አንዳንድ ሰዎች አሉ፤ ሳይደክሙ፣ ሳይለፉ በሌላው ላብ የሚያድሩ:: ሌሎች ደግሞ አይጠፉም፣ ዕድሜያቸውን በብልጠት የሚሻገሩ፤ ኑሯቸውን ባልሆነ መንገድ የሚመሩ:: በእኔ ዕምነት እንዲህ አይነቶቹ ‹‹ክፉ›› ከመባል ያነሰ ስያሜ ሊቸራቸው አይችልም:: ሁሌም ለራሳቸው ጥቅም የሌላውን ሕይወት ይነጥቃሉ፤ ለእነሱ ደስታ የብዙሃንን ልብ ይሰብራሉ::
የአንዳንድ ሰው ራስ ወዳድነት ደግሞ በእጅጉ አይጣል ያሰኛል:: ሁል ጊዜም የማንነቱ መሠረት ከሌሎች ድካም የሚቆረስ ነው:: ሆን ብሎ ኑሮውን መመሥረት የሚሻው በአንዱ ትከሻ ላይ ተንጠልጥሎ፣ በአቋራጩ መንገድ አሳጥሮ ነው:: ይህ አይነቱ ሰው ምን ተአምር ቢመጣ ይሉኝታ በሚባል መንገድ አያልፍም:: ከራሱ በላይም ሌሎችን ፈጽሞ አያስበልጥም:: ጥቅም ይኑረው እንጂ ያየ፣ ያገኘውን ሁሉ ያለ ሀፍረት ያጋብሳል፤ ያግበሰብሳል::
ከሰሞኑ አንድ አስገራሚ ዜና በማህበራዊ ሚዲያ ደጋግሞ ሲመላለስ አስተዋልኩ:: እርግጥ ነው እንዲህ መሰሉን ወሬ ከዚህ በፊትም ማንበቤ ብርቅ አይደለም:: አሁን ግን ጉዳዩ በዛብኝ መሰል የውስጤን ልተነፍሰው ግድ አለኝ:: በእጄ የገባውን ታሪክ በግርምታ ስደጋግመው ቆይቻለሁ:: ጉዳዩን ፈጽመዋለች በተባለችው ሴት ፎቶ ገላጭነት አነበብኩት እውነታው ግን አሁንም አስደንጋጭ ሆኖብኛል::
መረጃው ድርጊቱ የተፈፀመው በመዲናችን አዲስ አበባ ስለመሆኑ ያስረዳል:: ከዚህች ሴት ምስል ጎን በግልጽ የሚታዩት በቁጥር ጥቂት የማይባሉ፣ ዘመን ወለዱ ቴክኖሎጂ የሚራመድባቸው ዘመናዊ ስልኮችና ላፕቶፖች ናቸው:: እንደ ታሪኩ ጥቆማ የዚህች ሴት ዋነኛ ዓላማ የተዘረፉ ንብረቶችን ከሌቦች በመግዛት መሸጥና ያለአግባብ መክበር ነው::
ሴትየዋ ሕጋዊ የኤሌክትሮኒክስ መሸጫ ሱቅ ባለቤት እንደመሆኗ ተፈላጊ የሚባሉ ሞባይሎች፣ ላፕቶፕችና ታብሌቶች በእጇ ናቸው:: ገዢዎች በመጡ ጊዜም ያሻትን ገንዘብ ለመደራደር ወደ ኋላ አትልም:: ሁሌም ቢሆን የምትጠየቀውን ከገዛችው ዋጋ በላይ አጉና ለገበያ ታቀርባለች:: የሚገዛው ይገዛታል፤ ያልተስማማም ደጋግሞ ይከራከራታል::
በግብይቱ ሂደት በጣም የሚገርመው የገዢዎቹ ልበ ሙሉነት ነው:: አብዛኞቹ ሞባይልና ላፕቶፕ ለመግዛት ሲሄዱ ስለሕጋዊነቱ ጉዳይ ደንታ የላቸውም:: ከሚታወቀው የገበያ ዋጋ ዝቅ እስካለ ድረስ ተደራድሮ ለመግዛት ዓይናቸውን አያሹም:: እንዲህ አይነት ሰዎች ልክ እንደጭቃ ውስጥ እሾህ ናቸው:: ሲረገጡም፣ ሲወጉም በግልጽ አይታዩምና::
በዚህ ታሪክ ላይ በግልፅ እንደተቀመጠውም በሱቁ የተያዙት ንብረቶች በዘረፋ የተገኙና ከሌቦች እጅ በአነስተኛ ዋጋ የተገዙ ናቸው:: እነዚህ ሕገወጥ ንብረቶች ሕጋዊ ሱቅ ተከፍቶላቸው በአደባበይ ሲሸጡ ከጥርጣሬ ዓይኖች እንዲርቁ ለማድረግ ሊሸፋፈን፣ ሊደባበቅ ይችላል:: ደላሎች፣ አቀባባዮች፣ ሻጭና ገዢዎች በሚመላለሱበት መስመር ግን ምስጥር ሆኖ እንደማይዘልቅ ግልጽ ነው::
እውነታውን ራቅ አድርገን እንመርምር ካልን ደግሞ ችግሩ ከብዙ ጥጎች ሊያደርሰን ግድ ይላል:: ማንም እንደሚረዳው ንብረቶቹ በአግባቡ የመጡ አለመሆናቸው ይታወቃል:: በእንዲህ አይነቶቹ አጋጣሚዎች ደግሞ ከዝርፊያና፣ ድብደባ የተሻገረ ሕይወትን ሊነጥቅ የሚችል ወንጀል ጭምር ይፈጸማል::
የዘራፊዎቹ የመጀመሪያ ዓላማ ዓይናቸው የገባን ንብረት ባሻቸው ስልት ከባለቤቱ ነጥቆ መውሰድ ነው:: በዚህ ሂደት፣ ተዘራፊው፣ ቢጎዳ አልያም ቢሞት ለእነሱ ተለምዷዊ አጋጣሚ ብቻ ይሆናል:: የገዚዎቹ ተሳትፎ እንደፊተኞቹ ይሆናል ባይባልም እነሱም በእጅ አዙር ድርጊቱን ከመቀላቀል አይርቁም:: ግብይቱ ከተለመደው የገበያ ዋጋ ቅናሽ ካለውና አዲስ ዕቃ አለመሆኑ ካታወቀ ግን ሂደቱ ሌላኛውን አቅጣጫ ስለመያዙ አስረጂ አይሻውም::
ገዢዎቹ እውነቱን አምነው ለመቀበል ባይደፍሩም በርካሽ እየገዙት ያለው ንብረት ውድ የሰው ልጅ ሕይወትና ላብ የተከፈለበት፣ ዕንባና ደም በከንቱ የፈሰሰበት ታሪክን የያዘ ሊሆን ይችላል:: አንዳንዶቹም ይህንኑ ሀቅ አሳምረው ያውቁታል:: ከህሊና በላይ የሆነ ራስ ወዳድነታቸው ግን ጥቅምን ለማስቀደም ወደ ኋላ የሚል አይደለም::
አንዳንዴ አንዳንድ ሰዎች በእዲህ አይነቱ ድርጊት ተሳትፈው ሲያዙ የሚሰጡት ምላች ያስገርማል:: በተለይ ገዢዎች ሆነው ሲገኙ ሽምጥጥ አድርገው ለመካድ ቃላቸው በአንድ የታሳረ ነው:: ብዙዎቹ ዕቃዎቹ የተሰረቁ መሆናቸውን እንደማያውቁ ይናገራሉ:: ጥቂት የማይባሉትም እነዚህን ዕቃዎች መግዛት ወንጀል ስለመሆኑ ግንዛቤው እንደሌላቸው ለማስረዳት ይሞክራሉ::
‹‹ሕግን አላውቅም›› ማለት ግን መቼም ቢሆን ከተጠያቂነት አያድንም:: በዚህ የሽያጭ ሂደት ዘራፊው፣ ደላላው፣ ሻጭና ገዥው ሁሉ በሕግ ፊት እኩል ናቸው:: ማናቸውም ከተጠያቂነት ሊያመልጡ፣ ሊደበቁ አይችሉም::
በብልጠትና በራስ ወዳድነት ልማድ የሚጓዙ ብዙዎች ስለሌላው ሕይወት ደንታ ቢሶች ናቸው:: ነፍስ ቢጠፋ፣ ደም ቢፈስ፣ ንብረት ቢነጠቅ፣ ጉዳያቸው አይደለም:: እነሱ መቼም ቢሆን ሕይወትን ከገንዘብ አያወዳድሩም:: ሁለቱንም በእኩል ሚዛን ቢያኖሩላቸው ፍላጎታቸው ጥቅምን ወደሚያሳፍሳቸው ንዋይ ብቻ ያጋድላል::
እነሱ ላብ፣ ዕንባ ኀዘንና ችግር ይሏቸውን እውነት የሚሸከም ትከሻ ኖሯቸው አያውቅም:: በየጊዜው የሚሆነውን እየሰሙና እያዩ መልሰው በዚሁ መንገድ ለመራመድ ፈጣን ሆነው ይገኛሉ:: እንዲህ አይነቶቹ ልማደኞች ማንነታቸው ከሌሎች ሰዎች ይለያል:: ንብረቶች ተዘርፈው፣ ሰዎች ተጎድተው በሚመጣ ልዩ ጥቅም፣ ላልተገባ ብልጽግና ይሮጣሉና::
የመንድ ላይ ዘራፊዎች ዕድሚያቸው መርዘም የቻለው የሚነጥቁትን ንብረት በሚገዟቸው ሕገወጥ ነጋዴዎች ብርታት ነው:: ለእነዚህ ነጋዴዎች መበራከት ምክንያቶቹ ደግሞ በአነስተኛ ዋጋ ተደራድረው የሚገዙ ተጠቃሚዎች ተጠያቂ ሊሆኑ ግድ ይላል::
ማንም ይሁን ማን በላብ በጉልበቱ ሰርቶ መኖር ሲችል በሚፈጠሩ ጥልፍልፍ የግንኙነት መረቦች ብዙሃን ሕይወታቸው ሲጠፋ፣ ንብረታቸው ሲዘርፍ ቆይቷል:: ዛሬም ቢሆን ይህ ችግር በጠራራ ጸሀይ ጭምር እየተፈጸመ ስለመሆኑ የምናስተውለው እውነታ ነው:: አንዱ ከአንዱ ጋር በሚፈጥረው ያልተገባ ትሰስር ውስጥ ለውስጥ ያልታሰቡ የወንጀል ድርጊቶች ይፈጸማሉ::
‹‹ሌባ ሲሰርቅ ሳይሆን ሲከፋፈል ይጣላል›› እንዲሉ ሆኖ በአብዛኛው እንዲህ አይነት ምስጢሮች የሚጋለጡት የአንደኛቸው በጥቅም አለመስማማት በሚፈጥረው አፈንጋጭነት ነው:: ብዙ ጊዜ ሕገወጥ ሂደቶች በየአደባባዩ ሲከወኑ በድብቅ ነው ለማለት አይቻልም:: አንድ ጉዳይ የሚወጠን የሚፈጸመው በሰዎች መሀል የመሆኑን ያህል፤ የሚታይ የሚጋለጠውም መልሶ በሰዎች እይታና አንደበት ይሆናል::
ለዚህም ነው ፖሊስ ይህን ስልት ተጠቅሞ እውነታውን ፈልፍሎ የሚያወጣው:: አንዳንዴ ግን ህብረተሰቡ ራሱ፣ እየተዘረፈና ምስጢሩን እያወቀ ሁኔታውን የማያጋልጥበት አጋጣሚ ይበረክታል:: እንዲህ ማድረጉ ወንጀሉን ከማስፋፋት ያለፈ ግን ለማንም የሚበጅ መፍትሄ አይሆንም::
ከሰሞኑ ዘገባ ለማወቅ እንደተቻለው በግለሰቧ እጅ ላይ የተገኙ በርካታ ሞባይሎች፣ ላፕቶፖችና መሰል ኤሌክትሮኒክስ ዕቀዎች ለሌሎች ከማለፋቸው በፊት እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል:: ፖሊስ እንዳለውም ‹‹ንብረት ተዘርፎብናል፣ ጠፍቶናብል የሚሉ ወገኖች ቢገኙ ተገቢ ማስረጃዎቻቸውን በማሳየት ንብረቶቻቸውን መውሰድ እንደሚችሉ ተገልጿል::
እንደ እኔ ግን ሰዶ ከማሳደድ ይልቅ ሁሉም አካባቢውን ቢፈትሽ፣ ከሕገወጦች ተባባሪነት ራሱን ቢያርቅ እወዳለሁ:: ‹‹የሰው በልቶ አያድሩም ተኝቶ›› ነውና በሰው ንብረት መጠቀም፣ በሌላው ቁስል እንጨትን እንደ መስደድ፣ በሌሎች ሕይወትና ኑሮ እንደመቀለድ መሆኑ ሊታሰብበት ይገባል:: በዚህ አጋጣሚ የሚያዙ ግለሰቦችም ስለሰሩት ሕገወጥነት ፍትሃዊ ፍርድ ሲሰጣቸው ማየትን ልንላመደው ግድ ይለናል:: በሕጋዊነት ሽፋን መቀለድ የጭቃ ውስጥ እሾህ እንደ መሆን ነውና::
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 15 ቀን 2016 ዓ.ም