– ኤል ቲቪ ሠራተኞቹን የቀነሰው ኪሳራ ስላጋጠመው መሆኑን ገልጿል
አዲስ አበባ፡- በሁለት የግል መገናኛ ብዙኃን የሚሰሩ ጋዜጠኞች ያለአግባብ ከሥራቸው መባረራቸውንና ህጋዊ መብቶቻቸውም ያልተከበ ሩላቸው መሆኑን አስታወቁ።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ ያነጋገራቸው የሁለቱ መገናኛ ብዙኃን ሰራተኞች ምክንያቱ ምን እንደሆነ በማያውቁት ሁኔታ ከሥራ እንደሚባረሩና በስራ ላይም ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶቻቸው የሚጣስበት ሁኔታ መኖሩን አመልክተዋል። አንዳንዶቹም ክብረ ነክ ስድብ እንደሚሰደቡ ተናግረዋል።
‹‹ስሜ አይጠቀስ›› ያለው የኤል.ቲቪ. ሰራተኛ በቅርቡ የስንብት ደብዳቤ እንደተሰጠውና በደብዳቤው ላይ የተገለጸው የቴሌቪዥን ጣቢያው ስለከሰረ ተብሎ ቢሆንም በብቃት ችግር የሚል ሌላ ተደራቢ ምክንያት እንዳለም ተናግሯል። ከተቀጠረበት ጊዜ ጀምሮ ጥሩ አፈጻጸም ያለው እና በቴሌቪዥን ጣቢያው ውጪ አገር ድረስ በመሄድ ሥልጠና እንዳገኘም አመልክቷል።
‹‹የቴሌቪዥን ጣቢያው ክስረት ካጋጠመው ሰራተኛን መበተኑ አይፈረድበትም፤ ያለው አማራጭ ሰራተኛን መቀነስ ነው›› ያለው ሰራተኛው፤ ይሄ ምክንያት እውነት ስለመሆኑ ግን ጥርጣሬ እንዳለው ገልጿል። ጥናቱ ተሰራ የተባለው ውጭ አገር ነው፤ ሰራተኞች ስለጥናቱ እንደማያውቁ ተናግሯል።
ሌላኛው የቴሌቪዥን ጣቢያው ሰራተኛ በበኩሉ፤ የታሰበው ባለቤቱ የሚፈልጋቸውን ሰዎች ብቻ ማስገባት ነው፤ ለዚህ የፈጠረው ምክንያት እንጂ ድርጅቱ ክስረት ያላጋጠመው መሆኑን አስረድቷል።
የኤል ቲቪ ሥራ እስኪያጅ አቶ መስፍን ብሩ ስለጉዳዩ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ተጠይቀው ሰራተኞችን መቀነስ ያስፈለገበት ምክንያት ድርጅቱ ክስረት ስላጋጠመው እንጂ ሌላ ምክንያት የለውም ብለዋል። ‹‹በማህበራዊ ገፆች ብዙ ነገር ቢባልም ህግ ከሚፈቅደው ውጪ የተደረገ ነገር የለም። ሥራውን በጥቂት ሰራተኞች ብቻ ለማስቀጠል ስለሚገደድ በንፅፅር የተሻሉ ናቸው ያላቸውን አስቀርቶ አሰናብቷል። ተመሳሳይ ሙያ ቢኖራቸውም አንዱን ከአንዱ ማወዳደር ያለ አሰራር ነው›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።
በተመሳሳይ በብስራት ሬዲዮና ቴሌቪዥን የሚሰሩ ሰራተኞች የሰራተኛ ህግና ደንብ እንደማይከበርላቸው ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ገልጸዋል። ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገው የጣቢያው ሰራተኛ እንደሚለው፤ ለሰራተኞች የሥራ ልምድ አይጻፍም፣ የቅጥር ውል አይፈጸምም፣ ማሰናበት ባስፈለገው ጊዜ ያለምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ በጥበቃ እንዲመለሱ ይደረጋል።
ስለጉዳዩ እውነትነት ለማጣራት የኦያያ መልቲሚዲያ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ መሰለ መንግስቱን ለማግኘት በተከታታይ ስልክ ብንደውልም ሊነሳልን አልቻለም፡፡ የጋዜጣው ሪፖርተር በአካል ጣቢያው ድረስ በመሄድ የሚከተለው አጋጥሞት ተመልሷል።
የዝግጅት ክፍሉ ጋዜጠኛ በመጀመሪያ አቶ መሰለ መንግስቱን ለማነጋገር ሲጠይቅ አለመኖራቸውንና እርሳቸውን ለማነጋገር አስቀድሞ ቀጠሮ መያዝ እንደሚገባው ፀሃፊው ገልፃለታለች። ይሁንና በአጋጣሚ አቶ መሰለን በመንገድ ላይ አግኝቶ ከየት እንደመጣና የመጣበትን ጉዳይ አብራርቶ ምላሽ እንዲሰጡት ቢጠይቃቸውም ‹‹ጊዜ የለኝም›› የሚል ምላሽ ሰጥተውታል። ይሁንና ጋዜጠኛ ከሦስት ደቂቃ በላይ እንደማይወስድባቸው ቢያስረዳቸውም ለማንም መገናኛ ብዙኃን በምንም ጉዳይ ላይ ቃለ መጠይቅ እንደማይሰጡ፤ ቢሰጡት እንኳን ከሦስት ወር በኋላ ሊሆን እንደሚችል ነግረውታል።
በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የህግ አማካሪና ጠበቃ አቶ ዝናቡ ይርጋ እንደሚሉት፤ ሰራተኞች የሚዳኙት በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 ነው። በአዋጁ መሰረት አንድ አሰሪ ሰራተኛ ሲቀጥር ቢበዛ በአሥራ አምስት ቀን ውስጥ ውሉ ወደ ጽሑፍ መቀየር አለበት። በውሉ መሰረትም ሰራተኛው በየወሩ ደሞዙን ሊያገኝ ይገባል። ከወር ደሞዙ ላይ በህጉ መሰረት ግብር ይከፈላል።
እንደ ህግ አማካሪው ገለጻ፤ አንድ ሰራተኛ በሳምንት 48 ሰዓት ነው መሥራት ያለበት። አንድ አሰሪ የሰራተኞችን መብት የማያስከብር ሆኖ ከተገኘ ሰራተኞች ወደ አሰሪና ሰራተኛ ቦርድ ሄደው ቅሬታቸውን ማቅረብ ይችላሉ። ጉዳዩ በአንድ ሰራተኛ ላይ ብቻ ከሆነም ወደ መደበኛው ፍርድ ቤት መውሰድ ይገባል። አሰሪው የሰራተኛውን የሥራ ልምድ የሚከለክል ከሆነ በግልጽ የተቀመጠ ህግ ስላለ ጉዳዩን ወደ መደበኛው ፍርድ ቤት መውሰድ ይቻላል፡፡
የአሰሪና ሰራተኛ ህጉ እንዳስቀመጠው ለአሰሪና ሰራተኛ ክርክር የዳኝነት አይከፈልም። እንዲህ አይነት ህግ መተላለፍ ድርጅቶችን እስከማሰረዝ ይደርሳል።
አንድ ድርጅት ኪሳራ አጋጥሞት ሰራተኞችን ማሰናበት ከፈለገ ከማስጠንቀቂያ ነው የሚጀምረው። ይህንንም ሲያደርግ እነማን መቀነስ አለባቸው የሚለውን ቅድመ ሁኔታ አስቀምጦ ነው። ለሰራተኛውም እንደየቆይታው የሥራ ስንብት ይከፈለዋል። ከአንድ ዓመት በላይ ያገለገለ ሰራተኛ ሲሰናበት የቀጣዮቹ ዓመታት አንድ ሦስተኛ ሊከፈለው ይገባል።
ቀጣሪው ድርጅት ሳይከስር ከስሪያለሁ ቢል ህገወጥ ሽኝት ነው። ህገ ወጥ ሽኝት ደግሞ የካሳ ክፍያም ያስከፍላል።
‹‹ቀጣሪ ድርጅቶች የሥራ ልምድ የማይጽፉበት ምክንያት ግብር የመክፈል ግዴታቸውን ስላል ተወጡ ሊሆን ይችላል›› ያሉት የህግ አማካሪው፣ ይህም ከግብር የመሸሽ ሙከራ እንደሆነ ይገልጻሉ። የተጻፈው የሥራ ልምድ የግብሩን መጠን ስለሚናገር ያንን ለመደበቅ ነው።
በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ታየ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ከሰራተኞች ቅሬታዎች ሲነሱ ጉዳዩ የሚታየው በአሰሪና ሰራተኛ ወሳኝ ቦርድ ነው። ቦርዱ ከአሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን እና ከሰራተኛና ማህበራዊ የተወከለ ሲሆን ከሰራተኞች ቅሬታ ሲመጣለት መረጃ ይዞ ይከታተላል። በደል የደረሰበት ሰራተኛ በሚያመጣው መረጃ እንደ ፍርድ ቤት ሆኖ ደመወዙ ይወሰናል።
ዋለልኝ አየለ