በኢትዮጵያ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ረቂቅ አዋጅ ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ሰሞኑን አንድ ውይይት ተካሂዶ ነበር። የፓርላማው የዴሞክራሲና የፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በረቂቅ አዋጁ ላይ ሰሞኑን ባካሄደው ሕዝባዊ ውይይት ላይ የተቀናቃኝ ፓርቲ አንዳንድ መሪዎች ስብሰባውን ረግጠው በመውጣት ቁጣቸውን መግለፃቸው የመገናኛ ብዙሃንን ቀልብ ስቧል። ለዚህ እርምጃ እንደምክንያት እየተጠቀሰ ያለው በረቂቅ አዋጁ እንዲካተቱ ያቀረብናቸው ሐሳቦቻችንና አስተያየቶቻችን አልተካተቱም የሚለው ነው።
በረቂቅ ሕጉ ላይ ተቃውሞ ያስነሱ ሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች ይጠቀሳሉ። ከእነዚህም መካከል አንዱ የመንግሥት ሠራተኞች ለምርጫ በእጩነት ከተመዘገቡበት ጊዜ ጀምሮ የምርጫ ሂደቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ ከሥራ ገበታቸው በጊዜያዊነት እንደሚለቁና ደመወዝና ጥቅማ-ጥቅማቻቸውም እንደማይከፈል መጠቀሱ ነው::
ሌላው ቀደም ሲል ክልላዊ ፓርቲ ለመመስረት 750፣ ሀገር አቀፍ ፓርቲ ለመመስረት ደግሞ 1500 የመስራች አባላትን የድጋፍ ፊርማ የሚጠይቅ ቢሆንም አሁን ግን በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ለክልላዊ ፓርቲ 4000፣ለሀገር አቀፍ ፓርቲ ደግሞ 10 ሺ መስራች አባላትን መጠየቁ ቅሬታን አስነስቷል።
የመንግሥት ሠራተኞች ወደምርጫ ውድድር በሚገቡበት ወቅት በጊዜያዊነት ከመንግሥት ሥራቸው እንዲለቁ በረቂቅ አዋጁ መደንገጉ አንድ ከፍተኛ ክርክር ያስነሳ ጉዳይ ነው። ተቀናቃኝ ፓርቲዎቹ ይህ አንቀጽ የመንግሥት ሠራተኞችን የምርጫ ተሳትፎ ይገድባል ሲሉ አጥብቀው ይቃወማሉ። አንዳንዶች ደመወዝ እየተከፈለው ጭምር ሲታመም እንኳን በነጭ ሽንኩርት የሚታከም ምስኪን የመንግሥት ሠራተኛ ጭራሽ ደመወዝ ተከልክሎ ምርጫ ተሳተፍ ማለት ቀልድ ነው ሲሉ ድንጋጌውን ይቃወማሉ።
እነዚህ በአዲሱ ረቂቅ ሕግ የተካተቱ ነጥቦች ጥቂት የማይባሉ የተቀናቃኝ ፓርቲዎችን አላስደሰተም። እናም የውይይት መድረክ መርገጥና ጥሎ መውጣት የተከሰተው በዚህ ምክንያት ነው።
የምርጫ ሕግ አርቃቂ ቡድን አባላት ይህ አንቀጽ በፓርቲ እና በመንግሥት ሥራ መካከል ያለውን መደበላለቅ ለማጥራት ወሳኝ ነው በማለት የእርምጃውን ትክክለኝነት ያስረዳሉ። በእርግጥም በመንግሥት የሥራ ሰዓትና ጊዜ፣ በመንግሥት ተሽከርካሪና ነዳጅ የምርጫ ሥራ ውስጥ የሚገቡ ሹማምንት ብዙ ከመሆናቸው አንፃር ሲገመገም የሕግ አርቃቂ ቡድኑ ሐሳብ ውሃ የሚያነሳ ይመስላል። የሚገርመው በዚህ ረቂቅ ሕግ ይበልጥ ተጎጂ የሚሆነው ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ዝምታን በመረጠበት ሁኔታ የአንዳንድ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች መቆጣት ‹‹የምትወልደው እያለች የምታሸው ወገቤ ተበጠሰ አለች›› የሚለውን ሀገርኛ ብሂል የሚያስታውስ ሆኗል።
ሌላው አከራካሪ የሆነው ጉዳይ በፓርቲ ምስረታ ወቅት ለክልላዊ ፓርቲ 4ሺ፣ ለአገር አቀፍ 10 ሺ የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብን በግዴታ መልክ መደንገጉ ነው። እዚህ ላይ የሚነሳው ክርክርም ይህን ያህል ደጋፊ ለማሰባሰብ አስቸጋሪ በመሆኑ የአዲስ ፓርቲዎች ምስረታ ይገታል፤ ይህ ደግሞ በነፃ የመደራጀት መብትን ይገድባል በሚል የሚቀርብ ነው። የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ መቶ ሚሊየን በሚኖርበት አገር ይህን ያህል ደጋፊ ፊርማ ማምጣት እንደችግር መነሳት የለበትም በሚል መልስ መስጠታቸውም ተሰምቷል።
ረቂቅ ሕጉ ምን ያሳካል?
በገለልተኛ ሕግ አርቃቂ ባለሙያዎች ረቂቁ ተዘጋጅቶ በሚኒስትሮች ምክርቤት ይሁንታን አግኝቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት የተላለፈው የኢትዮጵያ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ረቂቅ አዋጅ አሁን በሥራ ላይ ያለውን መሰል አዋጅ የሚያሻሽል ነው። ሕጉ ካስፈለገበት መሠረታዊ ምክንያቶች መካከል የምርጫ እንቅስቃሴ ዓለም አቀፍ የምርጫ መርሆዎችን አካቶ በያዘ ሕግ መምራት በማስፈለጉ ነው።
ዜጎች በሚመሰርቱት ወይንም በአባልነት በሚቀላቀሉት የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ የሚኖራቸውን መብትና ግዴታ እንዲሁም ፓርቲው ሕጋዊ ሰውነት የሚያገኝበት ሁኔታ እና በድርጅትነት ሲንቀሳቀስ መከተልና ማክበር ያለበት መሠረታዊ መርሆዎችን መደንገግ በማስፈለጉ ረቂቅ ሕጉ ተዘጋጅቷል።
በተጨማሪም የፖለቲካ ፓርቲዎች በመዋሀድ፣ ግንባር በመፍጠር ወይንም በመቀናጀት ሊንቀሳቀሱ የሚችሉበትን ሁኔታ መደንገግ አስፈላጊ በመሆኑ ረቂቅ ማሻሻያው መዘጋጀቱን የአዋጁ መግቢያ ላይ በግልጽ ተመልክቷል።
ተዋሀዱ ወይም ተሰባበሩ
“ተዋሀዱ ወይንም ተሰባበሩ” የሚለው አባባል በተለይ በምርጫ 1997 በተቃዋሚ ጎራው አካባቢ ጎልቶ የሚሰማ ድምጽ ነበር። በወቅቱ ሰብሰብ ለማለት የሞከሩት ቅንጅት እና ሕብረት ከፍተኛ የመራጭ ድምጽ ማግኘት የቻሉትም መሰባሰብ በመቻላቸው ምክንያት እንደሆነ ይታመናል። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሐሳቡ ሲነሳ ሲወድቅ ቢቆይም የተቃውሞ ጎራውን ስፋት በሚመጥን መልክ መልስ ማግኘት አልቻለም።
የተሞከሩ የመሰባሰብ አዝማሚያዎችም የንትርክና የአለመግባባት ምንጭ ሆነው ብዙ ሳይራመዱ ጨንግፈዋል። አንዳንዶቹም በመኖርና በመሞት መካከል ሲወዛወዙ ከርመዋል። በዚህ ረገድ በቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ አባላት መካከል ተከስቶ ፓርቲውን እስከመብላት የደረሰው አለመግባባት የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።
ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ ደግሞ ይኸው ጥያቄ ያውም በገዥው ፓርቲ መሪ በጠ/ሚ አብይ አህመድ አንደበት ተደጋግሞ በምክር መልክ ሲቀርብ አስተውለናል። ጠ/ሚኒስትር አብይ ከወራት በፊት “ኢህአዴግ 27 ዓመት ከነበረበት ጫና ወጥቶ እየተጠናከረ ነው፤ እንዳትዘናጉ። አሁን ባደረግነውና ወደፊት በምናደርገው መሻሻል ስለምንቀጥል፤ ሕዝብ ወደእኛ እየመጣ ነውና እንዲህ ተበታትናችሁ እኛን መደራደር አትችሉም።
ሕብረት ፈጥራችሁ በመደራጀት ጥሩ ተፎካካሪ ሆናችሁ ውጡ” የሚል መልዕክት ማስተላለፋቸውን የምንዘነጋው አይደለም። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ይህን መልዕክት ያስተላለፉት ከሀምሳ በላይ ሀገር አቀፍ፣ ክልላዊና ከውጭ አገራት ከመጡ ፓርቲዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ነበር።
ጠ/ሚ አብይ አህመድ እንደ ገዥ ፓርቲ የተቀናቃኞቻቸው መዳከምና መበታተን ለፓርቲያቸው ጥንካሬን የሚያስገኝ እንደመሆኑ እንደቀድሞው ኢህአዴግ ዝም ብለው ዕድሉን መጠቀም ይችሉ ነበር። ግን ጠ/ሚኒስትሩ እንደአንድ አገር መሪ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በመገንዘብ ትክክለኛውንና የሚበጀውን መንገድ ለመጠቆም የሄዱበት ርቀት ተቀናቃኝ ፓርቲዎቹ ተገቢውን ዋጋ የሰጡት አይመስልም።
እርግጥ ነው፤ የጠ/ሚኒስትሩን ምክረ ሐሳብ ታሳቢ አድርገው ጥቂት ፓርቲዎች ለመዋሀድ፣ ሙከራ አድርገዋል። የቀድሞ ፓርቲያቸውን አክስመው አዲስ ፓርቲ ለመመስረት ወይንም ለመቀላቀል የሞከሩም መኖራቸውን እያስተዋልን ነው። በሙከራ ደረጃ የተጀመሩ ሥራዎች በአዎንታ መታየት እንዳለበት የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ይገነዘባል። ሆኖም ፓርቲዎቹ በሀገር አቀፍ ደረጃ ካላቸው አጠቃላይ ቁጥር አንፃር ሲገመገም ጅምሩ ከበቂ በታች ነው ማለት ይቻላል።
ከምርጫ ቦርድ የተገኘ የቅርብ መረጃ እንደሚጠቁመው የተቀናቃኝ ፓርቲዎች ቁጥር ከአንድ ዓመት በፊት ከነበረው ከ80 በታች ቁጥር ዘንድሮ በፍጥነት ዕድገት አሳይቷል። በአሁኑ ወቅት የፓርቲዎቹ ቁጥር 135 ደርሷል። ምናልባት በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ባላት የፓርቲዎች ብዛት በአንደኝነት በዓለም ድንቃድንቅ መዝገብ (ጊነስ ቡክ) ልትመዘገብ የምትችልበት አጋጣሚም የቀረበ ይመስላል።
እነዚህ ብዛት ያላቸው ፓርቲዎች አብዛኛዎቹ በአባላት(ደጋፊ) ብዛት፣ በአደረጃጀት፣ በፋይናንስና የቴክኒክ አቋማቸው እጅግ የወረደና ተመሳሳይ ደረጃ ላይ የሚገኙ መሆኑ ሌላው ችግር ነው። የቁጥራቸው መብዛት በምርጫ ወቅት ብቻ ሳይሆን ከዚያም በፊት ጠንካራ አባልና ደጋፊ ለማሰባሰብ፣ ከመንግሥት የሚሰጣቸውን የፋይናንስ ድጎማ በሚጠቅም መጠን ለማግኘት የሚያስችል አቋም ላይ አለመሆናቸው መልሶ የሚጎዳቸው ይሆናል።
በምርጫ ወቅት በአንድ ምርጫ ጣቢያ አንድና ሁለት መራጭ ጭምር የማያገኙበት አሳዛኝ ክስተት ባለፉት ጊዜያት ማየት የቻልነውም ከድክመታቸው ጋር በተያያዘ ነው። ብዙዎቹ አባል አልባ፣ ቢሮ አልባ፣ ገንዘብ አልባ…ሆነው በግለሰቦች ኪስ ማህተምና ቲተር እየተያዘ ፓርቲ ነን የሚባልበት ቀልድ አሁንም መቀጠሉ በአሳሳቢነቱ መነሳቱ ምንም አይገርምም። እናም ተዋሀዱ ወይንም ተሰባበሩ የሚባልበት ትክክለኛ ጊዜ ቢኖር አሁን ነው።
ውህደቱ ገዥውን ፓርቲም ይመለከታልን?
የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) የአራት ፓርቲዎች (ህወሓት፣ አዴፓ፣ ኦዴፓ፣ ደኢህዴን) የመሰረቱት ግንባር ነው። ግንባሩን በአባል ድርጅቶች በመጨፍለቅ አንድ ውህድ ፓርቲ ለመመስረት ረዥም ጊዜ ያስቆጠረ ዕቅድ ቢኖርም በተለያዩ ምክንያቶች ዳር ሳይደርስ ቆይቷል። በያዝነው ዓመት መስከረም ወር የተካሄደው የኢህአዴግ ጉባዔ የውህደት አጀንዳ አጋር ፓርቲዎችን ባካተተ መልኩ አጀንዳውን በይደር ማሳለፉ ግንባሩ ለውህደት ያለውን ብርቱ ፍላጎት ህያውነት ጠቋሚ ሆኗል።
በመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት በሐዋሳ በተካሄደው የኢህአዴግ ጉባዔን በንግግር የከፈቱት ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር እንደስያሜው የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ድርጅት ይሆናል ሲሉ መናገራቸውን ማስታወስ አባባሌን ያጠናክራል።
ጠ/ሚኒስትሩ በዚሁ ንግግራቸው ከውህደት ጋር ተያይዞ ጥናት መደረጉንም ገልፀው ባለፉት ዓመታት በነበረው አገራዊ ሁኔታ ምክንያት ውህደቱ ለዘንድሮው ጉባዔ ሊደርስ አለመቻሉን ግን ጠቁመዋል።
በዚህ ወቅት ከመጠን በላይ የከረረው የብሔር ፌደራሊዝም ኢትዮጵያዊያን እንደልባቸው ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው እንዳይሠሩ አድርጓቸዋል። በጋብቻ ትስስር፣ በሥራ፣ በመንደር ሰፈራ ወይም በፍልሰት ምክንያት ፌደራሊዝሙ ካሰመረላቸው ክልሎች ውጭ የተገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችም ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶቻቸው ለመጨፍለቁም ምክንያት ሆኗል። በብሔር-ተኮር ድርጅቶች የሚመሩት ክልሎች በአንድ ውህድ ህብረ-ብሔራዊ ፓርቲ ቢመሩ ኖሮ ግን ችግሩ ሙሉ በሙሉ ባይቀረፍም እንኳን መሻሻል ያሳይ እንደነበር የብዙዎች ግምት ነው።
እንደሚታወቀው በ2000 ዓ.ም የተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ “ውህደት” (union) ማለት “ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ በሕግ መሠረት ተመዝግበው የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአንድ ላይ ተዋህደው አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ የሚመሰርቱበት ሁኔታ ነው” በማለት ይገልፀዋል። ስለሆነም ስለ ኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ውህደት ስናነሳ ድርጅቶቹ ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ አፍርሰው፣ አርማዎቻቸውንና ማህተሞቻቸውን ለምርጫ ቦርድ አስረክበው አባሎቻቸውን በቀጥታ የአዲሱ ህብረ-ብሔራዊ ፓርቲ አባል ያደርጋሉ ማለት ነው።
ከሀብት አንፃር ካየነውም በ2000 ዓ.ም የተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ አንቀፅ (31) የፖለቲካ ፓርቲዎች ውህደት ከፈፀሙ ምርጫ ቦርድ የእያንዳንዳቸውን ንብረትና ገንዘብ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ለውህዱ ድርጅት እንዲተላለፍ የማዘዝ ሥልጣን እንዳለው ይደነግጋል። ሆኖም የእያንዳንዳቸው የሀብት ብዛት አለመታወቁ አንድ ነገር ሆኖ በተለይ ግን ግዙፍ ሀብት ያላቸው የገዥው ፓርቲ አባል ድርጅቶች ሀብታቸውን ለውህድ ህብረ-ብሔራዊ ድርጅት ለማውረስ ፍቃደኛ ይሆናሉ ወይ? የሚለውም መልስ የሚፈልግ ነው።
ይህ የኢህአዴግ ዕቅድ በአራቱም የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች በኩል እኩል ተቀባይነት አለው ለማለት ተጨባጭ ሁኔታዎች አያስደፍሩም። ውህደቱን በግልፅ የሚቃወሙ ወይንም ውህደትን ሊያመጣ በማያስችል አቋም ላይ የሚገኙ አባል ፓርቲዎች መኖራቸው በቀጣይ አንድ ትልቅ ተግዳሮት እንደሚሆን ይገመታል። ኢህአዴግ ያፈነገጡ አባሎቹን አራግፎ በውህደት ታድሶ መቀጠል ወይንም ተፍረክርኮ ለ28 ዓመታት የዘራውን የብሔር ተኮር ፖለቲካ ፍሬ መሰብሰብ ከፊቱ የተጋረጠ አደጋ ሆኗል።
የስንብት ቃል
የኢትዮጵያ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ረቂቅ አዋጅ በየደረጃው ውይይቶች እንዲደረጉበት የተሄደበት ርቀት የሕጉን አርቃቂዎች ጨምሮ የሚመለከታቸው ወገኖችን የሚያስመሰግን ነው። በረቂቅ ሕጉ ውስጥ አንዳንድ አንቀጾች ቅሬታ ማስነሳታቸው የሚጠበቅ ሲሆን ረቂቅ ሕጉ ካስገኘው ሁለንተናዊ ጥቅም አንፃር የተነሱ ቅሬታዎች ሚዛን የሚደፉ አለመሆናቸውን የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በግሉ ያምናል። ዋናው ነገር በተለይ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች “ፓርቲ” የሚያሰኝ ቁመና እንዲኖራቸው መታገል ላይ ሊያተኩሩ ይገባል። አንድ የተቀናቃኝ ፓርቲ መሪ በድፍረት ያራመዱትን አቋም እዚህ ላይ ማስታወስ ተገቢ ይሆናል።
እኚህ ጎምቱ የፖለቲካ ሰው “ኢትዮጵያ ውስጥ ፓርቲ የለም፣ ያለው የታዋቂ ሰዎች ስብስብ ነው” ብለዋል። በእርግጥም ተጨባጩን እውነታ የዳሰስ ወርቃማ አባባል ይመስለኛል። ፓርቲዎች በመዋቅርና አደረጃጀት፣ በፋይናንስ እንዲሁም በአባልና ደጋፊዎቻቸው ዘንድ የሚኖራቸውን ቅቡልነት ለማሳደግ ያላቸው ብቸኛ ምርጫ ጠ/ሚኒስትር አብይ እንደመከሩት መሰባሰብ ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ ያለው የመበታተን መንገድ ብዙ ርቀት የሚያስኬድ ባለመሆኑ አሁንም የመተባበርን አጀንዳ በጥልቅት ሊያዩት ይገባል።
ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግም ከአክራሪ ብሔርተኝነት አጀንዳ ጋር ተያይዞ ከገባበት የቀውስ አዙሪት ለመውጣት አንዱ መንገድ የብሔር አጀንዳን በኢትዮጵያዊነት አጀንዳ መተካት እንደሆነ በብዙዎች ዘንድ ይታመናል። ግንባሩ ከህመሙ ለመፈወስ የጀመረውን የውህደት ሐሳብ ዳር በማድረስ ቢሠራ ምናልባት የተሻለች የወደፊቷ ኢትዮጵያን በመፍጠር ሂደት ውስጥ አዎንታዊ ሚናውን ለመወጣት እንደሚረዳው ይገመታል።
(የጸሐፊው ማስታወሻ፡- ለዚህ ጽሑፍ ጥንቅር የኢትዮጵያ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ረቂቅ አዋጅ፣የተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ፣ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ይፋዊ ድረገጽ፣ የምርጫ ቦርድ ይፋዊ ድረገጽ፣ ሪፖርተር ጋዜጣ…ዜናና መረጃዎችን በግብአትነት መጠቀሜን ከምስጋና ጋር እገልፃለሁ)
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 24/2011