አበው ‹‹ሊነጋጋ ሲል ይጨልማል›› ይላሉ፡፡ ይህም ለዘመናት የኖረን ችግር ለማስወገድ በሚደረግ ትግል ውስጥ ከባድ ፈተናና ትግል መኖሩን የሚያመላክቱበት ምሳሌ ነው፡፡ አገርን በማሳደግ ሂደት ውስጥ በርካታ ውጣ ውረዶች አሉ፡፡
አሁን በአገራችን እያጋጠመ ያለውም ይኸው ነው፡፡ በአገራችን የሚታየው የለውጥ እንቅስቃሴ አብዛኛውን ዜጋ የተስፋ ዳቦ ያስገመጠውን ያህል ጥቂቶችንም ስጋት ውስጥ መክተቱ አሌ የሚባል አይደለም፡፡
እዚህም እዚያም የሚታዩት ግጭቶች፣ ብሄርና ማንነትን ሽፋን እያደረጉ የሚፈፀሙ ጥቃቶች እንዲሁም የህግ የበላይነትን የሚፈታተኑ ድርጊቶች ለለውጥ ፈላጊው ህዝብና መንግስት ትልቅ ፈተናዎች መሆናቸው አልቀረም፡፡ ይህ ደግሞ በአብዛኛው ለውጡን በማይፈልጉና የግል ጥቅማቸው በተነካባቸው አካላት የሚፈፀም የአልሞት ባይ ተጋዳይነት መፍጨርጨር ነው፡፡
በዚህ የተነሳ በብሄር ስም እዚህም እዚያም ግጭት ለመፍጠርና ለዘመናት አብረው የኖሩትን የአገራችንን ብሄር ብሄረሰቦች እርስ በርስ ለማበጣበጥ እየሰሩ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር ጥረት ሲያደርግና እርምጃ ሲወስድ ማሊያቸውን በመቀየር በብሄር ውስጥ ይወሸቃሉ፡፡
የለውጥ ሃይሉም እነዚህን ሁለት ተቃርኖዎች እንደየአመጣጣቸው እየመለሰ ነው፡፡ በዚህም መሰረት በአንድ እጁ የእድገታችን መሰረት የሆኑ የልማት ተግባራትን አጥብቆ በመያዝ እየታገለ ሲሆን በሌላ እጁ ደግሞ ከህዝቡ ጋር እጅ ለእጅ በመያያዝ በአፍራሽ ሃይሎች ተጠልፎ እንዳይወድቅ እየታገለ ይገኛል፡፡ በዚህም መሰረት አገራችንን ለበርካታ አመታት ቀፍድዶ ከያዘው ድህነትና ኋላቀርነት ሊያላቅቁን የሚችሉ በርካታ የልማት ስራዎች እየጎሉ መምጣታቸው ተስፋችንን ይበልጥ ጉልህና ተጨባጭ እንዲሆን እያደረጉት ይገኛሉ፡፡ ከነዚህ ተስፋዎቻችንም ውስጥ የኢንዱስትሪ ፓርኮቻችንና ሜጋ ፕሮጀክቶቻችን ይጠቀሳሉ፡፡
በአገራችን እየተከናወኑ ከሚገኙ 15 የኢንዱስሪ ፓርኮች ውስጥ ሰባቱ ተጠናቀው ወደ ስራ የገቡ ሲሆን ሌሎቹም በግንባታ ሂደት ላይ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ አንጻር በ2025 አጠቃላይ ከ30 በላይ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባትና ወደ ስራ በማስገባት የአገራችን ኢኮኖሚ 20 ከመቶ እንዲሁም ከወጪ ምርቶች 50 ከመቶ በኢንዱስትሪ ለመሸፈን ታቅዶ እየተሰራ ሲሆን፣ይህም ለዘመናት በኋላቀር የግብርና ዘዴ ሲዳክር የነበረውን የአገራችንን ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ መር ለማሸጋገርና መካለኛ ገቢ ያለው ማህበረሰብ ለመፍጠር ትልቅ አቅም ይፈጥራል፡፡
ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ጎን ለጎን እድገቱን ሙሉ ለማድረግና ኢኮኖሚያችንን ወደ ፊት ለማራመድ የሚያስችሉ መንገድ፣ባቡር፣ የሃይል ማመንጫ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ስራዎችም በተፋጠነ ሁኔታ እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ ለኢንዱስትሪ ፓርኮች የሃይል አቅርቦት ችግሮችን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀርፍ የሚጠበቀው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታም ቀጥሏል፡፡ ከአራት አመታት በኋላ ግንባታውን ለማጠናቀቅ ታቅዶ በአዲስ መንፈስ ወደ ስራ ተገብቷል፡፡
ከዚህም ጎን ለጎን ተከማችተው የቆዩ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን በመፍታት የህብረተሰቡን ጥያቄዎች በተሟላ ሁኔታ ለመመለስ ከሁለት ወራት በፊት በአዲስ መልኩ የተዋቀረው የኢፌዲሪ መንግስት ካቢኔ የመቶ ቀናት እቅድ በማውጣት መሰረታዊ ችግሮችን ለመፍታትና በሁሉም ዘርፎች እመርታዊ ለውጥ ለማስመዝገብ እየሰራ ይገኛል፡፡
“ቁጥር ብቻ” እየተባለ የሚተቸውን የትምህርት ስርዓትም ከመሰረቱ በመለወጥ ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያስችል የትምህርት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ በየደረጃው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት እየተካሄደበት ሲሆን በሌሎች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችም የህብረተሰቡን ፍላጎት ባማከለ ሁኔታ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት እየተሰራ ይገኛል፡፡
እነዚህ ተስፋ ሰጪ የልማት ቡቃያዎች ፍሬ አፍርተው የድህነት እና የኋላቀርነት ድርቅን እንዲያለሙ ሰላማችንን መጠበቅ ትልቁ የቤት ስራችን ሊሆን ይገባል፡፡ ምክንያቱም ምንም ያህል የልማት ስራ ቢከናወን ሰላም እና መረጋጋት ከሌለ የዜሮ ድምር ውጤት መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ “እንኳን ዘንቦብሽ እንዲያውም ጤዛ ነሽ” እንዲሉ ገና በመውተርተር ላይ የሚገኘው የአገራችን ኢኮኖሚ በሰላም እጦት ግርሻ ከተመታ ወደ ኋላ ተመልሶ ከታሪክ መዝገብ ላይ እየተፋቀ ያለውን የድህነት እና የረሃብ ስማችንን መልሶ እንዳይተክልብን ጥንቃቄ ማድረግ የሁላችን ሃላፊነት ነው፡፡
ይህ እንዳይሆን ደግሞ ሰላማችንን ሊያደፈርሱ ለሚሞክሩ ሃይሎች ቀይ መስመር ልናሰምርላቸው ይገባል፡፡ ህዝባችንም ሰላምን ለማስከበር በሚደረገው ጥረት ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ ወስዶ ርብርብ ማድረግ አለበት፡፡ የህግ የበላይነትን የማስከበር ጅምሩም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት በድህነት ውስጥ የኖርን ህዝቦች ነን፡፡ ከዚህ በኋላ የሚከሰት ተጨማሪ ድህነት ደግሞ አጥፊያችን መሆኑን መረዳት ይኖርብናል፡፡ የርስ በርስ ግጭትም ድህነትን ከማባባስና አገራችንን ከማውደም ሌላ ምንም አይነት ፋይዳ እንደማይኖረው ተረድተን ለሰላም ዘብ ልንቆም ይገባል፡፡ ለልማት እንጂ ለጥፋት ቦታ ሊኖረን አይገባም፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8/2011