የኢትዮጵያውያን መዲና እንዲሁም የአፍሪካ ህብረትና የበርካታ ዓለምአቀፍ ተቋማት መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባ ምንም እንኳን ዕድገቷና ልማቷ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ቢመጣም ከብዙዎቹ የአፍሪካ አገራት ዋና ከተሞች ጋር ስትነፃፀር በብዙ ርቀት ቀደ ኋላ እንደ ቀረች ይነገራል፡፡ በተለይም ደግሞ እየጨመረ ከመጣው የነዋሪ ቁጥር ጋር የሚመጣጠን የመኖሪያ ቤትና መሰረተ ልማት ዝርጋታ የሌላት መሆኑ ለኑሮ ምቹና ተመራጭ እንዳትሆን አድርጓታል፡፡
የከተማዋ አስተዳደር የነዋሪዎቹን ችግር ለመፍታት ያስችለው ዘንድ በራሱም ሆነ በግል ባለሃብቱ ዕድል በመስጠት የተለያዩ የቤትና የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን አከናውኗል፤ በማከናወንም ላይ ይገኛል፡፡ ይሁንና ከችግሩ ስፋት አንፃር የነዋሪውን መሰረታዊ ጥያቄዎች ዛሬም ድረስ መመለስ አልተቻለም፡፡ በተለይም ደግሞ ከሁሉም ችግሮች የከፋው የጋራ መኖሪያ ቤቶች የግንባታ ሂደት መዘግየት አስተዳደሩን ተስፋ አድርገው ለዘመናት ሲጠበቁ የነበሩ ነዋሪዎች ልብ በማዘሉ ይተቻል፡፡ ለነገሩ ዕድሉ ደርሷቸው የቤት ባለቤት የሆኑ ጥቂት የማይባሉ ነዋሪዎች የተላለፈላቸው ቤት ከፍተኛ የሚባል የጥራትና የመሰረተ ልማት ያለመዘርጋት ችግር እንዳለበትም ይደመጣል፡፡ ቁሳቁሶቹ የጥራት ችግር ያለባቸው በአግባቡ ያልተገጠሙ በመሆናቸው ለተጨማሪ ወጪመዳረጋቸውን ነው የሚናገሩት፡፡
አዲስ ዘመን ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች የቤቶቹ የግንባታም ሆነ የዕጣ ማስተላለፉ ሂደት ውስብስብና የተንዛዛ መሆን በአስተዳደሩ ላይ ያላቸውን እምነት እያሳጣቸው መሆኑን ነው የሚጠቅሱት፡፡ ወይዘሮ ማርታ ተስፋዬ የተባለች የከተማዋ ነዋሪ እንደምትናገረው፤ በ1987 ዓ.ም የአዲስ አበባ መስተዳድር ለከተማዋ ነዋሪዎች ባወጣው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ምዝገባ ላይ ስትሳተፍ የ18 ዓመት ወጣት ነበረች፡፡ በወቅቱ ምዝገባውን ያካሄደችው በወላጅ እናቷ ግፊት ስለነበር ቀናት ቀናትን እየወለዱ እሷም ትዳር ይዛ የሦስት ልጆች እናት እስክትሆን ድረስ ያለመታደል ሆኖ የከተማ አስተዳደሩ ለነዋሪዎቹ በገባው ቃል መሰረት የቤት ባለቤት መሆን አልቻለችም፡፡
«መጀመሪያዎቹ ዓመታት ላይ ዕድሜዬ ገና ስለነበር ዕጣው ሲተላለፍ ብዙም አልጓጓም ነበር፤ ነገር ግን ትዳር ከያዝኩ በኋላ የቤት ኪራይ ዋጋ መናርና በአከራዮቼ በሚደርስብኝ እንግልት ምክንያት ዕጣው በተላለፈ ቁጥር ጉጉቴ እየጨመረ መጣ» የምትለው ወይዘሮ ማርታ፤ የቤቶቹ ግንባታም ሆነ የመተለለፉ ሂደት በጣም አዝጋሚ በመሆኑ የቤት ባለቤት እሆናለሁ የሚለውን ተስፋ እርግፍ አድርጋ እንደተወችው ትገልፃለች፡፡
እንደ ወይዘሮ ማርታ ሁሉ በሺዎች የሚቆጠሩ የከተማዋ ነዋሪዎች አስተዳደሩ ከነገ ዛሬ የቤት ባለቤት እንሆናለን በሚል ከእለት ጉርሳቸው እየቆጠቡ ተራቸውን በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹም በግንባታውም ሆነ ማስተላለፍ ሂደቱ መዘግየት ተስፋ ቆርጠው ቁጠባቸውን ማቋረጣቸውን በተለያየ መንገድ ሲገልፁ ይደመጣል፡፡ በተለይም ከ2008ዓ.ም ወዲህ አስተዳደሩ የቤት ማስተላለፍ መርሃግብሩ የቅሬታ ምንጭ እየሆነ መጥቷል፡፡
የአምስት ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ ዓለምፀሐይ ገብረእግዚአብሄር በበኩላቸው፤ በአስተዳደሩ ውስብስብ አሰራር ምክንያት ከቤት ባለቤትነት ይልቅ ቤት አልባ መሆናቸውን ይገልፃሉ፡፡ ግለሰቧ እንደሚናገሩት፤ በቤተሰቦቻቸው ስም በነበረ ጎላ ሚካኤል ከሚባል የቀበሌ ቤት ለዓመታት ኖረዋል፡፡ ይህ የቀበሌ ቤት በስማቸው ያልተመዘገበ በመሆኑ ሌሎችም የቤተሰብ አባላት የሚኖሩበት በመሆኑ በ1997 ዓ.ም አስተዳደሩ ባወጣው የኮንዶሚኒየም ቤት ምዝገባ አካሂደዋል፡፡ ከዘመዶቻቸው ጋር የሚቋደሱት በዚሁ የደባል ኑሮ በመመራታቸው ምክንያት ከዓመት ዓመት ዕጣው ወጥቶልኝ ከልጆቼ ጋር በነፃነት እኖራለሁ በማለት ተስፋ ሰንቀው ቆይተዋል፡፡
በድንገት ግን ይህንን ተስፋቸውን የሚያቀርብ ዜና ሰሙ፡፡ ይኸውም አካባቢያቸው በመልሶ ማልማት የሚፈርስ በመሆኑ ቤት ለፈረሰባቸው የቀበሌ ቤት ነዋሪዎች ሁሉ ምትክ ቤት ያለዕጣ የሚሰጥ መሆኑ ነው፡፡ ወይዘሮ ዓለምፀሐይ ግን ተስፋቸው ብዙም ሳይቆይ መጨለሙን ይገልፃሉ፡፡ «የክፍለ ከተማው አስተዳደር ከዚህ ቀደም በስምሽ የቤት ዕጣ የወጣ በመሆኑ ድጋሚ ቤት አይሰጥሽም ብለው የነበረኝን ተስፋ ወዲያውኑ እንደጉም አጥፍቶታል» ይላሉ፡፡ ይህንን መርዶ በሰሙ ማግስትም ቁጥራቸውን ይዘው በስማቸው ወጣ ከተባለበት ቤት ድረስ በመሄድ ሲያጣሩም አንድ ዶክተር በተመሳሳይ ቁጥር ቤቱ ወጥቶለት የተደላደለ ኑሮ እየኖረ መሆኑን ማረጋገጥ ችለዋል፡፡ ግለሰቧ የተለያዩ ኃላፊዎችን ቢሮ ቢያንኳኩም እስካሁን ድረስ ምላሽ ማግኘት አለመቻላቸውንና ከሁለት ያጣ ሆነው መቆየታቸውን ነው የሚያስረዱት፡፡
አስተዳደሩ ከነዋሪዎቹ የሚነሳበትን ዘርፈ ብዙ ቅሬታ ለመፍታት ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ መሆኑን በተለያየ ጊዜያት ሲገልፅ ቆይቷል፡፡ በተለይም በተያዘው በጀት ዓመት መጀመሪያ ከጥራት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን በመፍታት ጥቅምት 30 ቀን 2011 ዓ.ም ለነዋሪዎች ቤት አስተላልፋለሁ ቢልም ዳግም የዕጣ መውጫ ቀኑን አራዝሟል፡፡ ቤቶቹ ለተጠቃሚዎች የሚወጡበት ቀን ማስተላለፍ ያስፈለገው በዋናነት የመረጃና ደህንነት ኤጀንሲ የዕጣ አወጣጥ አሰራር ግልፅነት የጎደለውና በህግ ጥያቄ የሚያስነሱ ጉዳዮች በመገኘታቸው እንደሆነ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ መግለፁ ይታወሳል፡፡
በቢሮው የአስተዳደር ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ጀማል ሃጂ እንደሚያስረዱት፤ አስተዳደሩ በአዲስ መልክ አመራር ሲቀየር ከህብረተሰቡ በተደጋጋሚ የሚነሱ ቅሬታዎችን በመንተራስ የቤቶቹ የግንባታም ሆነ ዕጣ የሚተላለፍበት ሂደት የግልፅነትና የፍትሃዊነት ችግር ያለባቸው በመሆኑ አሰራሩን መፈተሽ አስፈልጓል፡፡ በዋናነትም ‹‹ሶፍት ዌሩ›› የሚመራው በአዋጅ የማስተዳደር ስልጣን ላልተሰጠው የመረጃ ደህንነት ኤጀንሲ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የ20/80ቤቶች መረጃ በሦስተኛ ወገን የሚፈተሽበትና እንደአስፈላጊነቱ የሚቀየርበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ይህም ለበርካታ ዓመታት የህዝብ ቅሬታ ምንጭ ሆኖ ቆይቷል፡፡
ይህም የሆነበት ዋነኛ ምክንያት አስተዳደሩ በወቅቱ የሰው ኃይልና የቴክኖሎጂ አቅም የሌለው በመሆኑ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ «በአሁኑ ወቅት ከዚህ ለማውጣት በራሱ ባበለፀገው ድርጅት አስጠግኖ ወደ ሥራ ማስገባት ሰፊ ተግባር ሲከናወን ቆይቷል» የሚሉት ኢንጅነር ጀማል፤ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ባለሙያዎች ተመድበው ሥራውን እየሰሩ መሆናቸውን ያመለክታሉ፡፡ ይህም ግልፅነት፣ የፍትሃዊነትና የተጠያቂነት ጥያቄዎች ከስር መሰረቱ ለመፍታት ትክክለኛ ሥራ ለመስራት የሚያግዝ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በተመሳሳይ ከ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን የማስተዳደር ስልጣን ለአስተዳደሩ የተሰጠ ቢሆንም እስካሁን ድረስ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቤቶቹን ሲያስተዳድር መቆየቱን ያስታውሳሉ፡፡ ይህም የህግ ጥሰት የሚያመጣ በመሆኑ ከባንኩ ጋር በመነጋገር የተገቡ ውሎችን የማፍረስ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንና የማስተዳደር ኃላፊነቱንም ኤጀንሲው መረከቡን ይናገራሉ፡፡
ለዚህ ደግሞ መመሪያ የማዘጋጀት ሥራ ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ የዕጣ ማስተላለፍ ሂደቱ እንዲዘገይ መደረጉን ያስረዳሉ፡፡ «ከሶፍት ዌሩና ከመመሪያው ጋር የተያያዙ ሥራዎች እንደተጠናቀቁ ቤቱ የሚተላለፍበት ቀን ብዙ ሳይርቅ እንገልፃለን» በማለትም ይናገራሉ፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን የቤት ተመዝጋቢዎችን መረጃ ያዛቡ ተቋማትና አካላትን ኦዲት የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም ቤቶቹ የሚተላለፉበት ተጨባጭ ምክንያቶች በመኖራቸው እንጂ እንዲሁ ጊዜ ለማራዘም አለመሆኑን ህብረተሰቡ ሊገነዘብ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
በቢሮው የግንባታ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ኢንጂነር ዘሪሁን አምደማርያም በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ በአጠቃላይ በ20/80 እና በ40/60 የቤት ፕሮግራሞች ውስጥ በዚህ ዓመት ለተጠቃሚዎች ይደርሳሉ ተብሎ ከታቀዱት 132ሺ ቤቶች ውስጥ በአሁኑ ወቅት በአብላጫ 42ሺ 341 የግንባታ ሂደታቸው ተጠናቆ ለተጠቃሚዎች የሚተላለፉበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡
«የቤቶቹ ግንባታ ከ80 እስከ 90 በመቶ የተጠናቀቁ ሲሆን፣ ከማስተላለፍ ጋር ተያይዞ የሚመጣው የህንፃው ውስጥ ቀሪ የማጠናቀቂያ ሥራዎች ተለይተው የሚታወቁ ስለሆኑ፣ ብዙዎቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚሰሩ ይሆናል» ይላሉ፡፡ የተወሰኑት ደግሞ የቤቶቹ ባለቤቶች ከታወቁ በኋላ የሚሰሩ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ከመሰረተ ልማት ግንባታና የማጠናቀቂያ ሥራዎች ጋር በተያያዘም የውሃና ፍሳሽ፣ የመብራትና የመንገድ ግንባታቸው ከሁለት ወር እስከ ሁለት ዓመት በሚሆን ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ነው የሚጠቅሱት፡፡
ኢንጂነር ዘሪሁን ከግንባታ ጋር ተያይዞ ቤቶች ግንባታ 80 እና 90 በመቶ ተጠናቋል እየተባለ ለነዋሪዎች የሚተላለፍበት መንገድ ከህብረተሰቡ ቅሬታ በተደጋጋሚ የሚቀርብበት መሆኑን ተጠይቀው ሲመልሱ፤ «የሚገነባው የመኖሪያ መንደር ነው፤ ውሃ መንገድ ፍሳሽ ማስወገጃ ኑሮ ለመጀመር የግድ ነው። የማይደበቀው ነገር የፕሮጀክት ማኔጅመንት ችግሮች ነበሩበት፡፡ ሁሉም መሰረተ ልማት ዝርጋታዎች የመዘግየት ችግሮች ነበሩ፡፡ ይህ ማለት በቅንጅት አይሰራም ማለት አይደለም» ይላሉ፡፡ ቅንጅቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱንና ከዚህም በበለጠ እየተሻሻለ መሄድ የሚጠበቅበት መሆኑን ይገልፃሉ፡፡
«መሰረታዊው ችግር ውሃ፣ መብራትና መንገድ በሌለበት ወደ ቤቶቹ እንዲገቡ ሰዎችን ማስገደዱ ነው» የሚሉት ኢንጂነር ዘሪሁን፤ በአሁኑ አሰራር ግን የሚመለከታቸው አካላት በፍጥነትና በቅንጅት እንዲሰሩ እየተደረገ መሆኑን ነው ያብራሩት፡፡ ከቤቶቹ ግንባታ ጥራት ጋር ተያይዞ በህብረተሰቡ የሚነሳውን ቅሬታ ለመፍታትም የቤት ማስተላለፉ ሥራ ከተካሄደ በኋላ ከነዋሪው ጋር በመነጋገር አቅም ያለው በራሱ የሌለው በአስተዳደሩ ወጪ እንደየፍላጎታቸው የሚጠናቀቅ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ግንባታ ከተጀመረበት ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ከ278ሺ 674 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተገንብተዋል፡፡ በመገንባትም ላይ ይገኛሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥም እስካሁን ከ12ቱ ዙር ከ182ሺ 600 ያላነሱ ቤቶችን ለህብረተሰቡ እንዲተላለፉ ተደርጓል፡፡ አሁን ላይ በአጠቃላይ እየተገነቡ ካሉት 94ሺ በላይ ቤቶች ውስጥ 21ሺ 720 ቤቶችን የግንባታ ደረጃቸው ከ85 እስከ 98 በመቶ የተጠናቀቁ በመሆናቸው እና ከነዚህም ቤቶች ጋርም ለሱቅ አገልግሎት የሚውሉ1ሺ 171 በድምሩ 22ሺ891 ቤቶችን ለአዲስ አበባ ቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ ለማስረከብ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በማጠናቀቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ የ40/60 የቁጠባ ቤቶች ልማት ፕሮግራም የተቋቋመው በ2005 ዓ.ም አጋማሽ ሲሆን በዚህ ጊዜ ቆይታው እየተገነቡ ካሉት 39ሺ388 የቁጠባ የጋራ ህንፃዎች መካከል የሰንጋተራና የክራውን ሳይቶች 1ሺ 292 ቤቶች ለመጀመሪያ ጊዜ በ2010ዓም ለተጠቃሚ ህብረተሰብ ማስተላለፍ ተችሏል፡፡
እንደ ኢንጅነር ዘሪሁን ማብራሪያ፤ 40/60 ቁጠባ ቤቶች ኢንተርፕራይዝ ተመዝግቦ ከሚጠባበቀው ቤት ፈላጊ አንፃር የግንባታ ፍጥነቱ የተጓተተ በመሆኑ ተቋሙን በአደረጃጀት፣ በአሰራር በሰው ኃይልና በማስፈፀም አቅም ዙሪያ ያሉበትን አጠቃላይ ችግሮች በመፈተሽ ለውጥ እንደሚያስፈልገው በመታመኑ የራሱን ‹‹ሪፎርም›› በመስራትና በማስተካከል በአሁኑ ወቅት ከ38ሺ በላይ የሚሆኑ ቤቶችን ግንባታ በአዲስ መንፈስ በመነሳሳት እየተሰራ ይገኛል፡፡
«ቀደም ሲል በነበረው አሰራር 20ሺ ቤት ለመገንባት የተሰራው አደረጃጀት ከፍተኛ ልምድና ብቃት ያላቸውን አንጋፋ ሙያተኞችን የሚጋብዝ ባለመሆኑ የግንባታ ሥራው በጀማሪ ባለሙያዎች መከናወኑ ከጥራትና ከሙያ ብቃት አንፃር ይታዩ ነበር» በማለትም ኢንጅነር ዘሪሁን ተናግረዋል፡፡ የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት ጭምር ሪፎርሙን ማሳካት ለነገ የሚተው እርምጃ ባለመሆኑ ይህንኑ በመተግበር በአሁኑ ወቅት ግንባታው ከደረጃ 1እስከ3 ባሉ ተቋራጮች ብቻ እንዲከናወን በማድረግ ቀሪ ከ38 ሺ በላይ ቤቶችን ምቹና ፅዱ የመኖሪያ መንደር ለመፍጠር ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡