
የአላባ-አንገጫ-ዋቶ እና ደምቦያ አስፋልት መንገድ፤ በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ባለቤትነት፣ በኢትዮጵያ ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን አማካሪነትና በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ተቋራጭነት እየተገነባ የሚገኝ ፕሮጀክት ነው:: በተቋማቱ መካከል በተገባው ውል መሠረት ፕሮጀክቱ ከሁለት ዓመት በፊት መጠናቀቅ ቢኖርበትም፤ አሁን ላይ ያለው አጠቃላይ አፈጻጸም 23 በመቶ ብቻ መሆኑን የአማካሪ ድርጅቱ ሪፖርት ያመለክታል:: የፕሮጀክቱ መጓተትም በአካባቢው ሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ እንግልትና ምሬት መፍጠሩ ተጠቅሷል::
በኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ግንቦት 23 ቀን 2017 ዓ.ም ከሦስቱ ተቋማት አመራሮች ጋር የፕሮጀክቱን አፈጻጸም ገምግሟል:: በቀጣይ ሊወሰዱ ይገባል ያላቸውን ርምጃዎች የሚመለከቱ አቅጣጫዎችንም አስቀምጧል::
ፕሮጀክቱን በአማካሪነት እየመራ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን የትራንስፖርት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጅነር አበበልኝ መኩሪያ ባቀረቡት የሥራ ሪፖርት እንደገለጹት፤ የፕሮጀክቱ የግንባታ ሥራ ውል የተፈረመው እ.ኤ.አ ሐምሌ 29 ቀን 2020 ነው:: የግንባታ ሥራ ውሉም አንድ ነጥብ 98 ቢሊዮን ብር ነበር:: በስምምነቱ መሰረት ግንባታው በሦስት ዓመታት ማለትም በፈረንጆቹ የዘመን አቆጣጠር ታሕሳስ 29 ቀን 2023 ለማጠናቅ ታቅዶ እንደነበር አስታውሰዋል::
በሂደት በተደረገው ግምገማ የፕሮጀክት ማጠናቀቂያ ክለሳ ተከናውኖ የተሻሻለው የፕሮጀክት ማጠናቀቂያ ጊዜ እ.ኤ.አ ሚያዝያ 26 ቀን 2025 እንዲሆን ተደርጓል:: ይህም ማለት የግንባታ ሥራው ከአንድ ወር በፊት መጠናቀቅ ነበረበት:: ይሁን እንጂ ግንባታው ከሚሸፍነው 65 ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ አስፓልት መልበስ የቻለው አራት ኪሎ ሜትር ብቻ ሲሆን፣ የፕሮጀክቱ አጠቃላይ አፈጻጸምም 23 በመቶ ብቻ ሆኗል።
ለፕሮጀክቱ መዘግየት በምክንያትነት ከተነሱት ጉዳዮች መካከል የወሰን ማስከበር በወቅቱ አለመከናወን አንደኛው ነው:: አካባቢው ላይ ለግንባታ ግብዓትነት የሚውሉ ጥሬ እቃዎች እጥረት መኖር እንዲሁም የፋይናንስ አቅርቦት ችግሮች መሆናቸውን ጠቁመዋል:: ሥራዎችን በቅንጅት አለማስተዳደርና የባለድርሻ አካላት ተናቦ አለመሥራትም ተጨማሪ እክል መፍጠራቸውን ገልጸዋል:: የወሰን ማስከበር በተከናወነባቸው ቦታዎች ላይም መሠራት የሚገባቸው ሥራዎች በሚጠበቀው ልክ እንዳልተሠሩ አስረድተዋል::
የተሻሻለው የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበት፣ ካሳ የሚከፈልበትና ተነሺዎች መልሰው የሚቋቋሙበት አዋጅ ቁጥር 1336/2016 የወሰን ማስከበርና ካሣ ክፍያን ለአካባቢው መሥተዳድርና ለክልሎች ኃላፊነት ተሰጥቷል:: የየአካባቢው መስተዳድሮች ይህን ተረድተው አካባቢውን ነጻ የማድረግና ፕሮጀክቱን የራሳቸው አድርገው በማየት በኩል እጥረቶች ተስተውለዋል።
በሥራው መጓተት ምክንያት የትራንስፖርት መስተጓጎልን ጨምሮ ማኅበረሰቡን ለምሬት የሚዳርጉ ሁኔታዎች መኖራቸው የገለጹት ኢንጅነር አበበልኝ፤ የኢትዮጵያ ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን እንደአማካሪ ድርጅትነቱ በሥራ ሂደት ያጋጠሙ ችግሮች እንዲቀረፉ ደብዳቤ ልውውጥን ጨምሮ የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ እንደነበር በማስታወስ፤ በሥራው መዘግየት እኛም የድርሻችንን ኃላፊነት የምንወስድ ይሆናል ብለዋል:: መጭው ጊዜ ክረምት እንደመሆኑ በፍጥነት ርምጃዎች ካልተወሰዱ ለአደጋ መንስኤ ሊሆን እንደሚችል በመጠቆም፤ ለሕዝቡ የሚጠቅመው በትብብር ሠርቶ ውጤት ማምጣት መቻል በመሆኑ ሁሉም አተኩሮ መሥራት ይጠበቅበታል ሲሉ አሳስበዋል::
የፕሮጀክቱን ግንባታ የሚያካሂደው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጅነር በእምነት ጋሻው በበኩላቸው የፕሮጀክቱ መዘግየት እና ሕዝቡ እየተንገላታ መሆኑን ይገልጻሉ። በእነሱ በኩል ለተፈጠረው ችግር ፕሮጀክቱ የገንዘብና የማቴሪያል እጥረት ያለበት መሆኑንን በመጥቀስ፤ ለአስፓልት ንጣፍ የሚያገለግሉ ጠጠር፣ ገረጋንቲና መሠል አስፈላጊ ግብአቶች ከሩቅ እያመጡ መሥራታቸው ሌላ ተግዳሮት እንደሆነባቸው አብራርተዋል።
ይሁንና የወሰን ማስከበር ችግሮች ሥራውን በእጅጉ እንደተፈነው በመጠቆም፤ በሕጉ መሠረት ሥራው በተጀመረ በአራት ወራት ውስጥ የወሰን ማስከበር ሥራዎች መጠናቀቅ ነበረባቸው:: እስካሁን ከ65 ኪሎ ሜትሩ አጠቃላይ ፕሮጀክት 40 በመቶ የሚሆነው የፕሮጀክት አካባቢ የወሰን ማስከበር አልተከናወነበትም:: ይህም ሥራውን በተቀመጠው ጊዜ ለማከናወን እንቅፋት ሆኗል ብለዋል። በተጨማሪም የፋይናንስ አቅርቦት ችግር፣ የዋጋ ንረት፣ የውጭ ምንዛሪና የነዳጅ ዋጋ ጭማሪም በምክንያትነት ጠቅሰዋል::
በአላባ አንጋጫ ዋቶ የመንገድ ፕሮጀክት ከወሰን ማስከበር ጋር በተያያዘ የሚታዩ ችግሮችን ከመቅረፍ አንጻር ከክልሉ ፕሬዚዳንት፣ ከመንገዶች አስተዳደር እና ከሌሎችም ባለድርሻዎች አካላት ጋር ውይይት ስለማከናወናቸው ጠቅሰዋል። በዚህም ምክንያት ችግሮችን በመቅረፍ መሻሻሎች መታየት መጀመራቸውን አመላክተው፤ በተቋራጩ በኩልም ከወሰን ማስከበር ጋር በተገናኘ የመፍትሔ አካል በመሆን በችግር ውስጥም ቢሆን ሥራዎችን መሥራት ስለመቻላቸው አስገንዝበዋል።
አሁን ላይ ሥራው እየተሠራ ያለው በብድርና በኪሣራ ነው ያሉት ኢንጅነር በእምነት፤ ከዚህ ፕሮጀክት ትርፍ አንደማይፈልጉ እና ሥራው በፍጥነት አጠናቀው ሕዝቡን መካስ እንደሚፈልጉ አመላክተዋል:: ለዚህ ወቅቱን የሚመጥን የዋጋ ክለሳ ያስፈልጋል ብለዋል። የኢትዮጵያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በማማከር እና በመቆጣጠር ረገድ በኮሪደር ልማትና መሠል ሀገራዊ የልማት ተግባራት ላይ በስፋት እየተሳተፉ መሆኑን በማስታወስ፤ ፕሮጀክቱን የወሰዱት በድርድር እንደነበር በመግለጽ አሁንም መፍትሔ ማምጣት የሚቻለው በመነጋገር ነው ብለዋል:: ስለሆነም ለውጤታማነቱ ከአማካሪውም ሆነ ከአሰሪ ተቋማቱ ጋር ተቀራርበው ችግሮችን መፍታት የሚቻልባቸው እድሎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
«የሥራው መዘግየት የአካባቢው ሕዝብ ላይ ትልቅ ቅሬታ ፈጥሯል:: ፕሮጀክቱ አሁን ባለው ሂደት ከቀጠለ ተጨማሪ ስድስት ዓመታትን ይፈልጋል:: » ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጅነር መልካ በቀለ ናቸው። ኢንጅነር መልካ በቀጣይ የሚጠበቀውን ሥራ ሲያብራሩ ቦታው ላይ በቂ ማሽነሪዎችን አስገብቶ ያለፉትን ጊዜያት በሚያካክስ መልኩ መሥራት ይጠበቃል:: የወሰን ማስከበር ችግሮችን ለመቅረፍ ከክልሉ አመራሮች ጋር መግባባት ላይ ተደርሷል:: ተቋራጩ በገባው ውል መሠረት ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ማጠናቀቅ ይኖርበታል። የፕሮጀክት ውሉን ተከትሎ የዋጋ ንረት ማሻሻያ እንጂ የዋጋ ክለሳ ማካሄድ የሚቻልበት አሠራር የለም ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ከሁለት መቶ በላይ ሠፋፊ ፕሮጀክቶች እያስተዳደረ ሲሆን፤ የደቡብ ሪጅንን ጨምሮ በሌሎችም ፕሮጀክቶች ውጤት ተኮር የተግባር ሥራ እያከናወነ ይገኛል። በዚህ መነሻነት ከሚያስተዳድራቸው ፕሮጀክቶች አንጻር ለአንድ ፕሮጀክት የዋጋ ክለሳ ቢያደርግ ይዞት የሚመጣው ጣጣ ከተቋሙ ብሎም ከሀገሪቱ አቅም በላይ ይሆናል:: ስለሆነም የስምምነት ውሉን ተከትሎ ችግሩን ለመፍታት መሥራት ተገቢ ነው። ኃላፊነትን በመገፋፋት ውጤት ሊመጣ ስለማይችል፤ ተቀራርቦ በመነጋገር የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ መሥራት ይጠበቃል ብለዋል።
በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ የቋሚ ኮሚቴ አባላት፤ መንገዱ በተቀመጠለት ጊዜ ባለመጠናቀቁ ሕዝቡ ለከፍተኛ እንግልት መዳረጉን አንስተዋል:: ለዚህ ደግሞ አማካሪ ድርጅቱም ሆነ ተቋራጩ ኃላፊነቱን መውሰድ እንዳለባቸው አመልክተው፤ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ ማጠናቀቅ ባሕል እየሆነ በመጣበት በአሁኑ ጊዜ በመንግሥት ተቋማት የሚሠራ መንገድ በዚህ ልክ መዘግየቱ ጥያቄ እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል::
ኃላፊነትን ለመሸሽ ችግሩን ወደሌሎች በተገፋ ቁጥር ሥራው ይበልጥ እየዘገየ፤ የሕዝቡ እንግልት እና ሥራው የሚጠይቀው ዋጋ እየጨመረ ስለሚመጣ መፍትሔ ላይ ማተኮር እንደሚገባም አሳስበዋል:: ጉዳዩ ሥራው ዘገየ ብቻ በማለት የሚታለፍ እንዳልሆነ በመግለጽም፤ ቋሚ ኮሚቴው ለችግሩ ምንጭ የሆኑ አካላት ተጠያቂ እዲሆኑ መሥራት እንዳለበት አመልክተዋል። በቀጣይም የሕዝቡን እንግልት የሚቀንስና ውጤታማ ሥራ መሥራት እንዲቻል ጠንከር ያለ አቅጣጫ እንዲሰጥም ጠይቀዋል::
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት የልማት ድርጅች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ መለስ መና በሰጡት ማጠቃለያ፤ ሦስት ታላላቅ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የሚሳተፉበት ፕሮጀክት በዚህ ልክ መጓተቱ የሚጠበቅ እንዳልሆነ አንስተዋል:: ፕሮጀክቱ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ባለመጠናቀቁ ሕዝቡ ለእንግልት መዳረጉን አመልክተው፤ በቀጣይ ሥራው ያለፉትን ጊዜያት መዘግየት በሚያካክስ መልክ ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል::
የየተቋማቱ የበላይ ኃላፊዎችም በጋራ ተወያይተው የደረሱበትን ውጤት በአማካሪው በኩል ለቋሚ ኮሚቴው ሪፖርት እንዲያቀርቡ አሳስበዋል:: በተጨማሪም የወሰን ማስከበር ሥራዎች በፍጥነት እንዲከናወኑ፤ የዋጋ ክለሳን ጨምሮ ሌሎችም ተግዳሮቶች በተቋማቱ ኃላፊዎች ውይይት ተደርጎባቸው ያሉ የሕግ አማራጮችን ታሳቢ አድርገው ሊፈጽሙ እንደሚገባ ጠቁመዋል:: አማካሪ ድርጅቱም የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ አሳስበዋል::
ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ በጋራ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ባለው መንገድ እንዲሁም ሕግና ሥርዓትንም ተከትሎ መሥራት እንደሚገባ አመላክተዋል። ፕሮጀክቱን እያከናወኑ ያሉት ሦስቱ ተቋማት ማለትም የኢትዮጵያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደርና የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ተግባራዊ እርምጃ በመውሰድ ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ ትኩረት ሰጥተው መሥራት አለባቸው ብለዋል።
ቋሚ ኮሚቴው ከዚህም ቀደምም በዚህ ፕሮጀክት ዙሪያ ተሰብስቦ ተቋማቱ ተመካክረው ተጨባጭ ውጤት ይዘው እንዲመጡ አሳስበው እንደነበርም አመልክተው፤ አሁን ላይ ከመጀመሪያው የተለየ ነገር አልቀረበም:: ስለሆነም ሁላቸውም ሥራው ላይ የሚያደርጉትን ክትትል አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተናግረዋል::
የአላባ-አንገጫ-ዋቶ እና ደምቦያ አስፋልት መንገድ ፕሮጀክት አጠቃላይ ሥራው 65 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚሸፍን ሲሆን፤ እስካሁን ባለው ሂደትም የአራት ኪሎ ሜትር አስፋልት ማንጠፍ፣ የ4 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የተፈጨ የጠጠር ዝርጋታ፣ የበአፈር ቆረጣና ሙሌት በ37 ኪሎ ሜትር ላይ የተሠራ ሲሆን፤ ሌሎች ተያያዥ ተግባራት እየተከናወኑ አጠቃላይ አፈጻጸሙ 23 በመቶ ላይ እንደሚገኝ ተመላክቷል::
በፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 30 ቀን 2017 ዓ.ም