በጋዜጠኝነት ሥራ ውስጥ ያልሆኑ፣ የጋዜጠኝነት ትምህርት ያልተማሩ፣ በአጠቃላይ በሌላ ዘርፍና ሕይወት ውስጥ ያሉ ሰዎች ሁሉ ሳይቀር በተደጋጋሚ ሲናገሩት የምንሰማው ነገር፤ መገናኛ ብዙኃን ‹‹ለሕዝብ ወገንተኛ ይሁኑ›› የሚል ነው፡፡ ለሕዝብ ወገንተኛ መሆን ማለት ምን ማለት ይሆን? በተለይ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ለሕዝብ ወገንተኛ መሆን ሲባል ለየትኛው ሕዝብ?… እያልን ከጠየቅን ብዙ ፍልስፍና ውስጥ ይከተናል፡፡ በጋራ የሚያስማማው ነገር ግን ለእውነተኛ መረጃ ታማኝ ይሁኑ፣ የውሸት ፈጠራ አያሰራጩ የሚለው ነው፡፡ ከዚያ ውጭ ያለው አሻሚና አወዛጋቢ ነው፡፡
በጋዜጠኝነት ጽንሰ ሃሳብ ውስጥ ‹‹ገለልተኝነት›› የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ ሳስብ ፤ ከምንኩስና ጋር ይመሳሰልብኛል፡፡ ምንኩስና ማለት አማኙ ዓለም በቃኝ ብለው ገዳም የሚገቡበት ነው፡፡ በሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቱ የሚከወን ነገር አለ፡፡ ሥርዓተ ክዋኔውን እንተወውና ዋና ነገሩ ግን ከምንም ነገር ገለልተኛ የሚሆኑበት ነው፡፡ የመነኮሰ ሰው በዚህ ዓለም በሕይወት እንደሌለ ነው የሚቆጠረው፡፡ በሕይወት እንዳለ ሰው ሆኖ በምንም ጉዳይ ላይ አስተያየት አይሰጥም፡፡ ለምሳሌ በወገኑ ላይ በደል ቢደርስ ተበደለብኝ ብሎ የተለየ ተቆርቋሪነት አያሳይም፤ የሚያስበው እንደ ሰው ልጅ ብቻ ነው፡፡
ይሄን ምሳሌ ያነሳሁት ጋዜጠኝነት ይህን ያህል ገለልተኛ ይሆናል ብየ አይደለም፤ የሙያው ሳይንስ የሚለው ግን ልክ እንደዚህ እንደምንኩስናው ነው። ከየትኛውም ነገር ገለልተኛ ነው መሆን ያለበት፡፡ ልክ እንደመነኩሴ ሁሉ በወገኑ ላይ በደል ቢደርስ የተለየ የተቆርቋሪነት ስሜት አለማሳየት ማለት ነው፡፡
በነገራችን ላይ የጋዜጠኝነት ሳይንሱ የሚለው ነገር የትኛውም የዓለም ሀገር ላይ የማይተገበር ነው። ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ፈጣሪዎቹ እነ ቢ ቢ ሲ፣ ሲ ኤን ኤን፣ አልጄዚራ… ወዴት እንደሚያዘነብሉ እናውቃለን። የዴሞክራሲ ቁንጮ ናቸው የሚባሉት የምዕራባውያን መገናኛ ብዙኃን የሚያነጣጥሩት በምሥራቁ ዓለምና በአፍሪካ ሀገሮች ችግር ላይ ነው፡፡ በአንፃሩ የምሥራቁ ዓለም መገናኛ ብዙኃን የሚያስጨንቃቸው የምሥራቁ ዓለም ደህንነት ነው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በሌላው ዓለም ሳይንሱ እንደሚለው የሚሠራ የለም፡፡ በጽንሰ ሃሳቡ መሠረት የጋዜጠኝነት ሙያ ችግር አለበት ከተባለ እንደአጠቃላይ ነው ችግሩ፡፡
አንድ ልብ መባል ያለበት ነገር ግን ጋዜጠኝነት ማህበራዊ ሳይንስ ነው፡፡ ይሄ ማለት እንደ ፊዚክስና ኬሚስትሪ ተፈጥሯዊ ሳይንስ አይደለም ማለት ነው። ከሀገር ሀገር ሊለያይ ይችላል፡፡ ሀገራት በሚከተሉት ሥርዓት ላይ ይወሰናል፡፡ እንኳን በሀገር ደረጃ በአንድ ሀገር ውስጥ ራሱ የተለያየ መገናኛ ብዙኃን የተለያየ አሠራር ሊኖራቸው ይችላል፤ የየራሳቸው ዓላማ ይኖራቸዋል። ለዚህም ነው የመረጃ መምታታት የሚያጋጥመው፡፡ አንዱ የዘገበውን ሌላው ካልፈለገው ‹‹ውሸት ነው›› ሊል ይችላል፡፡
ስለጋዜጠኝነት ሙያ ተደጋግሞ የሚነገረው ነገር ‹‹ወገንተኝነቱ ለሕዝብ ነው›› የሚለው ነው፡፡ አንዳንዶች ግን ይሄ ራሱ ትክክል አይደለም የሚሉ አሉ፡፡ ጋዜጠኝነት ወገንተኝነቱ ለማንም ሳይሆን በቃ ለእውነት ብቻ ነው።ያ እውነት ሕዝብ የሚጎዳ ቢሆን ራሱ መዘገብ አለበት ማለት ነው? የሚል ሌላ ክርክርም ያስነሳል፡፡
ጋዜጠኝነት ወገንተኝነቱ ለሕዝብ ብቻ ነው ከተባለ ሕዝብ ራሱ ሊሳሳት ይችላል፡፡ የአንድ አካባቢ ሕዝብ
የሌላን አካባቢ ሕዝብ ቢሳደብ መዘገብ አለበት ማለት ነው፡፡ ገለልተኛ ነው ከተባለ ስለምንም ነገር ሊያገባው አይገባም፡፡ በዚህ ሎጂክ ከሄድን ለሀገር ጥፋት ይሆናል ማለት ነው፡፡ ምን አገባኝ ብሎ ያየነውንና የሰማውን ሁሉ ከዘገበ ያ መረጃ ግጭት የሚያስከትል ሊሆን ይችላል ማለት ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ይሄኛው አይነት ገለልተኝነት በፍጹም ሊጠቅም አይችልም፡፡ መገናኛ ብዙኃን ማለት ለአንድ ሀገር እድገትና ብልጽግና፣ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መስፈን የሚሠራ መሆን አለበት፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የጋዜጠኝነት ሙያ ካየነው ዝብርቅርቁ የወጣ ነው፡፡ ለየትኛውም አልሆነም። ለሕዝብም ወገንተኛ ያልሆነ፤ ለእውነትም ወገንተኛ ያልሆነ ነው፡፡ ለዚህ ችግር ብዙ ጊዜ ተወቃሽ የሚሆኑት ጋዜጠኞችና በየዘመኑ ያለው መንግሥት ናቸው፡፡ ልብ ያልተባለው ችግር ግን የህብረተሰቡ የመገናኛ ብዙኃን ግንዛቤ (Media Litracy የሚባለው ማለት ነው) አለመኖር ነው፡፡ በአየር ሞገድ የሚሰራጭ ሬዲዮ ሁሉ ትክክል ይመስለዋል፤ ታትሞ የወጣ ጋዜጣና መጽሔት ሁሉ ትክክል ይመስለዋል፡፡ ይሄ ችግር አልተማረም በምንለው የህብረተሰብ ክፍል ውስጥ ያለ አይደለም፤ ይባስ ብሎ የተማረ በሚባለው ውስጥ ነው፡፡
የተማረ የሚባለው ችግሩ እንዲነገረው አይፈልግም፤ የሚፈልገው ውዳሴ ብቻ ነው፡፡ ባለሥልጣናት የግል መገናኛ ብዙኃን ዘገባ ሁሉ ውሸት መስሎ ይታያቸዋል፡፡ ለግል መገናኛ ብዙኃን ተከታዮችም የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘገባ ሁሉ ውሸት ነው፡፡ ገለልተኛ የሆነ ሰው ግን ዘውግ አይፈጥርም፡፡ ሁሉንም ያያል፤ የተጠራጠረውን ያጣራል፡፡
የጋዜጠኝነት ምሁሩ ዶክተር ተሻገር ሽፈራው ከአዲስ ማለዳ ጋዜጣ ጋር ባደሩት አንድ ቃለመጠይቅ ጋዜጠኝነትና የመብት ተሟጋችነት ተቃራኒ መሆናቸውን ገልጸው ነበር፡፡ በተለይም የክልል መገናኛ ብዙኃን እየሠሩ ያሉት የሠብዓዊ መብት ተሟጋችነትና የመብት ማስከበር ሥራ ነው፡፡ የመብት ተሟጋችነት ሥራ ትልቅ ሥራ ቢሆንም ራሱን የቻለ ዘርፍ እንጂ በጋዜጠኝነት የሚገለጽ ግን አይደለም፡፡ ጋዜጠኛ የሆነውን ሁነት ብቻ ነው ሳያዛባ መዘገብ ያለበት፡፡ የራሱ ወገን ተበድሎ ሊሆን ይችላል፤ በሙያው ውስጥ ግን ተቆርቋሪነቱ ለእውነት ብቻ ነው፡፡ ጋዜጠኝነት ዓለም አቀፍ ሙያ ነው፤ እንኳን በብሄር በሀገር ራሱ የሚታጠር አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው ግን በወገንተኝነት የታጠረ ነው፡፡
የምናወራው ስለሙያው ከሆነ፣ ለእውነት የቆምኩ ነኝ ካለ የራሱን የተከላካይነት ሙግት ብቻ ሳይሆን የሌላውንም ማየት ነው፡፡ የህሊና ሥራ ነው፡፡ ለምሳሌ፤ የሕግ ባለሙያ የሚመራው በተደነገጉ ሕጎች በአንቀጽ እየተመራ ነው፡፡ የህክምና ባለሙያ ወጥ በሆነ ሳይንስ እየተመራ ነው፡፡ ለየትኛው በሽታ ምን አይነት ህክምና ወይም መዲሃኒት እንደሚያስፈልግ ያውቀዋል፡፡ በዚያ መሠረት ይፈጽማል፡፡ እርግጥ ነው በዚህም ውስጥ የፈለጉትን መጥቀምና ያልፈለጉትን መጉዳት ይችላሉ። ሕግ ማዛባት ይቻላል፤ በሽታው የማይፈቅደውን መድሃኒት ማዘዝ ይቻላል፡፡ የጋዜጠኝነት ሥራ ግን ከእነዚህ ሁሉ በላይ የህሊና ሥራ ነው!
በአጠቃላይ፤ መገናኛ ብዙኃን የሕዝብ ወገንተኛ ነን በሚል ስም ለሆነ ቡድን ብቻ መቆም የለባቸውም።ለእውነት ወገንተኛ ነን በሚል ስም ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጭ መረጃ ሊያሰራጩ አይገባም፡፡ የመንግሥት ወገንተኛ ነን በሚል መንግሥትን ብቻ የሚያወድሱ መሆን የለባቸውም፡፡ ለሀገርና ሕዝብ የሚጠቅም፣ ሕዝብን የሚያቀራርብ፣ ወደ ሥልጣኔ የሚወስድ ሥራ ይሥሩ!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 8 ቀን 2016 ዓ.ም