‹‹መብትና ግዴታ ተነጣጥለው አይሄዱም›› እየተባለ ሲነገር ቢሰማም በተግባር ብዙዎች የሚጠይቁት መብታቸውን ብቻ ነው፡፡ ግዴታን እየዘነጉ መብትን መጠየቅ በመብዛቱ ምክንያት ክቡር የሰው-ልጅን መግደልም እንደ መብት እየተቆጠረ ነው። አካባቢው ‹‹የኔ ብሔር መኖሪያ ነው›› ብሎ የሰውን ንብረት ማቃጠል እና የሰውን ህይወት ማጥፋት፤ ማሳደድና ማፈናቀል ወንጀል ቢሆንም እንደ መብት የሚቆጥሩ ወገኖች እየተበራከቱ ነው፡፡
የመብትና ግዴታ ሚዛን እየተጠበቀ አይደለም፡፡ የእኔ መብት የሚከበረው የሌሎችን መብት እስከመደፍጠጥ ድረስ ዘልቆ አለመሆኑን ለመረዳት ብዙዎችን እያዳገታቸው ነው። መብቴን ስጠይቅ በአገር እና በህዝብ ላይ ስለሚደርሰው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ማመዛዘን እየተረሳ ነው ፡፡ ይህ አካሄድ አደገኛ በመሆኑ መታረምና መስተካከል አለበት፡፡
ከሰሞኑ በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ከተከሰተው ‹‹የመብቴ ይከበር›› ጥያቄ ጋር ተያይዞ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳደሩ ይታወቃል። በሃዋሳ የኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ የከተማዋ ነዋሪዎች በነበረው የብጥብጥ ስጋት ወደ ሥራ ያልሄዱት ብዙ ነበሩ፡፡ በዚህ ሳቢያ ፋብሪካዎቹ ሥራ ያቆሙ ሲሆን፤ በዚህ ሳቢያ ሥራን በሰከንድ የሚለኩት የውጭ ኢንቨስተሮችን ስጋት ውስጥ ገብተዋል፡፡ይህ ደግሞ አገርና ህዝብን የሚጎዳ ክስተት ነው።
‹‹መብት እንጠይቃለን›› በሚል በተፈጠረው ችግር ሥራው ተቆርጦ ባለሃብቶቹን ቅር ከማሰኘቱም ባሻገር፤ በሐዋሳ ዙሪያ የነበረው ንብረት ማውደምም እጅግ ሞራልን የሚነካ ዜጎች በገዛ አገራቸው የባይተዋርነት ስሜት እንዲሰማቸው የሚያደርግ እኩይ ተግባርና ወንጀል ተፈጽሟል፡፡ እንደ መብት ሰዎች የፈለጉትን ጥያቄ ማቅረብ ቢችሉም አጠያየቃቸው ሥርዓትን የተከተለ እና የሌሎችን መብት ባልገፈፈ መልኩ የሚከናወን ሊሆን ይገባል፡፡
ሥነ-ምግባር በጎደለው መልኩ የሰዎችን ነፃነት መጋፋት መብትን ማስከበር አይደለም። ይልቁኑም አላዋቂነት እና ከሰውነት በታች መሆንም ጭምር ነው፡፡ በማንኛውም መልኩ ሕጋዊ መብት እንዳለ ሁሉ ህጋዊ ግዴታም አለ፡፡ ከህግ በላይ በመሆን በማስገደድ መብት ለማስከበር መንቀሳቀስ ትክክል አይደለም፡፡ ሁሉንም እኩል የሚገዛ ደግሞ ሕግ አለ። ህግ የሁሉንም ዜጎች መብት እኩል የሚያስከብር ነው፡፡
የሁሉም መብት የሚከበረው ደግሞ እያንዳንዱ ግለሰብ ግዴታውን ሲወጣ ነው፡፡ ይህ ማለት የብዙኃኑን መብት ለማስከበር እያንዳንዱ ግዴታውን መወጣት አለበት፡፡ከዚህ ውጭ ጥፋት እያጠፉ ‹‹መብት ለማስከበር ነው›› አይቻልም፡፡ ጥፋት አለማጥፋት ግዴታ ነውና፡፡ ጥፋት የህግ ተጠያቂነትንም የሚያስከትል ነው፡፡ ይህ መታወቅ አለበት፡፡መንግሥትም የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ግዴታ አለበት፡፡ይህን ግዴታውን መወጣትም ይገባዋል፡፡
መንግሥት የዜጎችን በነፃነት የመኖር መብት ማስጠበቅ ካልቻለ ፋይዳው ጥያቄ ውስጥ ይገባል። ይሄኔ መንግሥት ለዜጎች ነፃነት ጥበቃ ለማድረግ ሲንቀሳቀስ ደግሞ መብቱን እንጂ ግዴታን መወጣት የማይፈልገው ኃይል ‹‹ታፈንኩ›› ብሎ ይጮሃል፡፡ ህግ አክባሪነት ከሌለ፣ ግዴታን ማወቅ ታሳቢ ካልተደረገ በህግ መገደብ የግድ ነው፡፡ይህ የመንግሥት ግዴታም ሥራም ነው፡፡
በእርግጥ ‹‹ሰዎች ለምን ስለመብታቸው ብቻ ያስባሉ የሰዎችን መብት ያለመንካት ግዴታ እንዳለባቸው ለምን አይረዱም›› ብሎ መጠየቅ ይገባል፡፡ የዚህ መንስኤው ከሕገ-መንግሥቱ ጀምሮ የተለያዩ ዝርዝር ህጎች፣ ደንቦች እና መመሪያዎች የዜጎቹን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ለማክበርና ለማስከበር የቆሙ ቢሆንም እነዚህ መብቶች ግዴታንም የሚያካትቱ መሆናቸውን በሚገባ ለማስገንዘብ ተገቢው ሥራ አለመሰራቱ ነው፡፡
ህጎች ብቻ አይደሉም፤ የመማሪያ መጽሐፍት የሥነምግባርና ሥነዜጋ ትምህርትን ጨምሮ የትምህርት ሥርዓቱም የሚያዘነብለው ወደ መብት ነው፡፡ ይህ በመሆኑም በቤት ውስጥ ሳይቀር ልጅ አባቱ የሚፈልገውን እንዲያሟላለት ይፈልጋል፤ ነገር ግን ለአባቱ አይታዘዝም፡፡ ነጋዴው መንገድ እንዲሰራለት፤ ውሃና መብራትን የመሳሰሉት መሰረተ ልማቶች እንዲሟሉለት ይጠይቃል፡፡ ግብር መክፈል ግዴታህ ነው ሲባል ግን ወገቤን ይላል፡፡ ተቀጣሪው በየወሩ ጊዜው ሳይዛነፍ ደመወዙን የማግኘት መብት እንዳለው ይጠይቃል፤ ሥራውን በሰዓቱ ሰርቶ የማስረከብ ግዴታ እንዳለበት ግን አያስብም፡፡
አሁን አሁን ደግሞ መብት በሚል ስም ሥርዓት አልበኝነት ነፍስ ዘርቶ በእግሩ እየተራመደ የሚሄድ ይመስላል፡፡ ለዚህ መፍትሄው ከመንግሥት ባሻገር ህብረተሰቡም የሚያውቀው ለማያውቀው መብት እስከምን መሆኑን ለቤተሰቡና ለአካባቢው ነዋሪ የማስገንዘብ ግዴታውን ሲወጣ ነው፡፡ እያንዳንዱ ሰው የሚያደርገው የመብት ጥያቄ እንቅስቃሴ ከግዴታ ጋር የተቆራኘ ሲሆን፤ መብት ጠያቂውም ከእርሱ የሚጠበቅበትንም ኃላፊነት መወጣት አለበት፡፡
የሚቀረፁት ህጎች መብትን ብቻ ሳይሆን ግዴታ ላይም ማተኮር አለባቸው፡፡ የትምህርት ሥርዓታችን ትውልዱን መብት ጠያቂ ብቻ ሳይሆን ግዴታውን የሚወጣ ትውልድን ማፍራትንም ማዕከል ማድረግ አለበት፡፡ ለዚህ ከትምህርት ሥርዓቱ ባሻገር መምህራን እና ወላጆችም ተገቢውን ሚና መጫወት አለባቸው፡፡ መንግሽትም የሰዎችን መብት በማክበርና በማስከበር ሂደት ውስጥ የሌሎች መብት እንዳይደፈጠጥ፤ መብታችን ይከበር የሚሉ ጥያቄዎች ግዴታዎችን ከመወጣት ጋር የተሳሰሩ መሆናቸውን ማስተማር አለበት፡፡
አዲስ ዘመን ሀምሌ 19/2019