ሠዓሊና የሥነ ጥበብ ታሪክ ተመራማሪ እሰየ ገብረመድህን እንደሚነግሩን፤ የሥዕል ጥበብ በአዲስ አበባና አካባቢዋ ተጸንሶ የተወለደ ነው። የአዲስ አበባ ከተማን መቆርቆር ተከትሎ ፎቶግራፍ ተለመደ። የፎቶግራፍ መለመድ ደግሞ ለዘመናዊ ሥዕል አጋዥ ሆነ።
እዚህ ላይ ግን ተመራማሪውን መሞገት ሳያስፈልግ አይቀርም! ከሥዕልና ከፎቶግራፍ የቱ ይቀድማል? እንዲያውም አንዳንድ ሠዓሊያን እንደሚሉት ደግሞ ፎቶግራፍ ኪነጥበብ አይደለም፤ በልምድ የሚገኝ ሙያ ነው። የባለሙያ እውቀት ቢፈልግም ውጤቱ የካሜራ ነው።
በሌላ በኩል ተመራማሪው እንደሚሉት ሥዕል፣ ከከተማ መቆርቆር ጋር የዘመነ ይሆን? ሥዕል የተጀመረው የሰው ልጅ በዋሻ ውስጥ ይኖር በነበረበት ጊዜ እንደሆነ በተደጋጋሚ የሚነገር ነው። ምናልባት ግን የተመራማሪውን ሀሳብ አምነን እንድንቀበል የሚያደርገን ሥዕሎች በጥንቃቄ የሚቀመጡትና ትኩረት የሚሰጣቸው ከተማ ውስጥ ነው። ዘመናዊ የመጠቀሚያ መሳሪያዎችም የሚገኙት ከተማ ውስጥ ነው፤ ይሄ ለመስፋፋቱ ምክንያት ሊሆን ይችላል።
‹‹ካለምንም ማጋነን የ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ሦስት አሥርት ዓመታት የኢትዮጵያ ሥዕል ፎቶግራፍ ነበር ማለት ይቻላል›› ይላሉ ሰዓሊና ተመራማሪው እሰየ ገብረመድህን። የ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ሦስት አሥርታት ማለት እስከ 1930ዎቹ ያለው ማለት ነው።ይሄ ዘመን ደግሞ ኢትዮጵያ የተለያዩ የዓለም አገራት የገቡባት ጊዜ ነው፤ በተለይም የጣሊያን ወረራም የነበረበት ነው። በእነዚህ አጋጣሚዎች ከሥዕል ይልቅ ፎቶግራፍ ሥራ ላይ ይውል ነበር። ብዙ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶችም የተዋወቁበት ነው። ዳሩ ግን ይሄ በፎቶግራፍ ጥበብ ይያዝ እንጂ ለሥዕል ያደረገው አስተዋፅኦ አሳማኝ አይሆንም፡፡
ተመራማሪው እንደሚሉት፤ ታዋቂዎቹ ሠዓሊ ያን እነ አገኘሁ እንግዳ፣ አፈወርቅ ተክሌ፣ አለ ፈለገሰላም ከነፃነት በኋላ የተገኙ ናቸው። ይሄ ግን ከዚያ በፊት ታዋቂ ሠዓሊያን አልነበሩም ለማለት ያስችለን ይሆን?
የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን በ2008 ዓ.ም ‹‹የኢትዮጵያ ሥነ ጥበብ ቅርሶች›› በሚል ርዕስ አንድ ዳጎስ ያለ የጥናት ስብስብ አሳትሟል። የመድብሉ ሙሉ ይዘት የሥዕል ጥበብ ላይ የሚያተኩር ነው። ይኸው መድብል ጥናቶችንና በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሠዓሊያንን ግለ ታሪክም የያዘ ነው። በዚህ መድብል ውስጥ የ45 ሠዓሊያን ግለታሪክ እና ሥራዎቻቸው ይገኛል። ከ45 ሠዓሊያንና ሥራዎቻቸው ውስጥ አምስቱ ሴቶች ናቸው። በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የአምስቱን ሴቶች ግለታሪክና ሥራዎቻቸውን እናያለን።
ደራሲ በዕውቀቱ ሥዩም ‹‹ሴቶች በዋሉበት›› በሚለው ጽሑፉ ‹‹እንደ እምነታችን እና እንደ ባህላችን ሁሉ ቋንቋችንም ለወንድ ያዳላል።በተለመደው አማርኛ፣ አንድ ሰው ‹‹ወንድ ነው!›› ሲባል ጀግና ነው ልበ ሙሉ ነው እንደ ማለት ነው። አንዲት ሞት የምትንቅ ሴት በጉልህ ብቅ ካለች ‹‹ወንድ ናት! ትባላለች›› ብሎ ነበር። በጽሑፉ ሐተታ ውስጥም በኢትዮጵያ የጦርነት ታሪክ ውስጥ የታሪክ ጸሐፊያን ልብ ያላሏቸውን የብዙ ሴቶች ታሪክ ይነግረናል።ዘመናዊ ጠብመንጃ ከመምጣቱ በፊት፤ ሴቶች ከሰል እና ጨው ወቅጠው የጥይት ባሩድ ያዘጋጁ ነበር።ባሩዱ ‹‹ዳሂራ›› ይባላል። የመጀመሪያው የጦር መሳሪያ ፋብሪካ የእናቶች ሙቀጫ ነበር ማለት ነው። ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ከራስ አዳል ጋር ጦርነት ሊያደርጉ መሆኑ ሲሰማ ሴቶች እንዲህ ብለው ዘፍነዋል።
ሴቶች ተሰብሰቡ እንውቀጥ ዳሂራ
ክርክር አይቀርም ከራስ አዳል ጋራ
‹‹ይሄ የጦርነት ታሪክ ከሥዕል ታሪክ ጋር ምን ያገናኘዋል?›› ትሉኝ ይሆናል፤ ምንም አያገናኘውም! ዳሩ ግን ብዙ ተደብቆ የቀረ የሴቶች ታሪክ መኖሩን ለማመላከት የተጠቀምኩት ነው። በአንድ መድብል ውስጥ ብቻ እንኳን ከ45 ሠዓሊያን አምስት ብቻ ሲገኙ፣ ይሄ ጥበብ ያላቸው ሴቶች አምስት ብቻ ናቸው ማለት አይደለም። (በእርግጥ መድብሉ ይሄንኑም ማጥናቱ ያስመሰግነዋል)። እነዚህ አምስቱ ሴቶች እንኳን የተገኙት በዚህ መድብል ውስጥ ነው። በጦርነትና በፖለቲካ ታሪካችን ውስጥ ብቻ ሳይሆን በኪነጥበቡም ውስጥ የሴቶች ሥራ አልተዘመረለትም። እስኪ እነዚህን አምስት ሴት ሠዓሊያን እነማን እንደሆኑ እናስተዋውቃችሁ።
ሠዓሊ ደስታ ሐጎስ
በትግራይ ክልል ዓድዋ ከተማ በ1944 ዓ.ም ተወለደች። ትምህርቷን በአዲስ አበባ እቴጌ መነን (በአሁኑ የካቲት 12) ትምህርት ቤት ተከታትላለች። ከልጅነቷ ጀምሮ የነበራትን የሥዕል ዝንባሌ በማዳበር ከሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት ተመርቃለች። በዚሁ ሙያ ከአሜሪካ አገር የመጀመሪያ ዲግሪ አግኝታበታለች።
ሠዓሊ ደስታ በአሜሪካ እና አዲስ አበባ በተደጋጋሚ የሥዕል ዓውደ ርዕይ አሳይታለች። ከህንድ ሜዳሊያ፣ ከታንዛኒያ ሜዳሊያና መጻሕፍት፣ ከጎልድ ሜርኩሪ የወርቅ ሜዳሊያና ሰርተፍኬት አግኝታለች።
ከሥራዎቿ ውስጥ፤ ዓይነ ሥውሩ፣ አንድነት፣ ገበያችን፣ የበረሃ ውበት እንዲሁም አዲስ አበባ በመስኮቴ የሚሉት ይጠቀሳሉ። የምትጠቀመውም ረቂቅ (አብስትራክት) የአሳሳል ዘዴ እንደሆነ ይነገርላታል። ሥራዎቿ እውነትን የጨበጡ ሲሆኑ፣ የብርሃን ውበትን እና የሕጻናት ክብካቤ ላይ የሚያተኩሩ ናቸው።
ሠዓሊ ደስታ ሐጎስ ንግድ ሥራ ኮርፖሬሽን የሥነ ጥበባት ዋና ክፍል ኃላፊ በመሆን አገልግላለች።
ሠዓሊ አሚራ አላማሪ
ርዕሳችን ‹‹የኢትዮጵያ ሴት ሠዓሊያን›› ነው የሚለው። እዚህ ላይ ግን አንዲት የተለያየ አገር መጠሪያን የያዘች ሴት ልናስገባ ነው። ኢትዮጵያዊና የመናዊ የሆነች ካናዳዊ ሴት። እንዴት በሦስት አገራት እንደተጠራች መድብሉ ዝርዝር የለውም።
ሠዓሊዋ አሚራ አላማሪ ትባላለች።ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት የተመረቀች ሲሆን፣ ዘወትር ከምትሰራቸው የፈጠራ ሥራዎቿ ጎን ለጎን የሴቶችን ትግል በሙያዋ ትደግፋለች፤ ታንጸባርቃለች።በሥዕል ዓለም አቀፍ ቋንቋን መናገር ይቻላል ብላ ታምናለች።
በግል እና ጋራ ካቀረበቻቸው የሥዕል ዓውደ ርዕዮች መካከል በኩርዲስታን፣ ቱርክ፣ ሻርጃህ፣ ቶሮንቶ፣ ዱባይ፣ ኒዮርክ፣ ኤድመንተን፣ የመን፣ አሊያንስ፣ በአዲስ አበባ ደግሞ፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በሸራተን፣ በብሔራዊ ሙዚየም የታዩ ናቸው።
ሠዓሊ ብርቱካን ደጀኔ
በአዲስ አበባ ከተማ በ1964 ዓ.ም ተወለደች። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷን በትንሳኤ ብርሃን ትምህርት ቤት ከተከታተለች በኋላ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በምስራቅ አጠቃላይ ትምህርት ቤት አጠናቃለች። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት በግራፊክስ አርት በዲፕሎማ በ1988 ዓ.ም ተመርቃለች። ሠዓሊዋ በማስተር የሥነ ጥበብና የቪዲዮግራፊ ስልጠና በ2000 ዓ.ም ሰርተፍኬት፣ በኢሜጅ ግራፊክስ ዲዛይን ትምህርት ቤት በሰርተፍኬት፣ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ባደረገው የሥዕል ውድድር በማሸነፍ ሽልማትና ሰርተፍኬት፣ ዳሽን ቢራ ባደረገው የሥነ ጥበብ ውድድር ሽልማትና ሰርተፍኬት፣ በጀርመን ከቋንቋ ኢንስቲትዩት በ2002 ዓ.ም ሰርተፍኬት ያገኘች ሲሆን፣ በ2008 ዓ.ም በቻይና የኢትዮጵያ ሠዓሊያንን በመወከል ለ40 ቀናት በመንገድ ላይና በገጠር አካባቢ ሥዕሎችን በመስራት ከአምስት አፍሪካውያን ሰዓሊዎች ጋር ዓውደ ርዕይ አሳይታለች። ሰዓሊ ብርቱካን በአገር ውስጥ ካሳየቻቸው ዓውደ ርዕዮች መካከል በጎሹ አርት ጋለሪ፣ በራሺያ ባህል ማዕከል፣ በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሲስ፣ በጣሊያን ባህል ማዕከል፣ በዓለም ጋለሪ፣ በሂልተን ሆቴል፣ በራዲሰን ብሉ ሆቴል፣ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ሙዚየም፣ በአሜሪካ ኤምባሲ፣ በኢምፔሪያል ሆቴል በግልና በጋራ አሳይታለች። ሠዓሊዋ ‹‹ዕለታዊ አዲስ›› በሚባለው ጋዜጣ ላይ በካርቱኒስትነት፣ በናዝሬት ትምህርት ቤት በመምህርትነት፣ በቁምነገር ህትመትና ማስታወቂያ ድርጅት በካርቱኒስትነት፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ‹‹አይ.ፒ.ኤስ.ኢ አር.ቲ.ፒ.ኦ›› በተባለና ሴ.ል መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በኢሉትሬተርነት ሰርታለች።
ሠዓሊ ቅድስት ብርሃኔ
በ1971 ዓ.ም በአዲስ አበባ ተወለደች። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ከጨረሰች በኋላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት በመግባት በ1995 በሥዕል ትምህርት ተመርቃለች። በግልና በጋራ ዓውደ ርዕይ ካሳየችባቸው ቦታዎች ማኩሽ ጋለሪ፣ ኢትዮጵያ ብሄራዊ ሙዚየም፣ ኢ.ሲ.ኤ፣ ላፍቶ ጋለሪ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሥነ ጥበብ ጋለሪ የሚጠቀሱ ናቸው። ሠዓሊ ቅድስት አብዛኛዎቹ ስራዎቿ በሴቶች ህይወትና በዶሮዎች ህይወት ላይ ያተኮረ ነው። በአፍሪካ ህብረት የ50ኛ ዓመት የሥዕል ውድድር ከሦስት አሸናፊዎች ሁለተኛ በመውጣት ስራዋ ተመራጭ ሆኗል።
ሠዓሊ ሚሊዮን ብርሃኔ
በአዲስ አበባ ከተማ በ1981 ዓም ተወለደች። መደበኛ የቀለም ትምህርቷን ከጨረሰች በኋላ አቢሲኒያ የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት የቀለም ቅብና ቅርጻ ቅርጽ በመማር ሰርተፍኬት አግኝታለች። በመቀጠልም እንጦጦ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት በመግባት በቅርጻቅርጽ ልዩ ጥናት ዲፕሎማዋን አግኝታለች። ሠዓሊ ሚሊዮን በግልና በጋራ በብዙ ወርክሾፖችና ኤግዚቢሽን የተሳተፈች ሲሆን፣ ከእነዚህም ቦታዎች መካከል የጎቴ ገብረክርስቶስ ደስታ ሴንተር፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትር፣ አዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል፣ አሊያንስ ኢትዮ ፍራንሲስ፣ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ሙዚየም እንዲሁም ላፍቶ አርት ጋለሪ የሚጠቀሱ ናቸው። በኢትዮጵያ ብሄራዊ ሙዚየም በካስትና ሞልድ ስራ ተቀጥራ ሰርታለች።
የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ‹‹የኢት ዮጵያ ሥነ ጥበብ ቅርሶች›› በሚል ርዕስ ያሳ ተመው መድብል የእነዚህን ሠዓሊያን ግለታሪክ አስነብቦናል። ባለሥልጣኑ በቀጣይ ጥናቱ ምን ይዞልን እንደሚመጣ ባናውቅም በአሁኑ ጊዜ ግን ብዙ ሴት ሠዓሊያን አሉ።እንደ አጠቃላይ የሥዕል ሥራዎች ላይ ትኩረት ባይሰጥም ሴት ሠዓሊያን ግን የሌሉ እስከሚመስል ድረስ ብዙም ሲባልላቸው አይሰማምና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሀሴ 4/2011
ዋለልኝ አየለ