
አዲስ አበባ:- የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ በከባድ የሙስና ወንጀል ድርጊት ተጠርጥረው ክስ ከመሰረተባቸው ተከሳሾች ላይ ያለ አግባብ የተዘረፈ ከ95 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ወደ መንግሥት ካዝና ገቢ ማድረጉን አስታወቀ።
የጠቅላይ ዓቃቤ ህግ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ቱኑ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ያለ አግባብ የተዘረፉ የመንግሥትና የህዝብ ሀብት የሆኑ ንብረትና ገንዘብ ለማስመለስ በ2011 ዓ.ም ትኩረት አድርጎ በሰራው ሥራ፤ በከባድ የሙስና ወንጀል ድርጊት ተጠርጥረው ክስ የተመሰረተባቸውን ተከሳሾች በሰሩት ወንጀል በህግ ተጠያቂ የማድረጉ ሥራ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በተከሳሾች ያለ አግባብ የተመዘበረ ከ95 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ወደ መንግሥት ካዝና ገቢ ተደርጓል፡፡
ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት፤ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ክስ ከመሰረተባቸው ተከሳሾች ከህዝብና ከመንግሥት የዘረፉትን ንብረትና ገንዘብ ለመንግሥትና ለህዝብ ተመላሽ ለማድረግ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ከመሆኑም ባሻገር፤ በርካታ የሙስና ወንጀሎች በህግ ጉዳያቸው እየታየ ይገኛል።
ለመንግሥት መመለስ ከሚገባው ገንዘብ በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በህግ ፊት ጉዳያቸው ከታየው ተከሳሾች፣ ከተከሳሾች ጠበቃና ተወካዮቻቸው ጋር በመደራደር በ2011 ዓ.ም በጀት ዓመት ከ95 ሚሊዮን ብር በላይ በክርክር ሂደት ውስጥ አልፎ ለመንግሥት ገቢ ሆኗል፡፡
ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ሌሎች ያለ አግባብ የተዘረፉ የመንግሥትና የህዝብ ንብረቶችና ገንዘብን ለማስመለስ ብዙ ክርክር እያደረገ እንደሆነ የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ ያለ አግባብ የተመዘበሩ ንብረትና ገንዘብ በክርክር ሂደቱ ለማስመለስ ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ፤ የክርክር ሂደቱን በማሳለጥ ጉዳዩን ቶሎ በመቋጨት ያለአግባብ የተመዘበሩ የመንግሥትና የህዝብ ሀብት እንዲመለስ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
‹‹በአጠቃላይ ከባድ የሙስና ወንጀል ድርጊትን ከመከላከልና በሙስና የተመዘበሩ የመንግሥትና የህዝብ ሀብትን ለማስመለስ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው። በዚህም በሙስና ወንጀል የተዘፈቁ አካላትን በመለየት በህግ አግባብ ተጠያቂ ከማድረግ ባሻገር ያለ አግባብ የዘረፉትን የመንግሥትና የህዝብ ሀብት የማስመለሱ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል›› ብለዋል ዳይሬክተሩ።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 3/2011
ሶሎሞን በየነ