አገራችን ከአምስት አስርት ዓመታት በፊት የነበራት የደን ሃብት ከ30 በመቶ በላይ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ። ይህ የደን ሃብት ግን ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ሲመናመን ቆይቶ ወደ ሶስት ከመቶ ወርዷል። ይህ ደግሞ አገሪቱን ለከፋ የተፈጥሮ አደጋ ሊዳርግ የሚችል ትልቅ ስጋት እንደሆነ የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ።
በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የኑሮ መሰረታቸው በግብርና ላይ ለተመሰረተ አገር ደን የሚኖረው አስተዋፅኦ ቀላል አይደለም። ደን የተፈጥሮን አየር ፀባይ ሚዛን በማስጠበቅ ረገድ ያለው ሚና የላቀ ነው። በተለይ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎችና ፋብሪካዎች ዓለምን ባጥለቀለቁበት በዚህ ዘመን የደን መመናመን ታክሎበት ተፈጥሮን ለከፋ ችግር እየዳረጋት መሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገር የቆየ እውነታ ነው።
በዚህ ዘመን በኢንዱስትሪ ከበለፀጉት አገራት በሚለቀቅ በካይ ጋዝ አማካይነት የከባቢ አየር መሳሳትና ይህንንም ተከትሎ የበረሃማነት መስፋፋት ትልቁ የዓለም ፈተና ሆኗል። ይህንን ለመከላከል የሚያስችል የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራም በአግባቡ ባለመከናወኑ ዓለም ለተለያዩ የተፈጥሮ አደጋዎች ስትጋለጥ ማየት የተለመደ ነው። አሁን አሁን በተደጋጋሚ የሚሰሙት የጎርፍ እና የአውሎ ንፋስ አደጋዎች ያስከተለው ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመቶችም የዚህ ውጤቶች ናቸው።
ይህ የተፈጥሮ መዛባትም ኢትዮጵያና ሌሎች አዳጊ አገራትን የሚያሳስብ ትልቅ ጉዳይ ከሆነ ሰነባብቷል። ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባትም የበለፀጉ አገራት ለአረንጓዴ ልማት ኢኮኖሚ ትኩረት እንዲሰጡ ኢትዮጵያ ስታሳስብ ቆይታለች። ከዚህም ጎን ለጎን የአረንጓዴ ልማት ኢኮኖሚን ተግባራዊ በማድረግ ዘርፈ ብዙ ጥረቶችን እያደረገች ትገኛለች። ከነዚህም ውስጥ የአረንጓዴ ልማት ኢኮኖሚን የሚደግፉ የሃይል አማራጮች፣ የባቡር ፕሮጀክቶች፣ የሸገር ፕሮጀክትና የደን ልማት ስራዎች ይጠቀሳሉ።
በዘንድሮ ዓመት አራት ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል የደን ሽፋንን ለማሳደግና የተፈጥሮ ሃብትን ለመጠበቅ እየተደረገ ያለው ጥረትም የዚህ ማሳያ ነው። በዛሬው እለት የሚከናወነው በአንድ ጀምበር ሁለት መቶ ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል መርሃ ግብርም የዚሁ አካል ሲሆን ይህ ቀን በአረንጓዴ ልማት ስራችን ላይ ትልቅ ትርጉም ያለውና አገራችን ለአረንጓዴ ልማት ስራ እየሰጠች ያለውን ትኩረት የሚያመላክት ነው።
የዛሬው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ለአገራችን ህዝቦችም ትልቅ የታሪክ አሻራ ጥለን የምናልፍበት የታሪክ አጋጣሚ ነው። ምክንያቱም ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ያወደምነው የደን ሃብት መልሶ እንዲያገግም በማድረግ ለቀጣዩ ትውልድ የተፈጥሮ ሃብቷ የተጠበቀ አገር ማውረስ የታሪክ ግዴታ ነውና።
ከድህነት ለመውጣት በከፍተኛ ጥረት ውስጥ በምንገኝበት በዚህ ወቅት የተፈጥሮ ሃብታችን ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል። ግብርና መር የሆነው አገራችን ኢኮኖሚ ከተፈጥሮ ጥገኝነት ተላቆ በመስኖ ላይ የተመሰረተ እንዲሆንም ጥረቶች አሉ። ነገር ግን ይህ እውን እንዲሆን ገና ብዙ ፈተናዎች አሉ። በመሆኑም አሁን ባለንበት ሁኔታ ወቅቱን የጠበቀ ዝናብና መልካም አየር ፀባይ ለግብርናችን መሰረታዊ ጉዳይ ነው። ይህ እንዲሆን ደግሞ የተራቆቱ አካባቢዎች መልሰው እንዲያገግሙና የደን ሽፋናችንም በእጅጉ እንዲያድግ ማድረግ ግድ ይለናል።
ይህንን እውን ለማድረግ የተጀመረው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር እነሆ በዘንድሮ ዓመት በተጠናከረ ሁኔታ ሲካሄድ ሰንብቶ ዛሬ ላይ በዓለም የችግኝ ተከላ ታሪክ ትልቁን የተከላ መርሃ ግብር የምናከናውንበት እለት ላይ ደርሰናል። በዛሬው እለት የምንተክለው ሁለት መቶ ሚሊዮን ችግኝ በአገራችን የአረንጓዴ ልማት ስራችን ውስጥ ትልቅ አሻራ የምናሳርፍበት ሲሆን ይህም ለቀጣይ ትውልድም በታሪክ ሰነድነት የምናኖረው ነው።
በመሆኑም በዚህ ታሪካዊ እለት በችግኝ ተከላው መርሃ ግብር ላይ በመሳተፍና ለምንተክላቸው ችግኞችም ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ታሪካዊ አደራችንን መወጣት ይጠበቅብናል። ከዚህም ባሻገር ችግኝ መትከል ብቻውን በቂ አለመሆኑን ተገንዝበን ዛሬ የተከልናቸው ችግኞች ራሳቸውን ችለው እስከሚቆሙ ድረስ ልንንከባከባቸው ይገባል። ዛሬ የምንተክላቸው ችግኞች በአግባቡ ተይዘው ካደጉ ነገ የእድገታችን ተስፋ ይሆናሉ። በመሆኑም ዛሬ በአግባቡ እንትከል፣ ነገ ደግሞ የተከልናቸውን እንንከባከብ።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 22/2011