
አዲስ አበባ ፡– ምእመናን የፍልሰታ ጾምን በጸሎት በመትጋት ፤ የተቸገሩትን በመርዳትና የተጣሉትን በማስታረቅ እንዲያሳልፉ ቤተክርስቲያኗ አሳሰበች።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ፅ/ቤት በላከው መግለጫ እንዳመለከተው የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን ባስተላለፉት መልዕክት ፣ ለመላው ኢትዮጵያውያን ካቶሊካውያን ምእመናንና የፍልሰታ ማርያም ክብረ በዓልን ለሚያከብሩ ሁሉ ለ2011 ዓ. ም. የፍልሰታ ጾም መልካም ምኞታቸውን ገልፀው፤ በፆሙ ወቅት የተቸገሩትን በመርዳትና የተጣሉትን በማስታረቅ በጎ ተግባር እንዲፈፅሙ ጥሪ አቅርበዋል።
ካርዲናሉ እንዳሉት፤ የፍልሰታ ማርያም ክብረ በዓል ቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋዋና በነፍሷ ወደ ሰማይ የወጣችበት በመሆኑ ከድንግል ማርያም በዓላት ሁሉ ከፍ ያለ ነው። ከነሐሴ 1 እስከ ነሐሴ 15 ለፍልሰታ ክብረ በዓል ምእመናን መንፈሳዊ ዝግጅት በማድረግ በፆምና በጸሎት መትጋት አለባቸው። ይህ ጾምና ምህላ በሙሉ ልብ መሆን ያለበትና የተቸገሩትን በመርዳት፣ የተጣሉትን በማስታረቅና የበደሉትን ይቅርታ በመጠየቅ የሚገለጥ ነው።
ድንግል ማርያም የተቸገሩትንና ድሆችን መርዳት አስፈላጊ እንደሆነ አስተምራለች። ምእመናን ከእርሷ የፍቅር ሥራና ትሕትና የተሞላበት ሕይወት በመማር በአሁኑ ሰዓት በየቤቱ በችግር ላይ ያሉ ወገኖችን ማሰብ አለባቸው ያሉት ካርዲናሉ፤ ሁሉም ክርስቲያኖች እግዚአብሔር ከሰጣቸው በረከት ለድሆች በማካፈል ጾሙን በተግባር መኖር ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
ካርዲናሉ‹‹በአሁኑ ወቅት በአገራችን የተለያዩ ስፍራዎች በሚከሰቱ ግጭቶች ምክንያት ከየቀያቸው ተፈናቅለው በችግር ላይ የሚገኙ በርካታ ቤተሰቦች አሉ። ቤተሰብ ሲፈናቀል ደግሞ በቅድሚያ የሚጠቁት ሕጻናትና እናቶች ናቸው።
በዚህ የጾም ወቅት ለነዚህ ወገኖች ልዩ ጸሎትና ድጋፍ ማድረግ አለብን። ቤተክርስቲያናችን እንደተለመደው ከህዝብ ጎን በመቆም ተፈናቃዮች ባሉበት ቦታ ተገኝታ አስፈላጊውን መንፈሳዊና ቁሳዊ ድጋፍ በማድረግ ላይ ትገኛለች።
ምእመናንም ይህንኑ ተግባር በመደገፍ በጸሎትና በተግባር ከቤተክርስቲያን ጋር መተባበር፤ እንዲሁም በየአቅራቢያቸው ለሚያጋጥሟቸው ተጎጂዎች የበኩላቸውን ድጋፍ ማድረግ አለባቸው›› ብለዋል ።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 1/2011
የትናየት ፈሩ