ሥረ ነገር
እኛ ኢትዮጵያውያን ዓለም በዋነኝነት የሚያውቀን በቀደምት ሥልጣኔያችንና በጀግንነታችን ነው። በአንድ እሴት ላይ ከራስ አልፎ በሌሎች ዘንድ ለመታወቅ ድርጊቱ በተግባር ተደርጎ … አስመስሎ ሳይሆን ሆኖ መገኘት አለበት። ከዚህ አኳያ እኛ ኢትዮጵያውያን በጀግንነታችንና በቀደምት ሥልጣኔያችን በዓለም ሕዝብ ዘንድ የታወቅነው በእርግጥም የጀግንነትን ተግባር ፈጽመን በተግባርም ሥልጣኔ ቀድመን እንደነበር አመላካች የታሪክ ምስክር በተጨባጭ ስላለን ነው።
አዎ! እኛ ኢትዮጵያውያን የሦስት ሺ ዓመታት አኩሪ ታሪክ ያለን፣ የራሳችን መገለጫ ያለን፣ ነፃነታችንን በክንዳችን አስከብረን በኩራት የኖርን፣ በዕድገትና በሥልጣኔም ከማንም ቀድመን ለዓለም የሥልጣኔ እርሾን የጣልን … ጥበብን ከጀግንነት ያዋሃድን ነን።
በአፍሪካ የራሳችን የሆነ ፊደልና የዘመን መቁጠሪያ ቀመር ያለን እኛ ነን። በኪነ ሕንፃ ጥበብ ዓለም ገና ባልዘመነበት ጊዜ አሠራራቸው ዛሬም ድረስ «በዕውቀት ተራቀቅን፤ በሥልጣኔ መጠቅን» ለሚሉት ሁሉ ምስጢር የሆኑ እንደ አክሱም፣ ላሊበላና ፋሲለደስን የመሳሰሉ ህያው የጥበብ ቅርሶችን አቁመናል።
በኪነ ጥበብም ገና በስድስተኛው ክፍለ ዘመን ከስመጥሮቹ ከነ ሞዛርት ቀድመን ዜማን በምልክት የቀመሩትን እንደነ ቅዱስ ያሬድ ያሉ ሊቃውንትን ቀድመን አፍርተናል። በኢኮኖሚና በፖለቲካ ተፅዕኖም ቢሆን ኢትዮጵያ ቀይ ባህርን ተሻግራ እስከ ደቡብ አረቢያና የመን ድረስ የተዘረጋ ግዙፍ ኢምፓየርን የምታስተዳድር፣ በወቅቱ በዓለም ላይ ከነበሩ አራቱ ኃያላን አገራት አንዷና ዋነኛዋ አገር እንደነበረች ታሪክ ይመሰክራል።
በዚያን ወቅት ኢትዮጵያ ለእስራኤል፣ ለግሪክ ለሌሎች አገሮች ወታደራዊ እርዳታ ታደርግ እንደነበር ከራሳቸው ዛሬ «ሰለጠነ» ከሚባለው ዓለም የተገኙ ድርሳናት ይመሰክራሉ። ለዚህም እንደነ ሆሜር፣ ሄሮዳተስና ድሩሲላ ዱንጅ ሂውስተን የመሳሰሉ ጉምቱ የታሪክ ምሁራንንና ሌሎች በርካታ የታሪክ ሊቃውንትን በአስረጅነት መጥቀስ ይቻላል።
ከቅርቡ ታሪካችን ብንጀምር እንኳን የነጭ ወራሪን በጦር ሜዳ ገጥመን ለመጀመሪያ ጊዜ አሸንፎ ለጥቁር ሕዝብ ሁሉ ኩራት የሆነ አኩሪ ድልን የሰራን ሕዝቦች ነን። ነፃነትን ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካውያን ወንድሞቻችንና ለመላው ጥቁር ሕዝብ ያወረስን፣ ከራሳችንም አልፈን እንደነ ኔልሰን ማንዴላ የመሰሉ እልፍ የነፃነት አርበኞችን ያሰለጠን የነፃነት ተምሳሌቶች ነን። ታዲያ በተባበረ ክንዳችንና በአንበሳ ልባችን የማይደበዝዝ አኩሪ ታሪክ ያስመዘገብን በመሆናችን ብንኮራ ይገባናል፤ ጀግና ብንባልና በዚሁ ብንታወቅም ያንስብናል እንጂ አይበዛብንም- አድርገንና ሆነን ተገኝተናልና!
አሁን ግን በዛሬዋ ኢትየጵያ የምንገኝ እኔና የእኔ ትውልድ ጀግንነታችንና ኩሩነታችንን አስጠብቀን ለመቀጠል የአባቶቻችን ልጆች መሆናችንን በተግባር ማረጋገጥ ይጠበቅብናል። ይህንን የምናደርገው ደግሞ ክብራችንን ዝቅ የሚያደርጉ ነገሮችን ሁሉ እንደ አባቶቻችን በጀግንነት ታግለን በድል መወጣት ስንችል ነው። ከዚህ አኳያ የአሁኑ ትውልድ እንደ እንደቀደምቶቹ ጀግና ነኝ ለማለትና ኩሩ ሆኖ ለመገኘት በርካታ ማሸነፍ የሚገባው ጠላቶች ቢኖሩበትም በዛሬው ትዝብቴ አንዱንና ዋነኛውን የትውልዱን ክብረ ነክ ጠላት ለማሳየት እሞክራለሁ።
በትውልዱ ላይ እየደረሰ ያለውን በደልና ውርደት፣ አባቶቻችን ባወረሱን በደማቁ ክብርና ጀግንነታችን ላይ እየፈጠረ ያለውን ጥላሸት በማመላከት በምን መልኩ አሸንፈን ክብራችንን ማስጠበቅ እንደሚገባን መፍትሔ ነው ያልኩትን ለማጋራት ብዕሬን አንስቻለሁ።
ክብረ ነኩ ድህነትና ክብራችን
በአሁኑ ሰዓት በዓለም ዙሪያ የናኘውን ክብርና ጀግንነታችን እያጎደፈብን የሚገኘው አንደኛው ጠላታችን ድህነት ነው። ሰብዓዊ ጠላት ወይም የውጭ ወራሪ ቢመጣብን ዛሬም ቢሆን የምንሸነፍ አይመስለኝም። አሁንም ቢሆን ነፃነታችንን የምናስደፍር፤ ክብራችንን አሳልፈን የምንሰጥ አይደለንም። በዚህ ላይ አሁንም ጀግኖች ነን፤ እንኮራለንም። ከወራሪ ጠላት ባልተናነሰ በዓለም ዙሪያ ክብራችንን እያዋረደ፣ ጀግንነታችንም ትዝብት ላይ እየጣለ የሚገኘውን ግዑዝ ጠላት፣ ድህነትን ለማሸነፍ ግን ጀግንነት አንሶናል።
በዚህም ብዙዎቻችን ድህነትን ማሸነፍ አቅቶን ታላቋን አገራችንን ጥለን ወደ ሰው አገር ተሰደናል፤ እየተሰደደንም ነው። ክብርና ኩራታችንን ጥለን በመላው ዓለም ተበትነናል። ከጎረቤት አገራት እስከ ደቡብ አፍሪካና እስያ … ከአውሮፓ እስከ አሜሪካ ድረስ ኢትዮጵያውያን ያልተሰደድንበት አገር የለም።
በአሁኑ ሰዓት ከሦስት እስከ አራት ሚሊዮን የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን በመላው ዓለም ተበትነው የሚኖሩ ሲሆን ከነዚህ መካከል አብዛኞቹ ወደ ሰው ሀገር የሄዱበት ምክንያት ደግሞ በድህነት ምክንያት በአገራቸው ምድር ላይ መኖር አቅቷቸው ነው። በስደት የሚኖሩት ደግሞ በውርደት ነው። በድህነት ምክንያት በስደት ወደ ሰው ሀገር መሄድና ለሌላ ጉዳይ በፍላጎት ወደ ሰው ሀገር መሄድ ይለያሉና።
ሰው የውጭ የትምህርት ዕድል አግኝቶ ወደ ሰው ሀገር ሊሄድ ይችላል፤ ለሥራ፣ ለንግድ፣ ደልቶት ሞልቶት የተሻለ ኑሮ ለመኖር ከራሱ አገር ለቅቆ በሰው ሀገር ኑሮውን ሊመሰርት ይችላል። ወደ እኛ ሀገር ስንመጣ ግን በዚህ መልኩ በፍላጎታቸው ወደ ሰው ሀገር የሄዱት ጥቂት ይመስሉኛል። ከዚህ ቀደም የሄዱት፣ አሁንም እየሄዱ ያሉት አብዛኞቹ በሰው ሀገር መኖሩን ወደውት በፍላጎታቸው ሳይሆን ኑሮን ማሸነፍ ግዴታ ሆኖባቸው ሳይፈልጉ በስደት ነው።
እናም እዚህ በድህነት ተማርረው የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ለማግኘት ግድ ሆኖባቸው አገራቸውን ጥለው የሚሰደዱ ዜጎች በአገራቸው መኖር እየቻሉ ፈልገው ሄደው በሰው ሀገር እንደሚኖሩት አይደሉም። የሚሰደዱት ድህነትና የውርደት ኑሮ ሰልችቷቸው ቢሆንም እዚያም በክብርና በድሎት አይደለም የሚኖሩት። በዕድገት ከእኛ ብዙም በማይልቁት አገራት ሳይቀር በስደት የሚኖሩት እህቶቻችንና ወንድሞቻችን በቤት ሠራተኛነት፣ በሕፃናት ሞግዚትነት፣ በጽዳት ሠራተኝነትና በእረኝነትና በጥበቃ ሥራዎች ተቀጥረው ነው የሚሰሩት።
ይህም የሠራተኞቹን ሞራልና ሥነ ልቦና የሚጎዳ ከመሆኑም በላይ የሚያገኙት ክፍያም ድካማቸውን የማይመጥንና ሕይወታቸውን በፈለጉት ልክ የሚቀይርም አይደለም። ይህ አልበቃ ብሎም ያለ ዕረፍት እንዲሰሩ ከማስገደድ ጀምሮ በሴቶች ላይ እንደ አስገድዶ መድፈር፣ ስድብና ማንቋሸሽ፣ ከፍ ሲልም ድብደባና ግድያ በአሰሪዎቻቸው ይፈጸምባቸዋል። ከፎቅ ላይ ይወረወራሉ፤ ፍል ውሃ ይደፋባቸዋል ሌላም ሌላም አሰቃቂ ግፍና በደል ይፈጸምባቸዋል።
ይህም በድህነት ምክንያት በሀገራቸው ከሚደርስባቸው በላይ ዜጎቻችንን ለከፋ ችግርና ለሌላ ስቃይ እየዳረገ ይገኛል። ሕይወታቸውን የሚያጡት ቁጥርም ቀላል አይደለም። ከሁሉም በላይ ግን ክብሩን ከማስደፈር ሞቱን ለሚመርጠው ሕዝባችን ከሚደርሰው ስቃይና ሞትም በላይ በዚህ ደረጃ ክብራችን መነካቱ እንደ እግር እሳት የሚያንገበግብ ነው። እንዲህ ዓይነት ግፍና ውርደት በማንኛውም የሰው ልጅ ላይ መፈጸም አስነዋሪ ነው። ድርጊቱ በጀግንነታችና በኩራታችን በምንታወቀው በነፃዋና በታላቋ አገር ዜጎች በእኛ ላይ መፈጸሙ ደግሞ ውርደቱ የበለጠ እንዲያሳዝነንና እንዲያስቆጨን ያደርገናል።
መሸነፋችን ጥፋታችን
በእርግጥ ለዚህ ሁሉ አሳፋሪ ውርደት የበቃነው በገዛ ጥፋታችን ነው። ማንንም ልንወቅስ አንችልም፣ ለደረሰው ጥቃትና ውርደት ተጠያቂዎቹ እኛው ራሳችን ነን። ምክንያቱም ያዋረደን ያሰደደን ድህነታችን እንጂ የሄድንበት አገር አይደለም። እነርሱማ ሄድንባቸው እንጂ አልመጡብንም። ዜጎቻችንን ለዚህ ሁሉ ግፍና በደል የዳረገውና እንደ ሀገር እኛንም እንዲህ እንድንዋረድ ያደረገን ዋናው አስጠቂ ጠላታችን ድህነታችን ነው።
ይህንን ክብረ ነክ ጠላታችንን አለማሸነፋችን ነው ጥፋታችን፤ ስደታችን ነው ውርደታችን። በዚህ የተነሳም እብሪተኛ ወራሪ የሰው ጠላትን አሸንፈን በነፃነትና በጀግንነት ተከብረን በኩራት በኖርንበት ዓለም ድህነት በተባለ ሕይወት በሌለው ግዑዝ ጠላት ተሸንፈን በገዛ ስንፍናችን ተዋርደን አንገት መድፋት ጀምረናል።
በድህነትና በስደት ምክንያት የደረሰብን ውርደት ቀላል የማይባል ቢሆንም ከሁሉም በላይ ከፍ ብሎ የተቀመጠው የአባቶቻችን የነፃነትና የጀግንነት ታሪካችን ስንፍናችንን እየሸፈነልን ውርደታችን ያን ያህል ሳያሸማቅቀን ብዙ ሙሉ በሙሉም ባይሆን ክብራችን ሳይጠፋ አሁን ላይ ደርሰናል። በድህነት ምክያንት የሚደርስብን ውርደት እዚህ ላይ የማያቆም ከሆነና በዚሁ የምንቀጥል ከሆነ ግን ከዚህም በላይ መዋረዳችንና አባቶቻችን ባላወረሱን አሳፋሪ ታሪክ መታወቃችን አይቀሬ ነው።
ይህም ትውልድ የጊዜውን ጠላት አሸንፎ የራሱን አኩሪ ታሪክ ካልጻፈ በአባቶቹ ታሪክ ብቻ ሁልጊዜ ተከብሮ ሊኖር አይችልም። ምክንያቱም ክብርና ጀግንነት ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ በየዘመኑ እየተዘራ የሚታጨድ የቅብብሎሽ ምርት እንጂ አንድ ጊዜ አፍርቶ ዘላለም የሚበላ ተዓምራዊ ፍሬ አይደለምና።
መፍትሔው ማሸነፍ ብቻ ነው
በድህነት ምክንያት ከሚደርስብን ውርደት ለመዳንና እንደ አባቶቻችን በኩራት ተከብረን ለመኖር መፍትሔው ማሸነፍ ብቻ ነው- የሚያዋርደንን ክብረ ነኩን ጠላታችንን ታግለን ማሸነፍ! እንዴትና በምን የሚለውን ወሳኝ የሆነውን ነጥብ ብቻ እንደሚከተለው በአጭሩ እንመለከተዋለን። እንደ ሀገር የውርደት ምንጭ የሆነውን ድህነትን ለማሸነፍና ስደትን ለማስቀረት የተባበረ ክንድ ያስፈልጋል።
እናም እኛ በዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ውስጥ የምንገኝ ኢትዮጵያውያን እንደ አባቶቻችን ሁላችንም አንድ ላይ ተባብረን በጠላታችን በድህነት ላይ መዝመትና ድል ማድረግ ይኖርብናል። ዛሬም እንደ ወትሮው ክብራችንን ሊደፍረን የሞከረውን ያዋረደንን ጠላታችንን ድህነትን በማሸነፍ ጀግንነታችንና ክብራችንን ዳግም ለዓለም ማሳየት ይጠበቅብናል። ይህ የሁሉም ኢትዮጵያዊ የጋራ ታሪካዊ ግዴታ ሲሆን ኃላፊነታችንን በአግባቡ ለመወጣት ያስችለን ዘንድ የመንግሥትንና የሕዝቡን ኃላፊነት ለይተን ለማመልከት እንሞክራለን።
1. መንግሥት
መንግሥት የሚመራውን ሕዝብ ከድህነት እንዲላቀቅ የማድረግና የሚገባውን ኑሮ እንዲኖር ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠር ትልቅ ኃላፊነት አለበት። ለዚህም አግባብነት ያላቸውን የኢኮኖሚና የማህበራዊ የልማት ፖሊሲዎች መቅረጽና መተግበር ተቀዳሚ ተግባሩ ሊሆን ይገባል። ሀገሪቱ ከሰባ በመቶ በላይ የሚሆኑት ዜጎቿ ወጣቶች በመሆናቸውና ከድህነት ጋር ተያይዞ ለሚፈጠሩ ችግሮች (በተለይ ለስደት) በአብዛኛው ተጋላጭ የሚሆነውም ወጣቱ የኅብረተሰብ ክፍል በመሆኑ ወጣቱ ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ይገባል።
ለዜጎች በቂ የሥራ ዕድል መፍጠር የመንግሥት ተቀዳሚ ተግባር መሆን ይገባዋል። ሥራ መፍጠር ብቻ ሳይሆን በሀገሪቱ ካለው የኑሮ ውድነት ጋር የሚመጣጠን፣ የሚያስመችም ባይሆን የሚያኖር ደመወዝ መክፈልም ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው። ካልሆነ ግን በአብዛኛው በውጭ ባለ ሀብቶች በተያዙት የኢንዱስትሪ ፓርኮቻችን እንደምናየው በቀን ስምንት ሰዓታትን ለሚሰሩ ወጣቶች ስምንት መቶ ብር የወር ደመወዝ እየከፈሉ «ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል እየፈጠርን ነው» እያሉ መፎከር ትርፉ ራስንና ዜጎችን ማታለል ካልሆነ በቀር ይህ ዓይነቱ የሥራ ዕድል ፈጠራ ለሀብታሙ እንጂ ለድሃው ከችግር ፈጠራ አይተናነስም።
ምክንያቱም በዚህ ክፍያ ተቀጥሮ የሚሰራ ድሃ ለሌላ ጊዜ የሚጠቅመውን ጉልበቱን የሥራ ዕድል ለተፈጠረለት ሀብታም ከማስበዝበዝ በቀር ከድህነት መውጣት አይችልም።
ከዚህም ባሻገር በገጠርና በከተማ፣ በሀብታምና በድሃ፣ በባለሥልጣንና በተራው ሕዝብ መካከል ያለውን ከፍተኛ የሆነ የኑሮ ልዩነት በማጥበብ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል መፍጠርም ድህነትን ለመቀነስ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው። ፍትሐዊ የፖለቲካ ሥርዓት በማስፈን፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በማክበር፣ በማስከበርና ከሕዝቡ ጋር ተቀራርቦ መስራትና እውነተኛ ዴሞክራሲን መተግበር ዜጎች አገራቸውን እንዲወዱና በአገራቸው ሰርተው እንዲለወጡ አስቻይ ሁኔታዎችን የሚፈጥር በመሆኑ በዚህ መንገድ ድህነትን በእጅጉ መቀነስ ይቻላል። በዚህም ዜጎች በሀገራቸው ሰርተው የሚለወጡበትን ሁኔታ በመፍጠር ለውርደት የሚዳርገንን ስደትን ከምንጩ ማድረቅ ይቻላል።
2. ዜጎች
ዜጎች በበኩላቸው መንፈሰ ጠንካራና በቀላሉ ተስፋ የማይቆርጡ መሆን ይጠበቅባቸዋል። በድህነትና በችግር ውስጥ ሆኖም ተስፋ ሳይቆርጡ በጽናትና በአሸናፊነት መንፈስ ከታገሉት ማንኛውንም ችግር ማሸነፍ እንደሚቻል ማመንና መስራት ይጠበቅባቸዋል። ለጠላትና ለችግር እጅ መስጠት የአባቶቻችን ባህል አይደለም። ጥራዝ ነጠቅ አላዋቂዎች እንደሚሉት ታሪክ ተራ ተረት ተረት ሳይሆን ሰዎች በተግባር አድርገውትና ሆነውት ያለፉት እውነተኛ የሥራ መዝገብ ነው። ከዚህም በላይ ታሪክ የፈለጉትን ማድረግና መሆን እንደሚቻል ሰዎች በተግባር ሞክረው ያረጋገጡበት የድርጊት ቤተ ሙከራና ቀዳሚው ትውልድ ለቀጣዩ የሚያወርሰው የአሸናፊነት ሥነ ልቦናም ነው።
የአሸናፊነት፣ የጀግንነትና የነፃነት አኩሪ ታሪካችንን ስናስብ ትርጉሙ እኛም አሁን ማሸነፍ እንችላለን ማለት ነው። አባቶቻችን አሸናፊዎች እንደነበሩ፣ በዚህም በዓለም ላይ ተከብረው እንደኖሩ እኛንም እንዳኖሩን እኛም የክብራችንና የኩራታችን ጠላት ሆነውን ድህነት ማሸነፍ እንችላለን። አባቶቻችን ባወረሱን የአሸናፊነት ሥነ ልቦና ላይ ዘመኑ የሚጠይቀውን ዕውቀት፣ ጥበብና ተግባር በመጨመር ድህነትን ማሸነፍና ክብራችንን መመለስ ይገባናል።
ለዚህም የንባብ ባህላችንን በማሳደግና የሥራ ባህላችንን በማሻሻል፣ ችግሮችን የመመርመር፣ የማወቅና የመፍታት ጥበባችንን በማጎልበት አስተሳሰባችንና አመለካከታችንን ጠቃሚ በሆነ መንገድ መለወጥ ተቀዳሚ ተግባራችን መሆን ይኖርበታል። እንዲህ ከሆነ ድህነትን ጨምሮ የማናሸንፈው ጠላት፣ የማንወጣው ዳገት አይኖርም።
እናም እኛም እንደ አባቶቻችን በክብርና በኩራት ከፍ ብለን መኖር ከፈለግን ዝቅ የሚያደርገንንና የሚያዋርደንን ድህነት ማሸነፍ ግድ ይለናል። መከበርና ጀግና መባል ከፈለግንም በተግባር ጀግና ሆነን መገኘት ይኖርብናል። አባቶቻችን እኮ በዓለም ላይ በጀግንነታቸውና በኩሩነታቸው ታውቀው በክብር መኖር የቻሉት እናንም አስከብረውን የኖሩት በተግባር አሸናፊና ጀግና ሆነው ስለተገኙ ነው።
እኛም ክብር ከፈለግን፤ «ኩሩ፣ ቆፍጣና ጀግና» መባል ካማረን ድህነትን በተግባር አሸንፈን ማሳየት… በተግባር ጀግኖች ሆነን መገኘት ይጠበቅብናል። አለበለዚያ በድህነት ምክንያት በየአገሩ በስደት እየተንከራተቱ፣ በልመና ስንዴ እየኖሩ ክብር የለም፤እየተሸነፉ ኩራት የለም!
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 8 / 2011
ይበል ካሳ