
አዲስ አበባ፤- “መንገድ ለሰው” በሚል በአዲስ አበባ ከተማ ሲካሄድ የነበረው ከተሽከርካሪ ነፃ መንገድ መርሐ ግብር በሚቀጥለው ዓመት በመኖሪያ ቤቶች አካባቢ በየሳምንቱ እንደሚካሄድ ኤጀንሲው አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንትን ኤጀንሲ ትናንት ከባለድርሻ አካላት ጋር በካፒታል ሆቴል ውይይት ሲያደርግ ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ጂሬኛ ሂርጳ፤ በስድስት ቦታዎች ይካሄድ የነበረው የመንገድ መርሐ ግብር በሚቀጥለው ዓመት በመኖሪያ አካባቢዎች የሳምንቱ እንዲካሄድ እቅድ መያዙን ተናግረዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ የዝግጅቱ ተሳታፊ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። ህብረተሰቡም የዝግጅቱ ባለቤት በመሆን በዝግጅቱ የተለያዩ ሁነቶች በመሳተፍ አዎንታዊ ለውጥ እያመጣ ነው።
ጤናማ ዜጋ በመፍጠርና ማህበራዊ ትስስር እያጠናከረ ነው። ኤጀንሲው የህብረተሰቡን ፍላጎት መሰረት በማድረግ በሚቀጥለው ዓመት የዝግጅቱን ተደራሽነትና ተደጋጋሚነት ታሳቢ ያደርጋል።
በአዲስ አበባ ከተማ በትራፊክ አደጋ ከሚሞቱ ሰዎች 80 በመቶ እግረኞች መሆናቸውን ያነሱት አቶ ጂሬኛ፤የሞት መጠኑ በየዓመቱ በ7ነጥብ6 እያደገ እንደሆነ፣ ከተሽከርካሪ ነፃ በሚለው መርሐ ግብር እየተፈጠረ ባለ ግንዛቤና በሌሎች ስራዎች ለውጥ እየተገኘ በመሆኑ ለኤጀንሲው ትልቅ ስኬት መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
በኤጀንሲው የመርሐ ግብሩ አስተባባሪ አቶ እያየህ ደረጀው በበኩላቸው ዝግጅቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፤ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ፤ የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽንና የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲና ሌሎች የግልና የመንግሥት ተቋማት የሚሳተፉበት መሆኑን ገልጸዋል።
ዝግጅቱ አማራጭ የትራንስፖርትን መንገድ መያዝን ፤ የትራፊክ አደጋ መቀነስን ፤ ለኑሮ ምቹና ከብክለት የጸዳ አካባቢ መፍጠርን፤ ጤናማ አኗኗርና ማህበራዊ ትስስር እንዲፈጠር አስችሏል።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 1/2011
አጎናፍር ገዛኽኝ