሽያጭ ማቅረብ ወይንም መግዛትንም ያጠቃልላል፡፡
ወደ ሀገር ውስጥ ሊገቡ ሲሉ ከሚያዙት ዕቃዎች መካከል የኤሌክትሮኒክስና የኤሌክትሪክ ዕቃዎች፣ ልዩ ልዩ አልባሳት፣ ሽቶዎች፣ መዋቢያዎች፣ ወሲብ ቀስቃሽ ፊልሞች፣ ደህንነታቸውና ፈዋሽነታቸው ያልተረጋገጡ መድሃኒቶች፣ አደንዛዥ እጾች፣ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ ሕገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር… ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ዕቃዎች በሱዳን፣ በኤርትራ፣ ኬንያ፣ ጅቡቲ፣ በኩል የሚገቡ ናቸው፡፡
ከሀገር ውስጥ ወደ ውጭ ሀገር በኮንትሮባንድ መልክ ከሚወጡት ሸቀጦች መካከል ቡና፣ የቁም እንስሳት፣ የእንስሳት ቆዳ፣ አልበሳት፣ ሲጋራ፣ ማዕድን፣ ጥራጥሬ፣ ጫት፣ ጤፍ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ስኳር፣ ዘይት፣ ነዳጅና መሰል ዕቃዎች ይገኙበታል፡፡
ለኮንትሮባንድ ንግድ መስፋፋት በርካታ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ፡፡ ለመንግስት የሚከፈል ታክስ ሽሽትና በሕገወጥ ውድድር ተጠቃሚ ለመሆን መሻት ቀዳሚዎቹ ምክንያቶች ናቸው፡፡ ዕቃዎቹ ሰነዶቻቸው የሀገሪቱን ሕግና መመሪያ መሰረት ያደረጉ መሆንና አለመሆኑናቸውን ለማረጋገጥ የተቋቋሙ የጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያዎችን ሽሽትም ሌላኛው ምክንያት ነው፡፡
ድሬዳዋ፣ ጅጅጋ፣ ሐረር፣ ገዳማይቱና አዳማ የኮንትሮባንድ ንግድ የሚካሄድባቸውና የማከማቻ ማዕከላት መሆናቸው በጥናት ተለይቷል፡፡ መዲናችን አዲስ አበባ ደግሞ በሕጋዊና በህገወጥ መንገድ የገቡ ዕቃዎች እኩል ይቸበቸቡባታል፡፡
ቁጥሮች ምን ይነግሩናል?
በአሁኑ ሰዓት የኮንትሮባንድ ንግድ እጅግ መንሰራፋቱን ለመረዳት ተከታዩን ቁጥር ማስተዋል ብልህነት ነው፡፡ ባለፈው ሐምሌ ወር 2011 ዓ.ም ብቻ የ 134 ነጥብ 37 ሚሊዮን ብር ወይንም በአንድ ቀን 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ገደማ ግምት ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
በሰላሳ ቀናት ከ134 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ኮንትሮባንድ ተያዘ ሲባል ሳይያዝ የገባው ደግሞ መጠኑ ከዚህ ስንት እጥፍ ሊልቅ እንደሚችል ሲገመት አስደንጋጭነቱ ወለል ብሎ ይታየናል፡፡
በአጠቃላይ ባሳለፍነው 2011 በጀት ዓመት 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ግምት ያላቸው ኮንትሮባንድ ዕቃዎችና ሕገወጥ ገንዘብ በቁጥጥር ስር መዋሉ ታውቋል፡፡ ከዚህ ውስጥ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን የገቢ ንግድ ኮንትሮባንድ ዕቃዎችና የገንዘብ ዝውውር ሲሆን፤ 334 ነጥብ 8 ሚሊዮን የወጪ ኮንትሮባንድና ሕገወጥ ገንዘብ ዝውውሮች ነበሩ፡፡
የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በመጠን ከፍ ያሉት አልባሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ምግብና መጠጥ ሲሆኑ፤በብዛት የተያዙባቸው ኬላዎች በቅደም ተከተል ሲቀመጡ አዲስ አበባ ኤርፖርት፣ ሐዋሳና ጅጅጋ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡
ቁጥጥሩ ለምን ላላ?
የገቢዎች ሚኒስቴር በህዳር ወር 2011 ዓ.ም የኮንትሮባንድና ህገ-ወጥ ንግድ ጉዳትና የመከላከል ቀጣይ አቅጣጫዎች በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክክር አካሂዶ ነበር፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት ተሳታፊዎች እንደገለጹት፤ የገቢዎች ሚኒስቴር፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የንግድ ሚኒስቴር እንዲሁም መሰል ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ባለመሥራታቸው የኮንትሮባንድ መከላከልና ቁጥጥሩን የላላ አድርጎታል፡፡
የእነዚህ ተቋማት አለመናበብ ኮንትሮባንዲስቶች ህገ-ወጥ ኤሌክትሮኒክስ፣ አደንዛዥ ዕፅ፣ ሲጋራና የትንባሆ ውጤቶች፣ የተበላሸ ምግብና መጠጥ እንዲሁም የጦር መሳሪያ ወደ ሀገር ውስጥ የሚያስገቡ ሲሆን፤ ህገ-ወጥ ገንዘብ፣ እህል፣ የቁም እንስሳት፣ ነዳጅና ጫት ወደ ውጭ ሀገር እንደሚልኩ እየታወቀ አስተማሪ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ብር ያለው በመደራደር በጥቁር አስፋልት ለፖሊሶች ሰላምታ እያቀረበ ሲያልፍ ብር የሌለው የሚያዝበት ሁኔታ እንዳለ በውይይቱ ላይ ተገልጿል፡፡
ከዚህ ባለፈ ኬላዎች የተጠናከሩ አለመሆን እንዲሁም ህብረተሰቡ ለኮንትሮባንድ ያለው የተዛባ አመለካከት ኮንትሮባንድን እያባባሱት ይገኛሉ፡፡በተለይ መንግሥት መሠረታዊ ፍጆታን ለመደገፍ ለልማት ይውል የነበረውን ገቢ ለህዝብ ሲል በመተው ከታክስ ነፃ የሚያስገባውን ፍራንኮቫሉታ (ዘይት፣ ስኳር፣) ለህብረተሰቡ የታለመለት ዓላማ ሳይደርስ ጥናት ሳይደረግ ፈቃድ የተሰጣቸው አንዳንድ ራስ ወዳድ ግለሰቦች መበልጸጊያ እየሆነ ነው፡፡
ይህም በመሆኑ ተዋደንና ተፋቅረን በምንኖር ህብረተሰብ መካከል ፀብ እንዲፈጠር ምክንያት እየሆነ በመምጣቱ መላ ሊዘየድለት እንደሚገባ ተሳታፊዎች ጥያቄያቸውን ለተቋማቱ ከፍተኛ አመራሮች ማቅረባቸው ተዘግቧል፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ከፍተኛ አመራሮች እንደገለጹት፤ ሀገራችን በለውጥ ጎዳና ላይ በመሆኗ ይህንን ለማስቀጠል ኮንትሮባንዲስቶችን በመግታት ፍትሃዊ የሆነ የንግድ ሥርዓት ሊኖር ይገባል ብለዋል::
ይህን ለማድረግ እስካሁን አሠራራችንን እየገመገምን አስተዳደራዊ እርምጃ እየወሰድን የሠራናቸው መልካም ተሞክሮዎች ቢኖሩም በተሳታፊዎች የተነሱትን ችግሮች ክብደት በደንብ ዓይተን በጋራ መሥራት ተገቢ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ህብረተሰቡ ህጋዊነትን ሊደግፍ እንደሚገባ ምክትል ኮሚሽነሩ አሳስበዋል፡፡
የንግድ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎችም አሁን ያለው ሀገራዊ ለውጥና የህግ የበላይነት የማይመቻቸው ኮንትሮባንዲስቶች ይኖራሉ ብለዋል፡፡ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወደ ሀገር የሚገባውን ነዳጅ ወደ ውጭ የሚልኩ፤ እንዲሁም የፍራንኮቫሉታ ፍቃዳቸውን ለህገ-ወጥ ድርጊት የሚጠቀሙበት ኮንትሮባንዲስቶችን ለማጋለጥ ሁሉም ባለቤት ሆኖ ተቀናጅቶ መሥራት እንዳለበት አመላክተዋል፡፡
የገቢዎች ሚኒስትር ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፤ ገቢና ወጪ ኮንትሮባንድ መብዛቱ የሀገር ህልውና አደጋ ላይ መሆኑን የሚያመላክት እንደሆነ ተናግረዋል:: እየተወሳሰበ የመጣውን ችግር ለመቋቋም የሚያስችል ህግና አደረጃጀት አለመኖር ሳይሆን ወደ ተግባር ስለማይቀየር ቢሆንም ከዚህ በላይ ዕድሜ እንዲኖረው መፍቀድ የለብንም፡፡
አሁን ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ ተጠናክረን ህብረተሰቡን ከጎናችን አሰልፈን ለውጥ የምናመጣበት ጊዜ ነው:: ስለዚህ ችግሮችን በየደረጃው ተረድተን በምስራቅ ኢትዮጵያ በሃይማኖትና በባህል ተሳስሮ በፍቅርና በአንድነት የሚኖረውን ህዝብ እስከማለያየትና ማጋጨት የደረሰውን ኮንትሮባንድ ለነገ ሳይባል እንዲሁም እንደተደራቢ ሥራ ሳይሆን በቋሚነት ሊሠራ ይገባል፡፡ ለኮንትሮባንድ ክፍተት የሆነውን ሁሉ ለመድፈን ኬላዎችን በማጠናከር የሌብነት መረብን ለመበጣጠስ ሁሉም የየበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ ሚኒስትሯ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
እንደማጠቃለያ
ኮንትሮባንድ ጥቂቶች የሚከብሩበትና ብዙሃኑ ሕጋዊ ነጋዴ አጨብጭቦ የሚቀርበት ሕገወጥ የንግድ ሥርዓት ነው፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ እንደከዚህ ቀደሙ ኮሚቴ አቋቁሞ በዘመቻ የመከላከል ሥራውን ለማስኬድ መሞከር የተሟላ መፍትሔ የማምጣቱ ነገር አጠራጣሪ ነው፡፡
እንደማይተማመን ባልንጀራ በየወንዙ እየተማማሉ ኮንትሮባንድን ያህል የሀገር ነቀርሳ ለመዋጋት ማሰብ የበዛ የዋህነት ይሆናል፡፡ ይልቅስ ከዚህ በፊት በሥራ ላይ የነበረውን ኮሚቴ ለምን ውጤታማ ሊሆን አልቻለም? ብለን እንጠይቅ፣ ለምን ቅንጅት አነሰው? ብለን እንመርምር፣ ስለቀጣዩ ከመወሰን በፊት ሳይንሳዊ ጥናት ይቅደም፡፡
ቁጥጥሩ በጠረፍ ብቻ ሳይሆን ወደሀገር ውስጥ ዘልቀው ገብተው በየመደብሩ፣ በየጎዳናውና በየሜዳው የሚሸጡ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን ወደማስቆም ካልተሸጋገረ መፍትሔው ግማሽ መሆኑ ሊካድ አይችልም፡፡ ከምንም በላይ ከኮንትሮባንድ ንግድ ጀርባ ያሉ የመንግሥት ሌቦች ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃ የማይወሰድ ከሆነ የኮንትሮባንድ ቁጥጥር የሚያስገኘው ውጤት እንደምን ሙሉዕ ሊሆን ይችላል? ኮንትሮባንድ ላይ የሚወሰደው እርምጃ በዘገየ ቁጥር ሕጋዊ ነጋዴዎች ሳይወዱ በግድ ከንግዱ ዓለም ተገፍተው እንዲወጡ ወይንም የኮንትሮባንድ ንግድ አማራጭን እንዲያዩ በር መክፈቱ አይቀሬ ይሆናል፡፡
የካንሰር ህመምን ልብ በሉ፡፡ በወቅቱ ካወቁትና ተገቢውን የህክምና ክትትል ካደረጉለት የሚድን ወይንም መቆጣጠር የሚቻል ሕመም ሲሆን፤ በወቅቱ ክትትል ከነፈጉት ደግሞ ስር ሰድዶ እስከ ሞት የሚያደርስ ጉዳትን ያስከትላል፡፡ የኮንትሮባንድ ንግድም እንዲሁ ነው፡፡ ከባድ ጉዳት ሳያስከትል በፊት ቀድሞ ማከም ይገባል፡፡
(የጸሐፊው ማስታወሻ፡- ለዚህ ጹሑፍ ጥንቅር፡- የገቢዎች ሚኒስቴር፣ የጉምሩክ ኮሚሽን፣ የኢዜአ… ዜናና መረጃዎችን መጠቀሜን ከምስጋና ጋር እገልጻለሁ፡፡)
አዲስ ዘመን ነሃሴ 8/2011
ፍሬው አበበ