ኢትዮጵያ በተያዘው የክረምት ወቅት 4 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል የያዘችው እቅድ አካል በሆነው የአረንጓዴ አሻራ ቀን የ200 ሚሊዮን ችግኞች ተከላ ትናንት ስታካሂድ ውላለች። በውጤቱም 353 ነጥብ 6 ሚሊዮን ችግኞች ተተክለዋል፡፡
በችግኝ ተከላው የክረምቱ ዝናብ፣ጭቃ እና ብርድ ሳይበግረው ከልኂቅ እስከ ደቂቅ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በነቂስ ወጥቶ ተሳትፏል። የክረምቱ ቁር፣ጭቃ እንዲሁም ችግኝ የሚተከልበት ወጣ ገባ አካባቢ ያልበገራቸው አዛውንቶች ለትውልድ አረንጓዴ አካባቢ ለማስተላለፍ ወጥተዋል፤ ወርደዋል፤ ጎንበስ ቀና ብለዋል። ከችግኞቹ ጋር አብረን እናድጋለን ያሉ ሕፃናት ከቤተሰባቸው ጋር በመሆን ችግኞችን ተክለዋል። የመንግሥት ሠራተኞች፣ የከተማና የገጠር ነዋሪዎች፤ የሃይማኖት አባቶች፣ የመከላከያ ሠራዊትና የጸጥታ አባላት፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ወዘተ በችግኝ ተከላው ተሳትፈዋል። በድምሩ ከ23 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ተሳትፏል፡፡
በችግኝ ተከላው ኢትዮጵያውያን ብቻ አይደሉም የተሳተፉት። አላማው ዓለም አቀፍም ጭምር ነውና አምባሳደሮች እና የዓለም አቀፍ ተቋማት ሠራተኞችም ተሳትፈዋል፡፡
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በጎንደር በመገኘት የችግኝ ተከላውን ያስጀመሩ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ደግሞ በአርባ ምንጭና ወላይታ ሶዶ በመገኘት ችግኞችን ተክለዋል።
የችግኝ ተከላው ውሎ ከማለዳ አንስቶ ቀኑን ሙሉ በመገናኛ ብዙኃን የቀጥታ ሽፋን እንዲያገኝ ተደርጓል። መገናኛ ብዙኃኑ መረጃ በማቅረብ ሰፊ ሽፋን ሰጥተዋል። ኅብረተሰቡ ስለችግኝ ተከላው ፋይዳ እንዲገልጽ በማድረግም ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል።
በሀገሪቱ ለዓመታት የችግኝ ተከላ በየዓመቱ በክረምቱ ወቅት ሲካሄድ መቆየቱ ይታወቃል። በተለይ በኢትዮጵያ ሚሌኒየም «ሁለት ዛፍ በሁለት ሺ» በሚል መርህ አንድ ቢሊዮን ችግኞች ተተክለዋል። በመቀጠልም ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከደለል ለመታደግ በሚልም በተመሳሳይ የችግኝ ተከላዎች መካሄዳቸው ይታወሳል።
የዘንድሮው የችግኝ ተከላ ደግሞ ከሁሉም በእጅጉ የላቀ ነው። የዘንድሮው የችግኝ ተከላ ካለፉት ዓመታት ይለያል። በዚህ የችግኝ ተከላ አንድ ሰው አርባ ችግኞችን እንደሚተከል ታሳቢ ተደርጎ 4 ቢሊዮን ችግኞች ለመትከል ነው የታቀደው። በእነዚህና የዚህ ችግኝ ተከላ አካል በሆነው የአረንጓዴ አሻራ ቀን 200 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ጀንበር ለመትከል መታቀዱ የችግኝ ተከላውን ልዩ አድርገውታል።
በአንድ ጀምበር 200 ሚሊዮን ችግኞች ተከላ እቅድ በሕንድ 66 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ቀን በመትከል ተይዞ የቆየውን ሪኮርድ ገና እኩለ ቀን ላይ 70 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል መስበር ተችሏል። ይህ በራሱ በዓለም አቀፍ ደረጃ አድናቆት የሚቸረውና የዓለም ክብረ ወሰንም እንደሚሆን የሚመጠበቅና ዜጎች በአረንጓዴ አሻራው አሻራቸውን በማሳረፍ ታላቅ የችግኝ ተከላ ስለመፈጸማቸው አንድ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል።
መንግሥት የዘንድሮው የችግኝ ተከላ ለእንክብካቤ እንዲረዳ በሚል በየአቅራቢያው እንደሚካሄድ ቢገልጽም፣ሕዝቡ ግን ከዚህም በመሻገር ከአዲስ አበባ እና ከተለያዩ ከተሞች ወደ ገጠር አካባቢዎች በመውጣት ችግኞችን በመትከል የችግኝ ተከላው ልዩ ገጽታ እንዲላበስ አድርገውታል። ደንን ማልማት የሚቻለው በገጠሩ ክፍል እንደመሆኑ ከከተሞች ወጣ ብሎ በክልሎች መትከል መቻሉ ሊደነቅ የሚገባውና በቀጣይ ዓመታት በእጅጉ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ታላቅ ተግባር ነው።
አራት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል በተሰጠው በዚህ ልዩ ትኩረት እስከ ሐምሌ 21ቀን 2011ዓ.ም 3 ነጥብ 1 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህ ክንውንም ሕዝቡ ለትናንቱ የአረንጓዴ አሻራ ቀን የ200 ሚሊዮን ችግኞች ተከላ እጁን እንዲያሟሽና በዕለቱም የሚካሄደው የችግኝ ተከላ ውጤታማ እንዲሆን አስችለዋል።
እነዚህን 200 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ጀምበር ለመትከል ታቅዶ የተመዘገበው የ353 ነጥብ 6 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ ስኬት በቀሪዎቹ ቀናት ተከላው ተጠናክሮ እንዲሄድ ለማድረግ ወሳኝ እርምጃ ተደርጎም ሊወሰድ ይገባል።
በችግኝ ተከላው የተመዘገበው ስኬት ሕዝቡንና ተቋማትን በማስተባበር ብዙ ርቀት መጓዝ የሚቻል ስለመሆኑ ሁነኛ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል። ሕዝቡ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ፣ በተፋሰስ ልማት፣ በአገር ሉአላዊነት ማስጠበቅና በመሳሰሉት እንዳደረገው ሁሉ መንግሥት የአረንጓዴ ሽፋን መመናመን የዘመኑ አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ ሕዝቡ በደን ልማት በመሳተፍ ዓለምንና ሀገሩን የአየር ንብረት ለውጥ ከሚያስከትለው ችግር እንዲታደግ ለቀረበለት ጥሪ ፈጣን ምላሽ የሰጠበት ነው።
እንደሚታወቀው መንግሥት በሀገራችን የመጣው ለውጥ ያልጣማቸው አካላት በሚሸርቡት ሴራ ሳቢያ ሀገሪቱን ከደረሰባት አለመረጋጋት ለመውጣት እየተከናወነ ካለው ተግባር በተጓዳኝ በልማቱ መስክም የተጠናከረ ተግባር እየተከናወነ ለመሆኑ ሌላ ማሳያ ነው። ሕዝቡ በአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ የራሱን አሻራ በማኖር ያስመዘገበው ስኬት ኢትዮጵያውያን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነውም መንግሥት ያስቀመጠውን እቅድ ለማሳካት እንዳለፉት ጊዜያት ሁሉ እየተረባረቡ መሆናቸውን ያመለክታል።
የደን ልማት ዘላቂ ሥራን ይጠይቃል። ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ተግባሮችም ሆኑ በዚህ የክረምት ወቅት በተለይም ትናንት የተከናወነው ተግባር የሥራው የመጀመሪያ ናቸው። በመሆኑም በአረንጓዴ አሻራው 200 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል መንግሥት ያሳየው ቁርጠኝነትና ሕዝቡ ለዚህ ታላቅ ጥሪ የሰጠው ምላሽ በችግኝ እንክብካቤውም ከርሞ በሚደረገው የችግኝ ተከላም መደገም ይኖርበታል። ይህን ለማድረግ የአረንጓዴ አሻራ ቀን በየዓመቱ እንዲኖረን ያስፈልጋል!!የአረንጓዴ አሻራ ቀን ይደገም !!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 23 /2011