በሀገራችን በተለያዩ የመንግሥት ሥርዓቶች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በዜጎች ላይ ሲፈፀሙ ተስተውሏል። ሰዎች ያለ ጥፋታቸው ሲታሰሩ፣ ሲገረፉ፣ ሲገደሉ… በጅምላ ሲቀበሩ መቆየታቸውን የምናውቀው ሀቅ ነው። በሥርዓቱ አገሪቱ የምትተዳደርበት ህግ ቢኖራትም የህግ አስፈፃሚው፣የሥርዓቱ ባለሥልጣናት፣ ግለሰቦች እና ሌሎችም ቡድኖች ህጉን ወደ ጎን በመተው በዜጎች ላይ ህገወጥ ተግባር ሲፈፅሙ ኖረዋል።
ሰዎችን ያለጥፋታቸው ለረጅም ጊዜና ዓመታት እንዲታሰሩ ፣ በ48 ሰዓት ፍርድ ቤት መቅረብ ሲገባቸው ሳይቀርቡ ለረጅም ጊዜ እንዲንገላቱ ማድረግ፣ በጨለማ ቤት ውስጥ ማስቀመጥ፣ ማግለያ ክፍል ማጎር፣ መደብደብ፣ ማሰቃየት፣ አካል ማጉደል የመሳሰሉት አጠቃላይ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች ሲፈፅሙ የነበረበት ሁኔታ ታይቷል። ዘግናኝ የሆነ ኢ- ሰብዓዊ ድርጊት የተፈፀመባቸው ግለሰቦችም ይሄንኑ በአደባባይ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃንም ሲገልጹ ተደምጠዋል።
ይሄ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በአገራችን ዳግም እንዳይፈጠርም የቀይ ሽብር ሰማዕታት ሐውልት ሲቆም «መቼም፣ የትም እንዳይደገም» የሚል ጽሑፍ እንዲሰፍር ተደርጓል። ይሁን እንጂ ይሄ ሀሳብ ከጽሑፍ ማድመቂያነት በዘለለ ሲያገለግል አልታየም። ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ይቁም በሚለው አካልና ሥርዓት ጭምር ኢ- ሰብዓዊ ድርጊቱ ገዝፎና ሰፍቶ ዘግናኝና አሳፋሪ በሆነ መልኩ ተፈፅሞ ታይቷል።
የዴሞክራሲ ምህዳሩ እየጠበበ፣ ዜጎች በብሔራቸውና በያዙት የፖለቲካ አስተሳሰብ ምክንያት የሚደርስባቸው በደል እየከፋ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ እየባሰ ሙስናው በሀገሪቱ እየተስፋፋ ሄዷል። ይሄ የሚያሳየው የህግ የበላይነት በጥቂቶች በተለይም በማን አለብኝነት በተደራጁ ጥቂት ኃይሎች እጅ ወድቆ እንደነበር ነው።
ባለፉት 27 ዓመታትም በፖሊስ፣ በደህንነት፣ በፍርድ ቤቶች፣ በማረሚያ ቤቶችና በሌሎችም የመንግሥት ኃላፊነቶች ላይ በሚገኙ ባለሥልጣናት ፈቃደኝነት፣ መሪነትና ተባባሪነት በዜጎች ላይ የተፈጸመው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ለጆሮ የሚከብድ፣ አእምሮንም የሚያደማ እና ህሊናን የሚያቆስል ነው።
በዜጎች ላይ ለተፈጸመው ጉዳትም መንግሥት እንዲሁም አራቱም የኢህአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች የ17 ቀናት ግምገማቸውን ሲያጠናቅቁ በጋራ በሰጡት መግለጫ ህዝብን ይቅርታ ጠይቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድም በበዓለ ሲመታቸው እንዲሁም በተለያዩ መድረኮች ህዝብን ይቅርታ መጠየቃቸው ይታወቃል። ይሄ ጥፋትን የማመንና የመጸጸት አንዱ መንገድ መሆኑ ይታመናል። ሆኖም ግን በቂ አይደለም። የድርጊቱ ፈጻሚዎች በህግም ተጠያቂ መሆን አለባቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ «ግፍ ሠርቶ መደበቅ፤ ዘርፎ መንደላቀቅ አይቻልም» በሚል ባስተላለፉት መልዕክት፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ በህግ የመጠየቁ መንገድ እንደከዚህ ቀደሙ ቂምና ቁርሾ ለማወራረድ በሚያመች መንገድና አኳኋን ሳይሆን የህግ የበላይነትን በሚያሳይ በህግና በህግ ላይ ብቻ በተመሰረተ መልኩ መሆን ይኖርበታል። ቂምና በቀልን ልናስበው አይገባም፤ ፍርድና ፍትሕን እንጂ፡፡ ይህን ሁሉ የሚደረገው ከጥላቻ በመነሳት ሳይሆን የህግ የበላይነት መስፈን ስላለበት ነው። ወንጀለኞቹ ማንም ይሁኑ ማን፣ ከየትኛውም ብሔር ገብተው ይደበቁ፣ የትኛውም ወገን ይጩህላቸው፣ በወንጀል እስከተጠረጠሩ ድረስ ካሉበት አድነን ለሕግ ማቅረባችን አይቀሬ ነው ብለዋል፡፡ይህን በተግባር እውን ማድረግ የግድ ይላል፡፡
ማንኛውም ዜጋ እንደሚያምነው ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈፀሙ ሰዎች በህግ ተጠያቂ መሆን አለባቸው። ይሄ የሚሆነውም ከምንም ከማንም በላይ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ነው። ማንም ሰው በዜጎች ላይ ኢ- ሰብዓዊ ድርጊት ፈፅሞ መሸሸግና ማምለጥ አይችልም።
ሰሞኑን በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የታየውና የተሰማው ኢ-ሰብዓዊነት ድርጊት በዓለም አቀፍ ደረጃም የኢትዮጵያዊነትን ክብር ያዋረደ፣ ሰብዓዊ ክብርን ያጎደፈ ነው። በመሆኑም እንዲህ አይነቱ ድርጊት ከዚህም በኋላ ዳግም እንዳይፈጸም ለሌላውም ማስተማሪያና ማንቂያ ይሆን ዘንድ ይሄንን ችግር የፈጠሩ አካላት በህግ ሊጠየቁ ይገባል። መጠየቅም አለባቸው።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 6/2011