በአንድ አገር ሥርዓት ሰፍኗል ሲባል ትልቁና ገዝፎ አዕምሯችን የሚመጣው ሕገ መንግሥትና የሕገ መንግሥታዊነት ጉዳይ ነው። ሕገ መንግሥታዊነት መነሻውም መድረሻውም ደግሞ ሕገ መንግሥቱ ነው።የሕገ መንግሥታዊነት ፅንሰ ሐሳብም ከሕገ መንግሥት ፅንሰ ሐሳብ ጋር አብሮ የዳበረ እንደሆነ በርካታ ተዛማጅ ጽሑፎችን በአስረጅነት ማሳየት ይቻላል።
ዋልተን ሐሚልተን የተባሉ የሕግ ባለሙያ ሕገ መንግሥታዊነትን ሲያብራሩ ‹‹ሕገ መንግሥታዊነት ሰዎች በሕገ መንግሥት በጽሑፍ ለተቀመጡት እና ለመንግሥታዊ ሥርዓት የሚሰጡት እምነት ነው›› ይላሉ።በጥቅሉም ሕገ መንግሥታዊነት ሲባል በተለይ መንግሥትን ጨምሮ ህዝብና የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ተግባራዊ ለማድረግ ያላቸው ዝግጁነትና እምነት ነው።
እምነት፣ ሰዎች በሕገ መንግሥቱ ተማምነው እና ሕገ መንግሥቱን እንደ ድጋፍ አድርገው በሥርዓቱ ውስጥ የሚኖሩበት ተስፋ ነው። ሰዎች ሕገ መንግሥቱን የሚያከብሩት ሌሎችም እንደኔ ሕገ መንግሥቱን ያከብሩታል፤ አናከብርም ቢሉ እንኳን መንግሥት ይሄን አመኔታየን ያስከብርልኛል ብለው ነው። ይህ ሕገ መንግሥታዊነት ነው። በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡት ድንጋጌዎች በሥርዓቱ ያላቸውን አመኔታና በሕገ መንግሥቱ ላይ ያላቸውን መመካት መገለጫም ነው።
የሕገ መንግሥታዊነት ዋነኛ ግብ እና ዓላማ፤ መንግሥትን በሕግ በተሰጠው ማዕቀፍ ውስጥ እንዲንቀሳቀስ እና ከተሰጠው የሥልጣን ገደብ ውጭ ዝንፍ እንዳይል እንደ መቆጣጠሪያነት ማገልገሉ ነው። በዴሞክራሲያዊ አስተዳደር መንግሥት የዜጎች ይሁንታ ውጤት እንደመሆኑ መጠን፤ ይሄ ይሁንታም በሕገ መንግሥቱ የተገለፀ እና በሕገ መንግሥታዊነት የሚተረጎም ነው።ዜጎች መንግሥታቸውን ሲመሰርቱ ‹‹ያንተ ሥልጣን እስከዚህ ነው፤ ከዚህ በላይ መጓዝ አትችልም›› ብለው በሕግ ለክተው ሥልጣኑን ለመንግሥት ይነግሩታል፤ መንግሥትም በተሰመረለት መስመር ልክ በሚገባ ይተገብራል።ያኔም ሕገ መንግሥታዊነት አለ እንላለን።ሥልጣኑ ተገድቦ ሕግን የሚተገብር መንግሥትም የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ዋነኛ ምሰሶ ነው።ዜጎችም ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በማክበር ለሕገ መንግሥታዊነት መርህ ተገዥ መሆን አለባቸው።
ከላይ ከተነሱ መሰረታዊ የሕገ መንግሥታዊነት መርህ ስንነሳ የሕግ የበላይነት በሚገባ ተግባራዊ መደረጉን ለማየት መሞከር ወቅታዊና አስፈላጊ ይሆናል። በመሆኑም በአገራችን በተለይም ለውጡን ተከትሎ ከሚስተዋሉ ጉዳዮች ውስጥ የሕግ የበላይነት በተለያዩ አካላት በሚፈለገው ልክ መተግበር አለመቻሉ ነው።እዚህ ላይ ግን ወሰን የሚያስፈልገው የመንግሥት ትዕግሥትም አንዱ ችግር ነው።
ዓመት የዘለቀው የለውጥ ሂደታችን ሕገ መንግሥቱ ያስቀመጣቸው መብቶች የተጣሱበት ለመሆኑ አንዳንድ አንቀጾችን በማንሳት አስረጅ እናቅርብ። የሕገ- መንግሥቱ አንቀጽ 15 የሕይወት መብት ‹‹ማንኛውም ሰው በሕይወት የመኖር መብት አለው።ማንኛውም ሰው በሕግ በተደነገገ ከባድ የወንጀል ቅጣት ካልሆነ በስተቀር ሕይወቱን አያጣም፡፡›› ቢልም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በተፈጠሩ ምክንያቶች የሰው ሕይወት ተቀጥፏል።መፈናቀሎችም አጋጥመዋል።
የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 15 የአካል ደኅንነት መብት ‹‹ማንኛውም ሰው በአካሉ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የመጠበቅ መብት አለው፡፡›› ምክንያቱ ጉራማይሌ ቢሆንም በጥይት፣ በዱላ እና በሌሎች ነገሮች የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች ቁጥራቸው በርካታ ነው።ድብደባ እና አላግባብ እንግልት የደረሰባቸውም የሚደበቅ ሀቅ አይደለም። አንቀጽ 24.1 የክብርና የመልካም ስም መብት ‹‹ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ ክብሩና መልካም ስሙ የመከበር መብት አለው።›› ይህ ማለት ሰዎችን የተለያዩ ስያሜዎችን በመስጠት መጥራት፣ ጥፋተኛ ተብለው በሕግ ያልተፈረደባቸውን ደምድሞ ክብራቸውን መንካት በዋናነት የሚጠቀሱ የሕገ መንግሥቱ አንጓዎች ናቸው፡፡
ከላይ ከተነሱ ውስን የሕገ መንግሥቱ ማሳያዎች ስንነሳ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ መንግሥት አንዳንድ አካላት እንደ አፍራሽ ሰነድ ቢመለከቱም ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ ስምምነቶችን ሙሉ ለሙሉ መቀበሉ፤ እንዲሁም ከአጠቃላይ ከአንቀጾቹ ሁለት ሦስተኛ ያህሉን የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ የደነገገ ነው።ታዲያ ይህ ሁሉ መብት በዝቶ ባለበት ሕገ መንግሥት የጎደለው ምንድን ነው ለሚለው ጥያቄ መልሳችን ‹ሕገ መንግሥታዊነት› ነው ብሎ መናገር ያስደፍራል፡፡
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ መንግሥትም ሕገ መንግሥታዊነት ወሳኝ እና ዋነኛ የሥርዓት አካል አድርጎ በመውሰድ በተለያዩ አንቀጾቹ ሕገ መንግሥቱ እንዲከበርና ሕገ መንገሥታዊነት እንዲሰፍን ያስገድዳል።በጥቅሉ በአንቀፅ 9 ንዑስ ቁጥር 3 ላይ ‹‹ማንኛውም ዜጋ፣ የመንግሥት አካላት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች ሌሎች ማህበራት እንዲሁም ባለሥልጣኖቻቸው ሕገ መንግሥቱን ማስከበርና ለሕግ ተገዥ የመሆን ኃላፊነት አለባቸው፡፡›› በማለት ሁሉም ዜጋ ላይ ግዴታን ይጥላል። ስለሆነም ሕገ መንግሥቱና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ እንዲከበር፤ መንግሥትም ሆነ ዜጎች ሕገ መንግሥታዊነት እንዲሰፍን ሊሠሩ ይገባል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25 ቀን 2011