እንግዲህ በሀብታም ኑሮ ጣልቃ ልገባ ነው ! (እነርሱም በድሃ ኑሮ ጣልቃ ይገባሉ እኮ።) ይህ የክረምት ወቅት ከገባ ጊዜ ጀምሮ በሬዲዮና በቴሌቭዥን የምሰማቸው ማስታወቂያዎች ይገርሙ ኛል። የክረምት ወቅት ትምህርት ቤቶች የሚዘጉበት ነው፤ በዚህም ምክንያት ተማሪዎች ረፍት ላይ ይሆናሉ።
በነገራችን ላይ ተማሪ እያለሁ እንደማስታውሰው (ለዚህ ያህል የሚሆን ተሞክሮማ አላጣም) ክረምት ሲመጣ የቀጣዩን ክፍል መጽሐፍ ነበር የምንፈልግ። መጽሐፍ እንኳን ቢጠፋ ከፊታችን ያሉ ጓደኞቻችን የተማሩበትን ደብተር እንዋሳለን። ለምሳሌ 5ኛ ክፍልን ጨርሰን ቀጣይ መስከረም 6ኛ ክፍል የምንገባ ከሆነ የ6ኛ ክፍል መጽሐፍና ደብተር እናነባለን።
በክረምት ወቅት ደግሞ የምናነበው ለፈተና ብለን ስላልሆነ ይገባናል፤ ምክንያቱም ተረጋግተን ነው የምናነበው። በዚያ ላይ የግድ የክፍል ትምህርት (አካዳሚክ) ብቻ ሳይሆን ሌሎች የጠቅላላ ዕውቀት መጻሕፍትም ይነበባሉ።
ወደ ማስታወቂያዎች ትዝብቴ ልመለስ። የአንዳንድ ማስታወቂያዎቹ ይዘት፤ ወላጆች ተማሪዎቻቸውን የት ማዝናናት እንዳለባቸው፣ ምን አይነት ‹‹ዲ. ኤስ ቲቪ›› እንደሚገዙላቸው የሚናገር ነው። ይሄም ክፋት አልነበረውም! በበጋ ወቅት ሲሰቃዩ እንደቆዩ ተደርጎ ነው የሚታሰበው። (ለነገሩ አንዳንድ ወላጅ እኮ ትምህርት ስቃይ ይመስለው ይሆናል!) ለጎበዝ ተማሪ ትምህርት ስቃይና መከራ ሳይሆን የሚደሰትበት ነው። ‹‹ዲ.ኤስ ቲቪ›› ከማየት በላይ በሚሰራው ሒሳብና ፊዚክስ ይደሰታል። በሚያመጣው የፈተና ውጤት፣ በሚይዘው የክፍል ደረጃ ይደሰታል። በክረምት እንዲዝናኑ ቢደረግ እንኳን የበጋው የትምህርት ወቅት ለምን እንደስቃይ ይቆጠራል?
በክረምት ተማሪዎች ልክ በበጋ ወቅት እንደነበረው ጠዋትም ማታም ያንብቡ ማለት ይከብድ ይሆናል። (ከተቻለ ግን ቢሆንም ችግር የለውም።) ዳሩ ግን ስለመዝናናት ብቻ ማውራት ለተማሪ ጥሩ ነው ? ምናልባት ከከተማ ወጣ አድርጎ ማዝናናቱ እኮ በወር አንዴ፣ በጣም ከበዛም በሳምንት አንዴ ሊሆን ይችላል። ዳሩ ግን እንደዋና ጉዳይ ተደርጎ የሚነገረው እሱ ነው። ምናልባት ይሄን የሚሰማ የተማሪ ወላጅ የግድ እንዲህ ማድረግ አለበት የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ይሆን? ይህን የሚሰማ ተማሪስ እኔንም ውሰዱኝ ብሎ ወላጆቹን ያስቸግር ይሆን?
እንዲህ የሚያደርጉ ወላጆችም ይኖራሉ ለማለት እንጂ ማስታወቂያው ግን ቀጥታ የወላጆች ሀሳብ አይደለም። የምርትና አገልግሎቱ ባለቤቶች እና ባለማስታወቂያዎች የተጠቀሙት እንጂ። እንደነርሱ ከሆነማ እኮ ተማሪው ሁሉ በክረምት ሲጫወትና ሲዝናና ብቻ ነው ማሳለፍ ያለበት።
እሺ! የምርትና አገልግሎት ባለቤቶች ለገበያቸው ሲሉ ነው እንበል! ምናለ ትምህርት ሚኒስቴር ተማሪዎች በክረምት ማንበብ እንዳለባቸው የሚያስተምር ማስታወቂያ ቢያሰራ? ትምህርት ሚኒስቴር ብቻ አይደለም፤ ማንኛውም አካል ቢሆን ስለክረምት የተማሪዎች ጥናት ቢያስተምርስ?
በዚሁ እግረ መንገድ ለማመስገን ያህል፤ ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት ከሚማሩት በላይ የሚያስተምሩም አሉ። አንድ የግል ትምህርት ቤት የሚያስተምር መምህር የነገረኝን ልንገራችሁ። የስነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት ላይ ነው። መምህሩ ለተማሪው የሞላለትን መልስ የአንድ ተማሪ ወላጅ ያየዋል። የተማሪው ወላጅ የመልስ መስጫ ወረቀቱ ላይ ግጥም አድርጎ ጽፎ ‹‹መልሱ ይሄ ነው ብለህ ለመምህሩ ስጠው›› ብሎ ተማሪውን ላከው። የተማሪው ወላጅ የሞላው መልስ የተብራራና ብዙ ማጣቀሻዎች ያሉት ነው።
እንዲህ አይነት ወላጆችም ይኖ ራሉ። ለምሳሌ ያ ወላጅ ባለሥልጣን ሊሆን ይችላል፤ ማለትም ለስነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት የቀረበ እውቀት ይኖረዋል። የዕድሜ ባለጸጋ ቢሆን ለታሪክ ትምህርት ቅርበት ይኖረዋል። የተማሪው ወላጅ ዳኛ ወይም ጠበቃ ቢሆን ለስነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት ቅርበት ይኖረዋል።
ወላጅ፤ ሐኪም ሊሆን ይችላል፣ መሐንዲስ ሊሆን ይችላል፣ ጋዜጠኛ ሊሆን ይችላል፣ ደራሲ ሊሆን ይችላል። ሁሉም እንደየሙያው ልጆቹን ቢከታተልና ቢያስጠና ውጤታማ ይሆናሉ።
ተማሪዎች በዚህ የክረምት ወቅት ጠንክራችሁ ብታነቡ የፈለጋችሁትን ውጤት ለማምጣት ያግዛችኋልና ከጨዋታና ከመዝናኛ ይልቅ ለንባብ የበለጠ ጊዜ ስጡ!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ፣ ነሀሴ 4/2011
ዋለልኝ አየለ