ሙዚቃ ስሜትን ያነቃቃል፤ ያለፈን ጊዜ ያስታውሳል፤ ጠንካራ ትስስር ይፈጥራል፤ ለሀገርና ለህዝብ መድሀኒት ነው ሲሉ ብዙዎች ይስማማሉ። ሙዚቃ ልዩ ውበት ያለውና በሰው ልቡና ውስጥ ሰርስሮ ሊገባ የሚችል ኃይል አለው። በመሆኑም ሙዚቃ ባህልን ከማስተዋወቅ ባለፈ ባህሪንም ይቀርጻል። ሀገርን ይገነባል።
አሁን አሁን የምናደምጣቸው ሙዚቃዎች ምን ያህል ከእኛ ጋር ተዋደዋል፤አንድነትን ከማስረጽ አኳያ ምን ያህል ተራምደዋል? የሚሉ ጥያቄዎችን አንስተናል። መጀመሪያ ሀሳባቸውን ያጋሩን የኢትዮጵያ የሙዚቀኞች ማህበር ፕሬዚዳንት፤የሙዚቃ ደራሲ፣አቀናባሪ፣ ፒያኒስት፣ ጊታሪስትና ቫዮሊኒስት አርቲስት ዳዊት ይፍሩ ናቸው። እርሳቸው እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበርን የመሰረቱት አዝማሪዎች ሲሆኑ ማህበሩ 55 ዓመታትን አስቆጥሯል። አዝማሪዎች በወቅቱ በርካታ የባህል ተጽዕኖ ቢኖርባቸውም በብዙ ትግል ውስጥ አልፈው ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ ታሪክ ሰርተዋል። ህብረብሔራዊነትን በአደባባይ አሳይተዋል፤በርካታ የሙዚቃ ባለሙያዎችም አፍርተዋል። ሙያው እንደሌሎች ሙያዎች ሁሉ ተከብሮ እንዲቀጥልና ሙያተኞች ተጠቃሚ እንዲሆኑም አስችሏል።
ማህበሩ ዛሬ ላይ 2ሺ200 አባላት ያሉት ሲሆን፤ ሁሉም በሥራው ላይ እኩል ተሳታፊ ነው ማለት እንደማይቻል የሚያነሱት አርቲስት ዳዊት፤ዛሬ ህብረብሔራዊነትን የሚያሳይ ስራ በስፋት አለ ለማለት እንደማያስደፍር ይናገራሉ። ለዚህም ምክንያቱ የተለያየ እንደሆነ ይገልጻሉ። የመጀመሪያው ሙያተኞቹ ችግር ሲገጥማቸው ብቻ ማህበሩን መጠቀማቸው ነው። ችግራቸው መፍትሄ ካገኘ በኋላ ጥጋቸውን ይይዛሉ። ይህ ደግሞ ለግል ጥቅም እንጂ በአንድነት ለመስራት እንደማይፈልጉ የሚያሳይ መሆኑን ይናገራሉ።
በህብረብሔራዊነት ላይ እንዳይንቀሳቀሱም ሌላ ምክንያት አላቸው የሚሉት አርቲስት ዳዊት፤ ኪነጥበብ ለሰው ልጅ አዕምሮ ቅርብና ፈጣን ምላሽ እንዲሰጥ የሚያደርግ ነው። ሆኖም አገሪቱ የሚጠበቅባትን ያህል ለዘርፉ ባለመስራቷ ገሸሽ የሚለው ይበዛል። ለዚህ ዋናው ምክንያት ለሥራ ምቹ ሁኔታ አለመፈጠሩ እንደሆነ ያስረዳሉ።
ሌላው ዘፋኞች ወይም ሙዚቀኞች የሚያቀነቅኑት ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነት ላይ ቢሆንም ባለቤቶቹ የዚህ ተቃራኒ መሆናቸው ነው የሚሉት አርቲስት ዳዊት፤ ሙዚቀኛው በዘፈኑ ብቻ ሳይሆን በኑሮውም ጠንካራ ኢትዮጵያዊነትን የሚያሳይ መሆን እንዳለበት ይናገራሉ። ይህንን መግለጥ ያለበት ደግሞ በሁለመናው መሆን ይገባልም ባይ ናቸው።
በሌሎች የትምህርት መስኮች የተመረቁ ባለሙያዎች ከምረቃ በኋላ በመንግስት ወይም በግሉ ዘርፍ ተቀጥረው ሙያቸውን እንዲያዳብሩ ይደረጋል። በሙዚቃው ዘርፍ ግን ከትምህርት ቤቶች ጀምሮ ሰፊ ውስንነት አለ። ከተመረቁ በኋላ ሥራቸውን ተግብረው ገቢ የሚያገኙበት እድል አልተፈጠረም። ይሄ ሙያተኛው አንድነት ላይ እንዲሰራ አላደረገውም። ምክንያቱም ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ እያየ እንዲፈስ ስለሚያስገድደው ነው ።
ሙዚቀኛው ዛሬ የእለት እንጀራውን ለማግኘት ብቻ ነው የሚሰራው፤አገራዊ የሆነውን ሥራ ትቶ ግላዊ የሆነ ተግባር ላይ ለመሰማራታቸው መንስኤው በሰሩት ሥራ ልክ የሚያገኙት ገንዘብ በቂ ባለመሆኑ ነው።
«የሰው ልጅ ከሙያው ተጠቃሚ ካልሆነ ለምን ብሎ ይሰራል»የሚሉት አርቲስት ዳዊት፤ የሙዚቃን ሙያ አብዛኛው ህዝብ የሚፈልገው ለመዝናናት ነው። ሲዝናና ደግሞ ለዚያ የሚገባውን ወጪ አያደርግም። ከዚያ አልፎም የሚወጡ አልበሞችን እንኳን ከገበያ ሳይገዛ ኮፒ ማድረግን ይመርጣል። ይህ ደግሞ የሙዚቃው ዘርፍ ባለሙያዎች ሙያ ባክኖ እንዲቀርና ወቅቱን አብነት ያደረገ ነገር ላይ ብቻ አተኩረው እንዲሰሩ አስገድዷቸዋል ባይ ናቸው።
የአገርን አንድነት ከመገንባት አንጻር በተለይም ወጣቶቹ በስፋት እየሰሩ እንደሆነ የሚያነሱት አርቲስት ዳዊት፤ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦችን ቋንቋ እየዘፈኑ ሀሳብ ያጋራሉ፤ አንድነትን፣ ፍቅርን፣ሰላምን ይሰብካሉ። ይህም በሁለት አይነት መንገድ ይገለጣል። የመጀመሪያው እየቀላቀሉ በመዝፈን ሲሆን፤ ሁለተኛው ብቻውን ዘፍኖ ማሳየት ነው። ይህ ደግሞ አንዱ የአንዱን ቋንቋና ባህል እንዲረዳ ያስችላል። ነገር ግን እዚህም ላይ ቢሆን ክፍተት መኖሩን ይጠቅሳሉ። የማያውቁት ነገር ላይ ገብቶ መዘባረቁና ተገቢ ያልሆነ አለባበስ የባህሉን ባለቤቶች ያስቆጣል። ስለዚህ ይህ ጥንቃቄ ያስፈልጋል ።
ሙዚቀኛውን ለአገር ገጽታ ግንባታ እንዳይሰራ ያደረገው ሌላው ጉዳይ የመንግስት ተቋማት ወጣቱን እንዴት መስመር መከተል እንዳለበት ማስተማር አለመቻላቸው ነው ይላሉ። በግል የሚሰራ ነገር ሀላፊነትም ሆነ ተጠያቂነት የለውም። ስለዚህ አሁን ባሉበት ሁኔታ ያቅማቸውን ይሰራሉ እንጂ ከዚህ በላይ ተራምደው ለህብረ ብሄራዊነት ማቀንቀን ይከብዳቸዋል ።
በደርግ ጊዜ ብሔራዊ መግባባትን ሊያመጡ የሚችሉ፤ህብርን የሚያሳዩ በርካታ ዘፈኖች በህብረት ይቀነቀኑ ነበር። አሁን ባለው ሁኔታ ግን በማህበር አገርን ከፍ የሚያደርጉና ብሔራዊነትን የሚያረጋግጡ ሥራዎች ሲሰሩ አይስተዋልም። ምክንያቱም ማህበሩን ለማበረታታት አቅሙ ባለመኖሩና የሥራ መድረኮች ባለመፈጠራቸው መሆኑን ያነሳሉ።
በእርግጥ ይላሉ አርቲስቱ፤በእርግጥ «በደርግ ጊዜ ብዙ ሙያተኞች ይህንን አድርግ ልንባል አይገባም። በነጻነት አገራችንን እናስተዋውቅ» ሲሉ ተቆጥተውና ተቃውመው ነበር። ሆኖም ዘመን ተሻጋሪ አገርን የሚያስተዋውቅ ምርጥ የሚባሉ ሙዚቃዎችን ለአለም አበርክተዋል። ዛሬ ግን ይህንን አታድርግ፤ ይህንን አድርግ የሚል ባለመኖሩ ስለ አገር የሚዘፈኑ ሙዚቃዎች ግላዊ ናቸው። እነዚህም ቢሆኑ በርቱ የሚላቸው የለም። ሙያተኛው እዚህ ላይ ጊዜዬንም ሆነ ገንዘቤን ማባከን አልፈልግም በማለት እያፈገፈገ ነው ብለዋል።
አርቲስት ዳዊት፤ በዚህ ጊዜ አስገድዶ አገራዊ የሆነ ሙዚቃ ማሰራት ፣ይህን ካላካተትክ ብሎ ማለት አያዋጣም። ይልቁንም ምቹ ሁኔታን ፈጥሮ ለምን ለመስራት አትሞክርም ቢባል የበለጠ ስኬታማ ያደርጋል። በመንግስትና በግል ተቋማት የውድድር መንፈስ መፍጠር፣የሰሩትን ማበረታታት ይገባል። ይህ ደግሞ ህብረተሰቡ ወጥ የሆኑ ሥራዎችን ከማግኘቱም በላይ ባለሙያውን ተጠቃሚ አድርጎ ለህብረ ብሔራዊነት እንዲሰራ፤አገርን እንዲያስተዋውቅና ለግንባታዋ እንዲፋጠን ያደርገዋል። ሙዚቃም አገራዊ መግባባት ላይ ያላትን አቅም በአግባቡ እንድታሳይና እንድትተገብር ያግዛታል። ይህ ካልሆነ ግን መቼም ቢሆን ሙያተኛው የግል ቢዝነሱን ከማሯሯጥ ወጥቶ በአገር ገጽታ ግንባታ ላይ ሊሰራ እንደማይችል ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ 33ኛውን እና የዓመቱን የመጨረሻ የሳይንሳዊ ገለፃና ውይይት መርሐ-ግብር ባደረገበት ወቅት አርቲስት አብርሃም ወልዴ እንደተናገረው፤ የኢትዮጵያ ሙዚቃ በህብረተሰቡ ውስጥ ያለን ባህል፣አስተሳሰብ እና መልካም መስተጋብር መርምሮ ከማሳየት ይልቅ ወደሌላው ዓለም የፈጠራ ሥራዎች የመቀላወጥ ችግር ይስተዋልበታል፡፡ ከቀድሞዎቹ ውስጥ በጣም ጥቂት ቢሆኑም ደፍረው ለህብረተሰብ ለውጥ የደከሙ፣የተበላሸ የማህበራዊና የፖለቲካ ሥርዓት የሚተቹ ነበሩ። ዛሬም ድረስ ጠንካራ ሙዚቀኞች የመኖራቸው ተምሳሌት እነርሱ ናቸው።
አብዛኛው በዘርፉ የተሰማራው የሙዚቃ አሳታሚም ሆነ ባለሙያ የሙዚቃን ማህበራዊ ፋይዳ በመዘንጋት ሐብት መፍጠሪያ መንገድ አድርጎታል የሚለው አርቲስት አብርሃም፤ ለዚህም የኢኮኖሚ እና የአመለካከት ድህነት የመጀመሪያው ምክንያት መሆኑን ያነሳል። የፖለቲካ ጥገኝነትም እንዲሁ ሌላው ዋነኛ የችግሩ ምንጭ መሆኑን ይገልጻል።
«የኢትዮጵያ ሙዚቃ የሚታወቀው ላለው ሥርዓት ማጎብደድ እንጂ የየዘመኑን አፋኝ የፖለቲካ ሥርዓቶች ፍላጎትና ጫና ተቋቁሞ ለዕውነተኛ የህብረተሰብ ለውጥ እየዋለ አይደለም’’ያለው ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ኤሜረተስ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ናቸው። እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ ትናንት ጫናውን አሸንፈው በሙዚቃዎቻቸው ትግል ያደረጉ፣ ዛሬም አድርባይነትን አሻፈረኝ ያሉ ጠንካራ ወጣት የሙዚቃ ባለሙያዎች አሉ። ነገር ግን የኢትዮጵያ ሙዚቃ ኢንዱስትሪ እንዳያድግ እና የህብረተሰብን ንቃተ-ሕሊና ለማነፅ እንዳይውል ያደረጉ በርካታ ችግሮች ተደቅነውበታል። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ዋነኛው የፈጠራ ነጻነት እጦት እና የምርምር ችግር ነው።
ሙዚቃ ከፖለቲካዊ ሃይልና ጫና ቀንበር ወጥቶ ሙያዊ ደረጃ እንዲይዝና ለማህበረሰቡ የሥነ-ልቦና፣የሥነ-ምግባርና የነፃነት አጋር እንዲሆን ከተፈለገ ጫናውን መቀነስ ያስፈልጋል የሚሉት ፕሮፌሰሩ፤ ከሙያተኛው ጥረት በዘለለ ሊታይና ማስተካከያ ሊደረግበት የሚገባው ዘርፉን ለማሳደግ ሳይንሳዊ ትምህርት መሰጠት መጀመር መሆኑን ያነሳሉ።
ዘርፉም ቢሆን ራሱን መመርመር፣ ማሳደግ፣ መምራት እንዲችል እና ፈጠራን አጎልብቶ ለህብረተሰብ አኗኗር፣ አመለካከትና ስብዕና መዳበር የድርሻውን እንዲወጣና ለአገር ገጽታ ግንባታ እንዲውል ከዘርፉ ባለሟሎች እስከ መንግስት ድረስ መሰራት አለበት። ማህበረሰቡም የራሱን ግዴታ መወጣት ይኖርበታል ብለዋል። እኛም የአገር ጉዳይ ከገል ጥቅም ይቅደም እያልን ሃሳባችንን በዚህ ቋጨን። ሰላም!
አዲስ ዘመን ሀምሌ 14/2011
ጽጌረዳ ጫንያለው