
አዲስ አበባ፡- ለሦስት ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያግዝ ስትራቴጂ እየተዘጋጀ መሆኑን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታ ወቀ፡፡ የሚዘጋጀው ስትራቴጂ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ያካተተ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ትናንት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የንግድና ኢንዱ ስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተካ ኃይለየሱስ እንደገለጹት፤ እየተዘጋጀ ያለው ስትራቴጂ ከዚህ በፊት ያጋጥሙ የነበሩ ችግሮችን መነሻ በማድረግ ነው፡፡
ስትራቴጂው ባለፈው ሐምሌ 16 እና 17 ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት የተደረገበት ሲሆን፤ በቀጣይም የአከዋወን ዝር ዝሮች ይዘጋጁለታል፡፡ ሰነዱ ተጠናቆ ወደ መሬት ሲወርድ ተዋናዮቹ ብዙ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ስትራቴጂው ገና ሰነድ እንደሆነ የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ መገናኛ ብዙኃንና የሚመለ ከታቸው አካላት ሊያስተዋውቁት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ስትራቴጂው ለአምስት ዓመት የተዘጋጀ ሲሆን፤ ቀጣይነት ያለው የሥራ ዕድል ለመፍጠር ይሰራበታል፡፡
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ፤ ስትራቴጂው በገጠር ያሉ ዜጎችን የሥራ ፈጠራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል ነው፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እየተስፋፉ በመሆኑ የአገር ውስጥ ግብዓቶች የሚገኙት ገጠር አካባቢ በሚፈጠረው የሥራ ዕድል ነው፡፡ ለዚህም የተቀናጁ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እየተሰሩ ናቸው፡፡
በአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ፤ በትግራይ ሁመራ፣ በአማራ ክልል ቡሬ፣ በኦሮሚያ ክልል ቡልቡላ እና በደቡብ ክልል ይርጋለም ያሉት ብዙ የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ፡፡ በደቡብ ክልል ይርጋለም ያለው ከሁለት ሺህ በላይ ለሆኑ አርሶ አደሮች አገልግሎት እየሰጠ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ስትራቴጂው በርካታ አካላት የተሳተፉበት መሆኑን እና የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት፣ የፌዴራል ጥቃቅንና አነስተኛ ማኑፋክቸሪንግ ማስፋፊያ ባለሥልጣን በጋራ መስራታቸው ተገልጿል፡፡
አዲስ ዘመን ነሃሴ 3/2011
ዋለልኝ አየለ