የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በቅርቡ ባደረኩት ግምገማ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ሜዳዎች ዓለም አቀፍ ውድድሮችን የማስተናገድ አቅም የላቸውም ሲል ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን «ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ሜዳዎች አንዳንቸውም የካፍን መመዘኛ አያሟሉም ተብለናል» ሲል ለዚሁ ማረጋገጫ ሰጥቷል። የካፍ የግምገማ ውጤት ሰሞነኛ ጉዳይ በመሆንም ሰንብቷል።
በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ስታድየሞች እየተገነቡ ባሉበት ወቅት እንዴት አንዱ እንኳን የካፍን መመዘኛ ማሟላት አቃተው? ሲሉም በርካቶች እየተጠየቁ ይገኛል። ጥያቄው ተገቢና መሰረታዊ መሆኑ የሚያሻማ አይደለም። የካፍ ግምገማን ተከትሎ ብዙ ብዙ የተባለላቸው ስታዲየሞቻችን አሁናዊ ቁመናን መፈተሽ ደግሞ ለዚህ ምላሽ ይሰጣል።
በኢትዮጵያ በየዓመቱ ሲከበር የቆየውን የብሔር ብሔረሰቦችን በዓልን መሰረት በማድረግ በመላ ሀገሪቱ ግዙፍ የሚባሉ ስታዲየሞች በመገንባት ላይ ቢሆኑም አንዳቸውም ሙሉ ለሙሉ አልተጠናቀቁም። ለአብነትም በአዲስ አበባ ከሚገኘውና የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታው እየተጠናቀቀ ካለው ብሔራዊ ስታድየም አንስቶ በባህርዳር፣ ሐዋሳ፣ መቐለ ላይ ያሉት በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። ከተመልካቾች መቀመጫና ውጫዊ ገጽታ ባሻገር የመጫወቻ ሜዳ ጥራት፣ አስፈላጊ ውስጣዊ ግንባታዎች ላይ የሚሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑም ዋጋ እያስከፈለ መጥቷል።
ብሄር ብሄረሰቦች የወለዷቸው ስታዲየሞች
በብሔር ብሔረሰቦች ቀን አማካኝነት ግንባታቸው ከተጀመሩ ታድየሞች መካከል በጋምቤላ ፣አፋር ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝና ሐረሪ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስታት የሚገነቡት ዋነኞቹ ናቸው፡፡ የስታዲየሞቹ ግንባታ ትልቅ ቁም ነገር ያለው ቢሆንም ፤ፕሮጀክቶቹ ሲታቀዱ “ማን ከማን ያንሳል” በሚል ስሜታዊነት በመሆኑ ፍጻሜያቸው እንዳጀማመራቸው ሳይሆን ቀርቷል። አንዳንዶቹ ባሉበት ቁመና የአገር ውስጥ ውድድሮች በማስተናገድ ላይ ይገኛሉ፡፡ ጥቂቶቹ ደግሞ መሠረታቸው ተጥሎ ግንባታቸው ከተጀመረ ሁለት አስርታት ዓመታት ሊሞላቸው ተቃርቧል።
የስታዲየሞቹ ግንባታ መሰረት የተደረገው ስፖርትን ሳይሆን ፖለቲካን በመሆኑ ክብረ በዓሉ እንዳለፈ አስታዋሽ በማጣታቸው ምክንያት ቆመው ቀርተዋል። ለምሳሌ በጋምቤላ ክልል ብሄር ብሄረሰቦች በዓልን ምክንያት በማድረግ የተጀመረው ስታዲየም ግንባታው የካቲት 12 ቀን 2007 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን በሁለት ዓመታት ውስጥ ተገንብቶ በ 2009 ዓ.ም ላይ ይጠናቀቃል ተብሎ ነበር፡፡ ለግንባታውም 648 ሚሊዮን 776 ሺ አምስት መቶ ዘጠና ብር ተበጅቶለትም ነበር፡፡ ምን ዋጋ አለው አሁን ላይ አርባ ዘጠኝ በመቶ ብቻ ተሰርቶ በፋይናነስ እጥረትና ተጓዳኝ ምክንያቶች ቆሞ ይገኛል።
ሌላው የብሄር ብሄረሰቦችን ቀንን መሰረት አድርገው መሰረታቸውን ከጣሉት ግዙፍ ስታዲየሞች አንዱ ደግሞ «አሕመድ ነስር» መታሰቢያ ስታዲየም ነው። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እየተገነባ የሚገኘው ይህ ስታዲየም ግንባታ የካቲት 23 ቀን 2006 ዓ.ም ነበር የተጀመረው። ጥቅምት 2011 ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሎ ነበር፡፡ አሁን ላይ የግንባታው ሂደቱ ሃምሳ በመቶ ላይ ነው የቆመው። የግንባታው ሂደት ከመጓተቱ ባሻገር የፋይናንስ አፈጻጸሙም ደግሞ ሌላ ተጨማሪ ጥያቄን የሚያስነሳም ሆኗል።
በ 460 ሚሊዮን ብር ወጪ ይገነባል የተባለው ይህ ስታዲየም ፤ እስከ አሁን 50 በመቶ ላይ ይገኝ እንጂ 340 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል፡፡ ይህ ገንዘብ የሙሉ ግንባታ ወጪን የሚስተካከል በመሆኑ ከስራው መጓተት ባሻገር የፋይናንስ አፈጻጸሙም ምርመራን የሚሻ መሆኑን ጠቁመን ወደ ሐረር ተሻገርን ።
በሐረሪ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የሚገነባው አባድር ስታዲየም ሚያዝያ 2008 ዓ.ም ነው የተጀመረው፤ ጥቅምት 2011 ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሎ ነበር፡፡ ግንባታውን በታሰበበት ጊዜ እንዲጠናቀቅ በ2010 ዓ.ም ሦስት መቶ ስልሳ ሚሊዮን ብር ተመድቦ የነበረ ቢሆንም አሁንም 600 ሚሊዮን ብር አስወጥቶ ከ65 በመቶ ላይ ግን ፈቅ ማለት አልቻለም ተብሏል። በአሁኑ ወቅት ግንባታው እንደቆመ የሚነገርለት ስታዲየሙ ሙሉ በሙሉ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር እንደሚፈጅ ታውቋል። የግንባታው መቋረጥ መንግስትን ለተጨማሪ ወጪ መዳረጉ የማይቀር መሆኑም ሊሰመርበት ይገባል።
የብሄር ብሄርሰብ በዓልን መሰረት አድርገው ከተገነቡና ክብረ በዓሉ ሲያልፍ ከተዘነጉ ከፍተኛ ወጪ ከወጣባቸው ስታዲየሞች አንዱ የሆነው የሰመራ ስታዲየም ሌላው የትኩረታችን አቅጣጫ ነው። ግንባታው ሐምሌ 18 ቀን 2009 ዓ.ም ነበር የተጀመረው በአራት ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅም እቅድ ተይዞለት ነበር። አንድ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ በጀት የተያዘለት ስታዲየሙ፤ በሶስት ዓመት ለማጠናቀቅ ውል ተገብቶ ቢጀመርም ፤ በአሁኑ ወቅት 44 በመቶ ላይ ደርሶ ቆሟል።
ይህም ስታዲየምም እንደሌሎቹ ሁሉ መጀመርን እንጂ መጨረስን መሰረት ያደረገ አልነበረም። ከላይ በማሳያነት የቀረቡትም ሆነ ይሄንኑ ዓላማ ማነጣጠሪያ አድርገው የተጀመሩት ሁሉ ግንባታቸው ከክብረ በዓሉ ማግስት ጀምሮ ተረስቷል። ምክንያቱ ደግሞ አነሳሱም ስፖርቱን ሳይሆን ፖለቲካውን የያዘ ከዛ ባለፈ ደግሞ የእርስ በእርስ ፉክክር የወለዳቸው ስለነበሩ ጣሪያ አልባ ሆነው የህዝብና መንግስትን ሀብት አላግባብ ሲባክንባቸው ቆይቷል።
መቋጫ አልባው ጅማሮ
በሀዋሳ ፣መቐለ፣ ባህርዳርና አዲስ አበባ የሚገኙ ስታዲየሞች የግንባታ ሂደት ምንም እንኳን ከላይ እንዳልነው ፖለቲካዊ አጀንዳን መሰረት አድርገው መጀመራቸው ለመጓተታቸው ምክንያት ቢሆንም ስፖርቱን ታሳቢ በማድረግ ግንባታቸው የተጀመሩቱም የችግሩ ሰለባ ከመሆን ካለመዳናቸውም በላይ ሙሉ ለሙሉ አለመጠናቀቃቸው ከካፍ መስፈርት ውጪ አድርጓቸዋል። ለዚህ ማሳያ ይሆን ዘንድ በባህር ዳርና መቐለ ከተማ እየተገነቡ የሚገኙት ስታዲየሞች የግንባታ ሂደት ዘርዘር አድርጎ መመልከቱ አስፈላጊ ይሆናል።
ማቱ ሳላህ
ትግራይ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ግንባታ በ2003 ዓ.ም ነበር የተጀመረው። የስታዲየሙን ግንባታ ውጥን ከአስር ዓመት በፊት ቢጀመርም ቅሉ ዛሬም ግንባታው አልተጠናቀቀም። ህብረተሰቡ የግንባታው ሂደት መጓተቱን አስመልክቶ «ማቱሳላ» የሚል መጠሪያ ሰጥቶታል፡፡ በእርግጥ ከህዝብና መንግስት በተገኘ ገንዘብ የሚሰራ ግንባታ በዚህን ያህል ጊዜ ሲቆይ ስሙ ከዚህም በላይ ቢባል ያንሰዋል።
የትግራይ ክልል ስፖርትና ወጣቶች ጽህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ገብረማርያም ዘሚካኤል ከወራት በፊት ለአዲስ ዘመን የሰጡት መረጃ እንደሚያመለክተው ፤ስታዲየሙን በ530 ሚሊዮን ብር ገንብቶ ለማጠናቀቅ ታስቦ ነበር ፤ የተለያዩ ችግሮች በማጋጠማቸው ግንባታው ተጓቷል ወጪውም ከታሰበው ከፍ ብሏል። በአሁኑ ወቅት የግንባታው የመጀመሪያው ምዕራፍ 90 በመቶ መድረሱንና ስድስት መቶ 57 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉን ነበር የነገሩን።
የግንባታው የመጀመሪያው ምዕራፍ አስር በመቶ የቀረው ቢሆንም ፤ ከ127 ሚሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ ወጪ አስወጥቷል። አቶ ገብረማርያም ፤የግንባታው ቀሪ 10 በመቶ ስራ «የፊኒሺንግ» ስራ ነው። ይሄውም የወንበር ገጠማና የሼድ ስራ ይቀራል፣ የመብራትና የድምጽ ሥርዓት፣ የካሜራ ሲስተም ዝርጋታና ጣሪያ የመግጠም ስራን ያጠቃልላል። ለዚህ ደግሞ የሚያስፈልገው ገንዘብ ግን ከ600 ሚሊዮን ብር ያላነሰ ነው። የግንባታው ሂደት መጓተት በህዝብና መንግስት ሀብት ላይ ጎትቶ ያመጣው ብክነት ግን ለትውልድ እዳ ይሆናል። የትግራይ ስታዲየምን መቋጫ አልባ የግንባታ ሂደት ተመለከትን እስቲ ወደ ባህር ዳር እንውረድ።
ጣሪያ አልባው ስታዲየም
የባህር ዳር ስታዲየም ግንባታ ታህሳስ 2 ቀን 2002 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን ፤የግንባታ ሂደቱ እንደሌሎቹ ሁሉ መጓተት ተስተውሎበታል። የባህርዳር ሁለገብ ስታዲየምን ለመገንባት በአማራ ክልል የቀድሞው ርዕሰ መስተዳድር አቶ አያሌው ጎበዜና በሚድሮክ ኢትዮጵያ ባለቤት በሼህ መሃመድ አላሙዲን አማካኝነት የውል ስምምነት ተፈርሞ በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቃል ቢባልም ይኸው እስከ አሁን አለ፡፡ 60ሺ ተመልካቾችን የመያዝ አቅም እንደሚኖረውም የተነገረለትና በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ በ700 ሚሊዮን ብር ሊገነባ ጉዞው የጀመረው ስታዲየሙ የመጀመሪያውን ምዕራፍ በ380 ሚሊዮን ብር ወጪም ነበር የተጀመረው።
ስታዲየሙ ለክልሉ ብቻ ሳይሆን ሀገሪቱ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ውድድሮችን ለማዘጋጀት የሚያስችል መሆኑ ብዙዎች እንዲናፈቁት ያደረገ ቢሆንም ከስድስት ዓመት በላይ ሳይጠናቀቅ አስቆጠረ። የአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ የግንባታው ሂደት መዘግየቱን አምኖ ሁኔታው ግንባታው ሲጀምር በዕቅዱ ያልተካተቱ ተጨማሪ ማሻሻያዎች በመኖራቸው ነው ሲል ምላሽ ሰጠ። ያልተጠናቀቁ ሥራዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በተጨማሪም ሁለት የእግር ኳስ ሜዳዎችን ሊገነቡ መታቀዳቸው ተናገረ፡፡
በመሆኑም ከተቋራጮች ጋር የነበረው የስምምነት ዕድሳት እና ከስድስት ዓመታት በፊት የነበረው የግንባታ ግብዓት ወጪ ተመጣጣኝ ያለመሆኑ እንዲዘገይ አድርጎታል። ቢሮው ይሄንን ሲል መጓተቱን ተከትሎ የደረሰውን ያለ አግባብ ወጪ ሳይሸሽግ ተናገረ 2003 ዓ.ም የስታዲየሙ ግንባታ ሲጀመር በ380 ሚሊዮን ብር ቢሆንም አሁን ላይ 589 ሚሊዮን ብር ደርሷል። እንደምንም ብሎም ስታዲየሙ በ2009 ዓ.ም 86 በመቶ ላይ መድረስ ቻለ። በዚሁ ዓመት ደግሞ የስታዲየም ዋና አካል የሆነው የጣራና የወንበር ተከላ ሳይጠናቀቅ የአማራ ክልላዊ መንግስት ርክክብ መፈጸሙ ተሰማ።
የአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሉአዳም ጌታነህ በወቅቱ፤ የተመልካች ወንበር ዝርጋታ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ እንደሚጠናቀቅና በ2010 ዓ.ም የሽፋን ግንባታ በሚድሮክ ኢትዮጵያ ለማከናወንም ስምምነት መደረሱንና በቀሪው ግንባታ ተጨማሪ 400 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ተናግረው ነበር። የጣሪያውም ሆነ የተመልካች ወንበር በተባለው ጊዜው ሳይጀመር ይኸው ሁለት ዓመት ተቆጠረ።
የባህር ዳር ስታዲየም ግንባታ በከፊል ከተጠናቀቀ በኋላ ከሰባት ያላነሱ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ሲያከናውን ቆይቷል። ኢትዮጵያ ለምታስተናግደው እግር ኳሳዊ ውድድሮች ከዓለም አቀፍም ሆነ ከአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ዕውቅናና ተቀባይነት በማግኘት እነዚህ ጨዋታዎችን ማድረግ ቢቻልም፤ቀጣይ ጨዋታዎችን ለማድረግ ማሟላት የሚገባው መስፈርት መኖሩን ካፍ ከሰሞኑ በደብዳቤ አስታውቋል። የትግራይ ስታዲየምም በተመሳሳይ እጣ ፈንታ ላይ ተቀምጧል።
ትኩረት ይሰጥ ዘንድ
በአጠቃላይ በመላው አገሪቱ የሚገነቡት ስታዲየሞች አንዳቸውም ሙሉ ለሙሉ አልተጠናቀቁም። ከተመልካቾች መቀመጫና ውጫዊ ገጽታ ባሻገር የመጫወቻ ሜዳ ጥራት፣ አስፈላጊ ውስጣዊ ግንባታዎች አለመጠናቀቅ ዋጋ እያስከፈለ መጥቷል። በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ተገንብተዋል የሚባሉትንና በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኙት በአጭር ጊዜ ማጠናቀቅ ከተቻለ ለስጋቱ ምላሽ የሚሰጥ ይሆናል። በተለይ ደግሞ ዋነኛ አማራጭ ሆነው የቀረቡትን የትግራይና ባህር ዳር ስታዲየሞች ቀሪ ስራዎቹን በከፍተኛ ትኩረትና ርብርብ መስራትን የግድ ይላል ።
ብሄራዊ ፌዴሬሽኑ እስካሁን ለዚህ ችግር ዘላቂ የሆነ መፍትሄ ለማምጣት ያሰበው ነገር ከመናገር ይልቅ ትግራይና ባህርዳር ስታዲየም ጊዜያዊ ፍቃድ ማግኘታቸውን አጉልቶ ማውራትን ነው የመረጠው። ሆኖም ሀገሪቱ ከገባችበት ምጥ ለመውጣት የሚቻለው ዘለቄታዊ መፍትሄ ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ነው የሚያስፈልገው::
በሌላ በኩል ከወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ጋር በመቀናጀት ለመፍትሄው በአብሮነት መስራቱ በይደር መተው የለበትም። በየክልሉ ግንባታቸው ተጀምረው በትኩረት እጦት ቆመው የቀሩትን ስታዲየሞች በማስቀጠል በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቁ መስራት ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 8 / 2011
ዳንኤል ዘነበ