መሪዎች ለህዝብ ሰላም መደፍረስ ምክንያት ሲሆኑና የተጣለባቸውን ታላቅ ኃላፊነት ረስተው ህዝብን ሲዘርፉ፣ ሲጨቁኑና ሲያሰቃዩ ይህንን ተከትሎም ሮሮ ሲበዛ ‘ህዝቤን ልቀቁ’ የሚል ድምፅ ከሰማያት እንደወጣ ታላቁና ቅዱሱ መጽሐፍ ያስነብባል።
መሪነት የራስን ክብርና የተደላደለ ህይወት በመተው ለህዝብ መኖር፣ እንቅልፍና ዕረፍት አጥቶ ለህዝቦች ህይወት መሻሻል መትጋት፣ ለሃገርና ለህዝብ መስዋዕት መሆንን የመሳሰሉ ቅዱስና አኩሪ ተግባራት የሚፈጽሙበት አውድ ነው። ይኸን ትልቅ ኃላፊነት ለተረዳ መሪነት ምን ያህል ከባድና ኃላፊነትን የሚጠይቅ ትልቅ ተግባር መሆኑ አይሰወርበትም።
ከላይ የጠቀስነው የመሪነት ታላቅ ኃላፊነት ገብቷቸው በዚያው ልክ ለህዝብና ለአገር የኖሩና ወጣትነታቸውን፣ ቤተሰባዊ ህይወታቸውንና መተኪያ የሌለው ህይወታቸውን ሰውተው ዓለም አሁን ድረስ በአድናቆት ስማቸውን የሚያነሳና የሚዘክረው እንቁና ብርቅዬ መሪዎችን ምድራችን አፍርታለች። እነዚህ ታላላቅ መሪዎች ጊዜያዊውን ምድራዊውን ክብርና ዝና ንቀው ዝቅ ብለው በመስራት አገርና ህዝባቸውን ከፍ አድርገዋልና ዘላለማዊ ዝክርና ምስጋና ይበዛባቸው ይሆናል እንጂ በፍጹም አያንሳቸውም።
ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል እንዲሉ ከዚህ በተቃራኒው ይኸን ትልቅና ክቡር ኃላፊነት በባሌም በቦሌም ብለው የተቆጣጠሩና ህዝብ የጣለባቸውን ኃላፊነት የዘነጉ ከንቱ መሪዎች መሪነትን ለጭቆና፣ ለብዝበዛና ለግል ህይወት መደላድል ሲጠቀሙበት ተስተውሏል። አሁንም እየተስተዋለ ነው። እነዚህ እኩይ መሪዎች ሳይወድና ሳይፈቅድ በላዩ ላይ ጉብ ባሉበት ህዝብ ላይ የሚያደርሱት ግፍ አልበቃ ብሏቸው ከሌላ ወንድም ህዝብ ጋር እያጋጩ በደም መነገድ መለያቸው ነው።
በአገራችን በኢትዮጵያም እየሆነ ያለው ይሄ ነው። ጨዋ፣ መልካምና የሃይማኖትና የብሔር ልዩነቱን እንደጌጥ ተቀብሎ በፍቅር ዘመናትን የዘለቀው ህዝባችን የሚፈልገውንና ይሰራልኛል የሚለውን መሪ ለመምረጥ ብዙም አልታደለም። ከዚህ ይልቅ እኛ እናውቅልሃለን በሚሉ ፊውዳላዊ አምባገነናዊ መሪዎች ስቃዩን ሲቆጥር ኖሯል። ለከፋ ድህነት ተዳርጎም አስከፊ ህይወትን እየመራ ያለው የስንዴነት ባህሪ በሌላቸው እንክርዳድ መሪዎች መዳፍ ሥር ወድቆ በመኖሩ ነው።
ህዝብ ከድህነትና ኋላቀርነት የሚወጣበትን ጥርት ያለ እቅድ አቅዶ የሚያሻግረውን መሪ ለዘመናት ቢመኝም ከዚህ ይልቅ የራሳቸውን ህይወት አደላድለው ሲኖሩና እነሱ በፈጠሩት የተዛባ አካሄድ ጦርነት የሰርክ ሥራው እስኪመስልና ጦር ናፋቂ እስኪባል ህዝባችን የመከራን ጽዋ ለመጎንጨት ተገዶ ኖሯል።
ህዝብ እንደ ህዝብ ተፋቅሮ፣ ተቻችሎና ተከባብሮ የመኖር ችግር ፈጽሞ የለበትም። ህዝብ ከህዝብ የሚጋጨው፣ የሚፈናቀለውና የሚሞተው በሽተኛ ፖለቲከኞች ጣልቃ ሲገቡበትና አወናብደውና አሳስተው በተዛባ መንገድ ሲመሩት ብቻ ነው። በምሥራቃዊው የአገራችን ክፍል ጅግጅጋ ባለፈውና በአሁኑ ዓመት ያለውን ተቃራኒ ሁኔታ መመልከት ከላይ ያነሳነውን ሃሳብ መሬት ያስረግጥልናል።
አምና የሶማሌ ክልል ኃላፊነት በማይሰማቸው አረመኔና፣ በደም ንግድ በሰከሩ መሪዎች ሲመራ አብሮት ከኖረውና ወንድምና እህቱ ከሆነው ህዝብ ጋር አጋጭተውት ንብረት እንዲወድም ህይወት እንዲጠፋና ቤተ እምነቶች ሳይቀሩ እንዲቃጠሉ በማድረግ ታሪክ የማይዘነጋውን የጥፋት አሻራ አሳርፈዋል።
እኒያ የጥፋት መሪ የሆኑ ትናንሽ ሰይጣኖች /እንደ አቶ ሽመልስ አብዲሳ አገላለጽ/ ከህዝቡ ሲለቁ ግን ጅግጅጋ የህዝቦች የአብሮነትና የፍቅር መናኸሪያነቷን ቀጥላለች። ተጠቂ ወገኖቹን ከጥፋት ኃይሎች ሸሽጎ ያስመለጠውና የክፉ ቀን ደጀን የሆነው የጅግጅጋና የአካባቢው ህዝብ ከክልሉ መንግስት ጋር በመተባበር ተጎጂዎችን አቋቁሟል፣ የመኖሪያና የንግድ ቤቶቻቸውን ጠግኗል፣ ቤተ መቅደሶችን አድሶና አሳምሮ ወንድማዊነቱን ገልጿል።
ከላይ እንደገለጽነው አጥፊ መሪ እንጂ አጥፊ ህዝብ፤ በደም የሰከረ መሪ እንጂ ህዝብ የለምና አሁንም ቢሆን የበግ ለምድ ለብሰው ከመልካም መሪዎች ጋር የተደባለቁና ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ አመራሮችን “ህዝቤን ልቀቁ” ብሎ ገለል ማድረግ አስፈላጊ ነው እንላለን።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ፣ ነሀሴ 4/2011