የመጽሐፉ ርዕስ፡- ጠርዝ ላይ
ደራሲ፡– በድሉ ዋቅጅራ (ፒ.ኤች.ዲ)
የታተመበት ጊዜ ፡–መጋቢት 2011
የገጽ ብዛት፡– 192
የመሸጫ ዋጋ 81 ብር
ዳሰሳ፡– ፍሬው አበበ
ከወራት በፊት ጠ/ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ወደሥልጣን የመጡበት አንደኛ ዓመት በዓለ ሲመት ላይ ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ የተናጋሪነት ዕድል ካገኙት ጥቂት ሰዎች አንዱ ነበር። ያገኘውንም ዕድል በመጠቀም ብዙዎች በአድናቆት ያጨበጨቡለትን ታሪካዊ መልዕክት አስተላለፈ። ባለፉት ዓመታት በተለይ ከመንግሥት አፍ “አልደራደርም” የሚል ቃል ተደጋግሞ ይሰማ ነበር።
“በሕገመንግስቱ አልደራደርም፣ በብሄር ብሔረሰቦች መብት አልደራደርም፣ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮት አልደራደርም፣ በመሬት ፖሊሲዬ አልደራደርም…”ሲል የሚደመጥበት ጊዜ ጥቂት አልነበረም። ይህን ግትር ፖለቲካዊ አቋም ዶክተር በድሉ እንዲህ ሲል ተቸ። “…አልደራደርም በሚለው ቃል ውስጥ የሌላውን ቃል መቀበል ቀርቶ ማዳመጥ አልፈልግም የሚል ትምክህትና ንቀት አለ። አልደራደርም የሚለው ቃል ውስጥ የዜጎች በሀገራቸው የመሳተፍ መብት የማይቀበል የአምባገነንነት ቡቃያ አለ። ይህን ይዘን ፖለቲካዊ ውይይታችን ወደዲሞክራሲ ሊያደርሰን አይችልም። ይህ መሞረድ አለበት።…”
ይህን ማስታወሴ በምክንያት ነው። የዶክተር በድሉ ዋቅጅራ “ጠርዝ ላይ” የተሰኘው በቅርቡ ለንባብ የበቃ መጽሐፍ የወቅቱን ማንነታችንን፣ ገመናችን፣ ጉድለታችንን ፊት ለፊት በመዘክዘክ የሚሞግት በመሆኑ ነው። ጠርዝ ላይ፤ የትኛዋ ኢትዮጵያ? የትኛው ቋንቋ? ምን ዓይነት ጋዜጠኝነት? ማህበረሰባዊ የሥነምግባር ዝቅጠት እያለ አንድ በአንድ ይፈትሻል፣ ይሞግታል። መጽሐፉ ኢትዮጵያን በሶስት ከፍሏታል፤ የድሮዋ፣ የዛሬዋ፣ የነገዋ ኢትዮጵያ እያለ።
የድሮዋ ኢትዮጵያ በዶክተር በድሉ ብዕር ይህን ትመስላለች። “…የድሮዋ ኢትዮጵያ ትልቅ ደምቆ የሚታይ ፍሬም/ህዳግ አላት። ችግሩ ፍሬሙ ውስጥ ያሉት ምስሎች እኩል አለመታየታቸው ነው። አንዱ ደምቆ፣ ገሚሱ ደብዝዞ፣ ሌላው ጨርሶ አይታይም። አንዱ ይነበባል- ፊደል አለው፤ሌላው አይናገርም-ልሳን አልባ ነው፤ ተናግረውም አይተረጎምለትም።
ያ ጎልቶ የሚታይ የኢትዮጵያ መንፈስ፣ ውስጡ የስስታም ዕቃ ቤት ነው- ያለው ከሌለው አይለይም። የሰለጠኑት የምዕራብ ሀገራት፣ ሀገራዊ መንፈሳቸው እንደኢትዮጵያ ጎልቶ ባይታይም፣ ውስጣቸው…ጓዳ ጎድጓዳቸው ጥርት ብሎ ይታያል። ምን እንዳለ፣ ምን እንደሌለ ይታወቃል። የትኛው ማሳ ቀድሞ እንዳፈራ፣ የትኛው ማሳ ዝናብ እንዳጣ፣ የትኛው ሰብል ዋግ እንደመታው ይታወቃል። የሰለጠኑት ሀገራት መንፈስ የሚነሳው ከሚኖርበት ጎጆ፣ከሚያደርሰው ማሳና ከሚሰራበት ፋብሪካ ነው።
የድሮዋ ኢትዮጵያ ምስልና የኢትዮጵያዊነት መንፈስ የዘመኑ ፖለቲካዊና ማህበረሰባዊ አስተሳሰብ ነጸብራቅ ነው። ቀድመን እንዳልነው፣ የድሮዋ ኢትዮጵያ እንጀራ በዶሮ ወጥ የሚቀርብበት ሌማት/መሶብ እንጂ፣ መርቃ ማቅረቢያ ቆሪ እና ቆጮ በክትፎ የሚቀርብበት ጣባ አልነበራትም።
ጎልቶ የወጣው ባህል “ኢትዮጵያዊ” ባህል ተደርጎ ፣ በየደረጃው ላለው ስርዓተ ትምህርት ውስጥ ተካቶ ይሰጣል። የትምህርት ሥርዓቱ ከዚህ “ኢትዮጵያዊ” ባህል ውጭ፣ ከሌላ ቋንቋና ባህል የተገኙ ሕጻናትን ከሚኖሩበት ባሕል እያፋታ፣ በማያውቁትና በማይኖሩት “ኢትዮጵያዊ” ባህልና መንፈስ ያጠምቃቸዋል። ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን ኖረው ሳይሆን እንደሃይማኖት ተሰብከው ይቀበሉታል…”
የዛሬዋ አትዮጵያ
“እስቲ ህወሓት/ኢህአዴግ በሃያ ሰባት ዓመት የፈጠራትን ኢትዮጵያ እንቃኛት። የህወሓት/ኢህአዴግ ኢትዮጵያ እልፍኟ ውስጥ የሁሉንም ብሔር ብሔረሰቦች ፎቶ ሰቅላለች፤ ለሁሉም ዕውቅና ሰጥታለች። ይህቺ ኢትዮጵያ የእያንዳንዱን ብሔር ብሔረሰብና ሕዝብ ምስል በተመሳሳይ መጠንና ቀለም ቀርጻ፣ በተመሳሳይ ፍሬም በእልፍኟ ውስጥ አለመስቀሏ ነው።
ለአንዳንዶቹ አስፈሪ ግርማ ሞገስ አጎናጽፋቸዋለች፤ ለአንዳንዶች ደግሞ አንጀት የሚያላውስ አሳዛኝነት አላብሳቸዋለች። ጠብድለው የሚያስፈራሩና ፈርተው የኮሰመኑ ብሔሮች ፎቶ በእልፍኟ ውስጥ፣ ፊት ለፊት ተሰቅሎ ሲታይ ሳቅ ያጭራል። የኢህአዴጓ ኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦች እኩል የምታደርጋቸው በዓመት አንድ ቀን ህዳር 29 ነው፤ አደባባይ አውጥታ “ተደሰቱ፣ጨፍሩ” ትላቸዋለች። ሁሉም ይጨፍራሉ።
ሌላው የህወሓት/ኢህአዴግ ኢትዮጵያ ችግር በእልፍኟ የደረደረችው ከሰማንያ በላይ ብሔር ብሔረሰቦች ምስል፣ በፍቅርና መተሳሰብ አቅፎ የያዘ ብሔራዊ (ሀገራዊ) ፍሬም አለመኖሩ ነው። የኢትዮጵያ ደማቅ ሀገራዊ መንፈስ በዘመነ ኢህአዴግ ደብዝዟል። እያንዳንዱ ብሔር ብሔረሰብ አንድ አድርጎ የያዘው የኢትዮጵያዊነት ብሔራዊ ፍሬም ሳይሆን፣ የህወሓት/ ኢህአዴግ ፍሬም ድርጅታዊ ፍሬም ነው።
የህወሓት/ኢህአዴግ ፍሬም ደግሞ በስልጣን ወርቅ ዘቦ የተንቆጠቆጠ፣ ከሀገርና ከደሀው ህዝብ በተዘረፈ ሀብት የናጠጠ ነው፤ ጠርንፎ የያዛቸው ብሄረሰቦችም የሚመዝናቸው ከዚሁ የሥነምግባር ዝቅጠት አንጻር ነው። የሥልጣን ወርቀ ዘቦውን እስካላራገፉ፣ በዘረፋ ላይ የተመሰረተ ድሎትና ምቾትን እስካልተጋፉ ድረስ ይኖራሉ። በህወሓት/ኢህአዴግ ፍሬም ውስጥ ደምቆ ለመታየትና ተሰቅሎ ለመቆየት መመዘኛው ለህወሓት ስልጣን ምርኩዝ መሆን ነው። ሀሳቡን ሀሳቡ ያደረገ፣ ፖሊሲውን ያጸደቀ ብሔረሰብ በተሰቀለበት ይቆያል፤ ይደምቃል። ሀሳቡን የተቃወመ ፣ ፖሊሲውን የተጻረረ በተሰቀለበት ይደበዝዛል።…”
/ኢህአዴግ ፍሬም ደግሞ በስልጣን ወርቅ ዘቦ የተንቆጠቆጠ፣ ከሀገርና ከደሀው ህዝብ በተዘረፈ ሀብት የናጠጠ ነው፤ ጠርንፎ የያዛቸው ብሄረሰቦችም የሚመዝናቸው ከዚሁ የሥነምግባር ዝቅጠት አንጻር ነው። የሥልጣን ወርቀ ዘቦውን እስካላራገፉ፣ በዘረፋ ላይ የተመሰረተ ድሎትና ምቾትን እስካልተጋፉ ድረስ ይኖራሉ። በህወሓት/ኢህአዴግ ፍሬም ውስጥ ደምቆ ለመታየትና ተሰቅሎ ለመቆየት መመዘኛው ለህወሓት ስልጣን ምርኩዝ መሆን ነው። ሀሳቡን ሀሳቡ ያደረገ፣ ፖሊሲውን ያጸደቀ ብሔረሰብ በተሰቀለበት ይቆያል፤ ይደምቃል። ሀሳቡን የተቃወመ ፣ ፖሊሲውን የተጻረረ በተሰቀለበት ይደበዝዛል።…”
….የህወሓት/ኢህአዴግ ኢትዮጵያ ጉዞዋን አገባዳ ከጠርዙ ላይ ደርሳለች። በዚህ መልክና አቋም ከትወልዱ ጋር ልትዘልቅ፣ ክብር አግኝታ ለመጪው ትውልድ ልትቆይ አትችልም። ይህ ዘመንና ትውልድ ፈቃዱን ነፍጓታል። የዛሬዋ ኢትዮጵያ ባንድ በኩል በይቅርታ፣ ፍቅርና መደመር መርህ ያጎነቀለ የለውጥ ተስፋ የሚያውዳት፣ በሌላ በኩል የለውጡ ተቃዋሚዎች በእንስሳዊ ደመነፍስ ሚዛን እንኳን ተቀባይነት የማያገኝ ግፍና ጭካኔ የሚፈጽሙባት ናት።
የዛሬዋ ኢትዮጵያ፣ ያለፈው ግማሽ ምዕተ ዓመት የደርግ አምባገነንነትና የህወሓት የጎሳ ፖለቲካ ድምር ውጤት ናት…
…ዛሬ በየክልሉ በሚነሳው ግጭት የሚሞቱ ኢትዮ ጵያዊ ሆነው የኖሩ ዜጎች የሚሞቱት ኢትዮጵያዊ ሆነው አይደለም። ጅጅጋ ላይ ኢትዮጵያዊ ሆነው የኖሩት ኦሮሞዎች- ኦሮሞ ብቻ ሆነው ሞቱ። ቤንሻንጉል ላይ ኢትዮጵያዊ ሆነው የኖሩ አማሮች አማራ ብቻ ሆነው ሞቱ። ሐዋሳ ላይ ኢትዮጵያዊ ሆነው የኖሩ ወላይታዎች ወላይታ ብቻ ሆነው ሞቱ። አሸዋ ሜዳ ላይ ኢትዮጵያዊ ሆነው የኖሩ ጋሞዎች፣ ስልጤዎችና ጉራጌዎች ብሄር ብሄረሰብ ሆነው ሞቱ። ጉጂ ላይ ኢትዮጵያዊ ሆነው የኖሩ ጌዲኦዎች ጌዲኦ ብቻ ሆነው ሞቱ። የዛሬዋ ኢትዮጵያ እንኳንስ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ለመሞት፣ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ለመሰደድም መንገድ የላትም…”
የነገዋ ኢትዮጵያ
የነገዋ ኢትዮጵያ የመሪዎቻችንን ህልም ሳይሆን፣ የህዝቦቿን ኑሮ የምትመስል፣ ካስማዋን በመሪዎች መሻት ላይ ሳይሆን በዜጎች ፈቃድ ላይ ያቆመች መሆን ይጠበቅባታል።(ሆኖ ባያውቅም…የመሪዎች ህልም ከህዝቦች ኑሮ ከሰመረ፣ መሻታቸው ከዜጎች ፈቃድ ከተጣመረም እሰየው)። የነገዋ ኢትዮጵያ መንፈስም ከኑሮአችን የሚሰርጽብን እንጂ፣ በስብከትና ፕሮፖጋንዳ ብዛት ደንቁረን የምንቀበለው ሊሆን አይችልም።
የነገዋ ኢትዮጵያ በዜጎቿ ሁሉ ተቀባይነት ያላትና እሷም ለዜጎቿ ሁሉ ተቀባይነት የምትሰጥ ሆና መሰራት አለባት።…የነገዋ ኢትዮጵያ፣ የብሄር ብሄረሰቡን ምስል፣ በእኩል መጠን በፊደል ተራ ቅደም ተከተል፣ በሰፊው እልፍኝዋ ግርግዳ ላይ በወርቅ ፍሬም የሰቀለች፣ በምስላቸው ያጌጠች መሆን አለባት። በእርግጥም በአንዱ ብሔረሰብ ባለአርባ ሚሊዮን ሕዝብ፣ ሌላው ባለመቶ ሺ ሊሆን ይችላል።
በምንገነባት ኢትዮጵያ ውስጥ ግን የሁለቱም ምስል፣ በእኩል መጠን፣ በአንድ አይነት ቀለም ተስሎ በተመሳሳይ ፍሬም ይሰቀላል። ዘመኑና ትውልዱ የሚፈቅዳት የነገዋ ኢትዮጵያ ዜጎችን በሰውነታቸው ብቻ የምታስተናግድ ናት። ለሁሉም እኩል ፍትሕ፣ ዴሞክራሲ፣ ፍቅር የምትሰጥ፤ በውስጧ ያላቸው ቦታ ከዚሁ ከሰውነታቸው የሚመጭ ነውና ተመሳሳይ ነው። አንዲት አያት ሁለት ለወለደች ልጇ እና አስር ለወለደች ልጇ ያላት ፍቅር አንድ እንደሆነ፣ ኢትዮጵያም ለልጆቿ (ብሄረሰቦቿ) ተመሳሳይ ፍቅርና ቦታ ሊኖራት ይገባል።”
ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ በመጽሐፉ “ምን አይነት ጋዜጠኝነት?” ሲል ሙያችን ላይ ያያቸውን ጉድፎች በድፍረት ይነቅሳል። “…በዘመነ ደርግ ሆነ በዘመነ ቀዳማዊ ኢህአዴግ (ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል) በተለይ በመንግሥት የብዙሃን መገናኛ ውስጥ የሚሰሩ ጋዜጠኞች ሙያው የሚጠይቀውን፣ የመጠየቅና በመረጃ ላይ ተመርኩዞ ጥያቄዎችን የመመርመር ፣ ትክክለኛውን መረጃና ትንታኔ ለሕዝብ የማቅረብ ክህሎት አላዳበሩም። ይልቁንም ያለመጠየቅን፣ የመንግሥት ቃል እንደመረጃ ያለ ጥያቄ አሜን ብሎ መቀበልን ሥራዬ ብለው በመያዝ የመንግሥት ፕሮፖጋንዳ ማውረጃ ቱቦዎች ሆነው ነው የኖሩት…” ሲል ይተቻል።
ማህበረሰባዊ የሥነምግባር ዝቅጠት ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ በሰፊው ከተቸው የሚጠቀስ ነው።”…ተከታትለው የመጡት የደርግ እና የህወሓት/ኢህአዴግ መንግሥታት የተከተሉት የአስተዳደር ሥርዓት የማህበረሰብን ጥቅም የማስቀደም ሥነምግባራዊ እሴት እንዲላሽቅ ትልቁን ሚና ተጫውተዋል። እነዚህ መንግሥታት ራሳቸው የማህበረሰብን ጥቅም የሚያስቀድሙ አልነበሩም።
የራሳቸው ስልጣን የሚያስቀድሙ ፣ዜጎች ከሥነምግባራዊ ግዴታቸው ከመውጣት ይልቅ፣ መንግሥት የሚያዛቸውንና ያለ ጠንካራ አመክንዮ ተቀብለው እንዲፈጽሙ አድርገዋል። በሁለቱም መንግሥታት የመንግሥትን ስልጣን አለመቀናቀንና ባለስልጣናትን ያለማስቀየም የሥነምግባር ልኬት ማጠንጠኛ ሆኗል። ማህበረሰባዊ ግዴታቸውን ከሥነምግባራዊ ልኬት ሳያዛንፉ የፈጸሙ ዜጎች ለእስር፣ ለሞትና ለስደት ተዳርገዋል። ማህበረሰቡ ግን ስለጥቅሙ ሲታገሉ፣ ግለሰባዊ መብታቸው ተገፎ ለታሰሩ፣ ለተገደሉና ለተሰደዱ ሰዎች ነጻነት ሲቆም የታየበት አጋጣሚ እጅግ ጥቂት ነው።”
“….አስመሳይነትና በአደባባይ ባወገዙት፣ በነቀፉት ተግባር ላይ መገኘት ነፍስን ፉንጋ ምስል ለማቆንጀት የሚከናወኑ በመሆናቸው ይመሳሰላሉ። ስብዕናን በዕውቀት፣ በሥነምግባርና በምክን ያት ላይ ተመስርቶ ከማቆንጀት ይልቅ፣ በማስመሰልና በምላስ የቃላት ቅብ የጨለመ ስብእና ብርሃን አልብሶ፣ ማህበራዊ ተቀባይነት ለማግኘት መሞከር የማህበረሰቡ መገለጫ ሆኗል።…”
ዶክተር በድሉ ማህበረሰቡን የተቸበት የሥነምግባር ሁኔታ በዚህ የሚቋጭ አይደለም። ጠንከር ያለ ዱላ አሳርፏል። “በየክልሉ አንዱ ብሔረሰብ የሌላውን ብሄረሰብ አባል ይገድላል፤ ያፈናቅላል። መንግሥት እሳት ከማጥፋት የዘለለ ሥራ ለመስራት አልቻለም። ለተገደሉ ሀዘኑን፣ ለተፈናቀሉ መጠለያና ምግብ ከማቅረብ ባሻገር ወንጀለኞችን ለፍትሕ አያቀርብም። ምክንያቱም ገዳይና ሟች ሰዎች አይደሉም፤ ብሔር ብሄረሰብ ናቸው። ከሱማሌ ኦሮሞች ተፈናቀሉ፣ በሐዋሳ ወጣቶች – ወጣቶችን በእሳት አነደዱ።
በጅግጅጋ ሱቆች ተቃጠሉ። ቤተክርስቲያን ከእነአገልጋዮችዋ ተቃጠለች። አዳማ..ሀረርጌ..ሁሉም የተደረጉት በሰዎች አይደለም፤ ብሔር ብሔረሰቦች ናቸው። በዛሬዋ ኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰብ ከሆንክ ሕግ አይሰራም። ዳኝነት የለም። ዋናው ብሄር ብሄረሰብ መሆን ነው። ብሔረሰብ ስትሆን ቀድመህ ከገደልክ፣ ከዘረፍክና ካቃጠልክ የብሄር ብሄረሰብ ምሽግህ ከህግ ይከልልሃል። ከተቀደምክና ከተገደልክ፣ ከተረፍክ፣ ከተቃጠልክ መንግሥት ሁኔታውን ያጠናልሃል።…”
“…ገመና ተንከባካቢው ባህላችን፣ አፈንጋጮችና ደፋሮችን የሌላውን ገመና ከረጢት አደባባይ እንዳያወጡ የሚጠብቅበት አባሪ ልማዶች አሉት፤ ጥፋቱን እንጂ የጥፋተኛውን ስም ያለመጥራት። በየእድሩ፣ በየደረጃው በሚካሄድ ስብሰባ፣ በየመገናኛ ብዙሃኑ ማህበራዊ ችግሮች ላይ ውይይት ይደረጋል፤ አብዛኛው ውጤት ባያመጡም። በስብሰባና በግምገማ ችግሮቻችን መፍታት የምንችል ህዝቦች ብንሆን ኖሮ ሀገራችን ችግር አልባ የምድር ገነት በሆነች ነበር። ግን አልሆነችም።
እድርተኞቹ አደጋ ሲገጥማቸው የወሰዱትን የእድር ዕቃ አሟልተው ባለመመለሳቸው ችግር የገጠመው እድር አባላቱን ሰብስቦ ያወያያል። እድሩ በዕቃ እጥረት የገጠመውን ችግር ላይ በዝርዝር ውይይት ይደረጋል። ይህ ከቀጠለ የእድሩ የወደፊት ዕጣ ምን ሊሆን እንደሚችል፣ የቀረቡ ትንቢቶች ላይ ውይይት ይደረጋል።
በመጨረሻም የወሰዱትን ዕቃ አሟልተው ያልመለሱ አባላት በወር ጊዜ ውስጥ እንዲመልሱ ውሳኔ ተሰጥቶ ስብሰባው ይጠናቀቃል። መዝገብ የያዘው ዕቃ ያልመለሱ አባላት ስም ሳይጠራ ስብሰባው ይበተናል። ችግሩ በአስቸኳይ ካልተቀረፈ እድሩ የመፍረስ ዕጣ ከፊቱ እንደተጋረጠበት በቁጭት የሚናገሩት ያልተመለሰ ዕቃ ጓዳቸው ውስጥ ያስቀመጡት ጭምር ናቸው።…”
ዶክተር በድሉ በተለምዶ ምሁራን የምንላቸውን “ፊደላዊያን” በሚል ይጠራቸዋል። “…የትምህርት ዋና አላማው በዕውቀት የበለጸጉና ለምርምር የተጉ ፊደላውያን (Academicians) መፍጠር ብቻ አይደለም። ከዚህ ጋር ማህበረሰባዊ ፋይዳ ያለው ዜጋ መፍጠር መቻል አለበት ይለናል።
የዶክተር በድሉ ዋቅጅራ ጠርዝ ላይ መጽሐፍ ዓይኖቻችን ስር ያሉ እውነታዎችን እየነቀሰ ሊያሳየን ይሞክራል። መንግሥትን፣ ማህበረሰቡን፣ ፖለቲከኞችን፣ ቡድኖችን፣ ግለሰቦችን ሚና ለያይቶ ይፈትሻል፣ ይተቻል፣ ያብጠለጥላል። ይህ ጹሑፍ አጭር ዳሰሳ ነው፤ ዳሰሳው ላይ የሰፈሩ ቁምነገሮችን የወደደ መጽሐፉን ፈልጎ ቢያነብ ይበልጥ ያተርፋል።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 1/2011
ፍሬው አበበ