የታሪክ ድርሳናትን ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንቃኝ የድሮዋ ኢትዮጵያ ከመሬቷ በአብዛኛው በደን የተሸፈነ፤ ይኽንንም ተከትሎ በቂ ውሃና ዝናብ የነበራትና የአፍሪካ የዳቦ ቅርጫት ተብላ እስከ መጠራት የደረሰች አገር እንደነበረች ያስረዱናል!
የኢትዮጵያ የደን ሽፋን በተመለከተ የቅርብ ጊዜ ትውስታቸውን ለአንድ መገናኛ ብዙሃን ያጋሩት የቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ በአየር በረራ ላይ ሆነው እንደሚያስታውሱት ወጨጫን ጨምሮ የደቡብና የምዕራቡ የአገራችን ክፍሎች ጥቅጥቅ ባለ ደን የተሸፈኑ እንደነበሩ አውግተዋል።
የዚያን ጊዜዋ አረንጓዴ ኢትዮጵያ ያለምክንያት ዕውን አልሆነችም። ለአረንጓዴነቷ ምስጢር የሆኑና በኋላ የተሸረሸረ ደንን የመጠበቅና የመንከባከብ ብሎም የደኑን ህይወት ከሰው ልጆች ህይወት እኩል የሚቆጥሩ ታላላቅ እሴቶች በተለያዩ የአገራችን ብሔር ብሔረሰቦች ዘንድ ስለነበሩ ነው።
ለማሳያ ያህል ጌዴኦን ብንወስድ በጌዴኦ ብሔረሰብ አንድ ሰው አንድን ዛፍ ለመቁረጥ ሲፈልግ በቅድሚያ አምስት ዛፍ ሊተክል ይገባል። በዚህም ብቻ ሳይገደብ አምስቱን ዛፎች ስለመትከሉ የደን ኮሚቴ ተብሎ ለተቋቋመ አካል ማረጋገጥ ይኖርበታል። ይሄን ሳያደርግ ደን መቁረጥ የሰው ህይወት የማጥፋት ያህል ስለሚቆጠር ከማህበረሰቡ ዘንድ ቅጣትን ያስከትላል።
አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ለቡና ኢንቨስትመንት ለመሰማራት ወደ ከፋ ባመራበትና መሬት በተረከበበት ወቅት የአካባቢው የአገር ሽማግሌዎች በመጀመሪያ ቃል ያስገቡት ነገር ቢኖር ለቡና ልማቱ ሲል ደን እንደማይጨፈጭፍ ቃል ማስገባት ነበር። እናም አስተዋዩ አትሌት ሻለቃ ሃይሌ ገ/ሥላሴ ደኑን ፈጽሞ እንደማይነካና እንዲያውም እየተንከባከበ ቡናውን እንደሚያለማ ቃል ገብቶ ኢንቨስትመንቱን ማካሄድ ችሏል።
በጉጂም ቢሆን አንድ ሰው ቤት ሊሰራ ሲፈልግ መጀመሪያ እንዲያደርግ የሚጠበቅበት ነገር ቢኖር በርከት ያሉ ዛፎችን መትከል ነው። እነዚህን ዛፎች ሳይተክል ቤት መስራት ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነው። የዚህ አሰራር ዋነኛ ግብም ለቤት መሥሪያ ተብሎ የሚጨፈጨፈውን ደን መተካት እንደሆነ ግልጽ ነው።
እነዚህን ከላይ የጠቃቀስናቸው ተምሳሌታዊ ተግባራት የደን ሃብታችንን ለመንከባከብና ለመጠበቅ ለዚህም የአካባቢ ምህዳርን የአየር ንብረትን ለኑሮ ተስማሚ ለማድረግ የራሳችን ሃብት የሆኑ በርካታ እሴቶች በእጃችን እንዳሉ ጠቋሚ ናቸው።
እነዚህን መሰል ታላላቅ እሴቶች በዘመን ሂደት እየተሸረሸሩ በመምጣታቸው በተለይም ባለፉት 50 ዓመታት በአገራችን ከፍተኛ የደን ውድመት ተከናውኗል። በዚህም እስከ 30 በመቶ ይገመት የነበረው የአገሪቱ የደን ሽፋን አሽቆልቁሎ ከ3 በመቶ በታች ደርሶ እንደነበር አይዘነጋም።
ማህበረሰቡ የእርሻ ቦታ ፍለጋና ለቤት መሥሪያ፣ ለኃይል ምንጭነት ከቆረጧቸው ደኖች ባልተናነስ በስመ ኢንቨስትመንት እጅግ አጓጊ የነበሩ የአገራችን ደኖች አሳዛኝ ጭፍጨፋ እንደተከናወነባቸው ኢሉአባቦራ፣ ሚዛን ቴፒና ከፋን በመመልከት መረዳት ይቻላል።
በስመ ኢንቨስትመንት በጋምቤላ ክልል መሬት የወሰደ አንድ የህንድ ኩባንያ ደኖችን እየጨፈጨፈ ጣውላ ለማምረት ኤክስፖርት እስከማድረግ ድረስ ዓይን ያወጣ አሳፋሪ ተግባር ሲፈጽም እንደነበርም አይዘነጋም። በወቅቱ ይኸንን ተግባር ያወገዙና የተቃወሙ የአካባቢው ነዋሪዎች “በስመ ልማት አደናቃፊነት” ብዙ ፈተና እንዳዩም በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ተዘግቧል።
አሁንም ቢሆን የአገራችን አየር የቀድሞው ምቹነቱን እያጣ እንደሆነ እየታዘብን ነው። ቀድሞ የተትረፈረፈ ዝናብ ያገኙ የነበሩ አካባቢዎች አሁን በዝናብ እጥረት እየተጠቁ ነው። የሙቀቱ ሁኔታ እየጨመረ መጥቶ በወይና ደጋነቷ በምቹ አየሯ የምትታወቀው አዲስ አበባንም እየፈተናት ነው። በመዲናችን አዲስ አበባ በአንዳንድ ህንጻዎች ላይ ተገጥመው የምንመለከታቸው የአየር ማቀዝቀዣ መሳሪያዎች ወዴት እየሄድን እንደሆነ አመላካቾች ናቸው።
ችግርን ሲያወሩት ቢውሉና ቢያድሩ መፍትሄ አይሆንም። መፍትሄው የችግሩን ምንጭ መለየትና የሚፈታበትን መንገድ ቀይሶ ሌት ተቀን መረባረብ ነው። እውነተኛ ችግርን መለየት የመፍትሄው ግማሽ መንገድ ነው አይደል የሚባለው! መፍትሔው ደግሞ የሌላውን ዓለም ተሞክሮ ስንቃኝ በእጃችን አለ። እንደ ጌዴኦ፣ ጉጂ፣ ከፋና ወዘተ ዓይነት እጅግ አስደናቂና ታላላቅ ደን የመትከልና የመንከባከብ ታላቅ እሴት እናም ራሳችን ላመጣነው ችግር የራሳችንን መፍትሔ ለመጠቀም አገራችን አረንጓዴ እናድርጋት እንላለን!
ላለፈ ክረምት ቤት አይሰራም ነውና ብሂሉ ተጠያቂው ማንም ይሁን ማን ዛሬ ላይ እጅ መጠቋቆሙ ምንም ጠብ የሚያደርግልን ፋይዳ የለም፤ አይኖርምም። ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ ለአገራችን የደን ሃብት ውድመት ተጠያቂዎቹ ራሳችን እኛው ኢትዮጵያውያን መሆናችን ነው።
ይኸንንም ለማድረጋችን ብዙ ዋጋ እንደከፈልን ሊዘነጋ አይችልም። በ1966፣ በ1977፣ 1988 እና በ2006 ዓ.ም በአገራችን ተከስተው የነበሩ የድርቅ አደጋዎች የደን ሃብታችን በአግባቡ ባለመጠበቃችን የደረሱብን ቅጣቶች ናቸው ብሎ መውሰድ ይቻላል። በተለይም በ1966 እና በ1977 ዓ.ም ድርቅ የበርካታ ዜጎቻችን ህይወት የቀጠፈና የአገራችንን ገጽታ በእጅጉ ያጠለሹ እንደነበሩ በቁጭት የምናስታውሰው ነው።ስለዚህ ችግሩን የፈጠርነው እኛው በመሆናችን መፍትሄውም በእኛ እጅ ነው ያለው።ለዚህ ደግሞ በአረንጓዴው አሻራ መርሐ ግብር ሆነ በሌሎች ወቅቶች ችግኞችን በመትከል የድርሻችን እንወጣ።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 20/2011