ፋሲል ከነማ ስፖርት ክለብ ሃዋሳ ከተማን በመለያ ምቶች በማሸነፍ የኢትዮጵያ ዋንጫን በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ ማሸነፉን ተከትሎ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ኮን ፌዴሬሽን ውድድር ተሳታፊ ሆኗል። የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን በ2009 ዓ.ም የውድድር ዓመት የተቀላቀለው ፋሲል በአጭር ጊዜ አህጉር አቀፍ መድረክ ላይ ተሳታፊ በመሆን ታሪክ ሠርቷል። ክለቡ በታሪካዊው የአፍሪካ ኮን ፌዴሬሽን ዋንጫ የተሳትፎ ምዕራፍ የታንዛኒያውን አዛም ክለብን ይገጥማል። የአፍሪካ እግር ኳስ ማህበር ካፍ መርሐ ግብር መሰረት በቀጣዩ ወር ነሐሴ 5 ቀን 2011 ዓ.ም በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ጨዋታውን ያደርጋል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ክለቦች ብዙም ርቀት በማይጓዙበት በአፍሪካ ኮን ፌዴሬሽን ዋንጫ የራሱን ታሪክ ለማጻፍ ክለቡ ከወዲሁ ዝግጅቱን መጀመሩን እየተናገረ ይገኛል። በተለይ ደግሞ በደጋፊ ፊት የሚያደርጉትን ጨዋታ በድል ለመወጣት ጠንካራ ልምምድ እያደረጉ መሆኑ ተሰምቷል። ለዚህም ቅድመ ዝግጅቱንም ከሐምሌ 21 ቀን ጀምሮ በውቢቷ በባህርዳር ከተማ እያደረገ ይገኛል። ቡድኑ በዝግጅቱ ውስጥ ለብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ጥሪ ከተደረገላቸው ተጫዋቾች በቀር ነባር እና አዳዲስ ፈራሚዎች ከቡድኑ ጋር በመቀላቀል ልምምዳቸውን እየሠሩ ይገኛሉ ተብሏል። ለብሔራዊ ቡድን ጥሪ የተደረገላቸው ያሬድ ባዬ፣ አምሳሉ ጥላሁን፣ ሱራፌል ዳኛቸው እና ሙጂብ ቃሲምም ከጅቡቲ ጨዋታ መልስ ቡድኑን የሚቀላቀሉ መሆኑን ከክለቡ የፌስቡክ ገጽ ያገኘነው መረጃ አመልክቷል።
አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ምንም እንኳ ከቡድኑ ጋር ለመለያየት የመልቀቂያ ደብዳቤ ያስገቡ ቢሆንም ይህን ኃላፊነት ለመወጣት ቡድኑን ለጨዋታው እያዘጋጁ መሆኑን በመረጃው ተካቷል። በክለቡ ነባር ውላቸውን ያጠናቀቁ ተጫዋቾችን በማነጋገር፤ አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደክለቡ ለመቀላቀል አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከክለቡ ቦርዶች ጋር በመሆን ሥራቸውን በተገቢው መንገድ እያከናወኑ ይገኛሉ ተብሏል። ወደ ክለቡ የሚቀላቀሉ ተጫዋቾችን እና ተመሳሳይ አዳዲስ የክለቡ መረጃዎች በሙሉ በይፋዊ የክለቡ ድህረ ገፅ እንደሚያሳውቅ ገልጿል።
በ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በመቐለ ሰባ እንደርታ ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ፋሲል ከነማ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን መድረክ ላይ ጥሩ እንቅስቃሴ ይኖረዋል የሚል ግምት ተሰጥቶታል። የታንዛኒያውን ክለብ ማሸነፍ ደግሞ የክለቡን በመድረኩ ወደፊት ላለው ግስጋሴ ወሳኝ መሆኑ ይታመናል። ተጋጣሚው ክለብ የታንዛኒያው አዛም ክለብ ከ12 ዓመታት በፊት የተመሰረተ ሲሆን በ2018/19 የውድድር ዓመት 3ኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል፡፡ ክለቡ በዚህ ጨዋታው ፋሲልን በሜዳው ለመገዳደር የሚያስችል አቅም ፈጥሮ እንደሚመጣም ተጠብቋል። የሁለቱ ክለቦች ጨዋታም በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ነሐሴ 5 ቀን በሚኖረው ጨዋታ ምላሽ የሚያገኝ ይሆናል።
ፋሲል ከነማ እና አዛም የመልስ ጨዋታቸውን በታንዛኒያ ከነሐሴ 17 እስከ 19 ባሉት ቀናት የሚያከናውን ሲሆን ይህን ዙር ካለፈም መስከረም ወር ከዛምቢያው ትሪያንግልስ እና ከብሩንዲው ቱኪንዞ ጋር ይጫወታል።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 24/2011
ዳንኤል ዘነበ