በሲዳማ ዞን ውስጥ የተፈፀመው የሰሞኑ ቅስም ሰባሪና አሳዛኝ ክስተት ይህንን ጽሑፍ እንድጽፍ ምክንያት ሆኖኛል። በአጠቃላይ የደቡብን ክልል በተለየ ሁኔታ ደግሞ የሲዳማ ዞን አካባቢዎችን የተወላጆቹን ያህል ባይሆንም በሚገባ ለማወቅና ለመረዳት በርካታ ዕድሎች አጋጥመውኛል።
ለዓመታት ያገለገልኩበት የቀድሞ መ/ቤቴ በሚሰጠኝ የተግባር ተልዕኮ አማካይነት በተደጋጋሚ ጊዜያት በሲዳማ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች ውዬ ለማደር ብቻ ሳይሆን ለቀናትና ለሳምንታት ያህል እየቆየሁ የዚያን መልካም ሕዝብ የፍቅር መስተንግዶ ተንበሽብሼበታለሁ።
ከዋናው የተልዕኮዬ ስምሪት በተጨማሪም የሲዳማ ብሔር ባህልና ነባር ዕውቀቶች እጅግ ይመስጡኝና ይማርኩኝ ስለነበር ወቅትና ጊዜ እያመቻቸሁ በራሴ ጊዜ በዞኑ ውስጥ በሚገኙ በአብዛኛዎቹ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ውስጥ ዘልቄ እየገባሁ ከዕድሜ ጠገብ አዛውንቶች ጋር ተወያይቻለሁ፤ ምርቃታቸውንም ተቀብያለሁ። በኋለኛው ዓመታት በባህል ጉዳይ ላይ ይበልጥ ጥናት እንዳደርግ ያገዘኝና የረዳኝ ይሄው ተሞክሮዬ ሳይሆን አይቀርም።
በሲዳማ ውስጥ ያከናወንኳቸው የጥናትና የምልከታ ውጤቶቼ ይነስም ይብዛ በግል ካሳተምኳቸው መጻሕፍት በአንደኛው ውስጥና በወቅቱ እመራው በነበረው መምሪያ ውስጥ ይታተም በነበረ ወርሐዊ መጽሔት ውስጥ በተቀነጫጨበ መልኩም ቢሆን ምስክርነቴን በህትመት ውጤቶች ላይ ለማስነበብ ሞክሬያለሁ። የእኔ የግል ጥረት እንዳለ ሆኖ ምናልባትም ከእኔም በተሻለ ሁኔታ በሲዳማ ዞን ውስጥ ደጋግሞ በመመላለስ እጅግ አመርቂ ጥናቶችን በማድረግ እንተጋገዝ የነበረውን የሥራ ባልደረባዬንና ጓደኛዬን ደራሲ ወንድዬ ዓሊን ባላመሰግን የህሊና ተወቃሽ እሆናለሁ።
ከእነዚህ ጥረቶቼ በተጨማሪም “በድንበር ዘለል ባህሎች” ላይ ትኩረት በማድረግ የወንጌል ሚሲዮናዊያንና የደቡቡን የሀገራችንን ክፍል እንደ መነሻ ወስጄ በውጭ ሀገር በትምህርት ላይ እያለሁ በሠራሁት የሁለተኛ ዲግሪ ማሟያ የጥናት ጥራዝ ውስጥም ስለ ሲዳማ ሕዝብ ባህሎች አንዳንድ መሠረታዊ ጉዳዮችን ለመጠቃቀስ ሞክሬያለሁ።
የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ከሰባት ዓመታት በፊት ሰላሳ ለሚሆኑ የማኅበሩ አባላት “ከቡስካ በስተጀርባ” በሚል መሪ ርዕስ አዘጋጅቶ በነበረው በደቡብ ኢትዮጵያ ውስጥ በተደረገው የጥበብ ጉዞ ወቅትም በሲዳማ ዞን ውስጥ በተለይም በይርጋለም ከተማና አካባቢዋ በተገኘንበት ወቅት በብሔረሰቡ አባላትና በተለይም በአንጋፋ አባቶችና እናቶች የተደረገልንን አቀባበል አልዘነጋውም። ከዞኑ የጎሳ መሪዎች ጋር የነበረን ቆይታም ትልቅ ትምህርት ያገኘንበትን አጋጣሚ ፈጥሮልን አልፏል።
ከዚህ ሁሉ ተሞክሮዬ የገበየሁት ትልቁ ዕውቀት የሲዳማ ብሔር በባህላዊ ሀብቶች የበለፀገ፣ ለታላላቅ አባቶች ክብር ያለው፣ እንግዳ ለመቀበልና ለማስተናገድ የሚሽቀዳደም፣ ርዕስ በርዕስ በመከባበርና በመደማመጥ በአርዓያነት የሚጠቀስ መሆኑን ነው። ማሕበረሰቡ የሚመራበት ባህላዊ መዋቅር ለዘመናዊውና ብዙ ለሚባልለት የፈረንጁ “ዲሞክራሲ” እንኳን ሳይቀር ትምህርት ይሆናል ቢባል ማጋነን አይሆንም።
ያለመታደል ሆኖ ባህር ተሻግሮ ለሚመጣ ቁሳቁስ ብቻም ሳይሆን ለአስተሳሰብና ለፍልስፍናውም ጭምር ቶሎ እጅ ሰጥተን ተገዢ የመሆን ድካም ተጭኖን እንጂ ከሲዳማና መሰል የሀገራችን ክፍሎች የሚቀዱ ሕዝባዊ እሴቶቻችንን በአግባቡ ብናጎለብት ኖሮ ብዙዎቹ የሀገራችን ችግሮች ዛሬ ገዝፈውና ሥር ሰደው አሳር ባላበሉን ነበር።
እነዚህን መሰል የሲዳማ ነባር እሴቶችና ባህሎች በፍፁም ነፋስ ይገባባቸዋል ተብሎ በማይገመት ሁኔታ ሰሞኑን ተነቃንቀውና አቅም አጥተው ያ ሁሉ ጥፋትና ውድመት ሲደርስ በግሌ ደንግጫለሁ፤ ተሳቅቄያለሁ፤ ተሸማቅቄያለሁ። ድርጊቶች በሲዳማ ሕዝብ መሃል ስለመፈጠራቸውም ተጠራጥሬያለሁ።
የሲዳማ ብሔር ሶንጎ (ሸንጎ) በመባል የሚታወቅ ጠንካራ የማሕበራዊ የዳኝነት ሥርዓት ዘርግቶ ለዘመናት ሲተዳደርበት መኖሩ ይታወቃል። ሶንጎ (ሸንጎ) ከላይ እስከ ታች የተዋቀረ የባህላዊ ዳኝነት ሥርዓት ነው። የሶንጎ የመጀመሪያ ደረጃ ኦሉ ሶንጎ በመባል የሚታወቅ ሲሆን፤ ትኩረት የሚያደርገውም በዋነኛነት በቤተሰብና በቅርብ ቤተዘመዳማቾች መካከል መለስተኛ ችግርና ያለመግባባት ሲፈጠር እርቅና ሰላም እንዲወርድ የሚደረግበት ባህላዊ የሸንጎ ሥርዓት ነው።
ከቤተሰብ ከፍ ብሎ በመንደሮች በተሰባሰቡ ማሕበረሰቦች (ኮሚዩኒቲ) መካከል ችግር ሲፈጠር ደግሞ የመፍቻ ዘዴው አይዱ ሶንጎ በሚል ስያሜ የሚታወቀው ሸንጎ ይቆማል። ሦስተኛውና ቦሰቴ ሶንጎ ደግሞ ከሁለተኛው ከፍ ባሉ ጎሳዎች መካከል ችግር ሲፈጠር መፍትሔ የሚሰጥ ሸንጎ ነው። አራተኛውና ከፍተኛው የሲዳማ ብሔር የሶንጎ ደረጃ ጋሬታ ሶንጎ በመባል ይታወቃል። ስልጣኑም የዚያኑ ያህል ከፍ ያለ ነው።
ከላይ በተዘረዘሩት ባለ አራት እርከን ሶንጎዎች (ሸንጎዎች) ውስጥ ከፍተኛውን ሚና የሚጫወቱትና የዳኝነቱን ሥርዓት የሚመሩት ሞቴ፣ ጋሮ፣ ወይንም ጌሎ በሚባሉና በተለያዩ ስሞች የሚጠሩ የየጎሳው መሪዎች ናቸው። የሲዳማ የጎሳ መሪዎች የሚጠበቅባቸው የዕለት ተዕለት ችግሮችን እንዲፈቱ ብቻ ሳይሆን ጠንካርና ኮስተር ባሉ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና መንፈሳዊ ጉዳዮች ላይም ስልጣን አላቸው።
እነዚህን መሰል የሲዳማ ብሔር ባህላዊና አስተዳደራዊ የዳኝነት ሥርዓቶች ለዘመናት ሲሰራባቸውና ሲተገበሩ ስለኖሩ የብሔሩ አባላት ያከብሯቸዋል፣ ይታዘዟቸዋል፣ ያለማንገራገርም ይተገብሯቸዋል። ችግሮችና ግጭቶች ሲፈጠሩም “ሀላሌ” በመባል በሚታወቀው የሐቅና የእውነት ማፈላለጊያ ጥበብ እየተጠቀሙ ፍትሕ ይከበራል።
አጥፊ ይቀጣል። ተበዳይም ይካሳል። ይህንን ሥርዓት የሚጥስና ላለማክበር የሚያንገራግር ግለሰብም ሆነ ቡድን የሚደርስበት ማሕበራዊ ቅጣት ከፍ ያለ ነው። ሤራ በመባል የሚታወቀው ቅጣት የማሕበራዊ፣ የኢኮኖሚያዊና የመንፈሳዊ ቅጣቱ ብቻ ሳይሆን የሚያስከትለው ሥነ ልቦናዊ ቀውስም በቀላሉ የሚሽር አይደለም።
በሲዳማ ብሔር የሶንጎ (ሸንጎ) አካሄድ ላይ የሚተገበሩ በርካታ ባህላዊ ሥርዓቶች ቢኖሩም በዚህ ጽሑፍ ውስጥ አጽንኦት ለመስጠት የሚሞከረው “አፊኖ” (Affino) በመባል በሚታወቀው ባህላዊ እሴት ላይ ይሆናል። “አፊኖ” በሶንጎ ውይይት ወቅት በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ላይ ተሰብሳቢው ያለመሸማቀቅና ያለ ፍርሃት በነፃነት ሃሳቡን እንዲገልጽ የሚፈቅድ ባህላዊ ሥርዓት ነው።
“አፊኖ” በጥሬ ትርጉሙ – “ሰማችሁ ወይ?” እየተባለ በሶንጎው ላይ የሚታደሙት ተሳታፊዎች የሚጠያየቁበት ጥበባዊ አካሄድ ነው። ተሰብሳቢው “ሰማችሁ ወይ?” እየተባባለ የሚጠያየቀው ለጉዳዩ ትኩረት ለመስጠት፣ ልብ ተቀልብ ሆኖ ለመደማመጥ፣ ክርክሩ (ውይይቱ) ፈርጁን እንዳይለቅና ከስሜታዊነት ለመጠበቅና እንዳስፈላጊነቱም ተገቢውን ጊዜ ወስዶ ነገሩን በአግባቡ ለማብላላትና ለማሰላሰል እንዲረዳ ጭምር ነው።
በሲዳማ ብሔር ታሪክና ባህል ላይ ያተኮረው መጽሐፍ ስለ አፊኖ የሰጠው ድንጋጌ እንደሚከተለው ይነበባል። “በሲዳማ ባህል ሰዎች ሲናገሩ “አፊኒ” ሳይባል ጣልቃ አይገባም። በሌላ መልኩ አንድ የተበደለ ሰው ማናቸውንም ዓይነት እርምጃ ከመውሰዱ አስቀድሞ በአጠገቡ ላሉት ወይንም ለታላላቆቹ “አፊኒ” በማለት ማስታወቅ ባህላዊ ግዴታው ነው።
ይህንን ሳያደርግ በግብታዊ እርምጃ የወሰደ እንደሆነ ባህላዊ ሤራ (ቅጣት) ይጣልበታል። “አፊኒ” እውነትን ከማፈላለግና ከፍትሕ አሰጣጥ ጋር በእጅጉ ይተሳሰራል። እውነትን በማጣራትና በማረጋገጥ ወደሚቀጥለው እርምጃ ለመራመድ “አፊኒ” በጉዳዩ ላይ እውቀት ያለው ማንኛውም ሰው መረጃ እንዲሰጥ ሰፊ ዕድል ስለሚሰጥ ነው።”
በባህላዊ የአስተዳደርና የዳኝነት ሥርዓት የበለፀገውና የከበረው የሲዳማ ሕዝብ ከዚህ በላይ ከተዘረዘሩትም በላቀ ቁጥር በርካታ ባህላዊ እሴቶችን አክብሮና ጠብቆ በመኖሩ የሚመሰገን ነው። በማሕበረሰቡ ውስጥ ግጭትና ሁከት እንዳይከሰትም ሆነ ከተከሰተ በኋላ ነገሮችን ለማረጋጋትና ወደ ቀድሞ ሰላማዊ ሁኔታ ለመመለስ የሚደረገው ባህላዊ ሥርዓት “ሲጮ” በመባል ይታወቃል። ውሳኔ ያገኙ ችግሮች፣ ግጭቶችና ሁከቶች በእርቅ እንዲያልቁና ዳግመኛ እንዳያገረሹ ቃል ኪዳን የሚገባበት ሥርዓት ደግሞ “ጎንዶሮ” በመባል ይታወቃል።
“ቀጌ ፊጫ”ም ሌላኛው ባህላዊ ሥርዓት ነው። “አንድ ሰው ሆን ብሎ የሌላውን ነፍስ ያጠፋ እንደሆነ በባህሉ መሠረት የሚወሰንበትን የደም ካሣ ከከፈለ በኋላ በሟችና በገዳይ ቤተሰቦች መካከል የጠላትነት ስሜት እንዳይኖር ለዘለቄታው እልባት የሚበጅበት ሥርዓት ነው።”
ሰሞኑን በሲዳማ ዞን የተፈጠረው ችግር መንስዔ ምንም ይሁን ምን የተገዳደረውና ጥፋት ያደረሰው እነዚህን መሰል ጠንካራና ፅኑ ባህላዊ ሥርዓቶችን ተላልፎ ስለመሆኑ በግሌ እገምታለሁ። የሲዳማ ዞን የክልል መብቱን መጠየቅና በሕግና በሥርዓት አግባብ ማስከበር ስለመቻሉ የሚያጠያይቅ አይደለም። ታሪካዊ ለሚሆነው ለዚህን መሰሉ ታላቅ ውሳኔ አሰጣጥ ጥቂት ወራት እንዲራዘም በመንግሥት መወሰኑም ለአተገባበሩ የተሻለ አውድ ለመፍጠር እንጂ እንደ እምቢታ ሊቆጠር ባልተገባ ነበር።
ከሲዳማ ነበር ባህልና ማሕበራዊ እሴት ባፈነገጠ ሁኔታ ተነጋግሮ መደማመጥ እየተቻለ ከትዕግሥት ይልቅ ቁጣ፣ ከመረጋጋት ይልቅ መደንበር፣ ከመደማመጥ ይልቅ መቃቃር፣ ከስክነት ይልቅ መጠቃቃት በተስተዋለበት በሰሞኑ ሀኔታ የደረሰው የሕይወትና የንብረት ጥፋት በእጅጉ የሚያሳዝን ብቻ ሳይሆን በዚያ በተከበረና ጠንካራ እሴት ባለው ሕዝብ መካከል በወደፊት ታሪክ ላይ ክፉ ጠባሳ ትቶ ያለፈ ድርጊት ስለመሆኑ አሌ አይባልም።
በአፊኖ ጥበብ፣ በጎንዶሮና በሲጮ እሴት ተኮትኩተው ቢያድጉም እሴቱ ፍሬ በውስጣቸው ባላፈራ ግልፍተኛ ወጣቶችና ጎልማሶች የተፈፀመው ታሪካዊ ስህተት ትቶ ያለፈው ጠባሳ በቀላሉ መሻሩ ያጠራጥራል። ጉዳቱ ምን ያህል የከፋ መሆኑ የተገለፀልን ተጎጂዎቹ በእንባ እየታጠቡ ሲተርኩ በመገናኛ ብዙኃን በተለይም በፖሊስና ኅብረተሰብ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ በዝርዝር ከተመለከትን በኋላ ነው።
የሲዳማ ብሔር ሞቴዎች፣ ጋሮዎች ወይንም ጌሎዎች ያንን መሰል አሰቃቂ ድርጊት ሲያስተውሉና ሲሰሙ ምን ዓይነት መሪር ሐዘን ሊሰማቸው እንደሚችል ለመገመት አይከብድም። የሀገር ሽማግሌዎች፣ የተከበሩ የሲዳማ እናቶች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ያንን የከፋ የዘረፋና የጥፋት ትዕይንት በዓይናቸው ፊት ሲፈፀም በምን ዓይነት ስሜት እንባቸውን ወደ ውጭ ብቻ ሳይሆን ወደ ውስጥም አፍሰው እንደነበር ስሜታቸውን ለመጋራት አይከብድም።
የንፁሃን ዜጎች ሕይወት በከንቱ በማለፉ፣ የንግድ ቤቶች ተቃጥለው ባለንብረቶቹ በአንድ ሌሊት መና መቅረታቸው፣ የሕዝብ መገልገያና መተቀሚያ የሆኑ ፋብሪካዎች እንደዋዛ በመጋየታቸውና ቤተ እምነቶች በመውደማቸውና በመዘረፋቸው ማን ምን ትርፍ አገኘ? በእነዚህ ሁሉ ያልተገቡ ጥፋቶች ነግዶስ የሚጠቀመው ማነው? ለሲዳማ ሕዝብ ከዚህ የከፋ ጥፋት ምን “የድል ዋንጫ” ተበረከተለት?
ይህ አንገት አስደፊ ክፉ ድርጊትና ውድመት ለሲዳማ ወጣቶችስ ምን ፋይዳ አትርፎ አለፈ። “ዳኤ ቡሹ” (አፈር ልሁንልህ፣ ልሞትልህ) እያለ ፍቅሩን ለእንግዳ በመግለጽ የሚታወቀው የሲዳማ ሕዝብ ይህንን ክፉ ጠባሳ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከታሪኩ ለመፋቅ ምን እርምጃ ቢወስድ ይሻል ይሆን?
በግል እምነቴ ክፉ ቀን ያጋጠመው የሲዳማ ሕዝብ ሕይወታቸውን ላጡ ንስሃ፣ ንብረታቸው ለወደመባቸው ምትክ፣ ልባቸውና ቅስማቸው ለተሰበረ ጉዳተኞች ድጋፍ፣ ኅሊናቸው የቆሰለውን በማከም ምሳሌነት ያለው ተግባር ፈጽሞ ሊያቋቁማቸው ይገባል ባይ ነኝ። ይህ ምክረ ሃሳብ ለሕዝቡ ይጠፋዋል ብዬ አልገምትም። የባህሉ አካል ነውና።
ጠንካራው የባህሉ እሴት በሚፈቅደው መሠረትም አጥፊዎችን ወደ ፍርድ ወንበር አቅርቦ ሊቀጣቸውና ሊያርማቸው እንደሚገባ ማስታወሱ አይከፋም። አቅሙ የሳሳ የመሰለው “የአፊኖ” እሴት እንደገና ጉልበቱን አድሶ ሊያንሰራራ ይገባል። እኔም በምወደው የሲዳማ የፍቅር መግለጫ “ዳኤ ቡሹ” ብዬ እሰናበታለሁ። ሰላም ይሁን!
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 24/2011