ባለፈው አንድ አመት ውስጥ በአገር ደረጃ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ እዚህና እዚያ በሚፈጠሩ ምክንያቶች ሰላማችን ተናግቷል።የደፈረሰውን የሰላም ችግር ዘላቂና አስተማማኝ ለማድረግ በመንግስትም ሆነ በልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሰሩ ስራዎችና ያለንበት የሰላም ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ስኬታማ ነው ብሎ መናገር አያስደፍርም።በመሆኑም በአንድ ወይም በሌላ መንገድ መፍትሄ ለማስቀመጥ በርካታ ጥረቶች ተደርገዋል።ነገር ግን የችግሩ ዋነኛ ምንጭ በሚገባ ሳይለይና ሁሉም ወገን እኩል ስምምነት ባገኘበት ሁኔታ ዘላቂ መፍትሄ እየተሰጠው ባለመምጣቱ ጭምር የሰላም ይኑረን ጥያቄው የጠነከረ ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የሚታዩት የእርስበርስ ግጭቶች አዝማሚያቸው እጅግ አሳሳቢ እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው።በመንግስትና በልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በኩል የሚሰራው ስራ እና ሰላምን አስተማማኝ ለማድረግ የሚከናወኑ ተግባራት ዘላቂ ሆነው ሊረጋገጡ አለመቻላቸው ሁሉንም ወገን እያሳሰበና እያነጋገረ ያለ ጉዳይ በመሆኑ ልዩ ትኩረት ይሰጠዋል።
በየጊዜው የሚከሰቱት ግጭቶች ፈጣን ምላሽ እንዳያገኙና በመፍትሄው ላይም ህዝቡ፣ ምሁራንና የሀገር ሽማግሌዎች በንቃት እንዲሳተፉ መድረኮች ቢዘጋጁም መልካሙን ሃሳብ የሚያመክን ተንኮል በመስራት በህዝቦች መካከል የሚዘሩ ክፉ ሀሳቦች በመኖራቸው ሰላማችን ዘላቂና አስተማማኝ አልሆነም።በዚህ ረገድ የሚነሱ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም ዋናው ጉዳይ ግን የለውጥ ሂደቱ የግል ጥቅማቸውንም ሆነ ስልጣናቸውን ያሳጣቸው ሀይሎች የሚጠነስሱት ተንኮል የጎላ ድርሻ ይዟል።ይህን በሚመለከት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ምሁራን አሳማኝ ማሳያዎችን በማቅረብ ምስክርነታቸውን እየሰጡ ናቸው፡፡
በአገራችን እጅግ የዳበረ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዜዴ እንዳለን ቢታወቅም ይህን እሴታችንን በሚገባ ተጠቅመናል ብሎ መናገር አይቻልም።ለዚያውም አማርጠን ልንጠቀምበት የሚያስችለን የሲዳማው፤ የኦሮሞው፤ የትግሬው፣ የአማራው፣ የጉራጌው ወዘተ… የየራሳቸው ልዩ የሆነ አስገራሚና እጅግ የተዋጣለት የግጭት አፈታት ባህል ባለቤቶች ሆነው ሳለ ጊዜ አመጣሽ የሆኑ ጥቃቅን ልዩነቶቻችንን በማጉላት ሁኔታውን ከማንነት ጋር እያቆራኙ ሰላማችንን ክፉኛ ጎድተውታል፤ በመሆኑም ሰላማችንን አስተማማኝና ዘላቂ ማድረግ አልተቻለም።
ይባስ ብለው አዳዲስ ግጭቶችን ከመቀስቀስ በስተቀር ግጭት ማስወገድና ማስታረቅ ያልለመደባቸው ፖለቲከኞችና አክቲቪስት ነን ባዮች ባህላዊ የእርቅ አፈታት ባህላችን እንዲዳከምና አቅም እንዲያጣ ጭምር የሀገር ሽማግሌዎችን ምክር መጠየቅ ቀርቶ ችግሮች እንደሌሉ አድርገው ብዥታን ይፈጥራሉ።በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎቻችን ነፍሳቸውን ለማዳን ከኖሩበት አካባቢ በግድ ሲፈናቀሉ፣ ሲሸሹና በግፍ ሲገደሉ እያዩ ኃላፊነት ያለባቸው አመራሮችም መፍትሄ ማስቀመጥ ሲገባቸው በቸልታ ማለፋቸው፤ በተለይ በአንዳንድ አካባቢዎች ራሳቸው ተዋናይ የሆኑበት ሁኔታ በገሀድ መታየቱ አሳፋሪ ተግባር ነው፡፡
በአጠቃላይ ችግሩ ከትናንት ዛሬ ብሷል፤ የነገው ከዛሬው የከፋ ላለመሆኑም ዋስትናችን ምንድን ነው ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው።ምንም አይነት ምክንያት ይሁን ሰላምን የማደፍረስ ስራው የሚሰራው አየር ላይ አይደለም፤ መሬት ላይ ሊያውም አገራችን ላይ በመሆኑ የችግሩም ሆነ የመፍትሄው አካል በዋናነት ህዝቡ ብቻ ነው፤ በመሆኑም ከህዝቡ ብዙ ይጠበቃል።ሌሎች አካላት ተጠያቂ ሊሆኑ የሚችሉት ከህዝቡ ቀጥሎ በሁለተኛና ሶስተኛነት ነው።ስለሆነም ህዝቡ ምሁራንና አክቲቪስቶች በማይጠቅም የፖለቲካ ትርክትና ውድድር ውስጥ መዘፈቀቃቸውን ከተገነዘብን የራሳቸውን የግል ፍላጎት እንዲሁም ችግራቸውን ህዝብ ሊሸከም አይገባም።እናም ህዝቡ ራሱ ለእነዚህና መሰል ፀረ- ሰላም ሀይሎች ቦታ ባለመስጠት ብዙ ስራ ሊሰራ ይገባል፤ ሊያስቆማቸውም የግድ ነው።
በዚህ ረገድ መገናኛ ብዙሃንና አግባብ ያላቸው የመንግስት ተቋማትን ጨምሮ አክራሪ በሆነ የማንነት ፖለቲካ ጫፍ እየረገጡ ያሉ ሀይሎችን በህግ የበላይነት ማዕቀፍ አደብ ማስያዝ ደግሞ የህዝብ እምነት የተጣለበት የመንግስት ሚና ነው።አመት የሞላው የለውጥ ሂደት ለዴሞክራሲያዊና ፍትሀዊ የልማት ተጠቃሚነትን ለማስፈን ብቻ የሚከናወኑ ተግባራት ላይ ጊዜና ጉልበት ማጥፋት ይጠይቀዋል።ይህንንም በተግባር ለማረጋገጥ በፅናት መጓዝ የወቅቱ አስገዳጅ ውሳኔ ሊሆን ይገባል።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 18/2011