በካታር አስተናጋጅነት በ2022 ለሚከናወነው የዓለም ዋንጫ የአፍሪካ ዞን ማጣርያ ድልድል ከትናንት በስቲያ በግብፅ መዲና ካይሮ ይፋ ተደርጓል። የአፍሪካ ዞን የማጣርያ ድልድሉ በዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ መመሪያ መሰረት ድልደላው መደረጉ ተነግሯል። የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ወርሐዊ የፊፋ ደረጃን መሰረት ያደረገው የማጣርያ አካሄድ የቅድመ ማጣርያ፣ የምድብ ማጣርያ እና የመለያ ሒደቶች የተከተለ ሲሆን በሀገራት ደረጃ ከዝቅተኞቹ የሚመደቡ ሃገራት የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች የሚጠብቃቸው እንደሆነ የፊፋ መመሪያ ያስረዳል።
በዚሁ መመሪያ መሰረት በአፍሪካ የሚገኙት ሃገራት በወቅታዊ ደረጃቸው ዝቅተኛ የሆኑትና የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታቸውን የሚያደርጉት 28 ሃገራት በቋት አንድ ተደልድለዋል። በቋት አንድ ከተደለደሉት ሃገራት ውስጥ ኢትዮጵያ፣ ዚምባብዌ፣ ሞዛምቢክ፣ ሴራሊዮን፣ ናሚቢያ፣ ጊኒ ቢሳዋ፣ ማላዊ፣ ቶጎ፣ ሱዳን፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ኢኳቶርያል ጊኒ፣ ኢስዋቲኒ እና ሌሶቶ ናቸው። ሃገራቱ እርስ በእርስ ተጫውተው አሸናፊ የሆኑት 14 ሃገራት ወደ ምድብ ማጣርያው የሚገቡ ይሆናል። በቅድመ ማጣሪያ ጨዋታው ማን ከማን እንደሚጫወት ለመለየት ከትናንት በስቲያ በግብዕ የዕጣ ማውጣት ሥነ ስርዓት ተከናውኗል።
በዚህ ቋት ውስጥ የምትገኘው በወቅታዊ ደረጃዋ 150ኛ ላይ የተቀመጠችው ኢትዮጵያ በቅድመ ማጣርያ ጨዋታዋን ከሌሴቶ ጋር ትጫወታለች። ኢትዮጵያም የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዋን ነሐሴ 26 በሜዳዋ የምታደርግ ይሆናል። ኢትዮጵያ እና ሌሴቶ ለ2017 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ በአንድ ምድብ እንደነበሩ የሚታወስ ሲሆን ባህር ዳር ላይ በተደረገው ጨዋታ ኢትዮጵያ በጋቶች ፓኖም እና ሳላዲን ሰዒድ ጎሎች 2 ለ 1 ስታሸንፍ በተመሳሳይ ሌሶቶ ላይም በጌታነህ ከበደ ሁለት ጎሎች ኢትዮጵያ 2 ለ 1 ማሸነፏ የሚታወስ ነው።
በተመሳሳይ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ በቋት አንድ የሚገኙትና ዝቅተኛ ወርሐዊ ደረጃን የያዙት ሃገራት የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታቸው የተለየ ሲሆን ፤ሶማሊያ ከዚምባብዌ፣ ኤርትራ ከናሚቢያ፣ ቡሩንዲ ከታንዛኒያ፣ ጅቡቲ ከኢስዋቲኒ፣ ቦትስዋና ከማላዊ፣ጋምቢያ ከአንጎላ፣ላይቤርያ ከሴራሊዮን፣ ሞሪሸስ ከሞዛምቢክ፣ ሳኦቶሜ ከጊኒ ቢሳው፣ደቡብ ሱዳን ከኢኳቶርያል ጊኒ፣ኮሞሮስ ከቶጎ፣ቻድ ከሱዳን እና ሲሸልስ ከሩዋንዳ ናቸው።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 24/2011
ዳንኤል ዘነበ