የጥንቱ ሰው የዛፍ ፍሬ እየለቀመ በጥሬው ከመመገብ ምግቡን አብስሎ መጠቀሙ የበለጠ ጥቅም ያለው መሆኑ ገብቶት እንዲሁም ራሱን ከብርድና ከጠላት ለመከላከል ድንጋይን ከድንጋይ በማጋጨት እሳትን ፈጠረ፡፡ በተናጠል ተበታትኖ ከመኖር አንድነት ኃይል መሆኑን ተገንዝቦ መንደር መስርቶ በህብረት መኖር ጀመረ፡፡
የዛፍ ፍሬ እየለቀመና እንስሳ እያደነ ከቦታ ቦታ እየተንከራተተ ከመኖር የተረጋጋ ቋሚ ኑሮ ለመምራት የሚያስችለውን የእርሻ ሥራ ጀመረ፡፡ ይህም ብቻ አይደለም የሰው ልጅ ህይወቱን ለማሻሻል ንግድ ቢጀምር፣ መንግስት ቢያቋቁም፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ በለውጥ ጎዳና በዕድገት ቢገሰግስ፣ ወደ ዘመናዊ የአኗኗር ዘይቤ ቢሸጋገር፣ በዕውቀትና በስልጣኔ ቢጎመራ፣ ኢንዱስትሪ ቢያብብ፣ ቴክኖሎጂ ቢመጥቅ፣ ዓለም መንደር ብትሆን፣ ጊዜ ቢዘምንም ሁሉም ህይወትን የማፍቀር የተሻለ ነገር የመፈለግ ውጤት ነው፡፡ እርግጥ ነው የሰው ልጅ አሁን ከደረሰበት የዕድገት ደረጃ ላይ የደረሰው በሥራው ነው፡፡
“ሰውን ሰው ያደረገው ሥራ ነው” የሚለው የቆየ ብሂልም ይህንኑ የሥራን ወሳኝነት ለማሳየት ታስቦ የተባለ ይመስላል፡፡ እኔ ግን እላለሁ ከሥራም በላይ “ሰውን ሰው ያደረገው ለህይወት ያለው ፍቅር ነው”። ምክንያቱም ሰው ስራን የፈጠረው የሚወዳትን ህይወቱን ለማስቀጠል ነው፡፡ እናም ሰው ለህይወት ባለው ጽኑ ፍቅር የተነሳ ኑሮውን ጣፋጭ ለማድረግና ሁሌም የተሻለ ህይወት ለመምራት ሥራን ፈጠረ፡፡ በዚህም በየጊዜው ዘመኑ የሚዋጀውን ሥራ እየሰራ፣ ከተፈጥሮ ጋር እየታገለ፣ የሚያጋጥሙትን ተግዳሮቶች እያሸነፈ አሁን የሚገኝበት የዕድገት ደረጃ ላይ ደርሷል። ህይወቱንም ቀድሞ ከነበረበት በእጅጉ የተሻለና ምቹ አድርጓል፡፡ መላው የሰው ልጆች ታሪክም ይኸው ነው – የህይወት ፍቅር፣ የተሻለ ህይወት የመምራት ፍላጎት፣ ሥራ! ዛሬም ቢሆን የእኛ የሰው ልጆች እጣ ፋንታ ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡
በህይወት እስካሉ ድረስ የህይወት ፍቅር አለ፤ ህይወትን ለማሳመር የተሻለ ነገር መፈለግም ምድር ላይ እስካለን ድረስ ይቀጥላል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሥራ ያስፈልጋል፡፡ ህይወትን መውደዳችንና ነገን የተሻለ ለማድረግ መፈለጋችን ተፈጥሯችን ነውና፤ ይህን የምናደርገውም “ሥራ” በተባለ ኑሮን የተሻለ ማድረጊያ መሳሪያ ነው፡፡
እናም ውድ አንባብያን በዛሬው ትዝብቴ የአንድና የሁለት ሰዎችን ብቻ ሳይሆን የብዙዎችን ህይወት የሚያሻሽል ለመሆኑ በጥናት ስለተመሰከረለት አንድ ድንቅ የሥራ መስክ(ቢዝነስ) ያለውን ዕውነታና የራሴን ምልከታ ላካፍላችሁ ወደድኩ፡፡ ውድ አንባቢያን ዓይናችሁን ሰጥታችሁኝ አብራችሁኝ ከቆያችሁ እንደ ዓይን ብርሃን በሚሊዮን ዶላር የማይገኝ ከፍ ያለ ዋጋ ታተርፋላችሁ፡፡
በአነስተኛ ወጪ ከፍተኛ ትርፍ
ይህን ቢዝነስ “በአንድ ዶላር ወጪ አምስት ዶላር ትርፍ የሚገኝበት ነገር ግን ብዙም ትኩረትን ያላገኘ አትራፊ ቢዝነስ” በማለት ቢሰራበት ከፍተኛ ትርፍ ሊያስገኝ የሚችል አዲስ የኢንቨስትመንት አማራጭ ሊሆን እንደሚችል የዓለም ባንክ በሰራው ጥናት ለባለሃብቶች ጥቆማ ሰጥቷል፡፡ በእኔ ዕይታ ይህ የቢዝነስ መስክ ለባለሃብቱ ከፍተኛ ትርፍ ሊያስገኝ የሚችል ብቻ ሳይሆን በሃገራችን ቢሰራበት የብዙሃኑን ህይወት የሚለውጥና በተለይም ከሃገሪቱ ህዝብ ከፍተኛውን ቁጥር የያዘውን ዝቅተኛ ገቢ ያለውንና ድሃውን የህብረተሰብ ክፍል ዘርፈ ብዙ ችግሮች የሚያቃልል ሆኖ ስላገኘሁት “ሰብዓዊ ቢዝነስ” ብዬ ብገልጸው የተሻለ ስሜት ይሰጠኛል፡፡
ለመሆኑ እንዲህ አዋጭ ሆኖ ሳለ በተለይም በእኛ ሃገር ብዙም ያልተሰራበት ይህ የቢዝነስ መስክ ምንድን ነው? ቢዝነሱን ለየት የሚያደርገውና ሰብዓዊ ያስባለው ምክንያትስ ምን ይሆን? በአዲስ መስመር እንመለከተዋለን፡፡
ይህ የቢዝነስ መስክ ኢትዮጵያን ጨምሮ በብዙ አፍሪካ አገሮች ብዙም ያልተሰራበትና ገና በውጥን ደረጃ ላይ የሚገኝ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የብዙዎችን ትኩረት እየሳበ የመጣው የ“ንጽህናና ጤና አጠባበቅ”(የእንግሊዝኛው አጠራር የበለጠ ግልጽ ያደርገዋል) Hyiegine and Sanitation የሚባለው ነው፡፡ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት
በዓለም ላይ የጥርስ መፋቂያ ቡርሽ ካላቸው ይልቅ የእጅ ስልክ ያላቸው ሰዎች በቁጥር ይበልጣሉ፡፡ ይህም ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑን ያሳያል፡፡ ከዘርፉ አስፈላጊነትና ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አኳያ ሲታይ መንግስትም ይሁን የግሉ ዘርፍ በቆሻሻ አወጋገድና በንጽህና አጠባበቅ ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ያላቸው ፍላጎት ዛሬም በሚፈለገው ደረጃ ላይ ደርሷል ለማለት ይከብዳል፡፡
ያም ሆኖ ግን ዘርፉ የሚያበረክተውን ሁለንተናዊ ፋይዳ በመረዳትና ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ የበለጸጉት አገራት ብዙ ርቀት ሄደዋል፡፡ እንደነ ጃፓን የመሳሰሉ አገሮች በተናቀው ቆሻሻ ላይ ኢንቨስት በማድረጋቸው የህዝባቸውን የኑሮ ሁኔታ በእጅጉ ከመለወጥ አልፈው ቆሻሻን በግብዓትነት በመጠቀም የአገራቸውን የኢኮኖሚ ዕድገት አፋጥነውበታል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በጃፓን ከእያንዳንዱ ቤት ውስጥ የሚወጣ ቆሻሻ ግዙፍ ካፒታል ለሚንቀሳቀስበት የመልሶ ጥቅም (ሪሳይክሊንግ) ኢንዱስትሪ በግብዓትነት የሚቀርብ ጥሬ ዕቃ እንጂ ተሰብስቦ የሚጣል አላስፈላጊ ውጋጅ አይደለም፡፡
በኢኮኖሚ ወደ ኋላ ወደቀሩትና ወዳላደጉት አገራት ስንመጣ ደግሞ በተቃራኒው ነው። በተለይም ሃገራችን ኢትዮጵያን ጨምሮ አህጉራችን አፍሪካን ስንመለከት እጅግ በጣም በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ምንም እንኳን የቴክኖሎጂ ዕድገታችንና የኢኮኖሚ አቅማችን የራሱ አስተዋፅኦ ቢኖረውም ለዘርፉ ያለን የተዛባ አመለካከትና የምንሰጠው ዝቅተኛ ግምት የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል፡፡
ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት
ነገር ግን የንጽህናና ጤና አጠባበቅ ዘርፉ ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶት ቢሰራበት የህብረተሰቡን የኑሮ ሁኔታ በእጅጉ ለማሻሻል የሚያስችል ከመሆኑም በላይ ለኢኮኖሚም ተጨማሪ አቅም በመሆን ለሃገራት ሁለንተናዊ ዕድገት ቁልፍ ሚና ሊጫወት የሚችል መሆኑን ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ጥናቶቹን ዋቢ በማድረግም የጽዳትና ጤና አጠባበቅን እንደ አንድ የኢንቨስትመንት አማራጭ አድርጎ መስራት ከፍተኛ ገቢ ከማስገኘቱና ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ በሌሎች ዘርፎች ላይ የሚደርሰውን ሰብዓዊና ኢኮኖሚያዊ ብክነትም በእጅጉ ለመቀነስ የሚያስችል መሆኑን አረጋግጠዋል።በዚህ ረገድ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ብቻ በቂ የሆነ የጽዳትና የንጽህና አገልግሎት ባለመኖሩ ከዚህ ጋር በተያያዘ ለሚመጡ በሽታዎች የሚወጣው ወጪ ከሰላሳ ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ መሆኑን የዓለም ባንክ ጥናት ያመላክታል፡፡
ይህም የኢትዮጵያ አጠቃላይ የዓመት በጀት ሦስት እጥፍ ይወድማል እንደማለት ነው፡፡በዚህ ምክንያት ከሚባክነው ከፍተኛ ገንዘብ ባሻገርም በንጽህና ጉድለት ምክንያት በሚፈጠሩት በሽታዎች የአምራች ኃይሉ የመስራት አቅም በከፍተኛ ደረጃ ይዳከማል፡፡ ይህም በተራው ምርትና ምርታማነትን እንዲያሽቆለቁል በማድረግ የሃገራቱን ጠቅላላ አመታዊ ምርት(ጂ.ዲ.ፒ) በሦስት በመቶ እንዲቀንስ ያደርገዋል፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገቱንም ወደ ኋላ ይጎትተዋል፡፡ ጥናቱ እንደሚለው ሁለንተናዊ የንጽህና አቅርቦትና አገልግሎትን በማሻሻል ብቻ በዓመት 74 ቢሊዮን የሚገመቱ የሥራ ቀናትን ከብክነት መታደግ ይቻላል።
የማኅበረሰብን ጤና ለማሻሻል
በሌላ በኩል የጽዳትና ንጽህና አጠባበቅ ሥራ የጤናውን ዘርፍ ለማሻሻል ዓይነተኛ ሚናን ይጫወታል። ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው የዓለም የጤና ድርጅት ያጠናው ጥናት ነው፡፡ በዚህ ጥናት መሰረት በዓለም ላይ በየዓመቱ 2000 የሚሆኑ ህጻናት ከንጽህና ጉድለት ጋር ተያይዞ በሚመጣ የተቅማጥ በሽታ አማካኝነት ያለ ዕድሜያቸው ይሞታሉ። እንዲሁም በዓለም ላይ ትልቁን የህክምና ወጪ የሚያስወጡት እነዚሁ ከንጽህና ጉድለት ጋር ተያይዘው የሚመጡ በሽታዎች ናቸው።
በያዝነው ክረምት በአዲስ አበባና በአብዛኛው የአገሪቱ አካባቢዎች የተከሰተውና የህይወትና የገንዘብ ዋጋ እያስከፈለ ያለው የኮሌራ ወረርሽኝም ዋነኛ መንስኤውና መተላለፊያው ንጽህ ናው ያልተጠበቀ የተበከለ ምግብና ውሃ ነው። ባደጉት አገራት ኮሌራ ከዓመታት በፊት የተረሳ በሽታ ሲሆን፤ እዚህ ግን አሁንም ድረስ ኮሌራ የስጋት ምንጭ ሆኖ መቀጠሉ በዘርፉ ያለንበትን ደረጃ በግልጽ የሚያሳይ ነው፡፡
በዓለም ላይ ያሉ ሆስፒታሎች አንድ ሦስተኛ
የሚሆነው አልጋቸው የተያዘው በእነኝሁ ተቅማጥና መሰል በንጽህና ጉድለት በሚከሰቱ በሽታዎች በተጠቁ ሰዎች ነው፡፡ እንዲሁም እያንዳንዱ ሰው በቂ የሆነ ንጹህ የመጠጥ ውሃና የመጸዳጃ አገልግሎት ቢኖረው ኖሮ በዓለም ላይ በየዓመቱ በጤናው ዘርፍ ከሚመደበው በጀት 12 ቢሊዮን ዶላር የሚሆነውን ገንዘብ መቆጠብ ይቻል ነበር፡፡
ይህ እንግዲህ በጽዳትና በንጽህና አጠባበቅ ሥራ ላይ ኢንቨስት ብናደርግ በጤናው ዘርፍ ብቻ ልናገኘው የምንችለው ትሩፋት ሲሆን፤ ዘርፉን ሰብዓዊ ቢዝነስ እንድለው ያደረገኝ ዋነኛው ምክንያትም ይኸው ነው፡፡ እንደምናውቀው በንጽህና ችግር የሚጠቃው በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደረውና ድሃው የህብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ በብዛትም ቢሆን አብዛኛውን የህዝባችን ቁጥር የያዘው ይኸው ክፍል ነው፡፡ አምራቹ የሃገራችን ኃይልም በብዛት የሚገኘው ከድሃው ህብረተሰብ ነው።
እንዲያውም ጉልበቱን በርካሽ ዋጋ እየተበዘበዘ፣ ሃገሪቱን የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንድትሆን ያደረገ፣ ሃብታሞችን ሃብታም ያስባለ፣ የኢኮኖሚ ዕድገቱ ዋልታና ማገር የሆነው ድሃው መሆኑ ተረሳ እንዴ? ታዲያ ይህንን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኘውን ብዙሃኑን አምራች ኃይል በንጹህ ውሃ እጥረት፣ በመጸዳጃ ቤት አገልግሎት እጦት በድህነት አረንቋ እየማቀቀ በንጽህና ጉድለት በችጋርና በበሽታ ውስጥ እየኖረ ዝም ብሎ ማየት በሰብዓዊነትና በሃገር ዕድገት ላይ መፍረድ አይደለምን?
ስለሆነም በጽዳትና የንጽህና አጠባበቅ ዘርፉ ኢንቨስት በማድረግ በአንድ ዶላር ወጪ አምስት ዶላር ትርፍ እያገኙ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኘውን የድሃውን ብዙሃኑን አምራች ኃይል ህይወት መለወጥ ከገንዘብ ትርፍም በላይ የህብረሰተብን ህይወት የሚለውጥ በመሆኑ ሰብዓዊ ቢዝነስ መባል ያንስበታል እንጂ አይበዛበትም፡፡ የችግረኛን ህብረተሰብ ህይወት እየቀየሩ ራስንም ሃብት ከማካበት ወዲያ ምን የሚያስደስት ነገር ይኖራል፡፡
ትምህርትን ለማስፋፋትና የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ
ቀላል ሚመስለው የጽዳትና የንጽኅና አጠባባበቅ የሥራና የቢዝነስ ዘርፍ ባለ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለው ነው ሲባል በምክንያት ነው፡፡ የዘርፉ ፋይዳ የሥራ እድልን በመፍጠር፣ ጤናማ ህብረተሰብን ከመፍጠርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግና ለኢኮኖሚ ዕድገት ሞተር በመሆን ብቻ አያበቃም፡፡ ትምህርትን ለማስፋፋትና የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግም ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት ጥናት እንደሚያመለክተው ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮች በቂ የንጽህና አገልግሎት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ሲሶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ልጆች በንጽኅና ጉድለት ምክንያት በሚመጡ በሽታዎች ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ አልያም ትምህርት ቤት ቢሄዱ እንኳን በክፍል ውስጥ ሆነው ለትምህርታቸው ትኩረት እንዳይሰጡ መንስኤ በመሆኑ ነው፡፡ ይህም በበኩሉ የተማረ የሰው ኃይል እንዲቀንስ የሚያደርግ በመሆኑ በሃገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ቀላል አይደለም፡፡
በሌላ በኩል ከሥርዓተ ፆታ ዕድገትና ከሴቶች ተጠቃሚነት አኳያ ስንመለከተው የዘርፉ ፋይዳ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ከላይ የተገለጸው የዩኒሴፍ ጥናት እንደሚያመለክተው ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሃራ በታች በሚገኙ በርካታ የአፍሪካ አገራት ብዙዎቹ ትምህርት ቤቶች ሴትና ወንድ ተብሎ የተከፈለ መጸዳጃ ቤት የላቸውም፡፡ ይህም ሴት ተማሪዎች በተለይም የወር አበባ በሚያዩባቸው ወራቶች ከትምህርት ቤት እንዲቀሩ መንስኤ መሆኑን ጥናቱ ያብራራል፡፡
በዚህ ሳቢያም አፍሪካ ውስጥ አንዲት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሴት ተማሪ በአራት ዓመታት የትምህርት ቆይታዋ በትምህርት ቤት ውስጥ በቂ የሆነ የመጸዳጃ አገልግሎት ስለማታገኝ 156 የትምህርት ቀናትን ከትምህርት ቤት ውጪ ታሳልፋለች፡፡ይህም ከጠቅላላው የትምህርት ህይወቷ አንድ ስድስተኛው ጊዜ መሆኑ ነው፡፡
በመሆኑም ሴት ተማሪዎች ከትምህርት ቤት ይቀራሉ፤ ትምህርታቸውን ያቋርጣሉ፤ ብዙ ልጆች ይወልዳሉ፡፡ ይህም በተራው ከኢኮኖሚ ዕድገት ጋር ላልተመጣጠነ የህዝብ ቁጥር መጨመር መንስኤ ይሆናል፡፡ በአንጻሩ ግን በጽዳትና የንጽህና አጠባበቅ ላይ ኢንቨስት ቢደረግ ከላይ የተዘረዘሩትን ችግሮች ስለሚቀርፍ የሴቶችን የትምህርት ተሳትፎ ትርጉም ባለው አሃዝ ማሳደግ ይቻላል፡፡ ይህም ለአገር ኢኮኖሚ ዕድገት የጎላ አስተዋፅኦ ያለው ሲሆን፤ በቀላሉ የሴቶችን የትምህርት ተሳትፎ በአንድ በመቶ ማሳደግ ቢቻል እንኳን የሃገርን ኢኮኖሚ በዜሮ ነጥብ 37 በመቶ ማሳደግ እንደሚቻል ዩኒሴፍ በሰራው ጥናት አረጋግጧል፡፡
ለክብርና ሥነ ልቦናዊ ከፍታ
ከዚህ ሁሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባሻገር ደግሞ ጽዳትና የንጽህና አጠባበቅ ከፍ ያለ በራስ መተማመን ለመፍጠርና በዓለም ፊት በክብርና በኩራት ቀና ብሎ ለመሄድ ያስችላል፡፡ ከተሞቻችን ጽዱ ቢሆኑ ብሔራዊ ኩራታችን ይሆናሉ፡፡ ለአብነት የአፍሪካውያን መዲና፣ የበርካታ ታላላቅ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባችን የእኛ ብቻ ሳትሆን የመላ አፍሪካውያንም መለያ ምልክት ተደርጋ ትቆጠራለች፡፡ ይሁን እንጂ አዲስ አበባችን ከስሟ፣ ከታሪኳና ከማዕረጓ ጋር የሚመጣጠን ንጽኅና የላትም በሚል በሰፊው ትታማለች፡፡ እውነትም ነው።
አሁንም ድረስ ከተማችን ላይ ቆሻሻ የትም ቦታ ይጣላል፣ በየአውራ ጎዳናው ሽንት ይሸናል፣ ደረጃውን የጠበቀ የፍሳሽ ማስወገጃ ሥርዓት የሌለ በመሆኑ በየአካባቢው ቱቦ እየፈነዳ የሚወጣው መጥፎ ጠረን የእኛንም ሆነ አክብረውን የሚመጡ ዓለም አቀፍ እንግዶቻችንን ያስቀይማል፡፡ የቆሻሻ አወጋገዳችንና የንጽህና አጠባበቃችን ሥርዓት ባለመያዙ ከከተማችን የሚወጣው መጥፎ ጠረን አካባቢያችን አይደለም እንዲሸት የሚያደርገው፤ ስማችንም ይሸታል፡፡
የአዲስ አበባ የጽዳት ጉዳይ ከዚህም አልፎ ሌላ አንድምታ አለው፡፡ ምክንያቱም ቆሻሻ ከተማ ለአፍሪካውያን መቀመጫ አይሆንምና ዋና ከተማነቱ ለእኛ ይገባናል ተብሎ ክርክር ቀርቦብንም ያውቃል። ዳሩ በንጽኅናችን ሳይሆን በአኩሪው ታሪካችን ማዕከልነታችንን አስጠብቀን ቀጥለናል፡፡ እናም በዚህ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ የአፍሪካውያን የኩራት ምንጭ የሆነችውን ታላቋን የነጻነት ከተማ አዲስ አበባን ለማስዋብ ቆርጠው መነሳታቸው ሸገርን የማስዋብ ብቻ ሳይሆን ለታላቋ አገር የሚመጥን ክብርና ስምን የማስቀጠል ጉዳይ ነውና ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡
እናም እንልዎታለን በዚህ ዘርፍ መዋዕለ ንዋይዎን ቢያፈሱና ኢንቨስት ቢያደርጉ በእርግጥም የዓለም ባንክ እንዳጠናው በአንድ ዶላር ወጪ አምስት ዶላር ትርፍ የሚያፍሱበትና በአጭር ጊዜ ውስጥ ሚሊየነር የሚሆኑበት አዋጭ ቢዝነስ ብቻ ሳይሆን የብዙሃኑን ህይወት የሚለውጡበት እጥፍ ድርብ ትርፍ የሚያገኙበት እንደሚሆንልዎት እናረጋግጥልዎታለን።
ሚሊዮን እያተረፉ የሚሊዮኖችን ህይወት የሚለውጡበት ቅዱስ ቢዝነስ ነውና እንዲሞክሩት በነባራዊው ዓለም ያለውን እውነታና በግንዛቤያችን የታዘብነውን ምልከታ ዝቅ ብለን በትህትና አቀረብንልዎት፡፡ መልካም ዕድል!
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 24/2011
ይበል ካሳ