ተወዳጇ ሁለገብ የጥበብ ባለሙያና የኢትዮጵያ እርቀ ሰላም ኮሚሽን ምክትል ሰብሳቢ ሎሬት የትነበርሽ ንጉሴ ከሰሞኑ በአንድ መድረክ ላይ ተገኝታ ባደረገችው ንግግር “ኢትዮጵያ በተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከዓለም አንደኛ ናት ተብሏል።ይኼ ከቤታቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ብቻ ነው።እኔን የሚያሳስበኝ በጣም ትልቁ ችግር ግን ከሙያቸው የተፈናቀሉ ብዙ ተፈናቃዮች መኖራቸው ነው።
ምክንያቱም አሁን ሁላችንም ፖለቲከኞች ሆነናል… እግራችን ነው እንጂ የቀረው አፋችንና ጭንቅላታችን ቤተ መንግስት ገብቷል።ሁላችንም ቤተ መንግስት ከመግባታችን የተነሳ ቤተ ክርስቲያን፣ ቤተ ሙከራና ቤተ መጻህፍት ውስጥ ማንም የለም…ምክንያቱም ብዙዎቻችን ከሞያችን ተፈናቅለን ፖለቲከኞች ሆነናል…ዛሬ ላይ የኢኮኖሚ ባለሙያው ሥራውን ትቶ የነ እንትና ብሔር ስንት ሆነ? ምናምን… የሚለውን ሲያወራ ነው የሚውለው፤ እናም እኔ የምለው ሁሉም ወደየራሱ ሙያ ይመለስ…”
በማለት አሁን ላይ በአገሪቱ ሁሉም ነገር ፖለቲካ እየሆነ መምጣቱ በጣም አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑን አጽንኦት ሰጥታ ተናግራለች።ይህ የሎሬቷ ሃሳብ ብቻ አይደለም።በርካታ ኢትዮጵያውያንም በዚህ ጉዳይ ላይ በተደጋጋሚ ተመሳሳይ ትችትና ወቀሳ ሲያቀርቡ ይሰማሉ።እውነት ነው በሚያስደነግጥ ሁኔታ አሁን ላይ ሁሉም ነገር ፖለቲካ ሆኗል።መንግስትን መተቸትና መደገፍ ይቅርና ከፖለቲካ ጋር ፍጹም ንክኪ የሌላቸው የሚመስሉ ጥቃቅን ጉዳዮች ሳይቀሩ በሚያስገርም የአዛምድ ቀመር እንደምንም ተጠጋግተው ፖለቲካዊ መልክ ሲሰጣቸው ማየት ዘወትር የተለመደ ክስተት ከመሆን አልፎ የኑሯችን አንድ አካል እየሆነ መጥቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት በዚህ አገር ፖለቲካ ያልሆነ ምንም ነገር የለም።መሳቅ ፖለቲካ ነው፣ ማልቀስም ፖለቲካ ነው፣ ዘፈን ፖለቲካ ነው፣ መዝሙርም ፖለቲካ ነው።ሥራ መስራትም፤ ከሠራ በኋላ መዝናናትም ፖለቲካ ናቸው።ስታዲየም የምትሄደው ጨዋታ አይተህ ራስህን ለማዝናናት አይደለም፤ የአንድ ክለብ ደጋፊ የምትሆነውም የምትደግፈው ቡድን የአጨዋወት ዘይቤ ማርኮህ የኳስን ጥበብ ለማድነቅ ሳይሆን የፖለቲካ አጋርነትህን ለማሳየት ነው።ውይ የኔ ነገር ስፖርትም ፖለቲካ ሆኗል ነው እንዴ ያልኩት።ዋነኛውን የፖለቲካ መድረክ።ሙዚቃን ለመንፈስ እርካታ ማዳመጥ፣ ፊልምን ለመዝናኛ መመልከት ቀርቷል።ጥበብ፣ ባህል፣ ሃይማኖት፣ ኢኮኖሚውም ንግዱም ሁሉም ከባህሪያዊ አውዱ ወጥቶ በፖለቲካ መነጽር ይመረመራል።
ጋብቻ፣ ፍች፣ ጓደኝነት፣ ጉርብትና፣ ዕድር ዕቁብ የቀደመ ነጻነቱን ካጣ ሰነባብቷል።በማህበራዊ ኑሮ ውስጥ ፖለቲካ ምን አገባው ድሮ ቀርቷል። ከሰሞኑ ሲሆን የነበረውን አላየንም እንዴ።አንድ ኑሮውን አሜሪካ ያደረገ ኢትዮጵያዊ ወጣት ከሚስቱ በላይ ሌላ ሴት ይዞ መታየቱና በትዳሩ ላይ ወሰለተ መባሉ ትልቅ ፖለቲካ ሆኖ ከአሜሪካ እስከ ኢትዮጵያ ዋነኛ መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ ሲሰነብት።ምነው ቢሉ ከሚስት ጋር መጣላትም ፖለቲካ ሆኗላ።ይህ እንዴት ይገርማል።ሞት ራሱ ፖለቲካ ሆኖ የለ እንዴ! በአጠቃላይ ባህል፣ ኪነ ጥበብ፣ ማህበራዊ ኑሮ፣ ራሱ የሃገር ታሪክ ሳይቀር ፖለቲካ ሆኗል፡፡
‹‹እንቅስቃሴዎች ሁሉ ዳንስ ናቸው›› የሚለው ዘፈን ‹‹እንቅስቃሴዎች ሁሉ ፖለቲካ ናቸው›› በሚለው ተቀይሯል።እናም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በዚህ ደረጃ ሁሉም ነገር ፖለቲካዊ አንድምታ እየተሰጠው ሁሉም ነገር ፖለቲካና ፖለቲካ ብቻ መሆኑ በእርግጥም የሚያስደነግጥም የሚያሳስብም ጉዳይ ነው።እኔም በዚህ አገር ላይ ስንት ነገር እያለ የሁሉም ትኩረት ፖለቲካው ላይ ብቻ መሆኑና የሚያገባውም የማያገባውም ሁሉም ፖለቲከኛ መሆኑ ከሚያሳስባቸው ሰዎች ወገን ነኝ።
ይሁን እንጂ እኔ ከእነዚህ ሰዎች የምለይበት አንድ መሰረታዊ ነጥብም አለኝ።ምክንያቱም አብዛኛው ሰው እያስጨነቀው ያለው ባልተለመደ መልኩ ሁሉም ነገር ወደዚያ እየተወሰደ ሁሉም ነገር ፖለቲካ መሆኑ ነው።እኔን ሁሉም ነገር ፖለቲካ ከመሆኑም በላይ አብዝቶ የሚያስጨንቀኝና የሚያሳስበኝ እንዲህ እንዲሆን ያደረገው ገፊ ምክንያቱ ነው።በመሰረቱ ሁላችንም ሊያሳስበንና ሊያስጨንቀን የሚገባው ወሳኙ ነገርም ይኼ ነው ብዬ አምናለሁ።ለመሆኑ ሎሬት ወይዘሮ የትነበርሽ እንዳለችው ተማሪውም፣ አስተማሪውም፣ ምሁሩም፣ ባለሙያውም፣ ቄሱም፣ ሸኩም ሁሉም የሚመለከተውን መስራት ትቶ ከሙያው እየተፈናቀለ ቤተ መንግስት የገባው ፖለቲካውን ወዶት ነውን? ጥያቄው ይኼ ነው፡፡
ሁሉም ፖለቲካ ውስጥ ገባ ወይስ ፖለቲካው ሁሉም ነገር ውስጥ ገባ?
በእርግጥም ሁሉም ነገር ፖለቲካ የመሆኑ ጉዳይ የሚያሳስበን ከሆነ መጠየቅ የሚገባን አንድ መሰረታዊ ጥያቄ አለ።ለመሆኑ ሁሉም ነገር ፖለቲካ ሁሉም ሰው ፖለቲከኛ የሆነበት ምክንያቱ ምንድን ነው? ሁሉም ነገር ፖለቲካ ሆነ ወይስ ፖለቲካ ሁሉንም ነገር ሆነ? ሰው ነው ፖለቲካ ውስጥ ገባው ወይስ ፖለቲካው ነው ሰው ህይወት ውስጥ የገባው? ሰው ሁሉ ፖለቲከኛ የሆነበት ምክንያት ወዶ ወይስ ተገዶ? የክስተቱን ትክክለኛ ገጽታ ለመረዳት እነዚህ መሰረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘት አለባቸው።በእኔ ዕምነት ለችግሩ ዋነኛው ተጠያቂ ፖለቲካው ራሱ ነው።
ሁሉም ነገር ፖለቲካ ለመሆኑ፤ ለችግሩ ዋነኛው ተጠያቂ ፖለቲካው ራሱ ነው።ሁሉም ሰው ፖለቲከኛ የሆነበት ምክንያትም ወዶ ሳይሆን ተገድዶ ነው ብዬ አስባለሁ።ሰው ሁሉ የሚመለከተውን ሙያውን እየተወ ፖለቲካ ውስጥ የገባው ፖለቲካውን ወዶት፤ ፖለቲከኛ መሆኑንም ፈልጎት ሳይሆን ፖለቲካው ህይወቱ ውስጥ ገብቶበት እንዲኖርበትም አስገድዶት ነው ብዬም አምናለሁ።ምክንያቱም የፖለቲካ ባህላችን በመጠላለፍና በመጠፋፋት የሴራ ፍልስፍና የተተበተበ፣ ዘመናት ሲለዋወጡ አብሮ ያልተለወጠ፣ በፍቅር ወንጌል ያልተጠመቀ፣ ፍርድና ፍርጃ በሞላበት የኦሪት ህግ ላይ ቆሞ የቀረ ኋላ ቀር በመሆኑ ነው።
ከመተባበር መጠላለፍን፣ ከመተማመን መጠራጠርን፣ ከፍቅር ፍርሃትን፣ ከህዝብ ጥቅም ራስን የሚያስቀድም እንዲህ አይነቱ ኋላ ቀር የክፋትና የጥፋት ፖለቲካ ደግሞ ህልውናውን ለማረጋገጥ የሚጠቀምበት ስልቱ እንደ ባክቴሪያ በየትኛውም ቦታ መኖርን ነው።
እናም ፖለቲካው ከመደበኛው ህዝብና መንግስትን የማስተዳደርና የመምራት ተግባሩ ወጥቶ በህብረተሰቡ ህይወት ውስጥ ይደበቃል።ምክንያቱም ፖለቲካ ማለት በዋነኝነት የመንግስትን ስልጣን ይዞ በሃገርና ህዝብ ጉዳይ ላይ መወሰን ማለት ነው።ይህም ከሚያስገኘው ጥቅም እኩል የሚያስጠይቅ ታላቅ ኃላፊነት ያለበት ነውና ራሱን ስልጣን ላይ ማቆየትን ብቻ ዓላማና ግቡ ያደረገው እንዲህ ዓይነቱ ኋላቀር የፖለቲካ ባህል ኃላፊነቱን መወጣት ስለሚከብደው ከተጠያቂነት ለመራቅ ከዋናው ተግባሩ ወጥቶ በማያገባው እንዲገባ ያደርገዋል።በዚህም ፖለቲካው ራሱን በትክክል መምራት ሲያቅተው ኢኮኖሚው ውስጥ ይገባል፣ ባህላዊ ጉዳዮች ውስጥ ይገባል፣ ማህበራዊ ኑሮ ውስጥ ይወሸቃል።ምን ይሄ ብቻ ፍጹም ወደማያገባው መስጊድና ቤተ ክርስቲያናት ውስጥም ይገባል።በአጠቃላይ ሁሉም ነገር ውስጥ ገብቶ እየተደበቀ ሁሉንም ነገር ፖለቲካ እንዲሆን ያደርገዋል።ሁሉም ነገር ፖለቲካ ሲሆን ደግሞ ወዶ ሳይሆን ተገዶ ሁሉም ፖለቲከኛ ይሆናል፡፡
ከእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ የሆነብን የ “እኛ” እና “እነርሱ” ፖለቲካ
እንዳለመታደል ሆኖ ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት የፖለቲካ ባህላችን እንደ ሌላው ታሪካችን የሚያኮራ አይደለም።በሴራና በክፋት የሚመራ እጅግ የሚያስጠላ የፖለቲካ ባህል ነው ያለን (በነገራችን ላይ ከሁሉም በፊት ቀድመን ሰልጥነን ከሁሉም ኋላ ለመቅረታችንም ዋነኛው ምክንያት ይኸው የፖለቲካ ባህላችን ነው ብዬ አምናለሁ።በዚህ ጉዳይ ላይ በሌላ ጽሁፍ በስፋት የምመለስበት ይሆናል)።ከ1950 ዎቹ ጀምሮ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት በተለይም ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ደግሞ “ከእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ ወትሮውንም ጎታች የሆነውን ቀሽሙን የፖለቲካ ባህላችንን የበለጠ አስቀያሚ ገጽታ እንዲላበስ ያደረገ “የብሔር ፖለቲካ” የሚባል ሌላ በሽታ ጨምረናል።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት የአንድ አገር ፖለቲካ የበለጠ እየተበላሸ በሄደ ቁጥር ከቤተ ሙከራ እንዳመለጠ ቫይረስ ከመደበኛ መኖሪያው ወጥቶ ወደ ሁሉም ቤት ይሰራጫል።የእያንዳንዱን ቤት ያንኳኳል።ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ፖለቲከኞችና የመንግስት መዋቅርና ባለስልጣናት አልፎ ወደ ሰፊው ህዝብ ይዛመታል።ወደእያንዳንዱ ሰው ህይወት ዘልቆ ይገባና የህዝቡን ህይወት ማናጋት ይጀምራል።በዚህም ምስኪኑ ህዝብ ሳይወድ በግድ ስለ ፖለቲካ ማውራት ይጀምራል፤ ምስኪኑ ህዝብ ሳይደርስበት የደረሰበትን ፖለቲካ ለመላመድ ሳይፈልገው ሁሉም ፖለቲከኛ ይሆናል።
አንድ ሁለት ማሳያዎችን እንጥቀስ።ከሦስት ወይም ከአራት ወራት በፊት ይመስለኛል።ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ደም ያፋሰሰ ግጭት ተነስቶ ነበር።ታዲያ የግጭቱ መነሻ ነው ተብሎ በመንግስት አካላት የተነገረው በጫኝና አውራጅ መካከል የተፈጠረ ፀብ ነበር።ኋላ ላይ ግን የሁለቱ ግለሰቦች ጸብ ፖለቲካዊ መልክ ይዞ ለያዥ ለገራዥ አስቸጋሪ ወደሆነ የህዝብ ግጭት ተቀይሮ ቀላል የማይባል የሰው ህይወት ከቀጠፈ በኋላ በስንት ጥረት መብረዱ የሚታወስ ነው።አንድ መኪና ላይ በሚሰሩ በሁለት ጫኝና አውራጅ ጓደኛሞች መካከል የተፈጠረ ቀላል የግለሰቦች ዕለታዊ ግጭት እንዴት በዚህ ደረጃ አድጎ ፖለቲካዊ መልክ ሊይዝና ህዝብን ጦርነት ውስጥ ሊያስገባ ቻለ? ያው ዘመኑ ሁሉም ነገር ፖለቲካ የሆነበት ክፉ ጊዜ ስለሆነ? ይህ ፈጽሞ አለማወቅ አለያም እያወቁ ራስን ማታለል ነው የሚሆነው።ሁሉም ነገር ፖለቲካ እየሆነ ስለመጣ አይደለም የግለሰቦች ፀብም ፖለቲካ የሆነው።የግለሰቦች ጸብ ሳይሆን ፖለቲካ የሆነው ፖለቲካው ነው ተራ የግለሰቦች ጸብ ድረስ ዘልቆ የገባው።ከፖለቲካም ሰውነትን ክዶ በግዑዝ መንጋ የሚያምነው ቆሻሻው የዘር ፖለቲካ! እርሱ ነው የወንድማማቾችን ተራ የዕለት ግጭት ብሔር በሚባል በግለሰቦች ምርጫ ሳይሆን በተፈጥሮ አስገዳጅነት ሰዎች ላይ በተጫነ መንጋ አቧድኖ ጎራ ለይቶ ወደ እርስበእርስ ጦርነት የሚያስገባ።
ታላቋ የሙዚቃ ንግስት ድምጻዊት አስቴር አወቀ እንዳለችው አባቶቻችንማ ዘር መርጠው አልነበረም እድር የሚገቡት።አሁን ግን ፖለቲካችን ዘቅጦ የመጨረሻው ደረጃ ላይ ሲደርስ እንኳን በህይወት እያለን ሞተን እንኳን ሬሳችን ከብሔራችን ውጭ በአገራችን የማይቀበርበት ደረጃ ላይ ደርሰናል።በቋንቋችን ካልሆነ በስተቀር እንዳንገበያይ የሚያስተምሩ ምሁራንን አፍርተናል፡፡
ስም ፖለቲካ ሆኗል።የታዋቂው ኢንተርናሽናል የእግር ኳስ ዳኛ በአምላክ ተሰማ ሙሉ ስም በቅርቡ ፖለቲካ ሆኖ እንደነበር አስታውሳለሁ።አብዛኛውን ጊዜ ዳኛው በአምላክ ተሰማ በሚለው ስማቸው ነው የሚታወቁት።ዳኛው በሙያቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ ዓለም አቀፍ ስምና ዝናን እያተረፉ ሲመጡ በተለይም የዘንድሮውን አፍሪካ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ለመምራት ከተመረጡት አራት ምርጥ ዳኞች መካከል አንዱ መሆናቸው ሲታወቅ አንድ ትልቅ ስም ያለው የመንግስት ሚዲያ ስለሰውዬው ዜና በሚሰራበት ወቅት በአምላክ ተሰማ ወዬሳ ብሎ መግለጹ ነበር ፖለቲካ የሆነው።
እንደዚሁ የሟቹ ኢታማዦር ሹም ጠባቂ ስምም “መሳፍንት ጥጋቡ መኮንን” መሆኑ ትልቅ ፖለቲካዊ አንድምታ ተሰጥቶት ተመልክተናል።ታዲያ ሁሉንም ነገር ከፖለቲካ ጋር እያገናኘ አስቸጋሪ ያደረገው ህዝቡ ነው እንዳትሉኝ።በ“እኛ” እና “እነሱ” ህልዮት በተቃራኒ ጎራ ተሰልፎ የቆመው ዋልታ ረገጡ የብሔር ፖለቲካችን እንጂ! የሰዎች መጠሪያ ስም ድረስ ዘልቆ ገብቶ ስምንም ፖለቲካ ያደረገው ካልከፋፈለ የማይሆንለት፣ ካልተለያየ የማይቆመው ይኸው ራስ ወዳዱ በጥፋት መንፈስ የሚጋልበው ሰይጣናዊው የብሔር ፖለቲካ እንጂ ህዝቡማ እንኳንስ ለእንዲህ ዓይነቱ የጥፋት ፖለቲካ የመልካም ነገር መሳሪያ ሆኖ ለሚያገለግለው ሰናይ ፖለቲካም ፍላጎት ኖሮት አያውቅም።“ፖለቲካ እሳት ነው፣ ፖለቲካን በሩቅ ነው” እየተባለና እያለ የኖረ ህዝብ ነው።እናም ሊገባን ይገባል ስም አይደለም ፖለቲካ ውስጥ የገባው፤ ፖለቲካው ነው ስም ውስጥ ገብቶ እየበጠበጠ ያለው፡፡
ፖለቲካውን ማሰልጠንና ሰውኛ ማድረግ ያስፈልጋል
እናም ወገኖቼ “ሁሉም ነገር ፖለቲካ ሆነ፤ ሰውም በማያገባው እየገባ ሁሉም ፖለቲከኛ ሆኖ አለቀ” እያልን ዋናውን ጉዳይ ትተን “መሆኑ” ላይ ተጣብቀን ክስተቱ ላይ ከማላዘን “ለምን?” ብለን መጠየቅ ይኖርብናል።መፍትሔውም አንድ እና አንድ ነው።እርሱም የችግሩን መሰረታዊ መንስኤ ማወቅ! የችግሩ ዋነኛ መንስኤም ፖለቲካው ራሱ መሆኑን ለማሳየት ሞክሬያለሁ።ለዚህም ሳንውል ሳናድር ኋላ ቀሩን የፖለቲካ ባህላችንን መለወጥ ይጠበቅብናል።እንዴት ለሚለው ባጭሩ በመጠላለፍ፣ በመጠፋፋት፣ በራስ ወዳድነት ላይ የተመሰረተውን የሴራና የክፋት ፖለቲካችንን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በማስወገድ በመደጋገፍ፣ በመተባበር፣ በፍቅርና በመልካምነት ላይ የተመሰረተ ስልጡንና ሰናይ የሆነ አዲስ የፖለቲካ ባህል መገንባት ይጠበቅብናል።ከፋፋዩንና አውዳሚውን አፓርታይድ ግርፍ የዘር ፖለቲካ ፍቅርና አንድነትን በሚያለመልም የተሻለ የአብሮነት ፖለቲካ መተካትም ተቀዳሚ አገራዊ ተግባራችን ሊሆን ይገባል፡፡
በአጭሩ ፖለቲካውን “ሰውኛ” ማድረግ ይገባል።ምክንያቱም ፖለቲካ ማለት እኛ እንደምናስበው “ያለ ሴራ የማይሆን”፣ “ውሸት ግድ የሚልበት”፣ “ስልጣን መያዣና ብዙሃኑን ማስገበሪያ” አይደለም።ሮማውያን እንደሚሉት እንዲያውም “ፖለቲካ ማለት ህዝብን ባለጸጋና የተሻለ ማድረጊያ መሳሪያ፣ ፖለቲከኛ ማለት ደግሞ የግል ህይወቱን ለህዝብ የሚሰዋ” ማለት ነውና ለፖለቲካ ያለንን አመለካከትና ግንዛቤ ማስተካከል የሁላችንም የቤት ሥራ ይሁን።ያኔ የፖለቲካ ባህላችን ተለውጦ ሰናይና ስልጡን ፖለቲካ ሲኖረን ፖለቲካው መግባት የማይገባው ቦታ እየገባ ሁሉንም ነገራችንን ፖለቲካ እያደረገ አይበጠብጠንም።ፖለቲካውን ለሚመለከተው ዓላማ ብቻ መዋል ይጀምራልና ሰላማችንን እናገኛለን፣ ሁላችንም በሞያችን ብቻ እንደሚገባን አገራችንን እናገለግላለን፣ ደስታና ብልጽግናም ይሆንልናል።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 1/2011
ይበል ካሳ