በያዝነው የትምህርት ዘመን በርካታ ተማሪዎች ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚደግፉትን ፓርቲ አርማና ሰንደቅ ዓላማ ይዘው ሲገቡ ተስተውሏል፡፡ አብዛኞቹ ተማሪዎችም ከትምህርት ይልቅ በፖለቲካዊ ልዩነቶች ላይ ጊዜያቸውን ያባክናሉ፡፡ በዚህም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የእውቀት ገበያ መሆናቸው ቀርቶ የሁከት መድረክ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡
ይህንን ታሳቢ በማድረግም ሰሞኑን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱን ቀጣይነት ባለው መልኩ ለማረጋገጥ አግባብነት ካላቸው የፌዴራል መንግስት ሴክተር መስሪያ ቤቶች የተወጣጡ የአመራር አካላት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የመስክ ግምገማ አካሂደዋል፡፡ በግምገማውም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኃላፊዎች ኃላፊነታቸውን አለመወጣት፣ የግብዓት በበቂ ሁኔታ አለመሟላት እና ተማሪዎች ለመማር ተዘጋጅቶ አለመምጣት ችግሮች እንደነበሩ ገምግመዋል፡፡
የመስክ ሪፖርቱን ያቀረቡት ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ እንደሚናገሩት፤ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ከታዩት ችግሮች ውስጥ ተቋማቱ በምክትል ፕሬዚዳንቶችና በተወካዮች መመራታቸው በተለይ በዲላ፣ በአዲግራት፣ በአሶሳ፣ በጋምቤላና በወላይታ ሶዶ እንደ አንድ ችግር የታየ ሲሆን በተቋማቱ ውስጥ የቦርድ አመራሮች መጓደል፣ የተመደቡባቸውም የቦርድ አመራሮች በተደራራቢ ስራ መጠመድ፣ ቦርድ አመራሩ ከተቋማቱ ፕሬዚዳንቶች ጋር ተቀናጅቶ አለመስራት፣ የተቋማቱ አመራር በተማሪዎች ተቀባይነት ማጣት ተጨማሪ ችግሮች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
ከላይ የተቀመጡት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮች በቦታው አለመኖር ችግሮች ሲነሱ መፍትሄ ለመስጠት አስቸጋሪ ማድረጉን ይናገራሉ፡፡ የተቋማቱ የቦርድ አመራሮች በፖለቲካ ስራና በተመደቡበት ስራ በመጠመዳቸው ተቋማቱ ችግር ሲገጥማቸው በፍጥነት ለመፍታት አስቸጋሪ ማድረጉን ይጠቅሳሉ፡፡ አንዳንድ ተቋማት ውስጥ ብጥብጥ ሲነሳ ፕሬዚዳንቶች ስልካቸውን እንደሚዘጉም ይጠቁማሉ፡፡
ከግብዓት ችግር ጋር በተያያዘም የላቦራቶሪ እቃዎች አለመሟላት፣ የመምህራን እጥረትና የመቅጠር ስራው መጓተት፣ የውጭ መምህራን የአገሪቱን የትምህርት ሥርዓት ባለመረዳታቸው የአቅም ማነስና የውሃና የመጸዳጃ ቤቶች አለመኖር እንደሚገኙበት የጠቀሱት ዶክተር ሳሙኤል፤ እነዚህ ጉዳዮች ተማሪዎቹ እንዲበጠብጡ መነሻ ምክንያት እንደሆናቸው ያስረዳሉ፡፡
እንደ ዶክተር ሳሙኤል ገለፃ፤ ውጤት ያልመጣላቸው ተማሪዎች በአካባቢው ቤት በመከራየት በዘረፋና በሁከቶች ላይ ዋነኛ ተሳታፊ መሆን፣ በተቋማቱ ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባል ለማፍራት እንቅስቃሴ መብዛት፣ የመውጫ ፈተናዎች እንደየተቋማቱ የተለያየ መሆን፤ ከአንድ ክልል የመጡ ተማሪዎች ተመሳሳይ ትምህርት ክፍል መመደብ፣ ተማሪዎችን በፆታና በሃይማኖት እንዲሁም በብሄር መከፋፈል እና ተማሪው ስራ አላገኝም በሚል መንፈስ ለመማር ተዘጋጅቶ አለመምጣት ችግሩን አባብሶታል፡፡
የደንቢዶሎ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት አቶ ዳላሳ ቡልቻ፤ በአዳዲስ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የአስተዳደር ችግሮች በመኖራቸው የተማሪዎችና የመምህራን መኖሪያ ቤቶች አለመኖር፣ የላብራቶሪ እቃዎች አለመሟላት፣ ወርክ ሾፕ መሳሪያዎች አለመኖር፣ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ችግርና የአጥር አለመኖር ችግሩን እንዳባባሰው ተናግረዋል፡፡
ተቋሙ ተማሪ ተቀብሎ ለማስተማር ሊኖሩት የሚገቡት ግብዓቶች ባለመሟላታቸው ተማሪዎቹ በቀላሉ ለፖለቲካና ለሌሎች ግጭቶች ተጋላጭ ማድረጉን ይጠቅሳሉ፡፡ በአዳዲስ ዩኒቨርስቲዎች በጀት ተመድቦ መሰራት ያለባቸው ስራዎች ቢኖሩም ብዛት ያላቸው ተማሪዎች እየተመደቡ መጨናናቅ እየተፈጠረ እንዳለም ያነሳሉ፡፡ በአካባቢው ሰላም ለማስከበር ከህብረተሰቡ ጋር ውይይቶች እየተካሄዱ መሆኑንና በተፈጠሩ ሁከቶች ወላጆች ልጆቻቸው ትምህርት አቋርጠው እንዲወጡ የሚያደርጉትን ግፊት ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑንም ይጠቁማሉ፡፡
የወሎ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አባተ ጌታሁን በበኩላቸው፤ በአሁን ወቅት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱ ያሉት ችግሮች ኃላፊነት መውሰድ ያለበት አመራሩ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ ለምሳሌ በወሎ ዩኒቨርስቲ ሰላም ለማስከበር ከአካባቢው ማህበረሰብ የተወጣጣ ኮሚቴ አቋቁመው በመስራታቸው ምንም አይነት ችግሮች አለመፈጠሩን ጠቅሰዋል፡፡
እንደ ዶክተር አባተ ገለፃ፤ የቤተ ሙከራ እቃዎች አለመሟላት፣ የመብራት መቆራረጥ፣ የውሃና መፀዳጃ ቤቶች አለመኖር እና የመምህራን እጥረት ተማሪው በወቅቱ ወደ ትምህርት ባለመሰማራቱ ጊዜውን በሌሎች ጉዳዮች እንዲያባክን አድርጎታል፡፡ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የፖለቲካ መድረክ እንዳይሆኑ የተሰሩ ስራዎችም በሚፈለገው መጠን ባለመሰራታቸው ተማሪዎች በሌሎች አጀንዳዎች ሲጠለፉ ይስተዋላል፡፡በዚህ የተነሳ ብዝሃነትን ከሚያሰፉ ስራዎች ይልቅ በሃይማኖት፣ በብሄርና በፖለቲካ አመለካከት መከፋፈሎች በዝተዋል፡፡
በመሆኑም በሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙ ተማሪዎች ቶሎ ትምህርታቸውን እንዲጀምሩና ጊዜያቸውንም በዚሁ ተግባር ላይ እንዲያሳልፉ ማድረግ፤ ከዚህ ጎን ለጎንም በዩኒቨርስቲዎች የሚታዩ ችግሮችን መፍታት በዩኒቨርስቲዎች ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ጠቃሚ በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8/2011
በመርድ ክፍሉ