ወርቃማ በሚባለው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ዘመን የያኔው ሐረርጌ ክፍለ ሃገር ክለቦች የብሔራዊ ቡድኑ ጥንካሬና የጀርባ አጥንት በመሆን ዛሬ ላይ የምንዘክራቸው በርካታ ከዋክብት ተጫዋቾችን አበርክተዋል። በ1952፣ 54፣ 55 እና 57 ዓ.ም ለአራት ዓመት ጥጥ ማህበር (ኮተን)፣ ከ1953 እስከ 1956 ደግሞ ድሬዳዋ ሲሚንቶ ከክልላቸው አልፈው የኢትዮጵያ ቻምፒዮን ሆነዋል። በ1990 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በቂ ጥናት ሳይደረግበት፣ ያለ ጊዜው ከተወለደ በኋላ የከተማ ወይም ክልል ቻምፒዮናዎች ቀስ በቀስ ደብዛቸው እየጠፋ ሄዷል።
የከረረው የድሬ ጸሐይ ሳይበግረው በየሳምንቱ የከተማውን ክለቦች ፍልሚያ ይመለከት የነበረው የዚያ ዘመን ትውልድ እግር ኳስ አፍቃሪ ዛሬ በአንድ ክለብ ብቻ ቀርቶ በሁለት ሳምንት አንድ ጊዜ የድሬዳዋ ከተማ ጨዋታን ብቻ መመልከት እጣፋንታው ሆኗል። ይህም አንድ ለእናቱ የሆነው የድሬዳዋ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ለበርካታ ዓመታት ፕሪሚየር ሊግ ላይ ተሳታፊ መሆን ተስኖት ምስጋና ለሴቷ አሰልጣኝ መሰረት ማኔ ይሁንና ከሦስት ወይም አራት ዓመታት ወዲህ ነው በፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ ለመሆን የበቃው። አሁንም ቢሆን ድሬዳዋ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ከዓመት ዓመት ላለመውረድ እንጂ ለዋንጫ ተፎካካሪ ክለብ ሆኖ ደጋፊዎቹን የሚያረካና የሚመጥን ደረጃ ላይ መድረስ አልቻለም።
እንደ ድሬዳዋ ሁሉ የአዲስ አበባ እግር ኳስም ፕሪምየር ሊግ አመጣሽ በሆነ ነቀርሳ ቀስበቀስ ወደ ሞት እያዘገመ ነው። በሊጉ ላይ የአዲስ አበባ ክለቦች ቁጥር እያደር እየከሰመ፣ ተጽኗቸውም እየተዳከመ ሄዷል። የዚያኑ ያህል በከተማዋ የነበሩ ትልልቅ ክለቦች ከዓመት ዓመት ከአይን እየተሰወሩ ይገኛሉ። የመንግስት የልማት ተቋማት ክለቦች ቁጥር እየቀነሰ የከነማ ክለቦች ቁጥር እያበበ በሄደበት በዚህ ዘመን የሸገር ክለቦች አዲስ ፈተና ለመጋፈጥ ተገደዋል። ፕሪሚየር ሊጉ ከተጀመረበት 1990 ዓ.ም ወዲህ እንኳን በአገራችን እግር ኳስ ወጣቶችን በማፍራት ለብሔራዊ ቡድኑ በመመገብ የሚታወቀው የሁለት ጊዜ ቻምፒዮኑ መብራት ሃይል፣ ንግድ ባንክና መድንን የመሳሰሉት ክለቦች ከሊጉ መውረድ ብቻ ሳይሆን መፍረስም እጣ ፋንታቸው ሲሆን ተመልክተናል።
የከነማ ክለቦች ቁጥር መብዛት በመርህ ደረጃ መልካም መሆኑን በርካታ የስፖርት ቤተሰቦች የሚስማሙበት ቢሆንም የክለቦቹ የፋይናንስ አጠቃቀም በጤናማ መንገድ እስካልተጓዘ ድረስ የሚያስከትለው ውጤት የከፋ እንደሚሆን መገንዘብ ይቻላል። የከተማ ክለቦች የግብር ከፋዩን ህዝብ ገንዘብ በተጋነነ መጠን እግር ኳሱ ላይ ማፍሰሳቸው መሟላት ያለባቸው ብዙ ማህበራዊ አገልግሎቶችና ተንዶ የማያልቅ ችግሮች ላሉባቸው ከተሞች በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነው። የፋይናንስ ጨዋነት ደንብ ባለመኖሩም የተጫዋቾች ደመወዝና የፊርማ ክፍያ ግሽበት ከስፖርትም የዘለለ ዓላማ ያነገቡትን
አንዳንድ የክልል ክለቦች ቅጥ ላጣ ወጪና ብክነት አጋልጧቸዋል። ይህም በቀጥተኛነት በታክስ ከፍዩ ህዝብ ገንዘብ ላይ ያልተንጠላጠሉትን ህዝባዊ የሆኑ እግር ኳስ ክለቦችን ለፈተና ዳርጓል። በተለይም ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና እንደ ከነማ ክለቦች እጅግ ከፍተኛ ዓመታዊ በጀት የመመደብ አቅምና እምነትም የላቸውም ወይም አቅሙን እያጡ መጥተዋል። ተጫዋቾች በሌሎች ክለቦች ከፍ ያለ ክፍያ የሚከፈላቸው መሆኑ እያደገ ከቀጠለ ሁለቱን የሸገር ክለቦች የመምረጥ ዕድላቸው ጠባብ እየሆነ መሄዱ የግድ ነው። በዚሁ የክለቦቹ ተፎካካሪነትም አብሮ መዳከሙን እንደሚቀጥል ከወዲሁ አርቆ መመልከቱ አይከፋም።
እንደ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሪፎርም ጥናት ከሆነ በፕሪምየር ሊጉ፣ በከፍተኛ ሊግና በአንደኛ ሊግ እስከ ግንቦት 30 ድረስ የመንግስት ክለቦች የጨረሱት በጀት 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ይደርሳል። እስከ ሰኔ 30 ድረስ ያለውን ጨምረን ካሰላን ዘግናኝ ውጤት እንደምናገኝ ከግምት ይግባ። በፕሪምየር ሊጉ ላይ የሚሳተፉ የከተማ ክለቦች ዝቅተኛ ዓመታዊ በጀት የሚባለው 58 ሚሊዮን ብር መሆኑን አንድ አንድ መረጃዎች ይጠቁማሉ። የክልል ከተማ ክለቦች አቅም እየፈረጠመ እግር ኳሱ ላይ የሚያፈሱት መዋዕለ ንዋይ እየገዘፈ በሄደ ቁጥር እንደ ኢትዮጵያ ቡናና ቅዱስ ጊዮርጊስ አይነት ህዝባዊ ክለቦች ከዚህ በኋላ የዋንጫ ተፎካካሪ የሚሆኑበት ዘመን ቅርብ እንደማይሆን ብዙዎች ምክኒያታዊ ስጋት አላቸው።
ከዚህ ባሻገር የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተወዳዳሪ
ክለቦች ብዛት ሲጀምርም ጥናት ያልተደረገበት መሆኑ እያደር በእያንዳንዱ ክለብና በአገራችን እግር ኳስ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን በማስረጃ መመልከት ይቻላል። የፕሪሚየር ሊጉ ተሳታፊ ክለቦች ብዛት ከ12 ወደ 14፣ ከ14 ወደ 16 ያደገበት አሳማኝ ምክንያት የለውም። የሊጉ ክለቦች ቁጥር 14 በነበረበት በ2004 ዓ.ም መቀመጫቸውን ሸገር ላይ ያደረጉ ክለቦች ብዛት ሰባት ነበር።
በእርግጥ በዚያ ዘመን የሸገር ክለቦች የሊጉን እኩሌታ ቁጥር መያዛቸው በሌሎች የክልል ክለቦች ላይ የማይገባ የፉክክር ጥቅም ያስገኝላቸው እንደነበር መካድ አይቻልም። በሰንጠረዡ ግርጌ የጨረሰው ፊንጫ ስኳር በመኪና እየተዟዟረ ተዳክሞ ሲጫወት፣ ሰባቱ ክለቦች ብዙሃኑን የሊግ ጨዋታዎች ያለጉዞ ድካም በአዲስ አበባ ያካሂዱ ነበር። በዚያ ዓመት በሰንጠረዡ እስከ አራተኛ የነበረውን ቦታ ይዘው ያጠናቀቁት የአዲስ አበባ ክለቦች መሆናቸው አያስገርምም።
የእግር ኳስ ተንታኙ ጋዜጠኛ መንሱር አብዱልቀኒ በማህበራዊ ድረ-ገፅ ይፋ ያደረገው ስታስቲክስ እንደሚጠቁመው በሊጉ በጨዋታ የሚቆጠረው አማካይ የጎል መጠን 2 ነጥብ 34 የነበረ ሲሆን እስካለንበትም 2011 ድረስ ይህን ያህል ጎል በአማካይ የተመዘገበበት ዓመት ከዚያ ወዲህ አልታየም። የዘንድሮው ደደቢት በደረሰበት ከባድ የፋይናንስ ችግር ምክንያት ስብስቡን በማሳሳቱ ዘንድሮ የሊጉ እጅግ ደካማው ቡድን በመሆን በዘጠኝ ዓመታት ከታየው ሁሉ መጥፎውን የጎል ዕዳ ይዞ ወርዷል። ይህም የሊጉን የጎል ብዛት ያለምክንያት አሳድጎታል።
የ14 ክለቦች ሊግ ከ16 ክለቦች ሊግ የተሻለ መሆኑን ማየት ተገቢ ነው። 14 ክለቦች የሚፎካከሩበት ሊግ በጨዋታዎች መካከል በቂ የማገገሚያ ጊዜ የሚሰጥ መርሐግብር ስለነበር በንጽጽር ያልተዳከሙ ተጫዋቾች በየጨዋታው የመገኘታቸው ዕድል ከፍ ያለ ሲሆን የጨዋታውም ግለት የተሻለ እንደሚሆን ጥርጥር አይኖርም። በኢትዮጵያ የሊግ ክለቦች ቁጥር የሚጨመርበትና የሚቀነስበት በጥናት የጎለበተ ስፖርታዊ ምክንያት የለም። ሌላው ቢቀር በዓመት የ58 ጨዋታ ልዩነት ስለፈጠረ፣ የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫ ከሊጉ መርሃግብር ጋር ተጣጥሞ የመከናወኛ ጊዜ በማጣቱ ለዛ ቢስ እንዲሆን ምክንያት መሆኑን ማየት ይቻላል።
የሊጉ ተወዳዳሪዎች ብዛት በመደበኛነት 16 ሲደረግ የሊጉ አማካይ የጎል መጠን እያሽቆለቆለ መጥቷል። በሊጉ የአዲስ አበባ ክለቦች ብዛት በቀነሰ ቁጥር የቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና ጎል የማስቆጠር አቅም እየወረደ ሊሄድም ተገዷል።
በስምንት ዓመት ውስጥ የቅዱስ ጊዮርጊስ የዓመቱ መጨረሻ የግብ ክፍያ ከ39 ወደ 10 አሽቆልቁሏል። የሊጉ የጨዋታ አማካይ ጎል መጠንም ከ2004 እስከ 2010 ባለው የጊዜ ርቀት በጨዋታ በአማካይ በ0 ነጥብ 48 ጎል ቀንሷል። ያለግብ የሚጠናቀቁ ጨዋታዎች ብዛት እየጨመረ፣ የሊጉ አዝናኝነት እየቀነሰ ሲመጣም ተስተውሏል።
በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ቡና ጉዳይ ይበልጥ አስደንጋጭ ይመስላል። የሊጉ ቻምፒዮን ከሆነበት ከ2003 ወዲህ በየጨዋታው የሚሰበስበው አማካይ
ነጥብ ከ 2 ነጥብ 1 ወደ 1 ነጥብ 3 አሽቆልቁሏል። በሊጉ ላይ ሰባት የአዲስ አበባ ክለቦች በነበሩበት 2003 እና ሶስት ብቻ በቀሩበት በ2011 መካከል ቡና በአማካይ በየጨዋታው የ 0ነጥብ 8 ነጥብ ማሽቆልቆል አሳይቷል። በተመሳሳይ በጎል መጠንም ቢሆን በሁለቱ ዘመናት መካከል በጨዋታ 0 ነጥብ 8 ግብ ቀንሷል። ሊጉ በዚሁ መልኩ ከቀጠለ፣ ሁለት የሸገር ክለቦች ብቻ በቀሩበት በ2012 የኢትዮጵያ ቡና ዕጣ ምን ይሆናል? የሚለውን ስንመለከት እውነትም አስደንጋጭ መሆኑን መረዳት ይቻላል።
የቅዱስ ጊዮርጊስም ነገር እንዲሁ ሳይታይ መታለፍ የለበትም። ከፍተኛ ጎል ካስቆጠረበት ከ2006 ወዲህ በአምስቱ ዓመታት ‹‹የጎል ምርቱ›› ቀንሶበታል። ቢያንስ የ27 ጎሎች ልዩነት አሳይቷል። ይህ የሆነው በዘንድሮው ውድድር ‹‹ፈረሰኞቹ ሶስት ጨዋታዎችን ባለመጫወታቸው ነው›› የሚል ሙግት ሊነሳ ይችላል። ነገር ግን ሶስቱን ጨዋታዎች ቢጫወቱና በእያንዳንዳቸው ስምንት፣ ስምንት ጎሎችን ቢያስቆጥሩ እንኳን ልዩነቱ የሚጠብ አይሆንም። በ2006 አንድ ክለብ 26 ጨዋታዎች ሲጫወት፣ 30 ጨዋታዎች ከሚያደርግበት 2011 ጋር በአራት ጨዋታ እንደሚያንስም ልብ ማለት ይገባል። የጨዋታዎች ቁጥር በዝቶ የጎሉ መጠን ይህን ያህል ዝቅ የሚልበት አንድ አንገብጋቢ ምክንያት ከሌለ በስተቀር በጤና እንዳልሆነ ግልጽ ነው።
ስፖርታዊ ባልሆኑ ምክንያቶች በተለይ ከሜዳ ውጭ ተጉዞ ማሸነፍ ብርቅ በሆነበት በዚህ ዘመን 2012 ላይ የሊጉን ባህሪ በአዎንታ የሚቀይር ሰማያዊ ተዓምር ሊመጣ አይችልም። አካሄዱ ሁሉ ነገር ከድጡ ወደ ማጡ እንደሚሆን ምልክቶች መታየት ከጀመሩ ሰነባብተዋል። ጨዋነት የሚታይባቸው የክልል ክለቦች ያሉ ቢሆንም፣ በተጫዋቾች ላይ የስጋት ሸክም የሚጭኑ ስታዲየሞች የተበራከቱበት ሊግ ላይ ተጫዋችም ሆነ አርቢትር በሜዳ ላይ ያለጭንቀት፣ በስፖርታዊ መንፈስ ውስጥ ብቻ መቆየት አይችሉም። ክለቦቹ በራሳቸው ሜዳ እንደዕለቱ ብቃታቸው የላባቸውን የሚያገኙ ከሆነና በክልል ግጥሚያዎች ሆን ብለው ለመሸነፍ የሚገደዱ ከሆነ ከዚህ በኋላ የትኞቹም ክለቦች በልፋታቸው ልክ የዘሩትን ያጭዳሉ ለማለት ይቸግራል።
ይህም የከተማዋን ክለቦች የፉክክር ዕድል አደጋ ላይ ይጥለዋል። በ2012 ከምንጊዜውም በበለጠ የሸገር ክለቦች በጉዞ ይደክማሉ፣ ከሜዳ ውጪ ጨዋታዎቻቸው ይበዛል። ከ2011 ይልቅ ወደ ሶስት አዳዲስ የክልል ሜዳዎች ተጉዘው የመጫወት ግዴታ አለባቸው። በመከላከያ እግር ኳስ ክለብ ስንብት ምክንያት አዲስ አበባ በዓመት 30 ብቻ የሊግ ጨዋታዎች የሚደረጉባት ከተማ ሆናለች። የከተማዋ ክለቦች ከከተማዋ በራቁ ቁጥር ደግሞ የሁለቱ አንጋፋ ክለቦች አሸናፊነት ዕድል (ስፖርታዊ በሆኑም ይሁን ባልሆኑ ምክንያቶች) እየቀነሰ መሄዱ አዲስ አበባን በእግር ኳስ ቀጣይዋ ድሬዳዋ ሊያደርጋት እንደሚችል ግልፅ ይመስላል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 27/2011
ቦጋለ አበበ