እነሆ አዲሱ ዓመት ነግቷል። ብዙዎች ደግሞ አዲስነትን ባሰቡ ቁጥር አዕምሯቸው መልካምነትን ያስባል። እንዲህ መታሰቡ ‹‹እስየው ቢያስብል እንጂ አያስከፋም። በነዚህ ጊዚያት ብዙዎች ዕቅዳቸው ወደተሻለው ጉዳይ ብቻ ማመዘን ላይ እንደሆነ በግልጽ ይስተዋላል።
አንዳንዶች ዕቅድ ይሉትን ጉዳይ ሲወጥኑ ክፉ የሚባሉ ችግሮቻቸውን ማራገፉ ላይ ግድ ያላቸው አይመስልም። በእስከ ዛሬው ማንነታቸው በግልጽ የሚስተዋሉ እንከኖች እያላቸው ከነችግሮቻቸው ሌላ ዕቅድ ወጥነው ስለመሳካቱ ሲያስቡ፣ ሲጨነቁ ይከርማሉ። ይህ እውነት በበርካታ ግለሰቦች ላይ ዘወትር የምናየው እውነታ ነው። ብዙውን ጊዜ ሳይስተካከሉና ሳያርሙ የሚቀጥሉት ልማድ ነውና እንደነውር ሲቆጠር አይታይም።
በእያንዳንዱ ሰው ላይ የሚስተዋለውን እውነታ እንዳለ ሆኖ በአደባባይ ወደሚታዩና ነውርነታቸው በግልጽ ስለሚስተዋል እይታዎች እንሻገር። በእኔ በኩል የአደባባይ እውነታን ሳስብ በአእምሮዬ ቀድሞ የሚከሰተው የመንገድ ላይ መጸዳዳት ጉዳይ ነው። እውነቱን ለመናገር ይህን ጉዳይ ገና ሳስበው ከማፈርም በላይ ያናድደኛል ። እንዲህ ቢሰማኝ ደግሞ ለምን ያስብል አይመስለኝም።
አስተውላችሁ ከሆነ በከተማችን ዋና ዋና ስፍራዎች ላይ የጎዳና ላይ መጸዳዳት ህጋዊ የሆነ ያህል መለመድ ከያዘ ሰንብቷል። በተለይ ይህ አይነቱ ሀቅ ወንዶችን በቀጥታ ይመለከታልና ትኩረት ቢሰጡልኝ እወዳለሁ።
አሁን አሁን ሜክሲኮ፣ አራት ኪሎና ጀሞ በመሳሳሉ የከተማችን ዕምብርት ስፍራዎች ሽንት ቆሞ መሽናት ሕጋዊ ማረጋገጫ የተሰጠው ይመስላል። ‹‹ሕጋዊ›› ማለቴ በሆነ አካል ዕውቅና ተሰጥቶት የገቢ ጥቅም ጭምር እያስገኘ በመሆኑ ነው። እግር ጥሏችሁ መሀል ሜክሲኮ ብትደርሱ ዓይናችሁ ጉድ ያሳያችኋል። እኔ ለጉዳዩ ‹‹ጉድ›› ከማለት የበለጠ ቃል ባገኝለት ደስ ይለኝ ነበር።
በእነዚህ ስፍራዎች እንደጥሩ ወታደር አሰላለፋቸውን አሳምረው የቆሙ የፕላስቲክ ባልዲዎችን ብታዩ አይግረማችሁ። እያንዳንዱ ባልዲ የራሱ ተግባር አለውና ለሚጠቀምበት ባለጉዳይ ፈጽሞ አያስደንቅም። ችግሩ ከማየት አልፋችሁ ጠጋ ያላችሁ ከሆነ ነው። ባልዲዎቹ በላይ በላያቸው በሚሸናባቸው ቆሻሻዎች ተሞልተዋልና ቅድሚያ አፍንጫችሁን አልፎ መሀል አናታችሁን የሚበረቅስ ከባድ ሽታ ይቀባላችኋል።
አስገራሚው ጉዳይ እነዚህ ለወንዶች ብቻ የሽንት መጠቀሚያ ተብለው የተሰለፉ ባልዲዎች በጎዳና ዳርቻ ላይ ስለተቀመጡ ፍጹም ከእይታ አለመራቃቸው ነው። ሽንታቸውን ለመሽናት የሚፈልጉ መንገደኞችም ያለ አንዳች ነውር ጀርባቸውን ለተመልካች ሰጥተው የልባቸውን ይፈጽማሉ። ይህን ሲያደርጉ አንዳች ሀፍረትና መሸማቀቅ አይታይባቸውም።
በተለይ የሜክሲኮ አደባባይ ባልዲዎች አሳላለፍ ረጅም የታክሲ ሰልፍ በሚያዝበት አስፓልት መንገድ ላይ በመሆኑ ማንም ከዓይኑና ከክፉ ሽታ የሚያመልጥ አይሆንም። ባልሳሳት ይህ ግልጽ መንገድ ከአፍሪካ ህብረት የመሰብሰቢያ አዳራሽ የቅርብ ርቀት አላፊ አግዳሚው ያለ ሀፍረት ሲጠቀምበት ለማሳየት ምንም ማስተባበያና መሸፋፈኛን አይጠይቅም።
አዲስ አበባ አሁን ላይ ከፍተኛ የሚባል የልማት ተሀድሶ ላይ ትገኛለች። አሮጌ ቤቶች፣ ለዓይን የሚከብዱ ስፍራዎች፣ አመቺ ያልሆኑ እንከኖቹ ሁሉ በግልጽ ተለይተው እየተወገዱ ነው። ትልቅ ለውጥ በታየበት የሜክሲኮ አደባባይ ላይም ይህ አይነቱ እውነታ እውን መሆኑን በግልጽ አስተውለናል።
ይህ ከልማቱ ጎን ለጎን ተንተርሶ ስናየው የምንውለው ነውራችን ግን ዛሬም ድረስ አንዳች እርማት ሳይደረግበት ሕጋዊ በሚመስል ሂደት ቀጥሏል። ይህ የምላችሁ የባልዲ ውስጥ መጸዳጃ መሀል ሜክሲኮ ያለውን እንጂ
በየውስጣውስጡ በርከት ያሉ መጠቀሚያዎች እንዳሉ ግልጽ ነው።
መሀላችን አብሮን እየዋለ፣ ሰዎች በግልጽ እየተጠቀሙበትና ሌሎችም ጥቅም እያገኙበት የቀጠለው አላስፈላጊ መጸዳጃ ለጤናም ቢሆን ጠንቅነቱ ግልጽ እንደሆነ አያጠያይቅም። ጉዳዩ በእቃ ላይ ሆኖ አላፊ አግዳሚው በክፉ ሽታ እየተቸገረ፣ ለእይታም እያስጠላ፣ እያስነወረ ዛሬም ድረስ መቀጠሉ ደግሞ ያስገርማል።
ሁሌም እኛ ኢትዮጵያውያን እንደምንታማው እኛና የከተማችን ንጽህና ከሀሜት ላይ እንደጣለን ነው። ኢኮኖሚያዊ አቅማቸው ከእኛ በእጅጉ ያነሱ የአፍሪካ ሀገራት ሳይቀሩ ብዙ ሲተቹና ስማችንን ሲያጠፉት ኖረዋል።እኛ ግን ችግሮቻችንን ሳናርም፣ ክፉ ስማችንን እያደመቅን እስከዛሬ ቀጥለናል። አሁን እንዲህ አይነቱን ግልጽ ችግር ተሸክመን ለምንና እንዴት የምንልበት አፍ አይኖረንም።
በየጊዜው የከተማችንን ንጽህና አጠባበቅ አስመልክቶ ገዢ ሕጎች ይወጣሉ።ቆሻሻን ያለአግባብ የሚጥሉ፣ ተገቢ ባልሆነ ስፍራ የሚጸዳዱ፣ ግለሰቦች ተገቢው ቅጣት ሲያገኛቸውና በሕግ ሲጠየቁም አይተናል። ለእንዲህ አይነቱ አጠቃቀም ግን አንዳች ኮሽታ ሳይሰማ ይኸው ሌላውን አዲስ ዓመት ተቀብለናል።
ለመሆኑ ይህ አይነቱ የመጸዳጃ አይነት ከየትኛው መደብ የሚያዝ ይሆን? ሕጋዊነት አለው እንዳይባል ሁሉን አቀፍ አይደለም። ዘመናዊነት የዳሰሰው ፣ ንጽህና የጎበኘው አለመሆኑም ይታወቃል። ገቢ ስላስገኘ ብቻ በነውርነቱ መቀጠሉ ግን አሳፋሪም አስነዋሪም ሆኖ ዘልቋል።
ይህ አይነቱ ክፉ ልማድ አዲስ አመትን በእኩል ባይሻገር መልካም የሚባል ነበር። ልክ ከቤታችን አውጥተን እንደምንጥለው ቆሻሻ ሁሉ ይህ አይነቱን አጠቃቀም ልናስወግደው ይገባናል።መንግሥት አሁን ላይ የመጸዳጃ ቤት አጠቃቀምን ዘመናዊ አድርጎ መገንባት ጀምሯል። ጤናው የተጠበቀ ነዋሪ በጤናማ አጠቃቀም ህይወቱን ይመራ ዘንድ አሰራሩ እየተተገበረ መሆኑንም ልብ ይሏል።
ከተማዋን የማይመጥን ተጠቃሚውን አክብሮ የማያስከብር አጉል ዘዴ የትም አያራምድም። ይልቁኑም የእኛን ውድቀት በማስረጃ አስደግፈው ለሚያብጠለጥሉን አንዳንድ ሀገራት ጥሩ ማሳያ ሆኖ ስማችን ከማጉደፍ የዘለለ አይሆንም።
አሁን ላይ አስቸጋሪ በሚባሉ የገጠር ስፍራዎች ሳይቀር የመጸዳጃ ቤት አጠቃቀም በመልካም ግልጋሎት ተቀርጾ ይታያል። በተቃራኒው አዲስ አበባን ያህል ግዙፍና ዘመናዊ የአፍሪካ መዲና ተገቢ የማይባልና አሳፋሪነቱ በሚያመዝን የመጸዳዳት ልማድ ተዋርሶ መታየቱ እንደሰው ያሳዝናል፣ ያሸማቅቃል።
ብዙ ጊዜ አዲስ ዓመትን በአዲስ መንፈስ ለመቀበል ስናቅድ ይዘናቸው የማንሻገራቸው ክፉ ልማዶች ይኖራሉ።በማወቅም ሆነ በስህተት አብረውን የዘለቁ እንከኖች ችግራቸው ተስተውሎ መወገድ ቢችሉ ይጠቅሙናል እንጂ አያከስሩንም። እንዲህ አይነቶቹ ክፉ ልማዶች ደግሞ ቢቻል በዘመናዊ አሰራር ተተክተው፣አልያም ከነአካቴው ተወግደው ከስራቸው ሊነቀሉ ግድ ይላል።
የሰው ልጅ በማንነቱ ክቡርና ድንቅ ፍጡር ነው።በእንዲህ አይነት ስፍራ ላይ ማንነቱን ማጋለጡ ደግሞ በመልካም አያሳየውም። ሌላውም ተመልካች ቢሆን የአጥፊዎችን ነውርነትና ክፉ ልማዶች ሊሸከም ግድ አይለውም።
ዘንድሮ አዲስ አበባ በኮሪደሩ ልማት ወደፊት እንደምትቀጥል ይታመናል። እድገቷ ሙሉ የሚሆነው ግን እንዲህ አይነቶቹን ልማዶች ዳግም እንዳያቆጠቁጡ ሆነው ከስራቸው ሊነቀሉ ግድ ነው። ያለዚያ መንገዱ ሁሉ አንዱን ላጭቶ አንዱን አጎፍሮ እንዳይሆን ያሰጋል። በእኔ ዕምነት እንዲህ አይነቶቹን የልማትና የበጎ እይታ ጋሬጣዎች መንቀልና ማስወገድ ከግዴታም በላይ ግዴታችን ነው። መልካም አዲስ ዓመት።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን መስከረም 6 ቀን 2017 ዓ.ም