ዛሬ ቡሄ ነው። ‹‹እዚያ ማዶ ጭስ ይጨሳል…›› የሚለው የልጆች የሆያ ሆየ ዘፈን ይዘፈናል። በነገራችን ላይ ይሄ የልጆች የሆያ ሆየ ጭፈራ ውስጠ ወይራ ነው ይባላል። በድሮው ጊዜ የመገናኛ ብዙኃን አማራጭ አልነበረም። እረኞች በእንጉርጉሮ ስሜታቸውን ይገልጻሉ። ለዚህም ይመስላል በነገሥታቱ ዘመን ‹‹እረኛ ምን አለ?›› የሚል የዳሰሳ ጥናት ይደረግ ነበር ይባላል። የሕዝብን ስሜት ከእረኛ ይሰማሉ ማለት ነው። እረኞች ልጆች ስለሆኑ ከወላጆቻቸው የሚሰሙትን ያንፀባርቃሉ። ከእነዚህ የልጆች ሀሳብ ማንጸባረቂያ መድረኮች አንዱ ቡሄ ነው።
የዛሬው ቡሄ ልጆች በየመንደሩ እየዞሩ የሚጨፍሩበት (በተለይም ቀደም ባለው ዘመን) ነው። በስንኞቻቸው ያስደሰታቸውን የሚያወድሱበት፤ ያስከፋቸውን ሸንቆጥ የሚያደርጉበት ነው። እንዲህ አይነት ክስተቶች የዘመን ምስክር ናቸው። ያ ዘመን ምን ይመስል እንደነበር፤ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ሁኔታዎችን ያሳያሉ።
ከልጆች የሚሰሙ ስንኞች የድሮ ቃል ግጥሞች ብቻ አይደሉም፤ በዘመኑ ዓውድ ቀይረው አሁን ያለውን ለመግለጽ የሚጠቀሟቸውም አሉ። ለምሳሌ፤ በኢሕአዴግ ጊዜ መንግሥት በተደጋጋሚ ‹‹ኪራይ ሰብሳቢ›› ሲል ይሰማል። ይሄው ክስተት በልጆች ሆያ ሆየ ውስጥ ተካቶ ሲጨፈር ሰምተናል። ‹‹እረኛ ምን አለ? ማለት ይሄው ነው።
እንዲህ አይነት ቱባ የማኅበረሰብ የኪነ ጥበብ ውጤቶች ብዙም ሽፋን አያገኙም። ማኅበረሰብን ለማወቅ ግን ትክክለኛው መገለጫ ይሄው ነበር። በነገራችን ላይ የሠለጠኑ ናቸው በሚባሉት ሀገራት የተሠራ አንድ ጥናት አንብቤ ነበር። ጥናቱ የሥነ ማኅበረሰብ (ሶሾዮሎጂ) ጥናት ነው። አጥኚው አጠናው የተባለው መጠይቅ እየበተነ አይደለም። የከተሞችን የሌሊት ሕይወት (Nightlife) በማጥናት ነው። እንደ ለንደን፣ ፓሪስ፣ በርሊን…. የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ከተሞች የምሽትና የሌሊት እንቅስቃሴዎቻቸው ይቀረጻል። ትክክለኛውን ማንነት ማየት የሚቻለው በዚህ ነው ማለት ነው።
የእረኞችና የልጆች ጨዋታም እንደዚህ ነው። በራሳቸው ስሜት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ማለት ነው። ስለዚህ የዘርፉ ሰዎች ልብ እንዲሉት (እንዲያጠኑት) እየጠቆምን እስኪ አንዳንድ የቡሄ የጨዋታ ስንኞችን እናስታውስ።
ቡሄ መጣ
ያ መላጣ
ቅቤ ቀቡት እንዳይነጣ
ይሄ ከቃሉ ትርጉም ጋር የሚሄድ ነው። ‹‹ቡሄ›› ማለት ቡሃ ከሚለው ቃል የመጣ ነው፤ ቡሃ ማለት ገላጣ ማለት መሆኑን የሃይማኖት አባቶችና የቋንቋ ሰዎች በየዓመቱ ይናገሩታል።
የእኔማ ጌታ የሰጠኝ ሙክት
ከግንባሩ ላይ አለው ምልክት
መስከረም ጠባ እሱን ሳነክት
ይሄ የውደሳ ግጥም ነው። በድሮው ጊዜ ለሆያ ሆያ ልጆች ሙክት (ፍየል) ይሰጥ ነበር ማለት ነው። በነገራችን ላይ በገጠር አካባቢ ልጆች ከሆያ ሆየ የሚያገኙትን ብር ሙክት ገዝተው ነው የሚበሉበት። የቅጠል ድንኳን (ዳስ) ይሠራል። ከአካባቢው ሰዎች ይገባቸዋል ያሏቸውን (ሽማግሌና የሃይማኖት አባት) ይጠራሉ። ከዚያ ውጭ የመጣ ግን ቀላዋጭ ነውና የሚጠብቀው የልጆች ግልምጫና ውረፋ ነው።
ሆያ ሆየ ሲሉ ብር የሚቀበሉት እንደየሰዎች አቅም ነው። የአካባቢው ልጆች ስለሆኑ የየሰውን አቅም ያውቁታል። ሀብታም ከሆነ በቀላል አይላቀቁም። ‹‹ከአንተ ይሄን አንቀበልም›› ብለው ሆያ ሆየውን ይደጋግሙታል። ከእንዲህ አይነቱ ሀብታም ነው ሙክት የተበረከተላቸው ማለት ነው። ‹‹መስከረም ጠባ እሱን ሳነክት›› ማለት ከቀናት በኋላ የሚገባውን መስከረም ሳይሆን በዓመቱ የሚመጣውን ነው።
የእኔማ እመቤት የፈተለችው
የሸረሪት ድር አስመሰለችው
ሸማኔ አቅቶት ማርያም ሠራችው
ይሄም ውደሳ ነው። ይሄኛው ውደሳ ለእመቤቷ ነው። በዘመኑ የሴት ሙያ የሚለካው በፈታይነትና በባልትና ብቃት ነው።
ከድሮው የቃል ግጥም እንውጣና በቅርቡ ዘመን የተባሉትን ደግሞ እንያቸው። በዘመኑ የሚታየውን፣ የሚባለውን፣ የሚሆነውን የሚናገሩ ናቸው። ያም ሆኖ ግን መነሻ ስንኞቻቸው የቀደሞቹ ናቸው።
ወዲያ ማዶ አንድ ጋቢ
ወዲህ ማዶ አንድ ጋቢ
የኔማ እንትና ኪራይ ሰብሳቢ!
ምናልባት ይሄ በተባለበት ጊዜ ጭስ አልነበረም መሰለኝ በጋቢ ቀይረውታል። ኪራይ ሰብሳቢ የሚለውን ለመግለጽ ቤት እንዲመታላቸው ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹ጭስ›› ካሉ ሙሉ በሙሉ የድሮው ሊሆን ነው። ያስከፋቸውን ሰው ኪራይ ሰብሳቢ ብለው ሲሰድቡት ያስደሰታቸውን ደግሞ እንዲህ ብለዋል።
እዛ ማዶ አንድ በረኪና
እዚህ ማዶ አንድ በረኪና
የኔማ አባብዬ ባለመኪና
እዚህ ጋ የተቀየረው ሌላው ነገር ‹‹ጌታ›› የሚለው ነው። በድሮው ጊዜ ጌታ እና እመቤት የሚሉ ቃላት ነበሩ፤ አሁን አባዬ እና እማዘየ በሚል መሆኑ ነው። ለዚህም ነው ለሴቷ እንዲህ የተባለው።
እዛ ማዶ አሮጌ ትሪ
እዚህ ማዶ አሮጌ ትሪ
የእኔማ እማምዬ ማሪያ ኬሪ
ግን ‹‹አዲስ ትሪ›› ቢሉት ምን ችግር ነበረው? ወይስ አሮጌው ትሪ ያልገባኝ መልዕክት ይኖረው ይሆን? እንዲያውም ከማሪያ ኬሪ ጋር የሚሄድ አዲስ ትሪ ቢሆን ነበር (ለነገሩ ማሪያ ኬሪም እያረጀች ነው)። ችግሩ ዘፋኝም ተዋናይም የራሳችን እያሉን የውጭዋን ማስበለጣቸው ነው።
ተው ስጠኝና ልሂድልህ
እንደ አሮጌ ጅብ አልጩህብህ
የልጆችና የእረኞች ቃል ግጥሞች የአዋቂዎች እጅ ያለበት ይመስላል። እርግጥ ነው ሲወርድ ሲወራረድ የመጣ ነው፤ ግን ጨዋታው የልጆች ብቻ ስለሆነ ከልጅ ወደ ልጅ እንጂ ከአዋቂዎች ወደ ልጅ ይተላለፋል? ወይስ ነገር ስለምናጣምም እነርሱ ያላሰቡትን ትርጉም እየሰጠነው ይሆን? አይመስለኝም! ‹‹ያለአንድ ሰው አታስተኛ›› የተባለው መቼም የሆያ ሆየ ጎረምሳ ከአባወራ ቤት አልጋ ላይ ይተኛል ተብሎ አይደለም። የጌቶች ወንበር በቀላሉ አይገኝም ለማለት ነው።
እዚያ ማዶ ጭስ ይጨሳል
አጋፋሪ ይደግሳል
ይሄን ድግስ ውጬ ውጬ
ከድንክ አልጋ ተገልብጬ
ያቺ ድንክ አልጋ ነገረኛ
ያለአንድ ሰው አታስተኛ!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም