ቤተሰብ በሕግ ዓይን
ተደጋግሞ ሲነገር እንደምናደምጠው ቤተሰብ የአንድ ማህበረሰብም ሆነ የአገር መሠረት ነው። ቤተሰብ ማህበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው ማህበራዊ ውቅር ነው። በአንድ ቤተሰብ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች በስጋና በደም የተሳሰሩ በመሆናቸው ከየትኛውም የማህበረሰብ መዋቅር በላቀ ሁኔታ የጠነከረ ማህበራዊ ትስስር ያዳብራሉ። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ አክስት፣ አጎት፣ አያት እና ከዚያም ያለፈ የስጋ ዝምድና ያላቸው አባላት ሁሉ በአንድነት የሚኖሩበት ማህበረሰብ በበዛባቸው አገራት ቤተሰብ በማህበራዊ መስተጋብር ውስጥ የጎላ ሚና ይጫወታል።
የግለሰቦች የመጀመሪያ ትምህርት ቤት ቤተሰብ ነው። የግለሰቦች የማንነት መሠረት የሚታነጸው በቤተሰብ ውስጥ ነው። በቤተሰብ ውስጥ የግለሰብ ባህርይ ይቀረጻል። የቤተሰብ ጠንካራም ሆነ ደካማ አስተዋጽኦ ከግለሰቦች ሕይወት አልፎ በማህበረሰቡ ውስጥም የራሱ የሆነ ሚና አለው። በዚህ መነሻ መንግሥታት ቤተሰብ እንዴት ይመሰረታል፤ የባልና የሚስት እንዲሁም የልጆች ግንኙነት ምን መምሰል ይገባዋል፤ የቤተሰብና የንብረት ጉዳይ እንዴት ይመራል፤ ፍቺስ እንዴት ይፈጸማል ወዘተ የሚሉ የቤተሰብ ጉዳዮችን በተመለከተ ሕግ በማውጣት በቤተሰብ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ይገባሉ።
አገራችንና ሕዝቦቿም ለመንግሥትና ለሕግ እንግዳ አይደሉምና ለዘመናት ቤተሰብን በተመለከተ ሕግ በማውጣት ሲመሩበት ኖረዋል። ኋላም በ1952ቱ የፍትሐብሔር ሕግ የቤተሰብ ጉዳይ ከዋነኞቹ የሕጉ አምዶች አንዱ ሆኖ ተደንግጎ ቆይቷል። የፌዴራል ሥርዓት በተግባር ላይ ከዋለ ጊዜ ጀምሮ ደግሞ በሕገ መንግሥቱ እና አገሪቱ ተቀብላ በማጽደቅ የሕጎቿ አካል ባደረገቻቸው ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች ውስጥ ቤተሰብ ብርቱ ጥበቃ የተደረገለት ተቋም ሆኗል። በ1992 ዓ.ም. የፌዴራሉ መንግሥት የራሱን የቤተሰብ ሕግ በጥራዝ ሕግ (በኮድ) በማውጣት እስካሁንም እየሰራበት ይገኛል። ክልሎችም በሕገ መንግሥቱ በተሰጣቸው ሥልጣን መሠረት ከየራሳቸው ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር የየራሳቸውን የቤተሰብ ሕግ አውጥተዋል።
በኢትዮጵያ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ መሠረት ቤተሰብ አንድም በስጋ ዝምድና ማለትም አያት፣ አባትና እናት እንዲሁም ልጆች እየተባለ በተወላጅነት ይመሰረታል። በሌላ በኩል በጋብቻ ይመሰረታል ቤተሰብ። በጉዲፈቻም እንዲሁ። ከእነዚህ ሁሉ ታዲያ ቤተሰብ የሚመሰረትበት ዓይነተኛ መሣሪያ ጋብቻ ነው። ባልና ሚስት በትዳር ሲተሳሰሩ ሚስት የባሏ ወላጆችም ልጅ ወይም ምራት (Daughter in law) ትሆናለች፤ ባልም እንዲሁ የሚስቱ ወላጆች ልጅ ወይም አማች (Son in law) ይሆናል። በዚህ መነሻ ባልና ሚስት በሚጋቡበት ወቅት ከራሳቸው አልፈው ቤተሰቦቻቸውንም ጭምር በማጋባት የጋብቻ ዝምድና ስለሚፈጥሩ ሰፊ ማህበራዊ ትስስር ያለበት ግንኙነትን ይፈጥራሉ ማለት ነው።
ጋብቻ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ በሦስት ዓይነት መልኩ ከተከናወነ የጸና እና በሕግም ፊት ዋጋ ያለው ይሆናል። ጋብቻ በክብር መዝገብ ሹም ፊት ይፈጸማል። ይህም በአሁኑ ወቅት እንደ ልደት፣ ጋብቻ፣ ፍቺ እና ሞት ያሉትን ወሳኝ ኩነቶች በሚመዘግብ መስሪያ ቤት ውስጥ በባለሙያው ፊት ምስክሮች ባሉበት የሚፈጸም ጋብቻ ነው። ጋብቻ በምድር ላይ ከከበሩ ነገሮችም በላይ ክቡር ነገር ነውና በክብር መዝገብ ላይ በክብር ይመዘገባል።
ከዚህ ሌላ ተጋቢዎቹ በሃይማኖታቸው ወይም ከሁለቱ በአንዳቸው ሃይማኖት መሠረት የሚጸና ጋብቻ ለማቋቋም የሚያስፈልገውን ሥርዓት በመፈጸም የሃይማኖታዊ ሥርዓት ጋብቻ ይፈጽማሉ። ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች አገር ናትና አንድ ሴትና አንድ ወንድ በሚኖሩበት አካባቢ ባህል መሠረትም በሕግ የሚጸና ጋብቻ መመስረትም ይችላሉ። እነዚህ ሦስቱም የጋብቻ አፈጻጸም ሥርዓቶች በኢትዮጵያ ሕግ እኩል የሆነ እውቅናና ጥበቃ የተደረገላቸው ናቸው።
ጋብቻ ሳይፈጸም እንደባልና ሚስት አብሮ መኖር
በሕግ እውቅና ከተሰጣቸው የጋብቻ ሥርዓቶች በአንዱ ጋብቻ ሳይመሰርቱ በአንድ ጣሪያ ስር መኖር (Irregular Union) በተለይም በከተሜው ዘንድ የተለመደ ነው። እንዲህ ያለው ሁኔታ ቀደም ባሉት ጊዜያትም ቢሆን የነበረ ቢሆንም ዛሬ ዛሬ ተፈቃቅደው ከተዋደዱ ብዙም ሳይቆዩ ጎጆ ቀልሰው ሦስት ጉልቻን መስርተው የሚኖሩ ጥንዶች እጅግ በርካታ ናቸው። ሰዎች መደበኛ ጋብቻ ሳይመሰርቱ በእንዲህ ያለ ግንኙነት ውስጥ እንዲኖሩ የሚያስገድዷቸው ምክንያቶች የተለያዩ ቢሆኑም በተለይ በወጣቶች ዘንድ የሚስተዋለው የአፍላነትና የስጋ ፈቃድ (የግብረ ስጋ ፍላጎት) ዓይነተኛ የመተሳሰሪያ ገመድ ስለመሆኑ ነው የማህበራዊ ሳይንስ ልሂቃን የሚጠቁሙት።
በጉዳዩ ዙሪያ የተካሄዱ ጥናቶች ባይኖሩም በዕለት ተዕለት ከሚያጋጥሙን ሁኔታዎች እንደምንገነዘበው እጅግ በርካታ ጥንዶች በአንድ ቤት ውስጥ በሚኖሩበት ወቅት መደበኛ ጋብቻን ባይመሰርቱም ልክ ጋብቻ መስርተው የሚኖሩ ያክል ወይም ከጋብቻ ምንም በማይለይ የግንኙነት ሁኔታ ውስጥ እየኖሩ እንዳሉ አድርገው ነው በራሳቸው የሚያስቡት። ይሁንና በሕግ አንድምታ ከሦስቱ የጋብቻ መመስረቻ ሥርዓቶች በአንዱ ተጋብቶ መኖር እና ጋብቻ ሳይፈጽሙ በአንድ ላይ መኖር በጣም የተለያዩና ውጤታቸውም ለየቅል ሆኖ እናገኘዋለን።
ቀደም ባሉት ጊዜያት እንዲህ ያለው ግንኙነት በማህበረሰቡ ዘንድ የሚነቀፍና በዚህ ሁኔታ ውስጥም የተገኙ ጥንዶች መገለልና መድሎ ይደርስባቸው ነበር። ባስ ሲልም እንደ ኃጢያት የሚቆጠር አድራጎት ነበር ሳይጋቡ አብሮ መኖር። ይሁንና ማህበረሰብ እየሰለጠነና ጋብቻ ሳይፈጽሙ አብሮ መኖር ከዘመኑ ጋር ዳብሮ በስፋት እየተለመደ ሲመጣ ቅቡልነት ያለው አብሮ የመኖሪያ መንገድ ሊሆን ችሏል። (ያም ሆኖ በአሁኑ ወቅትም ቢሆን በሃይማኖት መሪዎችና አስተምህሮ ዘንድ ጋብቻ ሳይመሰርቱ እንደባልና ሚስት አብሮ መኖር አይፈቀድም) በዚህ መነሻ ይህ ዓይነቱ አብሮ የመኖር ሁኔታ በአገራችንም ሆነ በሌሎች አገራት ሕግጋት ዕውቅናና ጥበቃ የተደረገለት ሆኗል።
«ጋብቻ ሳይፈጽሙ እንደ ባልና ሚስት አብሮ መኖር» ከሚለው ስያሜው እንደምንረዳው በዚህ ግንኙነት ውስጥ ጥንዶቹ መደበኛ ጋብቻ ባይመሰርቱም የሚኖሩት ግን እንደባልና ሚስት ነው። በአንድ ጣሪያ ስር አብረው ይኖራሉ፣ ይረዳዳሉ፣ ይደጋገፋሉ፣ ቤተሰብ ይመሰርታሉ፣ ልጆችን ይወልዳሉ፣ ንብረት ያፈራሉ። ጋብቻ ባይመሰርቱም የመሰረቱት ቤተሰብ የማህበረሰብ መሠረት ነውና የሕግ ጥበቃ ያስፈልገዋል። ልጆችም ተወልደዋልና ለእነሱ ሲባል ጥንዶቹ ኃላፊነታቸው በሕግ የተሰጠ መሆን አለበት። ንብረት ማፍራታቸው አይቀሬ ስለሆነ ለዚህም ሕግ ያስፈልጋል ። ከዚህ መነሻ ነው እንግዲህ ሕግ ለዚህ ዓይነቱ ግንኙነት ዕውቅናና ጥበቃ ሊሰጥ የቻለው ማለት ነው።
ጋብቻ ሳይፈጸም እንደባልና ሚስት አብሮ መኖርና ሕጋዊ ውጤቱ
በኢትዮጵያ ጋብቻ ሳይመሰርቱ እንደባልና ሚስት አብሮ የመኖር ግንኙነት በ1952ቱ የፍትሐብሔር ሕግ እውቅናና ጥበቃ ከተሰጠው በኋላ በተሻሻለው የ1992ቱ የፌዴራል የቤተሰብ ሕግም በተመሳሳይ ዕውቅናና ጥበቃ ተደርጎለታል። ይሁንና የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ በረቂቅነቱ ለውይይት በቀረበበት ወቅት እንደባልና ሚስት አብሮ የመኖርን ግንኙነት በተመለከተ በሕግ እንዳይጸድቅ ጠንካራ ተቃውሞዎች ሲቀርቡበት እንደነበር መዛግብት ያስታውሳሉ።
በተለይም በአንድ በኩል በሕገ መንግሥቱ ዋነኛ የቤተሰብ መመስረቻ ቁልፍ ጋብቻ ሆኖ ሳለ ያለ ጋብቻ እንደ ባልና ሚስት አብሮ መኖር ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅና ስለሌለው በቤተሰብ ሕጉ ሊካተት አይገባም፤ ከዚህ ሌላ ጥንዶቹ በፈለጉ ጊዜ የሚያፈርሱት በመሆኑ የቤተሰብ ደህንነትን ስጋት ላይ የሚጥል ልጆችንም ለችግር ሴቶችንም ለጉዳት የሚዳርግ ነው የሚል ክርክር ነበር።
በተጨማሪም የተለያዩ የሃይማኖት መሪዎች ቤተሰብ የሚመሰረተው በጋብቻ እንጂ አብሮ በመኖር ባለመሆኑ እንደባልና ሚስት አብሮ መኖርን በሕግ መፍቀድ ከሃይማኖታዊና ከሞራላዊ ሕግጋት የሚያፈነግጥ ማህበረሰብን ለመገንባት በር ከመክፈቱም በላይ የጋብቻን ክብር የሚያጎድፍ ድርጊት ነው በማለት በጽኑ ተቃውመው ነበር። ይሁንና ለግንኙነቱ ጥበቃና ዕውቅና ሊሰጥ ይገባል የሚለው ሃሳብ በማየሉ ጋብቻ ሳይፈጸም እንደባልና ሚስት አብሮ መኖር በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ሊካተት ችሏል።
በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 98 ስር ጋብቻ ሳይፈጽሙ እንደ ባልና ሚስት አብሮ መኖር ማለት አንድ ወንድና አንዲት ሴት ጋብቻ ሳይፈጽሙ በትዳር መልክ የሚኖሩበት ሁኔታ ነው ይላል። በትዳር መልክ መኖር ማለት ደግሞ ጥንዶቹ የሚያሳዩት ሁኔታ በሕግ እንደተጋቡ ሰዎች ዓይነት መሆን አለበት ማለት ነው። በሌላ አገላለጽ ከሦስቱ የጋብቻ ሥርዓቶች በአንዱ ተጋብተው የሚኖሩ ባልና ሚስት የሚያደርጉትን ነገር ሁሉ ማድረግ ማለት ነው።
አብሮ መኖር፣ መከባበር፣ መተጋገዝ፣ መደጋገፍ፣ ቤተሰብን በጋራ መምራት፣ ንብረት ማፍራት፣ ልጆች መውለድ ወዘተ በትዳር መልክ በመኖር የሚከናወኑ ናቸው። ከዚህም ሌላ የጋራ ኑሯቸውን ወጪ ለመሸፈን እያንዳንዳቸው እንደአቅማቸውና ችሎታቸው መጠን አስተዋጽኦ ማድረግም አለባቸው። (ጥንዶቹ ግንኙነታቸውን በማናቸውም ጊዜ ማቋረጥ እንደሚችሉም ልብ ይሏል)
ጥንዶቹም ቤተዘመዶቻቸውና ማህበረሰቡም ተጋብተው እንደሚኖሩ ሰዎች የሚገምታቸውና የሚያውቃቸው መሆን አለባቸው ማለት ነው። ቤተዘመድና ማህበረሰብ ሰርግና ክርስትና ሲጠራ በጋራ እንዲገኙ የጋበዛቸው እንደሆነ፤ በሚኖሩበት አካባቢ ሲወጡም ሲገቡም ደጋግሞ አንድ ላይ የተመለከታቸው እንደሆነ፤ አንዳቸውን ስለሌላኛቸው ደህንነት ሲጠይቅ «ባለቤትህ/ሽ ደህና ነው/ናት?» የሚላቸው ከሆነ፤ ለቡና ጥሪ መልዕክት ሲልክ «እነ እከሌን ኑ ቡና ጠጡ ብለህ ንገር» ወዘተ የሚላቸው ከሆነ እንደ ባልና ሚስት ገምቷቸዋል ማለት ነው።
ከዚህ ውጪ ግን ጥንዶቹ በታወቀና በተደጋገመ ሁኔታ የሩካቤ ስጋ ግንኙነት መፈጸማቸው ብቻ በመካከላቸው ጋብቻ ሳይፈጸም እንደ ባልና ሚስት ግንኙነት አላቸው ለማለት በቂ ምክንያት እንደማይሆን ሕጉ በግልጽ አስቀምጦታል።
እዚህ ላይ አንድ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የተቋጨ ክርክርን ለማሳያነት እንዲሆን በአጭሩ አንስቼው ልለፍ። ኢትዮጵያዊቷ ግለሰብ አንድ የኢጣሊያ ሰውን ከ1998 ዓ.ም. እስከ 2003 ዓ.ም. ድረስ እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረበት ወቅት ጋብቻ ባይመሰርቱም እንደባልና ሚስት አብረው መኖራቸውን በመጥቀስ በዚሁ ግንኙነትም ልጆችን ባይወልዱም የተለያዩ የሚንቀሳቀሱም ሆነ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን በጋራ ካፈሩ በኋላ ግንኙነቱ በመቋረጡ ምክንያት ንብረት እንዲያካፍላት ፍርድ ቤት ክስ ትመሰርትበታለች። ኢጣሊያዊውም ከግለሰቧ ጋር በ1999 ዓ.ም. የወራት ግንኙነት ብቻ የነበረው መሆኑን ጠቅሶ ከዚያ በኋላ ግን በተለያዩ ጊዜያት ከሁለት ሴቶች ጋር የፍቅር ግንኙነት መስርቶ የኖረ መሆኑን ገልጾ ተከራከረ።
ግራ ቀኙም አሉን የሚሏቸውን ማስረጃዎች አቅርበው በየደረጃው ውሳኔዎች ከተሰጡ በኋላ በፍጻሜው በሰበር ችሎቱ እልባት አግኝቷል። ሰበር ችሎቱም ኢጣሊያዊው ያቀረባቸው ማስረጃዎች በአካባቢው ይኖሩ የነበሩና ስለግራ ቀኙ የሚያውቁ ግለሰቦች በመሆናቸውና በምስክርነታቸውም ከኢትዮጵያዊቷ ጋር የተወሰነ ጊዜ ከማየታቸው በስተቀር ኢጣሊያዊው ከዚያ በኋላ ከሌሎች ሴቶች ጋር ግንኙነት የነበረው መሆኑን ያውቁ እንደነበር በመመስከራቸው በሁለቱ መካከል እንደባልና ሚስት ያለ ግንኙነት የለም በማለት እልባት አበጅቶለታል። ከዚህ የምንረዳው ታዲያ ለአጭር ጊዜ በፍቅር ጓደኝነት አብሮ መኖር ብቻውን ጋብቻ ሳይኖር እንደ ባልና ሚስት አብሮ የመኖር ሕጋዊ ውጤት እንደማይኖረው ነው።
ጋብቻ ሳይፈጽሙ እንደባልና ሚስት የመኖር ሌላው ውጤት ዝምድናን በተመለከተ የሚያስከትለው ውጤት ነው። በዚህ ግንኙነት ውስጥ በወንድየውና በሴቲቱ የስጋ ዘመዶች መካከል እንዲሁም በሴቲቱና በወንድየው የሥጋ ዘመዶች መካከል አንዳችም የጋብቻ ዝምድና እንደማይኖር ሕጉ በግልጽ ደንግጓል።
ይህም ማለት በጋብቻ የተሳሰሩ ጥንዶች በቤተሰቦቻቸው መካከል ዝምድና ስለሚፈጠር በቀጥታ የጋብቻ ዘመዳሞች (በወላጆችና በተወላጆች) መካከል እንዲሁም ወደ ጎን በሚቆጠር የጋብቻ ዝምድና (ማለትም ባል ከሚስቱ እህት ወይም ሚስት ከባሏ ወንድም ጋር) ጋብቻ መፈጸም ክልክል ነው። ይሁንና ጋብቻ ሳይፈጽሙ እንደባልና ሚስት አብሮ በመኖር ግንኙነት ውስጥ የጋብቻ ዝምድና ስለማይፈጠር በቀጥታም ሆነ ወደጎን ባሉ ዘመዳሞች መካከል ጋብቻ የተፈቀደ እንጂ ክልክል አይደለም ማለት ነው።
ጋብቻ ሳይፈጸም እንደባልና ሚስት አብሮ በመኖር ግንኙነት ውስጥ በብዛት አከራካሪው ጉዳይ ሀብትን የተመለከተ ነው። ጥንዶቹ የንብረት አስተዳደራቸውን አስመልክቶ በመካከላቸው ውል ሊፈጽሙ እንደሚችሉ የቤተሰብ ሕጉ አመልክቷል። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ጋብቻ ሳይፈጽሙ ለሦስት ዓመት አብረው ከኖሩ በግንኙነቱ ውስጥ እያሉ ያፈሯቸው ንብረቶች የጋራ ሀብታቸው እንደሚሆኑ ነው ሕጉ የደነገገው።
ይህንኑ መሠረት በማድረግ ታዲያ ተቃራኒ ማስረጃ እስካልቀረበ ድረስ ጥንዶቹ አብረው በመኖር ላይ እያሉ የሚኖሯቸው ንብረቶች ሁሉ በግንኙነቱ ውስጥ የተፈሩ ሀብቶች ተደርገው እንደሚቆጠሩም ጭምር ሕጉ ግምት ይወስዳል። ይህ ብቻም ሳይሆን ጋብቻ ሳይፈጽሙ እንደባልና ሚስት አብረው የሚኖሩ ወንድና ሴት የሚገቧቸው ዕዳዎች አብረው በሚኖሩበት ጊዜ ለጋራ ኑሯቸው ወይም ከግንኙነቱ የተወለዱ ልጆችን መሠረታዊ ፍላጎቶች ለማሟላት ሲባል የተገቡ ዕዳዎች ተደርገው ይቆጠራሉ። እናም ለዕዳዎቹ አከፋፈል ሁለቱም በአንድነትና በነጠላ ኃላፊዎች ይሆናሉ።
በአንድ የሰበር የቤተሰብ ጉዳይ ዶሴ ውስጥ አንድ ዶክተር እና አንዲት ወይዘሮ ከአስር ለሚዘልቁ ዓመታት ጋብቻ ሳይኖር እንደባልና ሚስት አብረው መኖራቸውን በተመለከተ ክርክር ያደርጋሉ። ዋናው የክርክራቸው ማጠንጠኛ ታዲያ እንደባልና ሚስት አብረን ስለኖርን በዶክተሩ ስም ተመዝግቦ የሚገኘው ቤት የጋራ ንብረት በመሆኑ ተካፍሎ ሊሰጠኝ ይገባል የሚል ነበር። በየደረጃው ክርክሩ ተደርጎ የሰበር ችሎቱም በግራ ቀኙ መካከል እንደባልና ሚስት አብሮ የመኖር ግንኙነት የነበረ መሆኑን አረጋግጦ ከወሰነ በኋላ ንብረቱን በተመለከተ ግን የጋራ ንብረት ባለመሆኑ የዶክተሩ የግል ንብረት እንጂ ለወይዘሮዋ ተካፍሎ የሚሰጥ አይሆንም ሲል ወስኗል።
የዚህ ምክንያቱ ደግሞ እንደባልና ሚስት አብሮ መኖር በንብረት ላይ ውጤት የሚኖረው ከሦስት ዓመታት በላይ ሲኖሩ በመሆኑ ጥንዶቹ ከአስር ዓመት በላይ አብረው ቢኖሩም ቤቱ ግን የተፈራው ጥንዶቹ እንደባልና ሚስት አብረው በኖሩበት ጊዜ ውስጥ ሳይሆን ቀድሞ በዶክተሩ የተፈራ ሀብት በመሆኑ ወይዘሮዋ እንዲካፈሉ የሚያስችላቸው የሕግ መሠረት የለም የሚል ነው።
በመሆኑም ሴትና ወንድ ጋብቻ ሳይፈጽሙ እንደባልና ሚስት ለሦስት ዓመት አብረው ከኖሩ በግንኙነቱ ውስጥ እያሉ ያፈሯቸው ንብረቶች የጋራ ሀብታቸው እንደሚሆኑ፤ ተቃራኒ ማስረጃ እስካልቀረበ ድረስ ጥንዶቹ አብረው በመኖር ላይ እያሉ የሚኖሯቸው ንብረቶች ሁሉ በግንኙነቱ ውስጥ የተፈሩ ሀብቶች ተደርገው እንደሚቆጠሩ፤ ከዚያ በፊት በየግላቸው ያፈሯቸው ሀብቶች ግን የየግላቸው እንጂ የጋራ ተደርገው ግንኙነቱ በተቋጠ ጊዜ ሊከፋፈሉ እንደማይገባ ከዚህ ውሳኔ መረዳት እንችላለን።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 8 / 2011
ከገብረክርስቶስ