የትውልድ ሂደት ገባሮቹ በማይነጥፉ የታላላቅ ወንዞች ፍሰት ይመሰላል። ትናንትም ሆነ ዛሬ ፍሰታቸው ተገትቶ ከማያውቀውና ወደፊትም ይገታል ተብሎ ከማይሰጋባቸው ታላላቅ ወንዞች መካከል የቅዱስ መጽሐፉን የዘፍጥረት የመጀመሪያ ምዕራፍ በማስታወስ አራቱን ጥንታዊያን ማለትም የእኛውን ጉደኛ ግዮን (አባይ) የቅርብና የሩቅ ምስራቆቹን ጤግሮሶ፣ ኤፍራጠስና ፊሶንን ማስታወስ ይቻላል።
እነዚህ ወንዞች ዓለም ከተፈጠረ፤ ዘመን ከተቆጠረ ጀምሮ ፍሰታቸው አልተገታም፤ “እስትንፋሳቸውም” አልተቋረጠም። አይበለውና እነዚህ ወንዞች የተፈጥሮ ግታቸው ቢነጥፍ ኖሮ ለእኛም ሆነ ለጎረቤቶቻችን ሀገራት እና ለመካከለኛው ምሥራቅ ወገኖቻችን ጦሱ ክፉኛ በተረፈን ነበር።
አዋሽ፣ ዋቢ ሸበሌ፣ ተከዜ፣ ኦሞ፣ ባሮና መሰሎቹ የሀገሬ ወንዞች ስማችን ለምን አልተጠቀሰም ብለው በማኩረፍ በበጋ እንደማይከስሙ፤ በክረምትም እየፎገሉ በንዴት ጦፈው ጥፋት እንደማያደርሱ ተስፋ አደርጋለሁ።
አንጋፋው ደራስያችን ከበደ ሚካኤል “አዝማሪና የውሃ ሙላት” በሚል ርዕስ ከዛሬ ሰባ ሰባት ዓመታት በፊት የጻፉት ድንቅ ግጥም የኃያላን ዛቻም ሆነ እንደ ደራሲው ገለጻ የየዋህ አዝማሪ ጥዑም ዜማ የወንዝን ተፈጥሯዊ ፍሰት ሊገታ እንደማይችል ቢታወስ ቦታውም ጊዜውም ይፈቅድ ይመስለኛል። የዋሁ ማሲንቆ ደርዳሪ የወንዙ ሙላት እንዲቀልለት ፈረሰኛውን ውሃ ለማማለል በወንዙ ዳርቻ ቆሞ ሲያዜም የተመለከተው ሌላ መንገደኛ እንዲህ ነበር የመከረው። ከሃያ ሁለቱ የግጥሙ ስንኞች መካከል አራቱን ብቻ ልጥቀስ፤
‹‹እስኪ ተመልከተው ይህ አወራረድ፣
ያልሰማው ሲመጣ የሰማው ሲሄድ፣
ድምጡን እያውካካ መገስገሱን ትቶ፣
ማን ይሰማኝ ብለህ ትደክማለህ ከቶ …››
የትውልድ ፍሰትም እንዲሁ ነው። አይቋረጥም። ፉከራና ቀረርቶ፣ ሰንጎ መገን፣ አምባሰልና ትዝታ፣ አንቺ ሆዬንና መሰል ቅኝቶችን በማፈራረቅ በአራራይ ዜማ በማባበል የትውልድን ቀጣይ ፍሰት አስቆማለሁ ብሎ የሚያንጎራጉርም ሆነ የሚያጉረመርም ትርፉ ጅልነት፤ ጥረቱም በክሽፈት መደምደሙ አይቀሬ ነው።
በወንዝ የተመሰለው ትውልድ መምጣትና መሄድ የፀና እውነት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ሌላም ገጽታ እንዳለው ሊዘነጋ አይገባም። አንዳንድ ወቅት የወንዙ ሙላት በፈረሰኛ እየተመሰለ ሲገነፍልና ዱታ ነኝ እያለ በመፎከር ሲያቅራራ የሚያደርሰው ጥፋት በቀላሉ የሚገመት ላይሆን ይችላል። ሰብል ያጠፋል፣ መንደር ያወድማል።
ሕይወትና ንብረትን ለአደጋ ያጋልጣል። በተለይም ክረምት ሲያጉረመርም፤ በበጋ ወራት ደግሞ ያ ሁሉ የወንዙ ድንፋታ ሰክኖ የውሃው መጠን ስለሚቀንስ እንኳን ሊደነፋ ቀርቶ ድምጹንም ሳያሰማ መሰሰስ እያለ በአርምሞና በትካዜ ይጓዛል። ያው አንዱ ወንዝ ተከትሮ ብርሃን እንዲያመነጭ ወይንም በመስኖ ተጠልፎም የእርሻ በረከት ወይንም ለከብት እርባታ ሲሳይ ሆኖ ይገራል። ለዚህ ሁሉ ማስረጃ የምጠራው ከመጫ ማህፀን የሚመነጨውን አዋሽን ይሆናል።
‹‹አዋሽ የመጫ ሥር ፍሳሽ፣
የዳዳ የቱለማ ደም፣
በረሀ የምትደመድም፤
የሰባት ቤት ጉራጌ አድባር፣
የከረዩ ቅቤና ማር…›› (ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድኅን)
ትውልድም እንደዚያ ነው። የአንዳንድ ዘመን ትውልድ በራሱ ጀንበር መጥቶ ሂያጅ ብቻ ሳይሆን ለቀጣዩ ተተኪ ዘመንም አስቦና ተመራምሮ ውርስና ቅርስ አኑሮ ያልፋል። የአንዳንድ ዘመን ትውልድ ደግሞ እንደ ድመት ሙጭጭላ በእናት ሀገሩና በመሪዎች ጭካኔ ወይንም እርስ በርስ ተነካክሶ ይጠፋፋል፤ ግን የትውልድ ሰንሰለት ባይበጠስም።
ወጋችንን በሀገርኛ ታሪክ እያዋዛን ወደራሳችን መመልከቱ ብልህነት ይመስለኛል። አሳር የበላው የየዘመኑ የሀገሬ ትውልድና መሪዎች የጉዞ ጅረት ምን እንደሚመስል ረጃጅሞቹን ታሪክ ከምክመን፣ የተዳፈነውን ገላልጠን ለመመልከት ጥቂት መቶ ዓመታትን ብቻ ወደ ኋላ ተጉዘን በትንሹ እንቆዝም።
የሀገራችን የዘመነ መሳፍንት ትውልዶችና መሪዎች እርስ በእርስ ለስልጣንና ለክብር በየጦር ግንባሩና በየመንደሩ በሻምላ ሲሞሸላለቁ አሸናፊውና ተሸናፊው ሳይለይ ሁሉም ዘመናቸውንና ራሳቸውን በከንቱ ጥለው አለፉ። ሥልጣንና ሃይማኖት፣ ርዕይና ቅዠት፣ እልህና እብሪት፣ ምኞትና እውነታ እየተሳከሩባቸው ሲደነባበሩ ኖረው፤ ተነባብረው አለፉ። ጥቂቶች የማይባሉ ብዙዎች።
ተክለጻድቅ መኩሪያ በመጻሕፍታቸው ውስጥ የሀገራችንን ዘመነ መሣፍንት የገለጡት እንዲህ በማለት ነበር። “በዘመነ መሣፍንት በላስታ፣ በሰሜን፣ በትግሬ፣ በበጌምድር፣ በአማራ ሳይንት፣ በዳሞት፣ በጎጃም የተነሱት ብዙዎች ናቸው። እርስ በእርሳቸው ያደረጉት ጦርነት፤ ጦርነቱም የተነሳበት ምክንያት ብዙ ነው። ምክንያቱም የጦርነቱ ቦታ፣ ዘመኑም እርስ በእርሱ የተወሳሰበ ነበር”
ይህንን ዝርዝር ሃተታ በአጭር አገላለጽ የሚጠቀልልልን ስለ እስራኤላውያን ዘመነ መሣፍንት በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ የተገለፀው ምጥን ግን ሰፊ ሃሳብ ነው። እንዲህ ይላል፤ “በዚያም ዘመን ‹በዘመነ መሣፍንት› ሰው ሁሉ በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን ያደርግ ነበር።”
አክሱምን ያነፁት፣ ላሊበላን የፈለፈሉት፣ በሶፍ ኡመር የተጠበቡት፣ ጎንደርን የከተሙት፣ ሐረርን ያጠሩት፣ ጂማን የቆረቆሩት፣ ወላይታን ያኮሩት፣ ቤኒሻንጉልን ያስዋቡት ወዘተ… መሰል ጀግኖቻችን ግን ከላይ ከተዘረዘሩት ተርታ አፈንግጠው ታሪክ ሰርተውና በታሪክ ተመስግነው ህያው እንደሆኑ በልባችን ጽላት ላይ ተቀርፀው እንደተከበሩ አሉ።
በዚህ በእኛ ዘመን የጥንቱን የመሰለ ዘመነ መሣፍንት አይኑር እንጂ “ዘመናዊ ዲሞክራሲ” በተሰኘ “ወርቀ ዘቦ” በተለበጠ ፍልስፍና አማካይነት የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን “ዘመነ መሣፍንት” ደጃፋችንን ሲያንኳኳ እየታዘብን ነው። በአንዳንድ አካባቢዎችማ በሩ ወለል ተደርጎ ስለተከፈተለት ወደ ውስጥ ዘልቆ በመግባት ርስት የተሰጠው ይመስል ተደላድሎ እስከ መንሰራፋት ደርሷል።
በጋራ ቋንቋ መግባባት ተስኖን የጋራ ችግሮችን የምንፈጥርባቸው አጀንዳዎች አቤት አበዛዛቸው። ጉዳዮቹ ከእኛም አልፈው ለተከታዩ ትውልድ የሚተላለፍ ዕዳ እየሆኑ እንዳለ ለማስተዋልና ወደ ቀልባችን ለመመለስ እንኳ የልቡናችን ዓይኖች ሊበሩ አልቻሉም። “ብልህ ከታሪክ መማሩ፤ በመጃጃል የተኮነነው ደግሞ ያለፈ ታሪክን ስህተት መድገሙ” የተገለጠልን እስከማይመስል ድረስ በእውር ድንብር የምንጓዝባቸው ሀገራዊ ጉዳዮቻችን በርካቶች ናቸው።
ብዙ ሀገራት ቀዳሚው ትውልድ “ፈጽሞት አልፏል” የሚሉትን ህፀፆች በታሪክ ሰነዳቸው ውስጥ አኑረው በጋራ በሚያግባቧቸው ጉዳዮች ላይ ተከባብረው አብረው ሲኖሩ እያስተዋልን ነው። በእኛው ሀገር ግን “ዕንቆቅልሽ/ህ” እየተባባልን ያለፈውን ትውልድ የስህተት አስከሬን ከመቃብር ውስጥ ቆፍረን በማውጣት ከእኛ መልክና አምሳል ጋር ኃላፊውን ዘመን እያነፃፀርን በሃሳብ ሳይሆን በሾተል ስንሞሻለቅ ነግቶ ይመሻል።
ዐፄ ዮሐንስ 4ኛ (1864-1881)፣ በዘመናቸው የዕውቀታቸውን ያህል፣ በግዛታቸው ስፋት ልክ፣ ዘመኑ በፈቀደው ንቃተ ህሊና መጠን ሀገርና ሕዝብ መርተው ከመሃዲስቶች ጋር ሲፋለሙ ወደቁ። እኒህን መሪ ልንዘክራቸውና ልናከብራቸው የሚገባው በዘመናቸው ልክ ስላስመዘገቧቸው መልካም ውጤቶች እንጂ በእኛ ዘመን የሚዛን ልክ ለክተን መሆን አልነበረበትም። ለዛሬው ተሟጋች ትውልድ የዕዳ ቁልል ጥለው እንዳለፉ መታሰብም አልነበረበትም። እንሞግታቸው ብንልስ እርሳቸውንና ዘመናቸውን በምን ጥበብ እንዲሟገቱ ልንፈቅድ እንችላለን። “ሠርተዋል” የምንላቸው ስህተቶች መመዘኛ ው መቼና ማን ነው?
ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስም (1847-1860) ቢሆኑ ዘመናቸው የፈቀደላቸውን ርዕይ ለማሳካትና ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን በምኞታቸው ልክ ለመምራት ሲሞክሩ፤ ሽቅብና ቁልቁል በሚሳሳቡ ሃሳቦችና ቡድኖች ተጠልፈው “ጨካኙና ጀግናው” የሚል መንታ ቅጽል ወጥቶላቸው መራሩን የሞት ጽዋ በራሳቸው እጅ ተጎንጭተው አለፉ። ቴዎድሮስ የሞቱለትን ዓላማ “ትክክልና ስህተት” ብሎ ለመበየን ማንም ሰው ከመቶ ዓመት በኋላ ብያኔ ልስጥ ቢልና በትውልዱ ላይ ዕዳ እንደጫኑ አፉን ሞልቶ ቢናገር ከእውነት ጋር ብቻም ሳይሆን ከራሱም ጋር መላተሙ አይቀርም። ተሟጋቹ በሌለበት ሞጋች የሚፏልልበት መድረክ ከመሆንም አይዘልም።
የዳግማዊ አጤ ምኒልክ (1881-1906) ጉዳይም እንደዚሁ ነው። ቴክኖሎጂ ወዳዱ ምኒልክ ዘመናቸውና ትውልዳቸው በሚፈቅድላቸው ዐውድ ልክ የሀገረ መንግሥት ምሥረታ ሂደቱን ተግባራዊ በማድረግ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን “እምዬ” እየተባሉ መርተው አልፈዋል። ግብራቸውንና አሻራቸውን በአግባቡ ማወደሱ እንኳ ቢቀር ለዛሬው ትውልድ ዕዳ አሸክመው አልፈዋል ተብሎ “ክስና ኪሳራ” እንዲቆረጥባቸው መሞከሩ ወግ ያለው ስብዕና አይደለም።
ልጅ ኢያሱ ሚካኤል (1906-1909)፣ ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ (1906-1922)፣ ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ (1923-1967) እነዚህም መሪዎች የአቅማቸውን፣ የዕውቀታቸውን፣ የዘመናቸውን የአመራር ጥበብ እየተጠቀሙ ሀገርንና ሕዝብን መርተው አልፈዋል። ግፍና ጭካኔ፣ ወይንም ስኬትና ውጤታቸው በታሪክ ድርሳናት ተመዝግቦ ስለሚተላለፍ ይህ የዛሬው ትውልድ ባጠለቀው መነፅሩ ልፈትሻቸውና ላስፈርድባቸው ብሎ አደባባይ ቢያቆማቸው አሻራቸውን እንጂ በድናቸውን ስለማያገኝ ባለ ዕዳው እነርሱ ሳይሆኑ ከዘመን እየተጣላ ያለው “ዐቃቤ ምንትስ” ራሱ ነው፤ ተሟጋች በሌለበት ልሞግት የሚለው።
የደርግ (1967-1983) እና የኢህአዴግ (1983-20 . . ?) መሪዎችንና ትውልዶችን የምንፈትሸው ግን ለየት ባለ መነፅር ይሆናል። ለምን ቢሉ አብዛኛው የዛሬ ትውልድ በሁለቱም ሥርዓቶች ውስጥ አንድም “የወይን ዋንጫ” ጨብጦ እየተጎነጨ፤ አለያም የመከራ ከርቤ በሰፍነግ እየተጋተ የኖረና እየኖረ ያለ ስለሆነ ምልከታችንን ትንሽ ለየት ያደርገዋል።
የሁለቱም ዘመን ትውልዶች ዛሬም እንደ ትናንት ከትናንት ወዲያ አዝማናት እየተለማመድን ላለነው “ዘመናዊ ዘመነ መሣፍንት” ዋነኛ ተጠያቂዎች ናቸው። ብዙዎቹ ደም እየተቃቡ በመኖር የተለ ማመዱት ቆሌ የሰላም አዋጅ፣ በንግ ግርና በውይይት የመተማመን አቅም እንዳይኖራቸው አሽመድምዶ አስነክሷቸዋል። እነርሱ የለመዱት “ግፋ በለው እንጂ” ተነጋግረን እንደማመጥ ተመካክረን እንደጋገፍ አይደለም። ጥቂት የማይባሉት የሁለቱ ሥርዓት ውልዶች ከመሰባሰብ ጸጋ ይልቅ የሚጥማቸው መቅኒ የሌለው የአጥንት ቅልጥም ነው። እነርሱ በትዕቢት ተሞልተው የትናንቱ ትውልድ ለሀገሪቱ የመከራ ዕዳ ትቶ አንዳለፈ ሲከራከሩ፣ በአንፃሩ ግን እነርሱም በተራቸው ለመፃኢው ትውልድ የዕዳ ጫና እየቆለሉበት እንደሆነ የገባቸው አይመስልም። ትምህርታቸው ለግትርነት፣ ዕውቀታቸው “እኔ ብቻ አዋቂ” ለሚል ራስ ተኮር ጦስ እንደዳረጋቸው እንኳ ነቅተው ሊባንኑ አልቻሉም።
እነርሱ መሆን ያቃታቸውን የትናንቱ ዘመነ መሣፍንት ለምን አላደረገውም ብለው ይከራከራሉ። የዘመነ መሣፍንትን የጎጥ አገዛዝ እያወገዙ እነርሱ ግን መሰባሰብ ተስኗቸው አንድ መቶ ሰላሳ ፓርቲ መስርተው “የዘመናዊ ዘመነ መሣፍንት” ምርጫ ሊያደርጉ ሽንሻኖውን እየመተሩ በማለም ላይ ናቸው። ከትናንት እንቅልፍ አልባነኑም፤ አልነቁም። ዘመንኛው ወጣት እንዲህ እያለ በቅኔ ሲሞግታቸው እንኳ ስለማይገባቸው የተወደሱ መስሏቸው በየአደባባዩ ያጨበጭባሉ። በዕውቀቱ ስዩምን ልጥቀሰው፤
አያቶች! በባዶ መስክ ተመራምረው፣
ጥበባቸውን፣ ዕድሜያቸውን፣ ገብረው፣
የጎጆ ንድፍ ሲያበጁ አረጁ።
ዘመናቸውን ፈጁ።
አባቶች! መላ ዘመናቸውን፣
ጎጆ በመቀለስ አሳለፉ፣
ሳይኖሩበት አለፉ።
ልጆች! ጎጆውን ለመውረስ ሳይከጅሉ፣
እንዲህ አሉ፣
“ያባቶቻችን ጎጆ ይኹን ባዶ፣
ይኹን ኦና በኛ ቁመት፣
በኛ መጠን አልተቀለሰምና።
ሰላም ይሁን!
አዲስ ዘመን ነሃሴ 1/2011
(በጌታቸው በለጠ/ዳግላስ ጴጥሮስ)