የትግራይ ክልል ሦስት ክለቦች በተባበሩት ዓረብ ኢሜሬትስ በሚካሄዱ የቅድመ ውድድር የወዳጅነት ጨዋታዎች ሊያደርጉ ነው። የአልነጃሺ ኢትዮጵያ ቱር ኤንድ ትራቭል ፕሬዚዳንት መምህር ያሲን ራጁ እንዳሉት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮኑ መቐለ ሰብዓ እንደርታ፣ወልዋሎ ዓዲግራትና ስሑል ሸሬ በዱባይ በሚከናወኑ ጨዋታዎች ላይ ይሳተፋሉ። ክለቦቹ ግጥሚያቸውን የሚያደርጉት ከነሐሴ 20 እስከ 30 ቀን 2011 ዓ.ም ሲሆን ግጥሚያዎቹን የሚያካሂዱት ከሦስት የአገሪቱ ክለቦች ጋር እንደሚሆነ ተናግረዋል።
ጨዋታዎቹ የስፖርት ቱሪዝምን ለማስፋፋት፤ወጣቶች በስፖርት ታንፀው ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራትና ልምድ ለመቅሰም ዓላማ እንዳላቸው አብራርተዋል። ጨዋታዎቹ “እግር ኳስ ለፍቅር፣ ለወዳጅትና ለጤንነት” በሚል መርህ የሁለቱ አገሮችን የህዝብ ለህዝብ ትስስር ለማጠናከር እንደሚደረግ መምህር ያሲን አስረድተዋል። ክለቦቹ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና ከባህልና
ቱሪዝም ሚኒስቴር የትብብር ደብዳቤ እንደተጻፈላቸውም አስታውቀዋል።
የወልዋሎ ዓዲግራት ክለብ ሥራ አስኪያጅ አቶ አሸናፊ አማረ በሰጡት አስተያየት ክለባቸው ከአገሪቱ ክለቦች ጋርም በሚያደርጋቸው የወዳጅነት ጨዋታዎች ድጋፍ ለማግኘት እንደሚጥር ገልጸዋል።
የትግራይ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሸን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አንገሶም ካሕሳይ ክለቦቹ አጋጣሚውን ዓለም አቀፍ ልምድ ለማግኘት፣ከባለሀብቶች ጋር ለመተዋወቅና የስፖርት አካዳሚ ለመክፈት ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ የዘገበው ኢዜአ ነው።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 24/2011