
የሲዳማ ክልል በርካታ የተፈጥሮ ሀብቶች መገኛ ነው። ክልሉ ያለው ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብት ከራሱ አልፎ ለሀገር ይተርፋል። በተለይ በግብርና ምርቶቹ የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ ለሌሎች ለመትረፍ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ። የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች፣ የጥራጥሬ ሰብሎች፣ የቡና፣ የወተት እና ሌሎች የግብርና ምርቶች በብዛት በክልሉ በመመረት ላይ ናቸው።
በክልሉ ለመስኖ ልማት ትኩረት ተሰጥቶ በመሥራቱ፤ የግብርና ምርቶችን ዝናብ ጠብቆ ከማምረት ባሻገር በመስኖ በማልማት ትልልቅ ለውጦች እና አበረታች ውጤቶች እየታዩ ናቸው። በክልሉ ከለውጥ በኋላ ከመስኖ ልማት አንጻር ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ የሚገልጹት የክልሉ የመስኖ ልማት ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር አቶ አሸናፊ ጎበዛየሁ ናቸው።
እሳቸው እንደሚሉት፤ በክልሉ ለመስኖ ልማት ትልቅ ትኩረት በመሰጠቱ የመንግሥትን የመስኖ ልማት የፖሊሲ አቅጣጫን ተከትሎ የተለያዩ ደንቦች ላይ በመመሥረት የተሻለ ሥራ መሥራት ተችሏል። ከእነዚህ መካከል በመንግሥት ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራበት ያለው የቤተሰብ ብልፅግና አንደኛው ነው። በክልሉ ‹‹የቤተሰብ ብልፅግና ፓኬጅ›› መስኖን እንደአንድ ምሰሶ በመውሰድ ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው።
የክልሉ የመሬት መጠን አነስተኛ ነው። ይህን ተከትሎ ያለውን ሀብት በአግባብ ጥቅም ላይ ማዋል ያስፈልጋል። በመጀመሪያ በክልሉ የሚገኙ ሀብቶችን በደንብ በማጥናት የትኛው አካባቢ ላይ መስኖ ቢለማ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ይቻላል? የሚለውን ለመለየት ሙከራ ተደርጓል። የክልሉ ሀብት ከተለየ በኋላ፤ የክልሉ አግሮኢኮሎጂ በብዙ ቦታዎች ስለሚከፈል መንግሥት ባስቀመጠው የትኩረት አቅጣጫ መሠረት በቆላማ አካባቢዎች በመስኖ ማልማት ትኩረት ተሰጥቶታል። በዚህ መሠረት ሀዋሳና ወንዶ ገነት ላይ ብዙ ሥራዎች እየሠሩ ናቸው።
በሀዋሳ አብዛኛው አካባቢ የገጸ ምድር ውሃ የለም። በእነዚህ እና በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች መስኖን ለመጠቀም የሚቻልበት መንገድ ለማመቻቸት ብዙ ሚሊዮን ብር ተበጅቷል። በዚህም አምስት ትላልቅ ጥልቅ ጉድጓዶች ማዘጋጀት የተቻለ መሆኑን እና ከ250 እስከ 300 ሜትር ጥልቀት ያላቸው ጉድጓዶች ተቆፍረው ሥራው መጀመሩን ያመላክታሉ።
ከእነዚህ አምስት ፕሮጀክቶች መካከል ትልቁ እንደሞዴል የሚታይና ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ረገድ የፀሐይ ኃይል (ሶላር ኢነርጂ) መጠቀም ያስቻለ 150 ሄክታር መሬት የሚያለማ የመስኖ ፕሮጀክት መኖሩን ይገልፃሉ። አጠቃላይ በሀዋሳ ዙሪያ ብቻ በጥልቅ ጉድጓድ በመስኖ ፕሮጀክቶች የሚለሙ ወደ 500 ሄክታር መሬት መኖሩን ይናገራሉ። አያይዘውም ሀዋሳ ዙሪያ የሚለሙትን የመስኖ ፕሮጀክቶች ለሲዳማ ክልል ሞዴል ለማድረግ በማሰብ፤ በክልሉ ፕሬዚዳንት የሚመራ ኮሚቴ ተዋቅሮ ብዙ ሥራዎች መሠራታቸውንም አስታውቀዋል።
ምክትል ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት፤ የመስኖ ግንባታን ብቻ መገንባት ትርጉም የለውም። የለማና ብዙ ብር የወጣበትን የመስኖ ፕሮጀክት ለተጠቃሚ በሥነሥርዓት እንዲተላለፍ ማድረግ ያስፈልጋል። እስከ አሁን በኢትዮጵያ የሚታወቀው የውሃ ተጠቃሚ ማኅበር ደንብ የሚል ብቻ ነበር። አሁን በሲዳማ ክልል ለየት ባለ መልኩ ከውሃ ተጠቃሚዎች ማኅበር ውጪ ኢንተርፕራይዞች ተቋቁመዋል። ለእዚህም በክልሉ ምክር ቤት አዲስ ደንብ በማቋቋም ‹‹የመስኖ ውሃ ተጠቃሚነት ማኅበራት ደንብ›› ን በማፅደቅ ወደ ሥራ ተገብቷል።
ከእዚህ ጎን ለጎን እነዚህ የመስኖ ፕሮጀክቶች ለአርሶ አደሩ ብቻ ሳይሆን፤ ለሌሎች ወጣቶችም የሥራ ዕድል መፍጠርና ተጠቃሚ መሆን ስላለባቸው በኢንተርፕራይዝ ደረጃ እንዲቋቋሙ ያፀደቀ መሆኑንም ይናገራሉ።
ሀዋሳ ዙሪያ ከአምስቱ ፕሮጀክቶች ጋር ተያይዞ ለሃምሳ ሦስት ሰዎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል። እንዲሁም ወንዶገነት አካባቢ ለጊዜውም ቢሆን እንደኢንተርፕራይዝ እንዲደራጅ ከማድረግ፤ ጎን ለጎን መስኖን ለምግብ ዋስትና እና ለሥራ ዕድል ፈጠራም እንዲያገለገል የሚያደርግ ሥራ ተሠርቷል።
በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ በሀዋሳ ዙሪያ ጥቅም ላይ በዋሉት መስኖዎች የተመረቱ ምርቶች ለሀዋሳ ብቻ ሳይሆን፤ ለክልሉ እና ብሎም ለሀገሪቱ ተደራሽ ተደርገዋል። ውሃ ተጠቃሚ ማኅበራት እና ኢንተርፕራይዞች ቀደም ሲል ብዙ ገንዘብ ቢሰበስቡም ለጥገና የመጠቀም አቅም እንዳልነበራቸው ገልጸው፤ አሁን ላይ ኢንተፕራይዞቹ በሁለትና በሦስት ወር ብቻ ከ300ሺ ብር በላይ ሰብሰበው ራሳቸውን እያደራጁ ይገኛሉ ሲሉ አብራርተዋል።
ምክትል ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤ የመስኖ ልማት ዋና ዓላማ ማኅበረሰቡን መስኖ በማስጠቀም በምግብ ራሳቸውን ማስቻል እና ከራሳቸው አልፈው አካባቢው ላለው ማኅበረሰብ በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማገዝ ነው። ይህንን ለማረጋገጥ ክልሉ የቤተሰብ ብልፅግና ፓኬጅ ቀርጾ፤ ከአስራ ስድስት ወረዳዎች በላይ ለይቶ በ32 መንደሮች የደሃ ደሃ የሚባሉትን ለመደገፍና ለማዳረስ አስቦ ብዙ ሥራዎች እየሠራ ይገኛል። እነዚህ 32ት መንደሮች በመስኖ ብቻ ሳይሆን በሌማት ትሩፋት፣ በወተት፣ በዶሮ እና በመሳሰሉ የተለያዩ ፓኬጆች የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ መስኖን እንደ አንድ ግብዓት መጠቀም እንዲችሉ እየተደረገ ይገኛል።
መስኖ አብዛኛውን ጊዜ ዝናብ በሌለባቸው ጊዜያት ሥራ ላይ የሚውል በመሆኑ፤ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው ሰብሎች የሚመረትበት ነው ያሉት አቶ አሸናፊ፤ እንደ ቲማቲም፣ ሽንኩርት፣ ቃሪያ፣ ድንች፣ ጥቅል ጎመን የመሳሰሉት ከተመረቱ በኋላ ወደ ገበያ ሲወሰዱ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው ምርቶች ላይ ትኩረት ተደርጎ ቢሠራ ውጤታማ መሆን ይቻላል ብለዋል።
በመስኖ እየለሙና እየተመረቱ ያሉ ሰብሎች የክልሉን ገበያ ከማረጋጋት ባለፈ፤ ቲማቲም፣ ሽንኩርት የመሳሰሉ እና ሌሎችም በክልሉ ያልተለመዱ የፍራፍሬ አይነቶችን ጨምረው እየተመረቱ መሆኑን መዘንጋት እንደማይገባ ይገልጻሉ። በሌላ በኩል የመስኖ ልማቱ ለወጣቱም የሥራ ዕድልን በመፍጠር አስተዋፅዖ እያበረከተ እንደሆነ ያመላክታሉ።
‹‹ውሃ ትልቅ ሀብት ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የምናወጣው ወጪ ከፍተኛ በመሆኑ ያለንን ሀብት ጥቅም ላይ ስናውል የተሻሉ ምርቶችን ለማምረት ካላዋልነው ከጠቀሜታ ይልቅ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል። ስለዚህ ያለው ተሞክሮ እንደሚያሳየው የተሻለ ገቢ ለማግኘት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸውን ሰብሎች መጠቀም ይገባል። ›› ሲሉ አስገንዘበዋል።
በተጨማሪ በመስኖ ፕሮጀክቶች ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ከመጠቀም አንጻር በሀዋሳ ዙሪያ ያሉ ፕሮጀክቶች ላይ የተጀመሩ ሥራዎች እንዳሉ ገልጸው፤ በፀሐይ ኃይል በ(ሶላር) እየለማ ያለው 150 ሄክታር መሬት ጥሩ ለውጦች እየታዩበት ነው። አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለመጀመር መነሻ በጀታቸው ከፍተኛ ቢሆንም፤ ጥቅም ላይ ከዋሉ በኋላ ኦፕሬሽንና ጥገና ላይ ሲደርሱ ዋጋቸው በዚያው ልክ እየቀነስ ይመጣል ሲሉ ያመላክታሉ። አብነት ጠቅሰው ሲያስረዱ፤ ነዳጅ ከውጭ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እየገባ በመሆኑ ነዳጅ ከመጠቀም ይልቅ፤ አዳዲስ ቴክኖሎጂ በመጠቀም መስኖዎችን ወደ ሶላር ኢነርጂ መቀየር ይቻላል። በእዚህም የነዳጅ ወጪን ከመቀነስ በተጨማሪ ኦፕሬሽንና ጥገና ላይ እምብዛም አያስቸግሩም ሲሉ አስረድተዋል።
ነዳጅና የመብራት ኃይል ከመጠቀም ይልቅ ይበልጥ አዋጭ የሚሆነው በሶላር ኢነርጂ መጠቀም በመሆኑ፤ በሲዳማ ክልል ደረጃ በቀጣይ የሚጠኑ ፕሮጀክቶች እነዚህን መሠረት ያደረጉ ወደ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የሚወስዱ መንገዶችን እየተከተሉ መሆኑን ያመላክታሉ።
እስካሁን ተገንብቶ ጥቅም ላይ የዋለው በክልሉ እስከ 5ሺ ሄክታር መሬት የሚሆኑት ብቻ መሆናቸውን አቶ አሸናፊ አመላክተዋል። ከክልሉ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ደረጃ ግንባታቸው የተጠናቀቀ 50 ፕሮጀክቶች እንዳሉ ጠቅሰው፤ እነዚህም የኦፕሬሽንና የጥገና ሥራ በማስተካከል ኅብረተሰቡ የበለጠ ተጠቃሚ የሚሆንበት ዕድል እየተፈጠረ ነው ብለዋል።
እንደዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ በክልሉ በተደረገ ጥናት ሰባት ሺህ አምስት መቶ ሄክታር እስከ አነስተኛ ሄክታር መሬት የሚያለሙ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ተጠንተው በዶክመንት ደረጃ የተቀመጡ አሉ። ከእነዚህ መካከል ክልሉ በራሱ አቅም የሚገነባቸው እንዳሉ ሆኖ በፌዴራል መንግሥት ድጋፍ የሚገነቡ መኖራቸውንም ይናገራሉ። እንዲሁም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ የሚሠጡባቸው ፕሮጀክቶች እንዳሉ ጠቁመዋል። ይሁንና በክልሉ አቅም የሚሠሩ ፕሮጀክቶችን ለመጀመር የሚያስችሉ ጥናትም ሆነ ግንባታ ዝግጁ ተደርገዋል ብለዋል።
‹‹በክልሉ የመስኖ ፕሮጀክቶቹ ከተገነቡ በኋላ የራሴ ናቸው ብለው ተቀብለው እንደባለቤት የሚረከቡና የሚመሩ ሰዎች ያስፈልጋሉ። ›› የሚሉት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ ይህም በመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ላይ ከሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች መካከል ተጠቃሽ ነው ብለዋል።
እነዚህ የማኅበረሰብ ክፍሎች በሥልጠና የተለያዩ ግንዛቤዎች እንዲያገኙ ተደርጎ አቅማቸው መገንባት ካልተቻለ በስተቀር ፕሮጀክቶቹ ተገንብተው ብቻ የሚቀሩ ከሆነ አገልግሎት አሰጣጣቸውም ሆነ ጥቅማቸው እየቀነስ ይመጣል። ስለሆነም ማኅበረሰቡ ግንዛቤ እንዲኖረው በማድረግ እና በቂ ሥልጠና በመስጠት ተግዳሮቶችን መቀነስ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ማኅበረሰቡ መስኖን መጠቀም ብቻ ሳይሆን፤ ለመስኖ የሚያወጣቸው መዋጮዎች እንዳሉ ያመላክታሉ። ቀደም ሲል አባላት ውሃ በመጠቀማቸው የሚያዋጡት መዋጮዎች የሚሰበሰቡ ቢሆንም፤ ያንን ሥራ ላይ ከማዋል ይልቅ ከመንግሥት የሚደረገውን ድጋፍ የመጠበቅ ዝንባሌዎች መኖራቸው እንደተግዳሮት ሊታይ እንደሚችል ይገልጻሉ። በአሁኑ ወቅት እነዚህ ተግዳሮቶች ለመቀነስ ሥልጠናዎችን በመስጠት ማኅበረሰቡ ግንዛቤ እንዲኖረው እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፤ ኅብረተሰቡ መዋጮዎቹን ራሱ ሰብስቦ የተበላሸ ነገር ሲኖር፤ የጥገና ሥራው እንዲከናወን እየተደረገ መሆኑን ያስረዳሉ።
ዋና ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት፤ በቀጣይ በጥናት ደረጃ ሊሠሩ የታቀዱ ተጠንተው የተቀመጡ ብዙ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች አሉ። እነዚህ ፕሮጀክቶች ከአነስተኛ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ብዙ ሄክታር መሬት የሚያለሙ ፕሮጀክቶች ናቸው። ከእነዚህ መካከል ቆላና ዳዋ የሚባሉ ግድቦች ጥናታቸው የተጠናቀቀ ሲሆን፤ ከፌዴራል ጋር አብረው የሚሠሩ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ክልሉ በቀጣይ ወደ ሥራ ለማስገባት ዝግጅቱን አጠናቅቋል ብለዋል።
ሲዳማ ክልል በርካታ ቁጥር ያለው ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ሊያደርጉ የሚችሉ ከአነስተኛ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ድረስ የሚጠቀሱ ከ50 እስከ 60 ፕሮጀክቶች ጥናታቸው የተጠናቀቀ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሀዋሳ ዙሪያ ያለው የመስኖ ልማት ፕሮጀክት አምስት መቶ ሄክታር እያለማ መሆኑን ተናግረዋል። ይህም አንድ ሺህና ከዚያ በላይ ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ሊያደርግ እንደሚችል ታሳቢ ተደርጓል ብለዋል።
የክልሉ ወንዞች ብዙ ፕሮጀክቶች እየተሠሩባቸው በመቆየታቸው ወንዞች እያለቁ መሆኑን ተከትሎ፤ በ2018 ዓ.ም የግድብ ሥራ ላይ መሠማራት የግድ መሆኑን አመላክተዋል። ይህን መሠረት በማድረግ ስምንት የግድብ ፕሮጀክቶችን ከሲዳማ ዲዛይን ኮንስትራክሽንና ሱፐርቪዥን ከሚባል አማካሪ ጋር ስምምነት በማድረግ ጥናት እያስጠኑ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
የመስኖ ዋነኛው ዓላማ ማኅበረሰቡ አሁን ካለበት ደረጃ በተሻለ መልኩ በምግብ ራሱን ከመቻል አልፎ የአካባቢውን ማኅበረሰብ መድረስ እንዲችል ነው ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ መንግሥት መስኖ ልማት ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ በመሆኑ የክልሉ መንግሥትም የሀገሪቱን የፖሊሲ አቅጣጫዎች በመተከል ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ይሠራል ብለዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 2 ቀን 2017 ዓ.ም