መንግሥት በየዓመቱ ሰኔ መጨረሻ ላይ ከሦስት የገቢ ምንጮች የነደፈውን የቀጣዩን ዓመት ዕቅድ ለሕዝብ ይፋ ያደርጋል። ‹‹የገቢ ምንጮቼ ናቸው›› ብሎ የሚዘረዝራቸው ሀገራችን ከታክስና ከሌሎች የምትሰበስባቸው ገቢዎች፣ ከለጋሽ ሀገራት የሚገኝ እርዳታ እና የአበዳሪ አካላት ብድር ናቸው።
ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም የሚታየን እና በተለይ ሲደርስብን አራተኛ ሆኖ የሚታየን የመንግሥት የገቢ ምንጭ ከመንግሥት ሠራተኞች የመስክ (የፊልድ) ጉዞ የሚገኘው ነው። ‹‹ምን አይነት ሰው ነው ያጠናው?›› እስኪያሰኝ፤ እንኳን ዛሬ፤ ያኔ ከዓመታት በፊት የነበረውን የኑሮ ውድነት ያላገናዘበው ለየከተሞች የተመደበው የመስክ አበል ማነስ ጉድ ያሰኛል።
እኔ፤ ባለፈው ሰኔ መጀመሪያ አካባቢ ከሁለት ባልደረቦቼ ጋር ለሁለት ቀናት ጅማ የሄድኩበትን የመስክ ሥራ ገጠመኝ ላካፍላችሁ። የሄድነው በአውሮፕላን ሲሆን አውሮፕላኑን የተሳፈርነው ከጠዋቱ 5፡00 ነው። ጅማ እንደገባን የተቀበለን የቅርንጫፍ ጽ/ቤታችን መኪና ያደረሰን ሆቴል ዘንድ አልጋ የያዝነው በ150 ብር ነው። የምሳ ሰዓት ደርሶ ነበረና አንድ ኪሎ ጥብስ በ270 ብር አዘዝን። ይህ ለእያንዳንዳችን 90 ብር ይደርስብናል። አብሮ ደግሞ ውሃ ያስፈልጋልና ስድስት ስድስት ብር አውጥተናል። ማታም ይኸው ነው የተደገመው። በነጋታው ደግሞ ለቁርስ እያንዳንዳችን 50 ብር ያወጣን ሲሆን ምሳ በቅርንጫፍ ጽ/ ቤቱ ተጋበዝን። ጋባዥ ባይኖር ግን ያው የተለመደው የ90 ብር ጥብስ አይቀርም ነበር። እናም ‹‹ጋባዥ ይኖራል›› ተብሎ ተስፋ አይያዝምና ከስድስት ብር ውሃ ጋር እንደ ወጪ ይዘን እናስላው። ከቀኑ 11፡00 ወደ አዲስ አበባ ተመልሰን በነጋታው ሒሳብ ማወራረድ አለብንና ማስረጃችንን ስናቀርብ የገጠመን ነገር መንግሥት ምን አይነት አጥኚ እንዳለው እንድንታዘብ ብቻ ሳይሆን አራተኛ የመንግሥት የገቢ ምንጭነታችን ታየን።
ለጅማ ከ3ሺ 816 ብር በላይ ደመወዝተኛ የተመደበው የውሎ አበል 179 ብር ነው። ስለዚህ ለእያንዳንዳችን የሁለት ቀን 378 ብር ነው የተሰጠን። መስክ ሲወጣ ያለውን ዘና ማለት ‹‹ቅንጦት ነው›› ብለን እንለፈውና ከላይ እንደዘረዘርሁላችሁ ለመሥራት ራስን መመገብና ማሳረፍ አስፈላጊ በመሆኑ በነፍስ ወከፍ 392 ብር አውጥተናል። ይህ እንግዲህ ከተሰጠን 358 ብር በተጨማሪ ከኪሳችን የጨመርነው 14 ብር ነው። በዚህ ቢያቆም ጥሩ ነበር። ነገር ግን መ/ቤታችን ደግሞ ሲያወራርድልን ከአዲስ አበባ የተነሳን ዕለት ቁርስ እዚህ ስለበላን በተመላሽነት ተያዘብን። ቀጠለና ደግሞ ከጅማ 11፡00 ስለተመለስን የእራት እና የአልጋ መመለስ ስለምንገደድ ከተነሳንበት ዕለት ጋር በድምሩ 144 ብር ከ25 ሳንቲም እንድንመልስ ተጠይቀን ጅማ ላይ በተጨማሪነት ካወጣነው 14 ብር ጋር ለመንግሥት ሥራ ከራሳችን 158 ብር ከ25 ሳንቲም ደጎምን ማለት ነው። የኛን የጅማ ወጪ አቀረብኩንጂ ከኛ ቀደም ብላ ድሬዳዋ ለአምስት ቀናት የቆየች ባልደረባችን ስታወራርድ ከራሷ የጨመረችው ዘጠኝ መቶ ምናምን ብር ሳያንስ እንደኛ የሄደች ዕለት ‹‹ቁርስ አዲስ አበባ በልተሻል›› እና ስትመለስ ‹‹እራት ከነአልጋው አዲስ አበባ ነበርሽ›› ተብላ በድምሩ ከሺ ብር በላይ መንግሥትን ደጉማለች።
የጅማን እና የድሬዳዋን ምሳሌ አደረግኩንጂ የሚገራርም የውሎ አበል የተመደበላቸው አካባቢዎችን ስናይ ደግሞ ለሥራ መንቀሳቀስን አያስመኝም። ምናልባት፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ እንግዳ ተቀባይ ነው›› በማለት ታስቦ ካልሆነ በቀር ሰው እንዴት እስከ 2ሺ 248 ብር ደመወዝ ተከፋይ 83፣ ከ2ሺ 249 እስከ 3ሺ 816 ብር ደመወዝተኛ 92 እና ደመወዙ ከ3ሺ 816 ብር በላ ለሆነ 101 ብር የቀን አበል ከፍሎ ጋምቤላ እና ጋምቤላ ዙሪያ በሚገኙት አቦቦ፣ ጎግ፣ ጎደሬ፣ መኮወይ፣ ጅክዋ፣ መታሃር እና አኮቦ ላይ ዜጋውን ይልካል? የቤኒሻንጉሎቹ ሀሞሸ፣ አጊሎ ሚጤ፣ ሸርቆሌ፣ መንጌ፣ ፓዌ፣ ወንበራ፣ ድባጤ፣ በሎጂ፣ ሲርባ፣ ያሰ፣ ቡለን እና ቶንጎ ቦታዎችስ በሦስቱ የደመወዝ ደረጃዎች ብር 85፣ 96 እና 107 የውሎ አበል እየከፈሉ መላክ ግዞት ነው ወይስ የለበጣ ሥራ እንዲሠራ? በርግጥ አብዛኛዎቹ ቦታዎች የበረሀ አበል ቢታከልባቸውም ሄዶ ላየ ሰው የዜጋ ህይወት ምን ያህል እንዳልታየለት ይመሰክራል።
ለመሆኑ አንድ የመንግሥት ሠራተኛ መስክ ሲወጣ ስለ ሥራው እንጂ ስለሚያርፍበት እና ስለሚመገበው ማሰብ ነበረበት? እንደ ብዙዎቹ የግል ተቋማትና የመንግሥት ኃላፊዎች በቂ አበል የማይሰጥበት እና የአልጋ ደረሰኝ የሚወራረድበት ክፍያ የማይመደብበት ምክንያት ለምን ይሆን?
ለዚህ ነው አንድ የመንግሥት ሠራተኛ በህግ የሚያስጠይቁ የተለያዩ ጥፋቶችን የሚፈጽመው። ከጥፋቶቹ መካከል ሾፌሮች በያዙት መኪና ተሳፋሪ ጭነው ገንዘብ ይቀበላሉ። በመኪና የሄደ ሠራተኛ ከቆየባቸው ቀናት እጥፍ እና ከዚያ በላይ ጨምሮ (የሦስት ቀኑን ስድስት ቀናት በማድረግ) የውሎ አበል ይቀበላል። በትራንስፖርት እና በተለያዩ ደረሰኞች ላይ ማጭበርበርን ይፈጽማል። ይህ ሁሉ የሚሆነው ሰው ለማታለል ፈልጎ ሳይሆን ለመንግሥት ሥራ የተመደበው የውሎ አበል በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ ነው። ማጭበርበር ከሚመስለው ባሻገር ሰው ለሥራ በተላከበት ቦታ ዐይኑን በጨው አጥቦ ዘመድ ጓደኛ ዘንድ እየተሳቀቀ ያድራል ወይም ለሥራ የተላከባቸው ባልደረቦቹን ኪስ ይመለከታል አሊያም ለብድር ይዳረጋል፣ ሲከፋ ደግሞ ደረጃቸውን ባልጠበቁ መኝታ ቤቶች በመተኛትን ምግብ በመመገብ ለረሀብ እና ለበሽታ ይጋለጣል።
ይህን የተሳሳተ አሠራር ያወጡ የመንግሥት አካላት ግን በፕሮጀክት እና በሌላም ስም ራሳቸውን እየጠቀሙ እንደሚንቀሳቀሱ ሐገር ያወቀው፤ ፀሐይ የሞቀው የአደባባይ ምስጢር ነው።
ይህ፤ እንደ መምህራን እና የጤና ባለሙያዎች የ‹‹ደመወዝ ይጨመርልን›› ጥያቄ ‹‹ወቅቱን ያላገናዘበ ነው›› መባል የሌለበት ነውና መንግሥት፤ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን፣ ሌሎች ሀገራትን እና መሬት ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ አጥንቶ ለውጤታማ ሥራ ትክክለኛ እና ፍትሐዊ የውሎ አበል ምደባ ቢያደርግ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 27 /2011
በእስክንድር መርሐጽድቅ