የተወለዱት በቀድሞው ጎጃም ክፍለ ሀገር በ1954 ዓም ነው። አባታቸው የመንግሥት ሠራተኛ ስለነበሩ በተለያዩ ክፍለ ሀገራት ይዘዋቸው ይዞሩ ስለነበር የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን የተማሩት በነቀምቴ ከተማ ሲሆን ስምንተኛ ክፍልን በሀዋሳ ከተማ ነው። ከዘጠነኛ ክፍል በኋላ ግን እርሳቸውና ቤተሰቦቻቸው በመናገሻዋ ከተማ አዲስ አበባ ላይ ከተሙ። በአዲስ አበባም ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት እስከ 12ኛ ክፍል የተሻገረው ትምህርት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዘለቀ። በዚያም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በጂኦሎጂ ትምህርት ዘርፍ ወሰዱ። በዚህም ሳያበቁ ወደ ሆላንድ በመሄድ በሃይድሮ ጂኦሎጂ ዘርፍ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ያዙ። የዛሬው የዘመን እንግዳችን አቶ ሰብስቤ አለምነህ በተማሩበት ዘርፍ በተለይም በከርሰ ምድር ውሃ ፍኖተ ካርታ ሥራ በጂኦሎጂ ጥናት ኢንስቲትዩት ዘጠኝ ዓመት አገልግለዋል። በአሁኑ ወቅት በአማካሪነትና በግል ሥራ ውስጥ ይገኛሉ። በቅርቡ ደግሞ ከሙያቸው ወጣ ብለው የ‹‹ብሔር ማንነት ቅዠት›› የሚል መጽሐፍ ጽፈዋል። በፃፉት መጽሐፍና በሌሎችም አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገናል። እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ ከሰለጠኑበትና ከሚሰሩበት ሙያ ወጥተው መጽሐፍ ለመፃፍ ምክንያት የሆነዎት አብይ ጉዳይ ምን እንደሆነ ይንገሩንና ውይይታችንን እንጀምር?
አቶ ሰብስቤ፡- እኔ ይህንን መጽሐፍ ለመፃፍ ያነሳሳኝ በተለይ ኢህአዴግ ከመጣ በኋላ የኢትዮጵያ ህዝብ በብሄር ማንነት መከፋፈል ሲጀምር ከደረሱብኝ አንዳንድ ኢሰብዓዊ ድርጊቶች በመነሳት ነው። ምንአልባት ድርጊቱን መጥቀስ ካስፈለገም የመጀመሪያው ጉዳይ በመንግሥት መስሪያ ቤት ለዘጠኝ ዓመት ስሰራ በጣም ከምወደው ጓደኛዬ ጋር በብሄር ምክንያት መጣላቴ ነው። ከዚህ ግለሰብ ጋር በርካታ አመታትን በፍቅር ተቻችለን ብንኖርም ኢህአዴግ በህዝቡ ላይ በዘራው አስተሳሰብ ሳቢያ ብሄርን ተገን አድርጎ «አንተ ነፍጠኛ ነህ፣ እናንተ ጨቋኞች ናችሁ» እያለ ሰደበኝ። ያን ጊዜም ራሴን መጠየቅ ጀመርኩ። እኔ ባልሰራሁት ሥራ የምወቀስበትና የምሰደብበት ምክንያት ምንድን ነው ስል ማሰብ ጀመርኩ። በተመሳሳይ በሌሎች አካባቢዎች ለሥራ ጉዳይ ስሄድ «ይሄ እኮ የእኛ ሰው አይደለም» እያሉ ያገሉኝ ነበር። የሚገርመው ደግሞ እንደዚህ አይነት መገለል ያጋጠመኝ በመንግሥት ተቋም ውስጥ መሆኑ ነው። እነዚህ ነገሮች ነገሩን በጥሞና እንዳስብበት ነው ያደረጉኝ። በተለይ የብሄር ማንነት ጉዳይ ማሰላሰል ከጀመርኩ 25 ዓመታት በላይ ይሆነኛል። ይሁንና ልክ የዛሬ 15 ዓመት ገደማ ሳብሰለስለው የነበረውን ጉዳይ ምንነት ደረስኩበት። ከዚያ ከብዙ ብሄርተኞች ጋር መከራከር ጀመርኩ። የብሄር ማንነት የሚባል ነገር የለም፣ ማስረጃም የላችሁም በሚል ነው ክርክሬን የጀመርኩት።
አዲስ ዘመን፡- እንደዚህ አይነት ድምዳሜ ላይ ከመድረስዎ በፊት ያነበቡት፥ የደረሱበት ጥናት፥ ያገኙት ውጤትና ማስረጃስ ነበር?
አቶ
ሰብስቤ፡- ምንም የለም፤ እንዲሁ ማህበራዊ እውነታዎች
ላይ ነው መሰረት ያደረኩት። ወይንም ማህበራዊ እውነታዎችን ነው መመርመር የጀመርኩት። እርግጥ ከየት መጣ ለሚለው ለምሳሌ የብሄር ማንነት ለሚለው የተለያዩ መፃህፍትን አንብቢያለው፤ የእነ ስታሊን ትርጓሜዎችን፥ ማርክሲዝምና ሌኒኒዝም ላይ የተፃፉ መፃህፍትን በማንበብ ብሄርተኝነት ከቅኝ ገዢዎች የተወለደ እንደሆነ ተረድቻለሁ። ይኸው ጉዳይ በእኛም አገር መጥቶ በ1963 ዓ.ም አካባቢ የብሄር ጥያቄ ሆኖ መነሳቱን ለማንበብ ሞክሬያለሁ። የብሄር ማንነት የሚባል ነገር የለም ወደ ሚል ድምዳሜ የደረስኩበት ሌላው ምክንያት ብሄር የሚባል ነገር ስለመኖሩ የሚያረጋግጥ ስነ ፅሁፍ በአለም ላይ ባለመኖሩ ነው። የብሄር ማንነት ቅቡልነትን አግኝቶ እውነታው፣ በመረጃ የተደገፈና የተያዘ ጉዳይ ቢሆንም ግን የተቀመጠ መረጃና ማስረጃ የለም። ዝም ብሎ ተተረጎመ ግን የመረመረው ሰው የለም። ይህ አስተሳሰብ ወደ ኢትዮጵያም ሲገባ ማንም ለምርምር ጥረት አላደረገም።
ይህ የብሄር ማንነት አስተሳሰብ ቅኝ ገዥዎችም ለመከፋፈል በጣም የሚጠቀሙበት መሳሪያ ነበር። በተለይም ፋሺስት ኢጣሊያ የሚጠቀምበት ተንኮል የተሞላበት አስተሳሰብ ስለመሆኑ የታሪክ እውነታ ያስረዳናል። በዋናነትም በትምህርተ ጥቅስ ውስጥ አስገቢልኝና በቁጥር ትልቅ የሚባሉ ብሄሮች ተጠቅሞ ለመከፋፈል የተጠቀሙበት መንገድ መሆኑን አንብቢያለሁ። ይህም የሚያሳየው ክፋቱን እንጂ የብሄር ማንነት አለ የሚል ማስረጃን አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- የብሄር ማንነት ስለመኖሩ የሚያስረዳ ማስረጃ ባለመኖሩ የለም ብሎ ለማለት በራሱ ማስረጃ አያስፈልግም ወይ? ምክንያታዊነትስ ጥያቄ ውስጥ አይገባም?
አቶ ሰብስቤ፡- ድፍረት አልሆነብኝም። ምክንያቱም ያለኝ ተጨባጭ መረጃ ለእኔ መተማመንን የፈጠረልኝ በመሆኑ ነው። ያለኝ መረጃ በጣም ውስብስብ አይደለም። ማህበራዊ እውነታ ነው። ማንም ሰው ሊገነዘበው ሊረዳው የሚችል በጣም ቀላል ጉዳይ ነው። በመሆኑም ለእኔ ምንም ችግር አልሆነብኝም። በተለይ በአሁኑ ወቅት አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ብሄር አለኝ ብሎ የሚያስብበት ወቅት ነው። አንዳንዱ እንዲሁ ይጠላዋል፤ የሚጠላውም ውጤቱን አይቶ ነው። ውጤት ሲባልም ሰው ለሰው የሚያለያይ፣ የሚያጋድል፣ የሚያጣላ፤ ትዳር የሚያፋታ በመሆኑ ነው። እኔ አሁን ለምሳሌ ከአንዱ ጓደኛዬ ጋር በብሄር ምክንያት ተለያይተናል። እንደዚህ ሲደረግ ሲያዩ ውጤቱን መጥፎ ነው ቢሉም የብሄር ማንነት ያላቸው ይመስላቸዋል። ይህም ሲባል ውጤቱ እንዲሁ በእውቀት አይደለም የሚጠሉት።
ይህ አስተሳሰብ በተንሰራፋበት ዘመንና አገር ‹‹የብሄር ማንነት የለም›› ሲባል እንዳልሽው አንተ ራስህ አብደሃል ወይም ቃዥተሃል ሊያስብል ይችላል። ይሁንና የዓለምን ታሪክ ስትመለከችው ለምሳሌ መሬት ጠፍጣፋ ናት ተብሎ ሁሉም የዓለም ህዝብ በሚባል ደረጃ ተቀብሎት ነበር። ክሊኒከስ የሚባለው ተመራማሪ ግን ‹‹አይ መሬት ጠፍጣፋ አይደለችም ድቡልቡል ነች›› ብሎ ሲነሳ እብድ ነው አስብሎታል። ግን በመረጃ ግን አለምን ረቷል። በሌላ በኩል የሬዲዮን ግኝት ስትመለከቺ መጀመሪያ ሰው በአካል ሳይገናኝ ሬዲዮ በሚባል ኤሌክትሮ ማግኔቲክ ዌቭ መገናኘት ይችላል ብሎ ሃሳቡን ሲያቀርብ ይሄ ሰውዬ ‹‹ቀውሷል እብድ ነው›› ተብሎ ብዙ መከራ ተቀብሏል። ይሁንና እሱም በመረጃ ረቷቸዋል። ስለዚህ እኔም በዚህ ብሄርተኝነት አስተሳሰብ በጎላበት ውስጥ ማህበረሰብ የብሄር ማንነት የለም ብሎ መነሳት እንደ እብድ እና ቅዠታም ሊያስቆጥረኝ ይችላል። ግን መረጃ ነው የሚለውጠው።
አዲስ ዘመን፡- ምንድን ነው አገኘሁት የሚሉት ተጨባጭ መረጃ?
አቶ ሰብስቤ፡- የሰው ልጆች እንዴት እንደተፈጠሩ ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ እሳቤው ባሻገር የተለያዩ ፍልስፍናዎች እንዳሉ ይታወቃል። በመንፈሳዊውም ሆነ በሳይንሳዊው መንገድ ሁለቱም ሰው መፈጠሩን ይስማማሉ። ይሄ ሰው ሲኖር ግን ራቁቱን ጫካ ይኖር የነበረ ነው። ልብስ አልነበረውም፤ እንደ እንሰሳ ይኖር የነበረ ሰው ነው። ከተዋለደ በኋለ የአስተሳሰብ አንድነት እስኬለለ ድረስ ግጭት ይፈጠራል፤ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ አካባቢው ለኑሮ አልመቻቸው ሲል ደግሞ ይለያያል። ይሄ ሁሉ ለምንድነው የሚሆነው? ብለሽ ብትጠይቂ ደግሞ የሰው ልጅ ሲፈጠር ኑሮ ነው የጀመረው። ከችግር ጋር አብሮ ነው የተፈጠረው፤ ስለዚህ ሁልጊዜም ይታገላል። ምክንያቱም ሞትን ይፈራል። የሰው ልጅ በሞት የታሰረና በሞት ቁጥጥር ሥር የሚኖር ነው። ስለዚህ መሞት ስለማይፈልግና የተሻለ እድሜን መኖር ስለሚፈልግ ሁልጊዜ ከዚያ ሞት ለማምለጥ ሲል ችግርን ለመፍታት በሚያደርገው እንቅስቃሴ ነው መሬት ላይ የቆየው።
ስለዚህ ሲጣላም በይው፤ ለኑሮም አልበቃ ሲለው እሞታለው ብሎ ስለሚያስብ መጋጨት ሳይፈልግና ለህይወቱ ስጋት ሲፈጥርበት ይለያያል። እየተለያየ በመጣ ቁጥርና የሰው ልጅ ቋንቋ ሊናገርበት በሚችልበት ዘመን ሲመጣ ደግሞ የየራሱን ቋንቋ ነው የፈጠረው። መናገር የቻለውም የሰው ልጅ ከእንስሳ የሚለይበት የአዕምሮ ብስለትና አቅም ስላለው ነው። ያ አቅሙ ደግሞ ለመወያየት፥ ለመነጋገር ችግሩን ለመፍታት ነው። እስካሁንም ድረስ ማንኛውም የሰው ልጅ እንቅስቃሴ የሚያደርገው ችግሩን ለመፍታት ነው። ለመኖር እንጂ የብሄር ማንነት አስጨንቆት አይደለም። የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች ሲፈጠሩ ሁልጊዜ ለሞት ስጋት የሚሆንበትን ችግር መፍታት ነው ዋናው ትግሉ። ከዚያ አንፃር ስለሚበርደው የሚከላከልበትን ነገር ያስባል። ሲያስብ ደግሞ ወይ ልጥ ይለብሳል፤ የማሰብ አቅሙ በፈቀደለት መጠን ልጡን ወደ ቆዳና ጨርቅ እየቀየረው ይመጣል። ይህ ከችግር ለመላቀቅ የሚያደርገው ጥረትና አስተሳሰብ ከሌላው ማህበረሰብ የሚለይበት እንጂ ባህሌ ብሎ የሚይዘው በአዕምሯዊ ንብረትነት እውቅና ያለው ወይንም ያበቃ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ባህሌ ብሎ የሚይዘው ነገር አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- እያንዳንዱ ብሄረሰብ የራሱ የሆነ መለያ ቋንቋ ባህል አመጋገብና የተለያዩ መለያዎች ያሉት በመሆኑ ለራሱ እውቅና ሰርተፍኬት መስጠት አይችልም እያሉኝ ነው?
አቶ ሰብስቤ፡- ሲጀመር የብሄር ማንነት በሌለበት የምን ሰርተፍኬት ነው የሚሰጠው? ምክንያቱም ሰው ሁልጊዜም እንቅስቃሴ ላይ ነው ያለው። እየተውሽው ነው የምትሄጅው። ልጥ ይለብስ ነበር አሁን ትቶታል። ልጡን ሙዚየም ወይም በታሪክ ማህደር ውስጥ ማስቀመጥ ትቺያለሽ። ነገር ግን ይሄ በራሱ የሚያስደንቅ ነገርም አይደለም። ከዚያም ቀጥሎ ቆዳ መልበስ ጀመረ። ቆዳንም አስቀምጦ ጨርቅ መልበስ ጀመረ። እናስ ቆዳ መልበስ ነው ወይስ ልጥ መልበስ ነው ባህሌ ልትይው የምትችይው? ወይስ ዋሻ ውስጥ መኖሩ ነው? ወይንስ ራቆቱን መኖሩ ነው?። ወይስ እንደ እንስሳ እየገደለ ስጋ እያደነ መብላቱን ነው? ምኑን ነው ባህሌ የምትይው?። አሁን እኮ የሰው ልጅ ማርስ ላይ ለመኖር ዝግጅት እያደረገ ያለበት ወቅት ነው። ስለዚህ የተሻለ ኑሮ ሁልጊዜም ቢሆን ተለዋዋጭ /ዳይናሚክ/ እየሆነ ነው የሚመጣው። ስለዚህ የእኔ ብሄር ይሄ ነው ብለሽ ልትናገሪው የምትችይው ነገር የለም። ምክንያቱም የማይለወጥ የተባለው የሚለወጥ በመሆኑ ነው።
በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ወደ 7ሺ 200 የሚሆኑ ቋንቋዎች አሉ። የሰው ልጅ መናገር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ወደ 31 ሺ ቋንቋ ነበረው ተብሎ ይታሰባል። ነገር ግን ጉልበተኛው ደካማውን በመያዙ እየቀነሱ እንዲመጡ ተገደዋል። በተለይም ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ጀምሮ ደግሞ አገራት በኃይል እየተመሰረቱ ሲመጡ ቋንቋዎች እየጠፉና በኃይለኛውና ኢኮኖሚውን በሚቆጣጠረው ቋንቋ እየተዋጡ ሰባት ሺ ደርሰዋል። አሁንም እየቀነሰ ያለ ልምምድ ነው። በሌላ በኩል ለምሳሌ ኒውዮርክ ብትሄጂ ከየትኛውም ዓለም ያልመጣ ህዝብ የለም ለማለት እቸገራለሁ። ግን የሚጋሩት አንድ አይነት የአኗኗር ዘይቤ ነው። መኪና ይነዳሉ፤ በርገር ይበላሉ ፣ ይሄ የእኔ የምትይው ብሄር ሳይሆን ያለሽ ሁልጊዜ ችግርን የመፍታትና ወደ ተሻለ የኑሮ ደረጃ የመሄድ እንቅስቃሴ ብቻ መኖሩን ያሳየናል። አዲስ አበባ ብትመጪ እኔና አንቺን የሚለየን የለም። ከየትም ነይ ከየትም ልምጣ የምንለይበት ምክንያት የለም። የምንከተለው አንድ ዓይነት የኑሮ ዘይቤ ሆኖ እያለ እንዴት እከሌ ከእከሌ ብሄር ነው የመጣው ብሎ መለየት ይቻላል?
አዲስ ዘመን፡- ምንአልባት መልኩን አይተን ባንለየውና ብሄሩን ባይነግረኝም ከአነጋገሩ፣ ከሚያዘወትረው ነገር፣ ከልምዱ፣ ከአመጋገቡ ይህ ሰው የእገሌ ብሄር ተወላጅ ነው ልለው የምችልበት ሁኔታ የለም?
አቶ ሰብስቤ፡- በእኔ እምነት እንዲህ ነህ ተብሎ ስያሜ የሚሰጠው ለማይቀየር ነገር ነው። ለምሳሌ ወርቅ የትም ቦታ ብትወስጅው ወርቅ ወርቅ ነው። ብሄር ማንነት ግን ዛሬ እንዲህ ነው ብትይው የዛሬ 10 ዓመት ግን ሌላ ነው። ልክ እንደ ዝግመተ ለውጥ የሚለወጥ ነገር ነው። ለምሳሌ አንድ ሰው ቆጮ ስለሚበላ አንተ ከደቡብ ነህ ልትይው ትቺያለሽ፤ አሜሪካን አገር ባጋጣሚ በርገር ሲበላ ብታይው አሜሪካዊ ነህ ልትይው ነው?
አዲስ ዘመን፡- ከመላመድ የሚመጣ ነገር ሊሆን አይችልም?
አቶ ሰብስቤ፡- ለዚህም ነው በጊዜና በቦታ ይቀያየራል የምልሽ። ወርቅ ግን አይቀያየርም።
አዲስ ዘመን፡- ግን የመጣበትን ብሄርና ቦታ ሊክድ ይችላል?
አቶ ሰብስቤ፡- የመጣበትማ ማንም መጥቷል። ከዝቅተኛ የኑሮ ደረጃና ከራቁትነት ልብስ እየለበሰ ከየአካባቢው መጥቷል። ይሄ ዳይናሚዝም ነው። እንበልና ሆሞ ሳቢያን መጣ የሚባለው የዛሬ 200ሺ ዓመት ነው። እኔና አንቺ የመጣነው የዛሬ 200 ዓመት ብንሆን ፤ በዚያ ወቅት የነበርንበትን ሁኔታ ነው ብሄሬ የምትይው? ይሄ ሁሉም የሚጋራው ሰብዕና ነው። አሁንም ቢሆን የሰው ልጅ ሲወለድ ራቁቱን ነው። ስለዚህ ብሄር የሚሉት አስተሳሰብና ድርጊት ሊፈተሽና ሊጨበጥ የሚችል ማስረጃም የለውም። ለእኔ ብሄር ማለት በሌላ አስተሳሰብ መያዝ እና በእሱ ድርጊት ስትፈፅሚ ይሄ ሰው በአዕምሮ ሳይንስ ቃዥቷል ነው የሚባለው። በነገራችን ላይ ቅዠት እኔ የመረጥኩት ቃል አይደለም፤ ራሱ ሳይንሱ የወለደው ቃል ነው። ቃዠ ማለት ያለመረጃ እየኖረ ነው ማለት ነው። ስለዚህ የሰው ልጅ ከጫካና ከምንም ወደ ጨረቃ ላይ ወጥቶ እስከመፈላሰፍ ደርሷል። በየጊዜው የሚያድግና ልክ የሌለው ነው።
የዛሬ 300 እና 400 ዓመት ብትኖሪ አሁን እንደለበስሽው አይነት ልብስ አትለብሽም። ይሄ አሁን የሚያነሳኝ ካሜራ የብሄር ማንነት ያለው ሳይሆን ችግር ፈቺ ነው። የሰው ልጅ ሁልጊዜ የሚያላምደው ነገር ችግርን የሚፈታለትን ነገር ብቻ ነው። አየሽ! ማቃዠት ማለት ይሄ ነው። ስለዚህ ብሄር የሚባል ነገር የለም። በተለያየ የኑሮ ደረጃ እንደየአካባቢው ተሰደው በፈጠሩት «ብሄር» ተብለው የሚጠሩት የህዝቦች ስብስብ ናቸው። ግን እንደመፍጠር አቅማቸውና እንደየአስተሳሰባቸው የኑሮ ደረጃቸው የተለያዩ የሆኑት። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ 84 ብሄር ብሄረሰቦች ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ ብሄሬ ብለው ይዘውት የሚቀጥሉት ነገር የለም፤ እዛው ተጋርተው የሚኖሩት እንጂ። በአመጋገብም ብትይ ይሄ ምግብ የእከሌ ብሄር ነው ማለት አንችልም። ምክንያቱም በአጋጣሚ የመጣ ነው። ሰው ሲኖር ረሃቡን ሊያስታግስለት የሚችለውን ነገር አካባቢው የሰጠውን ነገር ነው የሚለምደው። ሲወለድም የአመጋገብ ስርዓት ይዞ አይደለም የሚወለደው። አካባቢ ስለሰጠን እንጂ ኢትዮጵያውያንም ጤፍ ተመጋቢዎች ሆነን አይደለም የተወለድነው።
አዲስ ዘመን፡- አንድ ሰው ጉራጌ ወይም አማራ ስንለው የራሱ የአለባበስ የአመጋገብ ባህል አለው፤ ይህ ባህል ታዲያ ምንአልባት በጊዜ ሂደት ዲዛይኑ ይለወጥ ይሆናል እንጂ መሰረታዊ ይዘቱን አይለቅም። ለዚህም ነው ከትውልድ ትውልድ እየተሸጋገረ እኛ ጋር የደረሰው። እና ይህ እውነታ እርሶ ከሚሉት ሃሳብ ጋር አይጣረስምን?
አቶ ሰብስቤ፡- ይኸውልሽ ዝም ብለሽ ልምዱን እዪ፤ እኔ ለምሳሌ የማላውቀውና የለም ብዬ የምለውን አንድ ብሄር ብትጠቅሽልኝና እዚያ የተወለደች ልጅ በተወለደችበት አካባቢ የአካባቢውን ልብስ ስትለብስ ኖራ አዲስ አበባ ስትመጣ ሱሪ ትለብሳለች። የሰው ልጅ የኑሮ ደረጃ የፈቀደለትን ይለብሳል እንጂ የኑሮ ደረጃው ቢያድግ የተሻለ የሚያምር ነገር ይላመዳል። በነገራችን ላይ አሁን አለ የምትይውም ባህላዊ አለባበስ ድሮ አልነበረም፤ ድሮ ሸማ ብቻ ነበር የሚለበሰው ።አሁን ግን ሸማ ብቻ ሳይሆን ሻማም ይለበሳል። ለምሳሌ 1966ዓ.ም ድረስ የሲዳማ ሴቶች ሙሉ ለሙሉ የበግ ቆዳ ከትከሻቸው እስከጥፍራቸው ድረስ ለብሰው ነበር የሚመጡት። ይሄንን አሁን ለምን አይለብሱትም ታዲያ? በቃ አለቀበት፤ በጊዜው የማሰብ ችሎታቸው የአኗኗር ደረጃቸው ያ ነበር። የኑሮ ደረጃ ድንበር የለውም። የኑሮ ደረጃ ድንበር ቢኖረው ኖሮ እኮ ቴክኖሎጂዎች በተፈጠሩበት ቦታ ተገድበው ይቀሩ ነበር። ሁሉም በሚባል ደረጃ ቴክኖሎጂዎችን ከውጭ ነው የምናስመጣው። ለዚህም ነው እኔ ይሄን አስተሳሰብ ነው ዝም ብለው የፈጠሩት ቅዠት ነው የምለው። ሲጠናወታቸው ከዚያ የቅዠት ዓለማቸው ላለመውጣት የሚሄዱበት ክርክር እንጂ ከልባቸው ቢያስቡበት ያገኙት ነበር። ግን ሚዛናዊ ሆነው ማሰብ አይፈልጉም።
ደግሞም እኮ በገጠር የሚኑሮ ሰዎች መኪና እያላቸው ነው በበቅሎ የሚሄዱት ወይም ጫማ እያላቸው ነው ባዶ እግራቸውን የሚሄዱት ብትይም ማንም አይቀበልሽም። የሰው ልጆች የተሻለ ኑሮ ለመኖር ጥረት ላይ ናቸው። አሁን እስቲ አሜሪካ በነፃ መሄድ ይቻላል ቢባል የኢትዮጵያ ህዝብ ከገጠር ጀምሮ አይሰለፍም? ምክንያቱም የተሻለ ኑሮ ስለሚፈልግ ነው። ይህንን የሚያደርገው አገሩን ከመጥላት አይደለም፤ የተሻለ ኑሮ ፍላጋ እንጂ። ሌላው ይቅርና ከፍተኛ አደጋ አለበት በሚባልበት አረብ አገር እንኳ ሰዎች ባህር ውስጥ እየተጣሉ መሆኑን እየተነገራቸው ብዙዎች እየጎረፉ አይደለም እንዴ? ለምን ታዲያ ብሄሬን ብሎ አይቀርም? የኑሮ ደረጃን ለማሻሻል እንጂ ሌላ ጉዳይ ኖሮት አይደለም። ብሄር የሚባለውን ነገር በሰው ልጆች አዕምሮ የፈጠሩት ለምሳሌ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የሚሰሩት ሴራና በተለይም አመክኗዊ የአስተሳሰብ አቅማቸው ደካማና ድሃ የሆነውን የድሃ አገራት የሚያተራምሱበት የተንኮለኞች ቃል ነው።
አዲስ ዘመን፡- ግን እኮ በሰለጠኑት አገራት በእነሱም አገር ብሄርተኝነት አለ፤ ለአብነት መጥቀስ ከተቻለ ጀርመኖች በብሄርተኝነት በጣም ይታወቃሉ። ስለዚህ ብሄርተኝነት ወይም የብሄር ማንነት ያለው ባልሰለጠኑት አገራት ብቻ ነው ማለት እንችላለን?
አቶ ሰብስቤ፡- እነሱም ብሄርተኛ የነበሩት ቅዠት ውስጥ ስለነበሩ ነው። ሂትለር ቅዠታም ነበር።
እንዳልሽው ጥቁር ብቻ አይደለም የሚቃዠው። እነሱ ነቅተው ግን ቀድመው አቁመውታል። በእርግጥ በአንዳንድ አገራት አሁንም አለ። ግን በዘመናዊ መልኩ በህግና በስርዓት አስታግሰውታል። አስተሳሰቡን ማራመድ ይቻላል ነገር ግን መተግበር አይቻልም፤ ምክንያትም በህግ በታሪክ ማህደር ታግዷል። ነገር ግን በደሃ አገራት በተለይ በርካታ ቋንቋ ባለባቸው አገራት ድህነት የተቆራኘ በመሆኑ ይህንን እድል በመጠቀም ምሁራንና በኢኮኖሚና በገንዘብ ኃያል ነን የሚሉ እያማለሉ ይጠቀሙበታል። ይህንን የምነግርሽ ዝም ብሎ ምናባዊ የሆነ መላ ምት አይደለም፤ በተጨባጭ ይጠቀሙባቸዋል። እነሱ የተያያዙት በፖለቲካ ስም ሥራ መፍጠር ነው። ህዝብ እያጋደሉና እያጫረሱ ግን ደግሞ እነሱ ብሄር የሚባል ነገር ሳይኖራቸው ነው የብሄር ማንነት የሚሉት። እነሱ የተሻለ ኑሮ እየኖሩ ደሃውን ለማጫረስ ማንነትህ ተረግጧል ይሉታል። የሚገርመው ባዩ ራሱ ነው ማንነት የሚለውን ነገር አይጠቅመኝም ብሎ ጥሎት የሄደው። በእንደዚህ አይነት መንገድ የሚያተራምሱ ምህረት የሌላቸውና ህሊናቸውን ያጡ ሰዎች መሳሪያ ነው የብሄር ማንነት።
አዲስ ዘመን፡- በእርስዎ እይታ ማንነት ከኢኮኖሚ ጋር አብሮ የሚያድግና የሚቀየር ነው ሲሉ ምን ማለትዎ እንደሆነ እስቲ ያብራሩልኝ?
አቶ ሰብስቤ፡- በትክክል እንዳልሽው ነው። አንደኛው ምክንያት በኢኮኖሚ ድሃ መሆን ነው። የድሃ አገራት አዕምሮ በምክንያታዊነት የዳበረ አይደለም። ነገሮችን የመመዘን ሚዛናዊ አስተሳሰብ የለንም። በድሃ አገር ውስጥ ምሁራን የሚባሉትም ኢትዮጵያን ጨምሮ መማር ከዳቦ እና ከችግር ጋር የተገናኘ ነው እንጂ ችግር ከመፍታት ጋር የተገናኘ አይደለም። ምክንያቱም ቤተሰቦቻቸው ድህነት ያራቆተው የኋላ ታሪክ ነው ያላቸው። ስለዚህ የትምህርቱ ሁኔታ ዳቦ መብላት ላይ ያነጣጠረ ነው። እንዲያውም ድህነቱ ሲብስ በፖለቲካ ስም ልትነግጂ ትቺያለሽ። የምክንያታዊነት አቅሙ የመመርመር ነገር የለም ። ለዚህም ነው ብሄርተኝነትን ሲያመጡብን ሳንመረምር የተቀበልነውና እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ቃል ሥራ ላይ የዋለው። የመመርመር አቅም ቢኖረን ኖሮ ከመጀመሪያውኑ ይህንን አጥፊ አስተሳሰብ ወደ ጎን ማድረግ ይቻል ነበር። አሁን ደግሞ 27 ዓመታትም ተሂዶበት እስካሁን እንደ አዲስ ነው የሚያገረሸው። ለምን ብትዬ ሰዉ በበሽታው እንደተጠቃ ነው። ብሄርተኝነትና የሚያራምዱት ሰዎች የሚያወሩትና የሚኖሩት ነገር ምንም ግንኙነት የለውም። እነሱ ሳይኖሩበት በአስተሳሰቡ ሌሎችን ይነዱበታል።
የሰው ልጅ ድርጊቱ ከአስተሳሰቡ ነው የሚመነጨው። አስተሳሰብ ከሌለ ድርጊት የለም። ለዚህም ነው ልክ ኮምፒዩተር ላይ እንደሚጫን ቫይረስ ነው ሰው ላይ የጫኑት። በተለይ በኢትዮጵያ ውስጥ ዶክተር የሆኑና የተማሩ ሰዎች የሚባሉት ሰዎች ናቸው ቃዥተው ሰውን ወደ አልሆነ መስመር የሚከቱት። ምክንያቱም እነሱ የሚናገሩት ሁሉ በህዝቡ ዘንድ ቅቡልነት ስላለው ነው። በእኔ እምነት የብሄር ማንነት የሚባል ነገር የለም፤ አንዳንድ ጊዜ ይገርመኛል ብዙ ተናጋሪ ያላቸውና ብዙ ቁጥር አለን ብለው የሚመኩትም ሆነ አነስተኛ ህዝብ ነው ያለን ብለው የሚቆጩትም ቃዥተዋል። ምክንያቱም ምንም ማስረጃ የላቸውም።
ኢትዮጵያ ውስጥ መሆን ያለበት የሰው ልጅ የሚያስፈልገውን አንድ አይነት የኑሮ ደረጃ ማምጣት ነው። የተረጋጋ ኑሮን የማይፈልግ ሰው አለ? ጫማ የማይፈልግ አለ? መኪና የማይፈልግ አለ? መኖሪያ ቤት የማይፈልግ አለ? ልብስ መልበስ የማይፈልግ አለ? አየሽ ሁሉም የሚጋሩት ጉዳይ አለ፤ ይኸውም በኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆንና የተሻለ ኑሮ መኖርን ነው። ስለዚህ በኢትዮጵያ ውስጥ በብሄር ማንነት ቅዠት ከማራመድ ይልቅ የተሻለ የኑሮ ደረጃን ለማምጣት ነው ትግል መደረግ ያለበት። የሰው ልጅ ትግል ሁልጊዜም ከኑሮ ጋር እና እዚህች ምድር ላይ ለመቆየት ነው። በነገራችን ላይ የብሄር ማንነትና አደረጃጀት ሳይንስ አይደለም፤ አገዛዝ እንጂ። አቃዠቶ የመግዛት አባዜ ነው።ለምሳሌ ፖለቲካ ሳይንስ ነው።ይህንን ስንልም ሳይንስ የሰዎችን ችግር ሁሉ በእኩልነት የሚፈታ ነው። ሞባይልን ብትወስጂም ሰዎች ሁሉ ይጋሩታል። ምክንያቱም ችግር ፈቺ የሳይንስ ግኝት ነው። አየሽ ሳይንስ ዓለምአቀፋዊ ነው። አስቀድሜ እንዳልኩሽ እንጀራን የምንበላው በአካባቢያችን ስላገኘነው ነው። ጀርመናዊ ኢትዮጵያ ውስጥ መጥቶ እሱ የለመደው ምግብ ስለሌ በርሃብ አይሞትም። አገሪቱ ያፈራችውን እንጀራ ይበላል። በነገራችን ላይ ሁልጊዜ የምትበይውም ምግብ ሱስ ያሲዝሻል፤ ይህ ተፈጥሯዊ እውነታ ነው። ከዚህ ውጭ እንጀራ የምንበላው ባህላችን ስለሆነ አይደለም። ለዚያ ለተወሰነ ምግብ የተፈጠረ ሰው የለም። በአንፃሩ ደግሞ የብሄር ማንነት ግን ዓለም አቀፍ ችግርን አይፈታም። ምክንያቱም ሳይንስ አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት ብሄርተኝነት የሚያራምዱም ሆነ የዜግነት ፖለቲካን የሚ ያራምዱ አካላት ዘረኞች ናቸው የሚል አስተሳሰብ ጎልቶ ይሰማል። በእነዚህ ሁለት አስተሳሰቦች ላይ ምንድነው ያለዎት አስተያየት?
አቶ ሰብስቤ፡- የብሄር ማንነት አስተሳሰብ ነው። ሳይኮሎጂካልና ማቴሪያሊስቲክ ነው። አገር በየትኛውም ዓለም ላይ በጉልበት ተመስርቷል። አገርንና ህዝብን በኃይል በማስገደድ የመሰረተው ህዝብ አይደለም፤ ግለሰብ አምባገነኖች እንጂ። ይሄ የኢትዮጵያ በሽታ ብቻ አይደለም፤ የዓለምም ጭምር እንጂ!።
አዲስ ዘመን፡- ይቅርታ ላቋርጦት እና ህገመንግሥቱ አገሪቱን የገነቡት ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች መሆናቸውን ይገልፃል፤ እርስዎ ህገመንግሥቱን ይቃወማሉ ማለት ነው?
አቶ ሰብስቤ፡- አዎ አልቀበለውም! ምክንያቱም አገርን የመሰረቱት ግለሰብ አምባገነኖች በመሆናቸው ነው። የሚነሳውም በግለሰብ ደረጃ ነው፤ በኢትዮጵያ አምባገነን መሪ ሲነሳ የሚያስገብረው በመጀመሪያ አጠገቡ ያለውን ቋንቋ ተናጋሪ ነው። ለምንድ ነው አምባገነኖች የሚነሱት? ካልሽኝም በመጀመሪያ ራሳቸውን ለመጠበቅ ነው። ሁሉ ነገር የሚነሳው ከራስ ነው። ራስን ለማስጠበቅ በአካባቢያችን ሁሉ ያለውን ለመቆጣጠር ጥረት እናደርጋለን በውድም በግድ ማለት ነው። ከሰፈር የተነሳው የማስገዛት በሽታ እየሰፋ እየሰፋ ሄዶ ድንበሮች የሚለዩት በወዲያኛው በኩል ያለው ሰውና በወዲህ በኩል ያለው ሰው አትድረስብኝ፤ አልደርስብም ተባብለው ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያም የተመሰረተችው በዚሁ መልክ ነው። ከአገር ምስረታ በፊት የሰው ልጆች በስርዓት አልበኝነት ነበር የሚመሩት። አንዱ አንዱን እየገደለ ነበር የሚኖረው።
አሁን እንኳን በኢትዮጵያ ውስጥ ኩታ ገጠም የሚባሉት ብሄርተኞች አንዱ አንዱን ካልሰደበ ካልገደለ ሚስት እንኳን አያገኝም። ይሄ የተመሰረተው ወሰን (ድንበር) አምባገነኖች ራሳቸውን በአስተማማኝ ቅጥር ቀጥረው በመቀጠልም በማስፋፋት ሌላውንም ቋንቋ ተናጋሪ ለማስገበር በራሳቸው አገዛዝ ስር ካስገቡ በኋላ ህግ የሚባል ነገር መጣ። ህግ ሲመጣ ነው ሰዎች በሰላም ወጥተው በሰላም መግባት የቻሉት። ከዚህ በኋላ አምባገነንነቱ አይቆምም፤ ሶሻል ርዕዮተ ዓለም ይቀጥላል። እኛ አገር ይህ ስላልመጣ ነው አሁን ያለው ማዕበል የሚታየው። ወደ ፊት ህዝብ የመረጠው አገዛዝ ሲመጣ ማዕበሉ ያቆማል። ስለዚህ እነዚህ አምባገነኖች በጊዜው አስፈላጊ ነበሩ። እዚህ ቁጭ ብለን የምናወራው ህግ ስላለ ነው።
ኢትዮጵያውያን ሲወለዱ ኢትዮጵያ ከምትባለው ምድር ጋር አብረው የተወለዱ አይደሉም። ነገር ግን ሰዎች ሲኖሩበት የነበረውን በሃይል፣ በጉልበት ዳር ድንበሩን ያስከበረ ሃይል አለ። ለምሳሌ የቀደሙት ነገስታት የአገራቸውን ድንበር አስከበሩ ግን ይዘውት አልተቀበሩም። ጥለውት ነው የሄዱት። በጊዜው ግን የራሳቸውን ንግስና ለማስቀጠል ህግና ስርዓት የሰፈነባት አገር ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል። ይሁንና ይሄ በዚያ አያበቃም። የሰው ልጅ የተሻለ የኑሮ ደረጃ ስለሚፈልግ አሁንም መጠየቁን አያቆምም። ይህ ተፈጥሯዊ የኑሮ ሁኔታ እያለ አሁን ላይ ቋንቋዬ፣ እንዲህ ሆኜ የብሄር ጭቆና ደርሶብኝ የሚባል ነገር የለም። ቋንቋዬ ማለት አይቻልም። ቋንቋ ባለቤት የለውም።
አዲስ ዘመን፡- ነገር ግን ብሄሬ ወይም ቋንቋዬ ተጨቁኗል ብሎ በሚያስብ ማህበረሰብ ውስጥ ጭቆና የለም ማለት የሰዎችን ህመም እንደ አለመረዳት አይቆጠርምን?
አቶ ሰብስቤ፡- ይህ አስተሳሰብ ካለመረጃ የሚመነጭ ነው፤ ይህን የሚለው ሰው ራሱ የነገሩትን ነው መልሶ የሚናገረው። ቁጭት እንዲፈጠርበት የነገሩትን የውሸት ትርክት ነው የሚናገረው። አንቺ እንድትከተይኝ ከፈለኩ አንቺ ላይ ቁጭት እንዲፈጠር እጥራለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ማንም ሳይነግረኝ ይህ ስሜት ሊያድርብኝ አይችልም ማለት ነው?
አቶ ሰብስቤ፡- ላመጣልሽ እኮ ነው፤ ይህንን ያደረጉት አምባገነኖች ናቸው አይደል የሚባሉት? አንደኛ አምባገነኖች የራሴ ብሄር አለኝ ብለው አያስቡም። ዝም ብለው ማስገበርና አምባገነነ የመሆን አስተሳሰብ ነው ያላቸው። አንቺ የፈለገሽዉን ቋንቋ ተናገሪ፣ የፈለገውን ብሄር አነጋገርሽ አለባበስሽ፣ የምትናገሪውን ቋንቋ ግድ አይሰጣቸውም። እነሱ ከብሄር ማንነት ጋር ጨዋታ የላቸውም። እኛን ባላችሁበት ብሄራችሁን ‹ ባህላችሁን‹ ቋንቋችሁን ጠብቁ፤ አሳድጉ የሚሉን ከፋፍሎ ለመግዛት ነው።ምኑ እንደሚጠበቅ አይታወቅም። በሳር ቤት በቆሻሻ ከከብቶች ጋር መኖርን ነው የምጠብቀው?። ወይስ በባዶ እግሬ መሄዴን ነው የምጠብቀው?። በከብት ማረሴን ነው የምጠብቀው? ህፃን ልጅ ከብት ስጠብቅ መኖሯን ነው መጠበቅ ያለብኝ? ይልቁንም ማሳደግ የሚገባን ከሳር ቤት ወደ ቆርቆሮ፣ ከባዶ እግር ወደ ጫማ ነው ማሳደግ አለብን ተብሎ መነገር ያለበት። ሁሉም ከብሄር ማንነት ቅዠት ውስጥ ወጥቶ ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ደፋ ቀና ማለት ይገባዋል።
አዲስ ዘመን፡- ግን ከኢኮኖሚያዊ እሳቤው ባሻገር ትርጉም የሚሰጥ እሴት የለም እያሉ ነው? ኪነጥበባዊ የባህል እሴቶችስ ከገንዘብ አንፃር የሚተመኑ ናቸው?
አቶ ሰብስቤ፡- እነሱ እኮ እሴት የሚሉት ይህንን ነው ፤በሳር ቤት ከከብት ጋር መኖርን ነው። ኪነጥበብም እኮ ማደግ አለበት። ለምሳሌ የዛሬ 100 ዓመት የነበረ ሙዚቃ ዛሬ አለ? ዛሬም ክራር እየገዘገዝኩ ልቀጥል ማለት መብትሽ ነው፤ ባህሌን እያልሽ መንገታገት ይቻላል። ግን የተሻለ መጫወትና ሙዚቃችንን ሊያሳምረን የሚችል መሳሪያ መጠቀም ብልህነት ነው። ምክንያቱም እንደዘመኑ ማደግ ስለሚገባን።
አዲስ ዘመን፡- ባለፈው ከቡራዩ ግጭት ጋር ተያይዞ አርባ ምንጭ ላይ ሊከሰት የነበረውን አደጋ በመታደግ ረገድ የጋሞ አባቶች ባህላቸውን ተጠቅመው ወጣቱን ያረጋጉበት መንገድ በበርካቶች ዘንድ አድናቆት እንዳስገኘ ይታወሳል። ይህ ባህላዊ እሴት ኋላቀር ነው ብለን ጥለነው ቢሆን ኖሮ ዛሬ እንዲህ ላለው የሰላም እጦት መፍትሄ ሊሆን ይችል ነበር?
አቶ ሰብስቤ፡- እሱ ሰዎች ባላቸው የኑሮ ደረጃ ወይም ንቃተ ህሊና ደረጃ ሰርተው ሊሆን ይችላል። የለም ማለት አይደለም። ሰው በማህበራዊ ዝግመተ ለውጥ ሰርቶ ሊሆን ይችላል። የዛሬ 50 ዓመት በኋላ አሁን የጠቀሽው እሴት ተቀባይነት ላያገኝ ይችላል። ያኔ የሚኖረው ወጣት የአባቶችን ምክርና ተግሳፅ የማይቀበል ሊሆን ይችላል። ይህንን ሁኔታ በመሰረታዊነት ሊፈታ የሚችለው ህጋዊ ስርዓት መዘርጋቱ ነው። ሳይንሳዊ ስርዓት ካለ ሁሉም በዚያ መሰረት ያድጋል። ባህላችን እንጠብቅ ብለው እንማር ሲሉ የነበሩ የላቲን አገራትም ስላለዋጣቸው ነው አሁን ወደ ሰለጠነው ስርዓት እየገቡ ያሉት።
አዲስ ዘመን፡- በኢኮኖሚ አደጉ የሚባሉት አገራት ሳይቀር በኢትዮጵያ ያለውን ባህላዊ እሴት ሲያሞግሱና ሲያወድሱ የሚታዩት እርሶ እንደሚሉት ኋላቀርነቱ ጠፍቷቸው ነው?
አዲስ ዘመን፡- እኔ ብዙ ተሞክሮ ያለኝ ሰው ነኝ፤ ውደሳውም ሆነ ሙገሳው ውሸት ነው። ለምሳሌ ወደ ኦሞ ያሉ ብሄረሰቦች ራቁት መሆናቸውን ባህል ነው እያሉ ነጮቹ ሲያደንቁልሽ እውነት ይመስልሻል?። አንድ ወቅት ላይ ለስራ ጉዳይ ከአንዲት የውጭ ዜጋ ጋር ሆነን ወደ ኦሞ አካባቢ ሄደን ነበር። ይህ የውጭ አገር ዜጋ ታዲያ የገጠሩን የአኗኗር ሁኔታ ትጎበኛለች። ከአንዷ አርሶአደር ቤት ገብታም ሰዎች እንዴት ከከብት ጋር አብረው እንደሚኖሩ፣ በምግብ እጥረት የተጎዱ የሚመስሉና ከወገብ በታች እርቃናቸውን የሆኑ ህፃናትን አይታ ከተመለሰች በኋላ ባየችው ነገር ያላትን አስተያየት ጠየኳት። እሷም አንቺ እንደምትዬኝ «የእናንተ ባህል በጣም ደስ የሚል ነው» የሚል ምላሽ ሰጠችኝ። እኔም በምላሿ በጣም ነው የተበሳጨሁት። ምክንያቱም ደስ ይላል የምትለው ለዲፕሎማሲ ወይም እኔን እንዳይከፋኝ እንጂ ያንን የተጎሳቆለ ህይወት ኑሪው ብትባል እሺ እንደማትል አውቀዋለሁና ነው። ይህንን ሃሳቤን በወቅቱ ገልጬላት ነበር። በነገራችን ላይ በዲፕሎማሲ ቋንቋ አንድ ሰው «አዎ» ካለሽ ሊሆን የሚችለው 50 በመቶውን ነው፣ «እስቲ እንሞክራለን» ካለሽ ደግሞ ፈፅሞ እንደማይደረግ ማወቅ አለብሽ። እነዚህ የውጭ አገር ሰዎች ጥሩ ነው የሚሉት እንዳናስብ፤ እንዲያውም የበለጠ እንድንደነዝዝ ነው፤ ለምሳሌ አንድ ሽንኩርት ነጋዴ እዚህጋ ሱቅ ቢከፍት ሌላ አጠገቡ ሌላው ቢከፍት ደስ ይለዋል? አይለውም!። ልክ እንደዚሁ ያደጉ አገራት ባህላችንን የሚያደንቁልን ሁልጊዜ አዕምሯችን ወደ እድገት እንዳያስብ ወደ ምርምር እንዳያስብ ለማድረግ ነው። ይህንን ስነግርሽ ዝም ብሎ ተረት ተረት እንዳይመስልሽ። በጣም በጥልቅት ስለማውቀው ነው።
አዲስ ዘመን፡- በሌላ ቃለ መጠይቅ ላይ አንድ ቋንቋ የሚጠፋው መጥፋት ስላለበት ነው፤ ብለዋል ይህን ሲሉ ምን ማለትዎ ነው? ፍረጃስ አይሆንም?
አቶ ሰብስቤ፡- እኔ እኮ አይደለሁም የማጠፋው፤ ምኞቴ ሆኖ አይደለም። ዝግመተ ለውጡ እኮ ነው የሚያጠፋው። ያየሁትን ነው የምናገረው። መጥፋት ስላለበት ነው የሚጠፋው። ለምሳሌ ናይጄሪያ ስትሄጂ ወደ 520 ቋንቋ ነው ያለው። ከተማ ውስጥ በ520ውም ቋንቋ አይደለም የሚጠቀሙት። የተሻለ ኑሮ ለማግኘት ሁልጊዜ የሰው ልጅ ይንቀሳቀሳል። ሲንቀሳቀስም በ520 ቋንቋ ሁሉ መነገር አለበት ከተባለ እዛው ቋንቋው በሚነገርበት ቦታ ነው መቀመጥ ያለበት። ግን አይቀመጥም፤ ምክንያቱም እዛ ደግሞ ድህነት አለ። የተሻለ ኑሮ ወደሚገኝበት ስትሄጂ ግን ወደድሽም ጠላሽም የዚያን አካባቢ ቋንቋ መናገር ይጠበቅብሻል። በታሪክ አጋጣሚ አንዱ ቋንቋ ሌላውን እየዋጠ ይሄዳል። እኔ አይደለሁም እንዲጠፋ የምፈልገው ፤ ግን እኔ ራሴ የዚያ ሁኔታ ተጠቃሚ ነኝ። ስለዚህ ብዙ ቋንቋ ተናጋሪ አገራት ውስጥ ሁልጊዜ አንድ በታሪክ አጋጣሚ የሚፈጠር ቋንቋ ይወጣል። ያ እያደገ ነው የሚሄደው። ማንም አይመልስውም። የራሱ ቋንቋ አራራ ያለበት ወደመጣበት አካባቢ መመለስ አለበት። ለኢኮኖሚ ሲባል አንድ ቋንቋ መጥፋቱ ግድ ነው። ደግሞም ያ ቋንቋ የኔ ነው ለማለት የእውቅና ማስረጃ ያስፈልገኛል። ቋንቋ ድምፅ ነው ማንም ባለቤት የለውም። በአለም ላይ ያለ ቋንቋ የግለሰቦች ንብረት ቢሆን ኖሮ የሁሉም ንብረት ነበር የሚሆነው። ግን እንደ እድል ሆኖ አይደለም። ቋንቋ ሃሳብን ካልተሸከመ ለእኔ እንደ በግ ድምፅ ነው። እሱ ብቻ አይደለም መረጃ ያለው ሃሳብ ካልሆነ ትርጉም አልባ ነው።
አዲስ ዘመን፡- አሁን የሚሉት ነገር ሰዎች ለዘመናት ተቀብለው ከሚኖሩት እሳቤ እንዲሁም በቅዱስ መፃሕፍት ሳይቀር አይሁዳዊ ግሪካዊ እያሉ በግልፅ የሚናገሩበትን እውነታ መጣረስ አይሆንብዎትም?
አቶ ሰብስቤ፡- እኔ አልተቃረንኩም፤ መጽሐፍ ቅዱስንም አነባለው፤ እንዲያውም እኔንነው የሚደግፈኝ፤ ግሪካዊ የሚባል ነገር እንደሌለ ነው የሚናገረው። ሁሉም በክርስቶስ አዲስ ሰው መሆኑን ነው የሚገልጸው። ምኑ ነው የለም የሚያስብለው ብለሽ ስትይ ደግሞ አስተሳሰባቸው ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት 83 ቋንቋዎች አብረው ለመኖር የለም ብለን ነው መነሳት የሚጠበቅባቸው። ይህም ደግሞ ሁሉንም ወደ ተሻለ ኑሮ ለመሸጋገርና የሚያጋሩት ነገር እንዲፈጠር ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- እርሶ «የብሄር ማንነት ቅዠት›› ብለው መፃፍዎ ለዚህ ህብረተሰብ ምን ይፈይዳል ይላሉ ? እንደ አጠቃላይ አሁን ላለው ፖለቲካዊ ችግር ምንስ መሰራት ይገባል ይላሉ?
አቶ ሰብስቤ፡- እኔ የፃፍኩት ችግር ፈቺ ማህበራዊ እውነታ ነው። ይህም አሁን ያለውን የኢትዮጵያ ችግር ብቻ ሳይሆን ለአለምም ጠቃሚ ነው የሚል እምነት አለኝ። ኢትዮጵያ የምትባል አገር አለችን በሃይል ማንም አገር እንደተመሰረተው ተመስርታለች። በዚህች አገር ውስጥ 80 በላይ ቋንቋ ተናጋሪ ቡድን አለ። ይህ ቡድን የየግሉን የኑሮ ደረጃ ይዞ እንደፈጠራ አቅሙ የሚኖር ህዝብ ስለሆነ አንድ የፖለቲካ ስርዓት የሰዎችን የኑሮ ደረጃ ሊያሻሽል የሚችል ፖሊሲ ቀርፆ ሁሉም ህዝብ በሚናገረው ቋንቋ እየተሸጠ ህዝብ ያዋጣኛል የሚለውን አስተሳሰቡን እንዲገዛ ማድረግ ይጠበቃል። ምክንያቱም የሁሉም ህዝብ ችግር ኢኮኖሚ በመሆኑ ነው። የችግሩን ደረጃ አቀራርቦ በመፍታት የተሻለ ኑሮ በፍትሃዊነት መስጠት ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- እንግዳችን ጥሪያችንን አክ ብረው ለቃለመጠይቁ ስለተባበሩን በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ ላመሰግን እወዳለሁ።
አቶ ሰብስቤ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
እነሱ የተያያዙት በፖለቲካ ስም ሥራ መፍጠር ነው። ህዝብ እያጋደሉና እያጫረሱ ግን ደግሞ እነሱ ብሄር የሚባል ነገር ሳይኖራቸው ነው የብሄር ማንነት የሚሉት። እነሱ የተሻለ ኑሮ እየኖሩ ደሃውን ለማጫረስ ማንነትህ ተረግጧል ይሉታል። የሚገርመው ባዩ ራሱ ነው ማንነት የሚለውን ነገር አይጠቅመኝም ብሎ ጥሎት የሄደው። በእንደዚህ አይነት መንገድ የሚያተራምሱ ምህረት የሌላቸውና ህሊናቸውን ያጡ ሰዎች መሳሪያ ነው የብሄር ማንነት፤
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሀምሌ 20/2011
ማህሌት አብዱል