«ሀብታም ለመሆን የተሻለው ጊዜ ወጣትነት ነው፤ ድሃ ለመሆንም ጊዜው ወጣትነት ነውና ወጣቶቻችን እባካችሁ የተሻለውን ምረጡ፤ የዚህ ዘመን ጀግኖች ወጣቶች ናቸው፤ ወጣቶች ተስፋ ሲኖራችሁ እኛም አገራችንም ተስፋ ይኖረናል» ይህ መልካምና በወጣቶች ላይ ተስፋን ያሳደረ ንግግር ሚያዝያ 7 ቀን 2010 ዓ.ም. በሚሌኒየም አዳራሽ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ የተነገረ መሆኑን ልብ እንላለን።
በርግጥም የአሁኑም ሆነ የወደፊቱ ታላቅ ተስፋ በወጣቱ ትውልድ ላይ የተጣለ ስለመሆኑ እንደምን መጠራጠር ይቻላል? ለዚህም ነው አበው « ወጣት የነብር ጣት» ሲሉ የሚያሞካሹት። የወጣቱ በሁሉም ዘርፍ ወንዝ ያሻግራል የሚል መተማመን መኖሩ በቀደመው ጊዜ እንደታየው ሁሉ ዛሬም ያንን የተመሰገነ ተግባሩን በተግባር ሊያሳይ የሚችልበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ዛሬን ሳይሰለቹ በትጋት መስራት ያስፈልጋል።
በአሁኑ ወቅት በዓለም ዙሪያ ያሉ ደኖች ለከፍተኛ ጉዳት የተጋለጡበት ወቅት ነው። በቀጣይ አስርት ዓመታት ይህን ጫና ለመቋቋም ከተቻለ ደኖችን ወደ ነበሩበት መመለስና የብዝሀ ሕይወት ሀብታችንን ከጥፋት መታደግ ልንፈጽማቸው ከሚገቡን ተግባራት ዋነኛው ነው። ይህ ተግባር ለአሁኑ ትውልድና ለመጪው ትውልድ ደህንነት ሲባል በሃላፊነት ሊሰራ የሚገባው ነው።
በጥቅምት 2002 ዓ.ም የብዝሀ ሕይወት ስምምነት አባል ሀገራት በአይኪ ጃፓን ባካሄዱት ጉባኤ ከ2003 እስከ 2012 ዓ.ም ባለው ጊዜ የሚተገበር አዲስ የብዝሀ ሕይወት ስትራቴጂክ እቅድ ማፅደቃቸው ይታወሳል። ይህ እቅድ 20 ግልጽና የሚለኩ ግቦች ያሉት ሲሆን፤ ከነዚህ ግቦች አምስቱ የደን ጥበቃና ዘለቄታዊ አጠቃቀምን የሚመለከቱ ነበሩ።
‹‹ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተፈጥሮ አካባቢዎችን (ደኖችን ጨምሮ) መመናመን ቢያንስ በግማሽ መቀነስ፣ ከተቻለ ዜሮ ማድረስ፤ በጥብቅ ደን ውስጥ ያሉ አካባቢዎች የብዝሀ ሕይወት ጥበቃን በሚያረጋግጥ መልኩ ዘለቄታዊ እንክብካቤ እንዲደረግላቸው፤ ቢያንስ17 ከመቶ ያህሉ የየብስና የውሃ አካላት በተለይ በብዝሀ ሕይወት ሀብት የበለጸጉ አካባቢዎች በውጤታማ ጥበቃ ሥር እንዲሆኑ፤ የማይተካ አገልግሎት የሚሰጡ ሥርዓተ ምህዳሮች ጤናና ውሃ፣ የማህበረሰቡን፣ የድሆችንና ለአደጋ ተጋላጮችን ፍላጎት ግምት ውስጥ በማስገባት እንክብካቤ ይደረግላቸዋል፤ የተመናመኑትና የተጎሳቆሉት ተመልሰው ይተካሉ። የሥርዓተ ምህዳር ጤናማነትና ብዝሀ ሕይወት ካርበን ለማከማቸት ያለው አቅም በጥበቃና ቢያንስ 15 ከመቶ ያህሉን የተጎዱ ሥርዓተ ምህዳሮች መልሶ በመተካት ይጠናከራል›› የሚል ነበር ።
ኢትዮጵያ እምቅ በሆነ የተፈጥሮ ሃብት የታደለች አገር ብትሆንም በተለያዩ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ክስተቶች ሳቢያ አገሪቱ ያሏት የደንና ሌሎች የአካባቢና የተፈጥሮ ሀብቶች ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባቸው ይገኛል። እያደገ ከመጣው የህዝብ ብዛት ጋር ተያይዞ ለምግብ አቅርቦት ሲባል በግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ የሆነ የአርሶ አደሩና ሰፋፊ የእርሻ መሬት መስፋፋት፣ ለማገዶ እና ለግንባታ ስራ የሚያገለግል የእንጨት ፍላጎት መጨመር፣ ለሰፈራና ለከተሞች መስፋፋት ሲባል የደን ምንጣሮና የደን ቃጠሎ ለደን ሀብታችን መመናመንና መጥፋት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል። በዚህም የተነሳ የዝናብ እጥረትና የስርጭት መዛባት፣ ተደጋጋሚ የሆነ ድርቅና የጎርፍ አደጋ ክስተት፣ የመሬት ሙቀት መጨመርና የበረሃማነት መስፋፋትና የድህነት መንሰራፋት ተከስቷል።
የግብርና ሚኒስቴር የቅርብ ጊዜ መረጃ እንደሚያሳየው፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የከርሰ ምድር ውሃን ሳይጨምር 123 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር የሚጠጋ የውሃ ሃብትና ከ36 ሚሊየን ሄክታር በላይ ሊለማ የሚችል መሬት ቢኖርም አገሪቱ ከተፈጥሮ ሃብቷ የምትፈልጋቸውን የሰብል ዓይነቶች ማምረት ባለመቻሏ እስካሁን የለማው መሬት 16 ሚሊዮን ሄክታር ብቻ መሆኑን ያሳያል። ለዚህም የተፈጥሮ ሃብት መመናመን ቀዳሚው መንስዔ ሆኖ ይጠቀሳል።
ዛሬ ላይ ሆነን የምናስተውላቸውን በአየር መዛባት የሚከሰቱ ችግሮች በብቃት መከላከልና የምንፈልገው ውጤት ላይ የምንደርሰው ባለፉት ዓመታት ሰርተናቸው ውጤት ያላገኘንባቸውን የመከኑ ተግባራቶቻችንን በማሰብ ተስፋ በመቁረጥ ስሜት ሳይሆን፤ አንድ ብለን በምንጀምረውና ነገ ውጤት እናገኝበታለን ብለን ተስፋ በምናደርግበት ወቅታዊ ስራችን ሊሆን ይገባል።
የፊታችን ሰኞ ሐምሌ 22 ቀን 2011 ልንተክል ያቀድናቸውን 200 ሚሊዮን ችግኞች አንዴ ተክለን እንደዋዛ የምንረሳቸው ሳይሆኑ ፍሬ አፍርተው ለልማታችን መድህን፣ ለጤናችን ፈውስ ሆነው ካንዣበበብን አደጋ እንዲታደጉን በመትከል እንደጀመርን ተንከባክበን በማሳደግ ማህበረሰባዊ ሃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባናል። የዚህ ዘመን ጀግኖች ወጣቶችም የመሪያችንን ጥሪ ተቀብለው ለውጤታማነቱ እንደሚተጉ አይጠረጠርም!
አዲስ ዘመን ሀምሌ 17/2011