ለመንደርደሪያ አንድ ጉዳይ በወፍ በረር ላስቃኛችሁ።ጉዳዩ ከክልል ጀምሮ በየደረጃው ባሉ ፍርድ ቤቶች ክርክር ተደርጎበት በመጨረሻ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ሐምሌ 30 ቀን 2007 ዓ.ም. ተቋጭቷል።ነገሩ እንዲህ ነው- ወይዘሮዋ ከሟች ባለቤታቸው ጋር ይዘውት የቆዩትንና የአባታቸው ወራሾች የሆኑትን የልጆቻቸውን የጋራ ይዞታ መሬት ለአንድ ባለሃብት ይሸጡላቸዋል።
የኋላ ኋላ ግን ሻጭ መሬቱን የሸጥኩለት አግባብቶኝ ነው በሚል ሰበብ ውል እንዲፈርስላቸው ገዥውን ባለሃብት ከስሰው ፍርድ ቤት አቆሟቸው። ጉዳዩም በሰበር ውሳኔ የመጨረሻውን እልባት አገኘ።በሰበር ችሎቱ የተሰጠው ውሳኔ ለዛሬው ጽሁፋችን ማሳያ ስለሚሆን ወደኋላ ላይ የምንመለስበት ሆኖ ከውለታ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ሕጉ ምን ይላል የሚለውን እንቃኝ።
ባለፉት ሁለት ተከታታይ ሳምንታት “ውል ለመዋዋል ችሎታ የሌላቸው ሰዎችና የሚያደርጓቸው ውሎች ውጤት” እንዲሁም “የተዋዋዮች የፈቃድ ጉድለት – ስህተት፣ ተንኮል፣ መገደድ እና መጎዳት” በሚሉ ርዕሶች አንድ ውል በሕግ ፊት ዋጋ እንዲኖረው ከሚያደርጉ አራት መሰረታዊ መለኪያዎች ሁለቱን ተመልክተናል። በዚህኛው ጽሁፋችን ደግሞ ሶስተኛው መለኪያ የሆነውን የውለታን ጉዳይ ሕጋዊነትና ለሞራል ተቃራኒ አለመሆንን እንዳስሳለን።
ስለ ውለታ ጉዳይ የሚመለከተው የፍትሐብሔር ሕጉ አንቀጽ 1711 በግልጽ እንዳሰፈረው ሕግ ከወሰናቸውና ከከለከላቸው ነገሮች በቀር ተዋዋዮች ሁሉ የሚዋዋሉበትን ጉዳይ እንደመሰላቸው የመወሰን መብት አላቸው።ስለተዋዋይ ወገኖች የመዋዋል ችሎታ ስናነሳ “ችሎታ” የሚል ፍሬ ነገር እንዲሁም የተዋዋይ ወገኖችን ፈቃድ ስንዳስስ ደግሞ “ፈቃድ” የተሰኘ መሰረታዊ አነጋገርን በተመለከተ ሰፊ ግንዛቤ መጨበጣችን ይታወሳል። ከዚህኛው ድንጋጌ ደግሞ “ውለታ/የሚዋዋሉበት ጉዳይ” የሚል ፍሬ ነገር እናገኛለን።
ፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመ “የኢትዮጵያ የውል ሕግ መሰረተ ሃሳቦች” በተሰኘው መጽሃፋቸው “የውለታ ጉዳይ”ን (Object of a Contract) ሲያብራሩ ይህ ሐረግ ለውል መመስረት ምክንያት የሆነውን የግራ ቀኙን ተነጻጻሪ ግዴታና መብት የሚመለከተውን ተግባር የሚያሳይ ነው ይላሉ።በሕጉ እንደተመለከተውም ይህ የውለታ ጉዳይ አንደኛው ወገን ለሌላኛው ተዋዋይ በአንድ ነገር ላይ ያለውን መብት ለመስጠት ወይም አንድ ነገር ለማድረግ ወይም ማድረግ የሚችለውን ነገር ላለማድረግ (ከማድረግ ለመቆጠብ) የሚስማማበት ጉዳይ ነው።ሌላኛው ወገንም በበኩሉ እንዲሁ የመስጠት፣ የማድረግ ወይም ያለማድረግ ተነጻጻሪ ግዴታ ውስጥ ይገባል።
የውለታ ጉዳይን በአጭርና ግልጽ ምሳሌ ለማስረዳት በአንድ የመኪና ሽያጭ ውል ውስጥ ገዥ የተስማሙበትን ዋጋ የመክፈል ግዴታ ያለበት ሲሆን፤ ሻጭ ደግሞ እቃውን የማስረከብ ግዴታ አለበት ማለት ነው።በዚህ ግንኙነት ውስጥ ታዲያ ሻጭ ከገዥው ገንዘቡን የመጠየቅ መብት አለው፤ ገዥም በበኩሉ መኪናውን
ለመረከብ የመጠየቅ መብት አለው። በዚህ መነሻ ተዋዋዮቹ ሁለቱም ባለገንዘብ እና ባለዕዳ ይሆናሉ።በጥቅሉ የመኪና ሽያጩ ጉዳይና በስምምነ ታቸው ውስጥ ግራ ቀኙ የሚኖራቸው መብትና የሚወስዱት ግዴታ የውለታ ጉዳይ ነው።
ተለይቶ የታወቀ፣ ሊፈጸም የሚችል፣ ሕግና ሞራልን ያልተቃረነ የውለታ ጉዳይ
የውለታ ጉዳይ የተዋዋዮች የፈቃድና የመዋዋል ነጻነት ዓይነተኛ ማሳያ ነው። ይሁንና ተዋዋዮች የሚዋዋሉበትን ጉዳይ እንደመሰላቸው የመወሰን መብታቸው ፍጹም ባለመሆኑ ሕጉ ራሱ የነጻነታቸውን ገደብ አስቀምጧል – “ሕግ ከወሰናቸውና ከከለከላቸው ነገሮች በቀር” ሲል።በመሆኑም የውለታ ጉዳይ በትክክልና በበቂ ሁኔታ የተገለጸ (ተለይቶ የታወቀ)፤ ሊፈጸም የሚችል እንዲሁም ለሕግ ወይም ለመልካም ጠባይ (ለሞራል) ተቃራኒ ያልሆነ ሊሆን እንደሚገባው በፍትሐብሔር ሕጉ ከቁጥር 1714 እስከ 1716 ተመልክቶ እናገኘዋለን። ስለዚህ የውለታ ጉዳይ በእነዚህ ሶስት መስፈርቶች የሚለካ መሆን አለበት።
የመጀመሪያውን የውለታ ጉዳይ መለኪያ እንየው። የውለታ ጉዳይ በትክክልና በበቂ ሁኔታ የተገለጸ (ተለይቶ የታወቀ) መሆን እንዳለበት በሕጉ ተመልክቷል። ከዚህ የምንረዳው ተዋዋዮች የሚዋዋሉበትን ጉዳይ መግለጽ ብቻውን በቂ እንዳልሆነ ነው።የመኪና ሽያጭ ለማድረግ ተስማምተናል ማለታቸው ብቻውን ውላቸውን ምሉዕ አያደርገውም።ከላይ በተጠቀሰው የሽያጭ ስምምነት ውስጥ የሚሸጠውን መኪና ዓይነት፣ ዋጋ፣ የአከፋፈልና የርክክብ ስርዓት፣ የውል መፈጸሚያ ቦታንና ሌሎች ዝርዝር የውለታ ጉዳዮችን በተመለከተ ሃሳብ ለሃሳብ ተስማምተው በግልጽ ማስቀመጥ አለባቸው።
ግራ ቀኙ ያለባቸውን መብትና ግዴታ ወስነው በውላቸው ውስጥ በግልጽ ማስቀመጥ አለባቸው።ከዚህ ውጭ ግን ተዋዋዮቹ ወይም አንዳቸው የገቡት ግዴታ በትክክልና በሚበቃ ሁኔታ ካልተገለጸ ውሉ ፈራሽ መሆኑ አይቀሬ ነው።ውል አድራጊዎች የተዋዋሉበት ጉዳይ በትክክልና በሚበቃ አኳኋን ባልተገለጸ ውል ምክንያት ተዋዋዮች ተካሰው በፊቱ የቀረቡለት ዳኛም ቢሆን እንዲህ ያለውን ውል “ተዋዋዮች እንደዚህ ሲሉ የገለጹት ይህንን ለማለት አስበው ነው፤ እንዲህ እንዲህ ማለታቸው እንደዚህ ማለታቸው ነው ወዘተ” በማለት ውል በመተርጎም ሰበብ ውል ሊፈጥር እንደማይችል በሕጉ በግልጽ ተደንግጓል።
ያም ሆኖ ሕጋችን ከላይ ለተቀመጠው ድንጋጌ ልዩ ሁኔታ ሳያስቀምጥ አላለፈም። ውሎች አስገዳጅነታቸው በውሎቹ በተነገረው ጉዳይ ላይ ብቻ ሳይሆን ከልማዳዊ አሰራር፣ ከፍትህ (ርትዕ) እና ከቅን ልቡና አንጻርም የውሎች ጉዳይ መቃኘት ይኖርበታል ይላል የፍትሐብሔር ሕጉ ቁጥር 1713። ውሎች በተዋዋዮች መካከል ሊኖር የሚገባውን የቅንነትና የመተማመን ግንኙነት መሰረት በማድረግና በጉዳዮቹ ውስጥ ያለውን ልማዳዊ ስርዓት በመከተል በቅን ልቡና ሊተረጎሙ
ይገባል ሲልም የሕጉ ቁጥር 1732 ይበልጥ ያጠናክረዋል።
በውሉ ላይ በግልጽ ባይሰፍርም እንኳን የመኖሪያ ቤት የተከራየ ሰው ያለ አከራዩ ፈቃድ ቤቱን ለሱቅ፣ ለማምረቻ ወርክሾፕ አልያም ለሆቴል አገልግሎት ሊጠቀምበት አይገባውም። ይህ ከነገሩ ልማዳዊ አሰራር አንጻር ሲመዘን ተዋዋዮች ከማድረግ ለመቆጠብ የሚጣልባቸው ግዴታ ነው ማለት ነው። መልካም ስምና ዝና ያተረፈበትን ቢዝነሱን (የንግድ መደብሩን) የሸጠ ሰው ከሸጠው የንግድ መደብር አጠገብ ተመሳሳይ ቢዝነስ ያለመክፈት ግዴታ አለበት።
ይህም የፍትህ እና ርትዕ ጉዳይ በመሆኑ በውላቸው በግልጽ ባይሰፍርም ሻጩ ከማድረግ የመቆጠብ ግዴታውን በመጣሱ ፍርድ ቤቶች ያልተገባ የንግድ ውድድርን ለመታደግ ሲሉ የውሉን መፍረስ ሊወስኑ ይችላሉ።ከቅን ልቡና አንጸርም የአንድን አምራች እቃ ለመሸጥ የተስማማ ተቀጣሪ የቀጣሪውን ደንበኞች የሌላ አምራችን ምርት እንዲገዙ ቢያግባባ ይህ ድርጊቱ ለቅን ልቡና ተቃራኒ ይሆናል።እነዚህ ማሳያዎች የውለታ ጉዳይ ከልማዳዊ አሰራር፣ ከፍትህ እና ከቅን ልቡና አንጻርም መታየት እንዳለበት የሚያመለክቱ ናቸው፡፡
ሁለተኛው የውለታ ጉዳይ መለኪያ ሊፈጸም የሚችል መሆኑ ነው።የውል ጉዳይ ሊፈጸም የሚችል መሆን ይገባዋል።ሕጉ እንደሚለው ተዋዋዮቹ ወይም አንዱ ወገን ሊፈጸም በማይቻል ነገር ላይ የተዋዋለ እንደሆነና የተዋዋሉበትም ነገር የማይቻልና የማይሞከር ጠባይ ያለው ሆኖ ከተገኘ ውሉ ፈራሽ ይሆናል። አንድን የውለታ ጉዳይ ሊፈጸም የማይችል ነው የሚባለው ደግሞ ተዋዋዮች ውል ከገቡበት ጉዳይ (ነገር) ዓይነት ወይም ከባህርዩ አንጻር ተመዝኖ ነው።
ባለቤቱ መረጃው ስላልነበረው ገደል ገብቶ ከጥቅም ውጪ የሆነውን መኪናውን ለመሸጥ የሚያደርገው ውል ሊፈጸም በማይችል ነገር (የውለታ ጉዳይ) ላይ የተደረገ ስምምነት ነው።ጣናን በዋና ለማቋረጥ የሚደረግ ውል ደግሞ የማይቻልና የማይሞከር ጠባይ ባለው ነገር (የውለታ ጉዳይ) ላይ የተደረገ ውል ማሳያ
ይሆናል። በመሆኑም ተዋዋዮች በሕግ ፊት ዋጋ የሚያወጣ ውል እንዲኖራቸው ውሉን ከማሰራቸው በፊት የሚዋዋሉበት ጉዳይ የሚፈጸም መሆኑን ጠንቅቀው ማወቅ ይገባቸዋል ማለት ነው፡፡
ሶስተኛው የውለታ ጉዳይ መለኪያ ለሕግ ወይም ለመልካም ጠባይ (ለሞራል) ተቃራኒ ያልሆነ ሲሆን ነው።ሁለቱም ተዋዋዮች ወይም አንዱ ወገን የገቡበት ግዴታ ሕግን ወይም መልካም ጠባይን የሚቃረን ከሆነ ውሉ ፈራሽ ስለመሆኑ ሕጉ ይደነግጋል።
በቅድሚያ አንድ የውለታ ጉዳይ ለሕግ ተቃራኒ የሚሆንበትን ሁኔታ በዝርዝር እንመልከት። ሕግ የአንድን ማህበረሰብ የኢኮኖሚ፣ የታሪክ እና የማህበራዊ አቋሞችን እንዲሁም የግለሰቦችንና የመንግስታትን ባህርይ የሚቀርጽ ሁነኛ መሳሪያ ነው። በመሆኑም ይህን አድርጉ፤ ያንን አታድርጉ እያለ ያስቀምጣል ሕግ።
በዚህ መነሻ አንድ የውል ጉዳይ በህግ አታድርጉ በሚል ከተቀመጠው ክልከላ አልያም አድርጉ ተብሎ ከተቀመጠው ግዳጅ በተቃራኒው ሆኖ ከተገኘ ሕገ ወጥ ነው ማለት ነው። እንዲህ ዓይነቱ ውል ታዲያ ከመጀመሪያውኑ ፈራሽ ነው።
የፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት በየካቲት 7 ቀን 2003 ዓ.ም. በሰጠው ውሳኔ ላይ ሕገ ወጥ ውልን በተመለከተ ጠቃሚ ማብራሪያ ሰጥቷል። ችሎቱ እንዳተተው ሕገ ወጥ ውል ማለት በሕግ እንዲደረግ ያልተፈቀደ የህግ ክልከላ ያለበት ውል ማለት ነው።ተዋዋዮቹ የተዋዋሉበት መሰረታዊ ጉዳይ ዓላማውና ይዘቱ ተዋዋዮቹ ስምምነት በማድረግ መብትና ግዴታ እንዲፈጥሩበት በሕግ ያልተፈቀደ ወይም ክልከላ የተደረገበት ሆኖ ሲገኝ ነው ሕገ ወጥ ውል የሚሰኘው።
የዚህ ዓይነቱ ውል በሕግ ፊት እንደሌለ የሚቆጠርና ምንም ዓይነት ህጋዊ ውጤት የማያስከትል ነው።ውሉንም በማናቸውም መንገድ ማስተካከል የማይቻል ስለሆነ ከጅምሩ ውሉ እንዳልተደረገና እንደሌለ ይቆጠራል።
በዚህ ጽሁፍ መግቢያ ላይ ወዳነሳሁት የመሬት ክርክር ጉዳይ ልመልሳችሁ።በመሬቱ ባለይዞታ ወይዘሮና በባለሃብቱ መካከል የተደረገው የውል ጉዳይ የመሬት ሽያጭ ነው።በኢፌዴሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 40/3 እንደተመለከተው ደግሞ መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ንብረት ነው።ስለዚህ መሬትን ለመሸጥም ሆነ ለመለወጥ መዋዋል ከመሰረቱ ሕገ ወጥ የውለታ ጉዳይ ነው። በዚህ መነሻ ውሉ ሕገ ወጥና ፈራሽ ይሆናል።ለዚህም ነው የሰበር ችሎቱ በወይዘሮዋና በባለሃብቱ መካከል የተደረገውን የመሬት ሽያጭ ውል እንዲፈርስ ውሳኔ የሰጠው።
ሌሎች የሕገ ወጥ ውሎችን ማሳያዎች እንጥቀስ። ማንኛውም ሰው በባርነት ወይም በግዴታ አገልጋይነት ሊያዝ እንደማይችልና ለማንኛውም ዓላማ በሰው መነገድ የተከለከለ ስለመሆኑ በህገ መንግስቱ ሰፍሯል።በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 596 እንደተደነገገውም ሰውን አገልጋይ ማድረግና በሰው መነገድ እስከ 20 ዓመት ጽኑ እስራት የሚያስቀጣ ከባድ ወንጀል ነው።ከዚህ በተቃራኒው ግን ለግዴታ ስራ ወይም ለባርነት የውል ስምምነት ማድረግ ከመሰረቱ ሕገ ወጥ ውል ነው።
በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 18 ላይ ማንኛውም ሰው በሕይወት እያለ በሕክምና ካልተፈቀደ በስተቀር አካሉን በሙሉ ወይም በከፊል አሳልፎ ለመስጠት የሚያደርገው የውል ግዴታ ዋጋ የሌለው ስለመሆኑ ተደንግጓል። በመሆኑም ኩላሊቴን ወስደህ ገንዘብ ስጠኝ በማለት ግዴታ መግባት ሕገ ወጥ የውል ጉዳይ ነው።ለሕዝብ የጤና ደህንነት ሲባል ወደ አገር እንዳይገቡ፣ እንዳይመረቱ፣ እንዳይዘዋወሩ ወይም እንዳይሸጡ ክልከላ የተደረገባቸውን ምርቶች በተመለከተ የሚደረግ ስምምነትም በተመሳሳይ ሕገ ወጥ ነው።
አንድ የውለታ ጉዳይ ሕግን የሚቃረን ከሆነ ፈራሽ እንደሚሆን ሁሉ ለመልካም ጠባይ (ለሞራል) ተቃራኒ ከሆነም ተመሳሳይ እጣ ይደርሰዋል።የውለታ ጉዳይ ለሕግ ተቃራኒ ነው የሚባለው በስራ ላይ ካሉት የአገሪቱ ሕጎች አንጻር ተመዝኖ ሕገ ወጥ የሆነ የማድረግ ወይም ያለማድረግ ግዴታን በተዋዋዮች ላይ ያስቀመጠ እንደሆነ ነው።
ይሁንና አንድ የውል ጉዳይ ከሞራል ተቃራኒ ነው ለማለት መለኪያው ቀላል እንደማይሆን መገመት አያዳግትም።ምክንያቱ ደግሞ ሞራል (መልካም ጠባይ) የሚባለው ከሰው ሰው፣ ከማህበረሰብ ማህበረሰብ፣ ከሐይማኖት ሐይማኖት የተለያየ አተያይና አንድምታ ያለው መሆኑ ነው።
በዚህ መነሻ የአንድን ውል ሞራላዊነት ወይም ኢሞራላዊነት የመወሰን ጉዳይ ለዳኞች የሕሊና ሚዛን የተተወ ነው።እናም አንድ የውል ጉዳይ ሞራላዊ/ኢሞራላዊ መሆኑ የሚለካው ከማህበረሰቡ ወግና ልማድ፣ ባህልና እምነት እንዲሁም ከአካባቢውና ከጉዳዩ ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ነው ይላሉ ፕሮፌሰር ጆርጅ ችችኖቪች Formation and Effects of Contracts in Ethiopian Law በተሰኘው መጽሃፋቸው በሰጡት ሰፊ ትንታኔ።
ስለዚህ አንድ የውል ጉዳይ ክብረ ነክ፣ ጨዋነት የተጓደለበት፣ አሳፋሪና አስነዋሪ ድርጊትን የያዘ ከሆነ ከመልካም ጠባይ ተቃርኗል ማለት ይቻላል።ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆኑት በወንጀል ሕግ በመልካም ጠባይ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ተብለው የተቀመጡ (አስገድዶ መድፈር፣ ግብረ ሰዶም፣ አመንዝራነት ወዘተ) ድርጊቶች ናቸው።ስለዚህ አንድ የውለታ ጉዳይ እነዚህን አድራጎቶች የተመለከተ ከሆነ ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ ነው ለማለት ይቻላል።
በአጠቃላይ የውለታ ጉዳይ ሕጋዊ አለመሆንና ከሞራል ማፈንገጥ ውጤቱ በተዋዋይ ወገኖች ላይ የማይተካ ጉዳትን ያደርሳል።ከሁሉም በላይ በችሎታ ማጣት አልያም በፈቃድ ጉድለት የተደረገ ውል የይሰረዝልኝ ጥያቄ ሊቀርብ የሚችለው ከተዋዋዮቹ ጉድለቱ የሚመለከተው ወገን ሲሆን፤ የውል ጉዳይ ሕገ ወጥ ከሆነ ግን ውሉን የይሰረዝልኝ ጥያቄ የማቅረብ መብት ያለው ከተዋዋዮቹ አንዱ ብቻ ሳይሆን ጥቅም ያለው አካል (ባለገንዘብ፣ ወራሽ…) ሊሆንም ይችላል።ይህ የሚያሳየው ሕገ ወጥ ውል ከጅምሩም እንደተደረገ የማይቆጠር ብሎም አንዳችም ውጤት የሌለውና ፍጻሜውም የማያምር መሆኑን ነው።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 24/2011
ከገብረክርስቶስ