ነገ ሀምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም ነው። በሀገራችን ትልቁ ታሪክ የሚሰራበት የአረንጓዴ ልማት አሻራ ቀን ነው። በዚህ ዕለት 200 ሚሊየን ችግኞች በአንድ ጀምበር በመትከል በዓለም የድንቃድንቅ መዝገብ ላይ የታሪክ አሻራችንን የምናስመዘግብበት እንደሚሆን ይታመናል። የአረንጓዴ ልማት አሻራችንን ለማኖር ይረዳ ዘንድ በሁሉም አቅጣጫ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተጠናቅቀዋል።
እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የታላቁን ህዳሴ ግድብ ለመገንባት ለተያዘው ፕሮጀክት ቦንድ በመግዛት፣ የገንዘብ እና የሞራል ድጋፍ በማድረግ አሻራውን እንዳሳረፈ ሁሉ ነገም በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅግ አሳሳቢ የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ስጋት ለመቋቋም በሚደረገው የአረንጓዴ ልማት አሻራን የማሳረፍ ቀን መሳተፍ ይገባል።
በዚሁ ዕለት በዘጠኙ ክልሎች በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች፣ በከተማና በገጠር፣ ወንድ ሴት፣ ወጣት አዋቂ ሳይል ሁሉም ሰው በነቂስ ወጥቶ በችግኝ ተከላው ላይ መሳተፍ ይጠበቅበታል። በከተሞች ደረጃ የሚሰራው ስራ እንዳለ ሆኖም አብዛኛው የችግኝ ተከላ ስራ ይሰራል ተብሎ የሚጠበቀው ሰፊ መሬት እና በርካታ ህዝብ ባለባቸው የገጠር አካባቢዎች ነው። የዚህ አካባቢ ነዋሪ ከዚህ ቀደምም በአካባቢው፣ በማሳው ዙሪያ ችግኝ የማልማት ልምድ ያለው ነው። አሁን ደግሞ ሀገራዊ ጥሪ ሲደረግ በነቂስ በመውጣት ሀላፊነቱን እንደሚወጣ ይታመናል።ሀላፊነቱን መወጣትም አለበት።
በሀገር አቀፍ ደረጃ በዘንድሮ የክረምት ወቅት አራት ቢሊየን ችግኝ ለመትከል እቅድ ተይዞ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተገብቷል። እስካሁን በተሰራው ስራ ሁለት ነጥብ ሰባት ቢሊየን ችግኝ በመላ ሀገሪቱ ተተክሏል።ቀሪው አንድ ነጥብ ሶስት ቢሊየን ነው። ነገ በአንድ ጀምበር የሚተከለው ሁለት መቶ ሚሊየን ችግኝም የዚሁ አካል ሲሆን ቀሪው እስከ ሀምሌ ወር መጨረሻ ድረስ ይቀጥላል። አሁን ባለው ስሜትና ተነሳሽነት። እስካሁንም ከታየው የችግኝ ተከላ በመነሳት ከዕቅድ በላይ ችግኞች ሊተከሉ እንደሚችሉ ይታመናል።
በችግኝ ተከላው ላይ ለመሳተፍ ክልሎች የየራሳቸውን የዝግጅት ስራ ሰርተዋል። ችግኝ ማፍላትና ጉድጓድ መቆፈር የመሳሰሉትን የዝግጅት ስራዎች ሰርተዋል።አሁን የምንተክለው ችግኝ አውቀንም ሆነ ሳናውቀው ያወደምናቸውን የብዝሀ ህይወት ሙሉ ለሙሉ ለመመለስ ባያስችል እንኳን ችግሩን በተወሰነ መልኩ ሊያቃልል ይችላል። የተቃጠሉ የደን ሀብቶቻችንን በመመለስ የሸሹ እንስሳቶችን ለመታደግ ያግዛል። ችግኝ መትከል ልምድ ሆኖ ከቀጠልም በዓለም አቀፍ ደረጃ ስጋት የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመታደግም የራሳችንን አስተዋጽኦ እናደርጋለን።
ዘንድሮ የሚተከለው ችግኝ እንደከዚህ ቀደሙ ለመትከል ብቻ ተብሎ የሚተከል ሳይሆን በጂፒኤስ ተደግፎ ማን የት ምን ተከለ? እንዴት እየተንከባከበውና እያጸደቀ ነው? የሚለውን መረጃ መከታተል በሚያስችል መልኩ ነው። ይሄ አካሄድ ምን ያህሉ ጸድቋል ለሚለው በቂ መረጃ መያዝም ያስችላል። እያንዳንዱ የተተከለው ችግኝ ተንከባካቢ ባለቤት እንዲሁም ጠያቂና ተጠያቂም እንዲኖር ያስችላል። በመሆኑ ሁሉም ሰው የተከለውን በማን አለብኝነት የሚተው ሳይሆን በሀላፊነት ይንከባከባል፤ ይጠብቃል።
የአዲስ አበባ ከተማም በዚሁ የአረንጓዴ አሻራ ማኖሪያ ቀን ሶስት ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል የችግኝ ዝግጅት፣ የቦታ ልየታ፣ የጉድጓድ ቁፋሮ ስራ መሰራቱን አስታውቋል። በዚሁ ስነስርዓት ላይም የመንግስት ሰራተኞች፣ ወጣቶች፣የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ እና ሌሎችም የፌዴራል ተቋማት እንደሚሳተፉበት አስታውቋል። በአጠቃላይ 31 ሺ ዜጎች እንደሚሳተፉም ይጠበቃል።
ችግኝ መትከል የሀገርን ብሩህ ተስፋና መጻኢ ዕድል መወሰን ጭምር ነውና ሀምሌ 22 ቀን በየችግኝ መትከያ ስፍራዎች በመገኘት አሻራችንን እናኑር።ለዚህ ሀገራዊ ጥሪ ምላሽ መስጠት ስንችል ነው የዜግነት ግዴታችንን ተወጥተናል፤ ለተተኪው ትውልድ ድርቅና ረሀብ ሳይሆን ለም መሬት እና ለምለም ሀገር አስረክበናል ማለት የምንችለው። ይህንን ሃላፊነት ሳይወጡ የዳር ተመልካች መሆን ውሎ አድሮ የህሊናም የታሪከም ተወቃሽ ያደርጋልና በችግኝ ተከላው ስራው ላይ በነቂስ ወጥቶ መረባረብ ይገባል።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 21/2011