ድሬዳዋ ከተማ አጥቂዎቹ ዮናታን ከበደ፣ ኃይሌ እሸቱ እንዲሁም ተከላካዩ ወሰኑ ማዜን በመጋቢት ወር መጀመሪያ አሰናብቷል። የክለቡን ውሳኔ በመቃወም ተጫዋቾቹ ለብሄራዊ ፌዴሬሽኑ ቅሬታን አስገብተዋል። ተጫዋቾቹ ቀሪ የስድስት ወራት የውል ኮንትራት እያለን ያለ አግባብ ተሰናብተናል ሲሉም አቤት ብለዋል። ፌዴሬሽኑ ጉዳዩን ከተመለከተ በኋላ ተጫዋቾቹ ያቀረቡት ቅሬታ ተገቢ ነው በማለት በ10 ቀን ውስጥ ለተጫዋቾቹ ደመወዛቸው እንዲከፈል የሚል የውሳኔ ደብዳቤን ለክለቡ ልኳል። ይሁንና ክለቡ ጋዜጣዊ መግለጫ በመስጠት ውሳኔው አግባብነት እንደሌለው በመግለጽ የብሄራዊ ፌዴሬሽኑን ጣልቃ ገብነት መሰረተ ቢስ መሆኑን አመላክቶ ነበር።
ሆኖም የክለቡ ጥያቄ በድጋሚ ውድቅ በመደረጉ ለሁለተኛ ጊዜ ፌዴሬሽኑ ለድሬዳዋ ማስጠንቀቂያ አዘል ደብዳቤን በድጋሚ ለመላክ ተገዶ ነበር። ክለቡ የፌዴሬሽኑን ውሳኔ ተፈጻሚ ባለማድረጉ ምክንያት የዲሲፕሊን ኮሚቴ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምንም ዓይነት አገልግሎት እንዳያገኝ አግዶ ቆይቷል፡፡ የክለቡ ቦርድ በስተመጨረሻም ተጫዋቾቹ የጠየቁትን ጥያቄ በመመለስ እጅ መስጠቱ ታውቋል። በጉዳዩ ላይ የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ አንበስ አውግቸው ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት፤ ክለቡ ባሰናበታቸው ተጫዋቾች ዙርያ የፌዴሬሽኑን ውሳኔ ተግባራዊ ሊያደርግ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
ለሁለት ተጫዋቾች የሦስት ወር ደመወዝ፣ ለአንድ ተጫዋች ደግሞ የአንድ ወር ደሞዝ ለመክፈል መዘጋጀቱን ገልጸዋል። «እንዲከፈላቸውም ተወስኗል። በሊግ ኮሚቴው ውሳኔው መሠረት ዞሮ ዞሮ እልህ መጋባት ስለሌለብን በሚል ነው። ነገር ግን ውሳኔው ብዙ ክፍተቶች ነበሩበት። የህዝብ ክለብ እንደመሆኑ መጠን ክርክር አያስፈልግም፤ የተባልነውን ውሳኔ ተግባራዊ አድርገን እገዳው እንዲነሳ እንጠይቃለን» ብለዋል፡፡
በክለቡ በኩል ክፍተት ስለመኖሩ የተጠየቁት አቶ አንበስ በሰጡት ምላሽ፤ « ክፍተት በኛ በኩል ምንም የለም ብለን ነው የምናስበው። ለምሳሌ የዲሲፕሊን ኮሚቴ በ25 ደብዳቤ ፅፎ በ26 ድረስ ምላሽ ስጡበት የሚልበት አግባብ ይህን ሁኔታ ይገልጸዋል፡፡ እንደዚያም አድርገን የእነሱ ደግሞ ውሳኔው ሁለት ወር ከሁለት ቀን በኋላ ዘግይቶ የመጣበት ሂደት ነው ያለው፤ ይሄ በራሱ የሚጋጭ ነው።
ለምን በጊዜ አልተወሰነም? ብዙ ክፍተት አለ፤ የተጠየቅነው ሌላ የተፈረደብን ሌላ ነው» ሲሉ መልሰዋል። በክለቡ ላይ በሙሉ ክፍተት የለበትም ማለት እንዳልሆነ የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፤ የዲሲፕሊን ኮሚቴው አካሄድ ግን መልካም እንዳልነበር ተናግረዋል።
አቶ አንበስ በመጨረሻም ‹‹በእርግጥ የተለያዩት ተጫዋቾች ውል ይቀራቸዋል፤ አቋማቸው ጥሩ ካልሆነ ግን ተሸክመን መጓዝ አንችልም በሚል ነው የተለያየነው፡፡ በመጨረሻ ቦርዱ ውሳኔም አሳልፏል። ክለቡ ታግዶ ይሄን ያህል መቆየት ስለሌለበት ደመወዛቸው ይከፈላቸው የሚል ውሳኔም ተላልፏል። ይህን ተፈፃሚ ለማድረግ ዝግጅት ጀምረናል። ደመወዛቸውን ከፍለን እገዳው እንዲነሳ ፌዴሬሽኑን እንጠይቃለን›› ብለዋል።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 24/2011
ዳንኤል ዘነበ