
አዲስ አበባ፡- በአምስቱም የአዲስ አበባ መውጪያና መግቢያ በሮች አርሶ አደሮች ምርታቸውን የሚያስቀምጡባቸውንና ለገበያ የሚያቀርቡባቸውን ማእከላት ለመገንባት መታቀዱን የከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል። የከተማዋ ነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለማቃለልም አንድ ሺህ 500 ሄክታር መሬት መዘጋጀቱ ተጠቁሟል።
የ2011ን በጀት አመት አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ ያቀረቡት ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ እንደተናገሩት፤ በአምስቱም የአዲስ አበባ መውጪያና መግቢያ በሮች ላይ አርሶ አደሮች ምርታቸውን የሚያስቀምጡባቸውንና ለገበያ የሚያቀርቡባቸውን ማእከላት ለመገንባት ዝግጅቶች እየተደረጉ ናቸው። በተጨማሪም
በተመጣጣኝ ዋጋ ለከተማው ነዋሪ የሚያቀርብ ግዙፍ የዳቦ ማምረቻ ኢንቨስትመንት ድጋፍ ተደርጎለት ወደ ግንባታ ስራ በመግባት ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን ለሚያመርቱ ሌሎች ኢንቨስትመንቶች የተለየ ድጋፍ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
“ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ 200 ሺህ ከሚደርሱ የከተማዋ ነዋሪዎች ጋር ፊት ለፊት መመካከር ተችሏል።” ያሉት ኢ/ር ታከለ፤ በበጀት አመቱ ለ163 ሺህ 141 የከተማዋ ነዋሪዎች የስራ እድል መፍጠር ተችሏል። ከተያዘው በጀት ተጨማሪ ሁለት ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ በመመደብ፤ በብድር አሰጣጡ ላይ ጫና የሚፈጥሩ መመሪያዎችን በመፈተሽ፤ በማስተካከል ወደ ስራ የተገባ መሆኑንም ነው የተናገሩት፤
በቀን 44 ሺህ ሜትር ኪዩብ ንጹህ የመጠጥ ውሃ የማምረት አቅም ያለውና ከ400 ሺህ በላይ የከተማዋን ነዋሪ ተጠቃሚ የሚያደርግ የውኃ ልማት ፕሮጀክት በሩብ ዓመት ጊዜ ውስጥ በፍጥነት ስራው ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት እንዲጀምር መደረጉንም ጨምረው አስታውቀዋል።
ምክትል ከንቲባው፤ የለውጥ አመራሩ ስራውን በማካሄድ ስርነቀል ማሻሻያ ለማድረግ እና ብልሽቶችን ለማስተካከል ወደ ውስጥ ማየት እና ራስን ለመለወጥ ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቶ እንደነበር ጠቁመው፤ የከተማዋ አስተዳደር ከካቢኔ ጀምሮ እስከ ክፍለ ከተማ እና ወረዳ ድረስ 47 ሺህ ሰራተኞችን ያቀፈ የመዋቅር ማሻሻያ እና ለውጥ ማደረጉን ተናግረዋል።
30 ቢሊዮን ብር የሚያወጣው “ሸገርን የማስዋብ” ፕሮጀክት ስራ እየተፋጠኑ ከሚገኙና የከተማዋን ገጽታ በከፍተኛ መጠን ከሚቀይሩ ፕሮጀክቶች መካከል በፍጥነት እየተከናወነ የሚገኝ መሆኑን የተናገሩት ምክትል ከንቲባው፤ በ60 ቢሊዮን ብር የሚገነባው የለገሃር ዘመናዊ የመኖሪያ መንደር ዝግጅትም እየተፋጠነ መሆኑን ጠቁመዋል።
እንደ ኢንጅነር ታከለ ገለፃ፤ የከተማዋ አስተዳደር ባካሄደው ሰፊ ንቅናቄ ከ10 ሺህ በላይ ወጣቶችን ከጎዳና ላይ ለማንሳት ተችሏል። ለቀጣዩ የትምህርት ዘመን ሰባት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ደብተር በነፃ ማቅረብ፣ ለ600 ሺህ የተማሪዎች የደንብ ልብስ በነፃ ማቅረብ እና ለ300 ሺህ ህፃናትም የምገባ ፕሮግራም የማስጀመር ዝግጅት በተሳካ ሁኔታ ተከናውኗል።
ጧሪ ደጋፊ የሌላቸውን አቅመ ደካማ አረጋውያን መኖሪያ ቤቶች በማደስ የተጀመረው የመተጋገዝ፣ የመተሳሰብ፣ የበጎ አድራጎት ስራ በአሁኑ ሰአት ወደ ቋሚ ባህልነት እያደገ ነው ለማለት የሚያስችሉ ምልክቶችን እያሳየ መሆኑን ጠቁመው፤ የከተማዋ ነዋሪዎችም በአስተዳደሩ ርምጃች ሁሉ የተበላሸውን በማስተካከል፣ የጎደለውን በመሙላት፣ ስህተቶችን በማረምና በሁሉም እንቅስቃሴዎች ላይ እገዛ በማድረግ ላበረከቱት አስተዋፅ ምስጋና አቅርበዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 26/2011
ምህረትሞገስ