በህብር ቀለማት የደመቀች፣ በድንቅ ባህል የተዋበች፣ በበዛ ጥበብ ያጌጠች የአብሮነት ጥላ ናት፤ ኢትዮጵያ። በዘርፈ ብዙ ኪን ከገፅታዋ ላይ የሚነበብ ድንቅ የባህልና ጥበብ መድረክ መሆኗንም ብዙዎች ይናገሩላታል። እናም በዚህች የአብሮነት የፍቅር ጎጆ ብዙዎች ይዋባሉ፤ ውህደታቸውንም ያሳያሉ። ይህ የሚገለጠው በብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦቿ ነው። የእነዚህ ቀለማት ህብረት የሚፈጥረው ድንቅ ውብት በስሌት የተቀመረ ሳይሆን በተፈጥሮ የተሰጠ ስለመሆኑ በርካታ የውጭ ዜጎች እማኝነታቸውን ይሰጣሉ። በተለይም በውብ ሙዚቃ ሲገለጥ ተመልካችን ያሰፋል።
ሙዚቃ ለባህልም ሆነ ለመዝናኛው እድገት ትልቅ አስተዋፅዎ አበርካች ስለመሆኑ ነገሪ አያሻም። ኢትዮጵያዊያን ደግሞ በዚህ የታደሉ ናቸው፤ በጥበብ ዘመናትን ተሻግረዋል። ከያሬድ ዝማሬ እስከ ሙላቱ አስታጥቄ ዘመናዊ ጃዝ ድረስ፤ ሙዚቃ በኢትዮጵያ የኖረ ነው። የአንዱን ብሔረሰብ ከሌላው ጋር አዛንቆ፤ የአንዱ ተለምዷዊ ዜማ ከሌላው ቋንቋ ጋር አዋህዶ ጥበብን ይከሽናል። ከጊዜው ጋር የሚሄዱ የጥበብ ስራዎች ሲፈልቁም ቆይተውበታል። ይህም የሙዚቃ መስክ የራሱን ጥበባዊ ለውጥ እንዲፈጥር አስችሎታል።
አሁንም የተለያዩ ባህላዊ ሙዚቃዎች ከዘመናዊ ሙዚቃ ስልት ጋር አዋህደው የሚያቀርቡ ሙዚቀኞች በርካታ ናቸው። ይህ ደግሞ ልዩ ጣዕም ያለው ሙዚቃ ከመፍጠርም በላይ ማህበረሰቡን ለማስተሳሰር ትልቅ አማራጭ ነው። የዘርፉን ተቀባይነትም ያሳድገዋል።
የብሔር ብሔረሰብ ሙዚቃዎች የማህበረሰቡ የእርስ በእርስ ትስስርን ያጎላሉ። ለአብነት ሰሞኑን በጊዮን ሆቴል «ህብር ኢትዮጵያዊያን» የተሰኘ የሙዚቃ ድግስን ማንሳት ይቻላል። ከመግቢያ መስፈርቱ ብንነሳ፤ ለመግቢያ የተጠየቀው በኢትዮጵያዊ ባህላዊ አልባሳት ተውቦ መገኘትን ነበር።
ታዲያ ይህ ዝግጅት በተለያዩ ብሔረሰቦች የባህል ሙዚቃ ደምቆና በተሳታፊዎች የአንድነት ህብር ጎልብቶ መታየት የቻለው ለዚህ ነው። በመድረኩ ላይ የቀረቡ የባህል ሙዚቃዎችም በተሳታፊው ምን ያህል ቅቡልነት እንደነበራቸው ማየት ይቻላል። በተለያዩ ብሔረሰቦች ቃና የተሰናዱ ዜማዎች ሁሉም ማህበረሰብ ጋር ጎልተው የመድረሳቸው ምስጢርም ሙዚቃ ለእርስ በእርስ ትውውቅና ትስስር መዋል የሚችል ኃይል ያለው በመሆኑ ነው።
ትዝታ፣ ባቲ፣ አንቺ ሆዬ፣ አምባሰል እያልን የምንጠራቸው አገራዊ ቅኝቶችም የማህበረሰቡ መገለጫ ናቸው። በእነዚህ ስልቶች ሀገሬው በተለያየ መልኩ ዜማን ቀምሮ እየኮመኮመ ዘመናትን ተሻግሯል። ኢትዮጵያዊያን የዜማ ቀማርያን ጥንትም የፈጠሩት ጥበብ ዘመን ተሻጋሪ መሆኑንም ማሳያው ይኸው ነው።
ተረካቢው ትውልድ ደግሞ በራሱ ዘመን የማህበረሰቡን ባህልን መሰረት ባደረገ መልኩ ዘመን ያቀረበለትን ተጠቅሞ ስልቱን በቀመር ከፍ ለማድረግ እየታተረ ይገኛል። የማህበረሰቡን ዜማና ቋንቋ በማዋሀድ የተለየ ቀለም ይፈጥርና እየተዝናና ያዝናናል። ህፃናት እንኳን ሳይቀሩ ቋንቋውን የማያውቁት ብሔረሰብ ዜማ እንዲያዜሙ ሆነዋል። ዛሬ ባዜሙት የብሔረሰብ ዜማ መነሻነት ነገ ስለብሔረሰቡ መጠየቃቸው፤ ስለ ባህሉና ወጉ መመርመርና ማወቃቸው አይቀርምና ይህም ሙዚቃ ትስስርና ትውውቅ የሚፈጥርበት አንዱ መንገድ መሆኑን እንረዳለን።
ከላይ እንዳነሳነው፤ የተለያዩ ዜማዎች በማዛነቅና የዜማና የቋንቋ ውህድ በመፍጠር ማቅረብ በሙዚቀኞች እየተለመደ ነው። አማርኛን ግጥም በኦሮምኛ ስልት፣ ጉራጌኛን ስልት በትግረኛ ቀንቋ፣ ወላይትኛን ምት በጋሞ ግጥም፣ የሀዲያውን ደግሞ በሱማልኛ ዜማ ወዘተ.. አዋህደው በበርካታ ቋንቋዎቻችን አዋዝተው ዜማን አክለው አስደምጠውን ተገርመናል፤ ሰምተን ተመስጠናል፤ በስለቶቹም ተወዛውዘናል።
እነዚህ ሥራዎች ተወድደው ተቀባይነትን ማግኘት ችለዋል። ይህን የሚያመላክተው ደግሞ ከየአቅጣጫው የሚሰጡ አስተያየቶች ናቸው። ከታዋቂና ስመጥር ሙዚቀኞች ጀምሮ ሙዚቃን «ሀ» ብለው የጀመሩ አዳዲስ ሙዚቀኞች የተለያዩ ብሔረሰቦች ዜማን አዋዝተው በተዋበ መልኩ በማቅረብ ከፍ ያለ ተደማጭነትን ማግኘት ችለዋል። በዚህ ስልት የሚቀርቡ ሙዚቃዎች ደግሞ ለሙዚቃው የሀገሬው አድማጭ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲያደምጥ የማድረግ ትልቅ ዕድል ፈጥሮለታል።
በዚህ ስልት ከጎሉ የሙዚቃ ባለሞያዎቻችንና ሙዚቀኞቻችን መካከል ታደሰ መከተ፣ አስጌ ዴንዴሾ፣ ዲና፣ መሳይ ተፈራ፣ ያሬድ ነጉ እና የመሳሰሉ ሙዚቀኞችን መጥቀስ ይቻላል። በቅርብ ደግሞ የበዛ የብሔረሰቦቻችን ዜማዎች ውህድ የሆነ ዘመናዊና ሙዚቃ በማቅረብ በብዙ የሙዚቃ አፍቃሪያን ዘንድ ተቀባይነት ያገኘው ሮፍናንን መጥቀስ ይቻላል።
ሮፍናን «ነጸብራቅ» ብሎ በሰየመው አልበሙ ውስጥ በጉራግኛ ምት /ጌት ቱ ወርክ/፣ በኦሮምኛ /ቀነኒሴ/ በፈረስ ኮቴ ድምጽ የታጀበ፣ የዶርዜ ብሔረሰብን የህብረት ዜማ መሰረት ያደረጉ ተዋዳጅ ሥራዎች አበርክቷል። በዚህ ስብጥር የተሰሩት 15 ዜማዎቹ በሙሉ ምን ያህል ኪነቱ ለባህላዊ ዜማዎቻችን እድገትና ለውጥ ምቹ ሁኔታ የፈጠረ መሆኑ መረዳት ይቻላል። የማህበረሰቡ ለሙዚቃዎቹ ያለው ቅቡልነትም መነሻው ከራሱ የተቀዳ እሱነቱን የሚገልፁለት የዜማ ክሽን በመሆኑ ነው።
ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ የብሔረሰብ ሙዚቃና ዜማዎች በአንድነት በዜማና በቋንቋ ተዋህደው ሲቀርቡ አድማጭ ይወዳቸዋል። የማናውቀው ቋንቋ ዜማ ከምናውቀው ቋንቋ ጋር ገጥሞ የተዋበ ሆኖ ሲቀርብ አዲሱን ቋንቋና ዜማ በቀላሉ ለመላመድም ያስችላል፡፡ ሙዚቃው አንዳችን ለሌላችን እውቅና እንድንሰጥ፥ መቀራረባችን እንዲጠነክር አንድንታችን እንዲጎለብት በጎ ተፅዕኖ ያሳድራል። መቀራረባችን ያሳድገዋል የባህል ልውውጣችን ያጠነክረዋል።
የማህበረሰባችን ልዩ ልዩ መገለጫዎች በሙዚቃዎች ተካትተው ቀረቡ ማለት ማህበራዊ እሴትና ባህላችን በቀላሉ ተደራሲያን ጋር በማድረስ አስተዋወቅን ማለት ነው። ወጣቱም የአገሩን ልዩ ልዩ መልክ እንዲረዳ በማድረግ ትልቅ አስተዋጾዎ ያበረክታል። የብሔሮች መገለጫ የሆኑ ባህሎችን ማስተዋወቅና ማወቅ ደግሞ አገርን በሚገባ ለማወቅ አንዱ መሰረት ነው።
በዚህ መልክ የሚቀርቡ ሙዚቃዎች በወጣቱ በኩል ባህላዊው በዘመናዊ መልኩ ተከሽኖ በልዩ ምትና በተዋበ ዜማ የሚቀርብ በመሆኑ ሲመርጠው፤ ለሌላው የማህበረሰብ ክፍል ደግሞ ሙዚቃው ባህላዊ መሰረቱን ሳይለቅ በውብ ድምጽ መሰራቱ ተወዳጅ ያደርገዋል።
በነገራችን ላይ፤ አንድ ብሔረሰብ ውስጥ ያለውን የዘፈን ስልት ከዘመናዊው ዜማ ጋር አዋህዶና አዋዝቶ ማቅረቡ የፈጠራ ስራ ነው። ሙዚቀኛው የአገሩን የተለያየ ብሔረሰብ ዜማ ሰርቶ ለማቅረብ፤ የብሔረሰቡን ዜማና ቋንቋ ማጥናትና መመርመር ግድ ይለዋል። በአጋጣሚው ለማህበረሰቡ ሙዚቃዊ ባህል እድገት ትልቅ ሚና እንዲወጣ እድል ይፈጥርለታል።
የመድረክ ዝግጅቶችን ደማቅ እንዲሆን የሚያደርጉ የሙዚቃ አጫዋቾች /ዲጄዎች/ የሙዚቃን አፍቃሪ ስሜት ጠንቅቀው የሚያውቁት ይመስላሉ። አስተውለን ከሆነ የሙዚቃ ምርጫቸው ለታዳሚው ስሜትና ፍላጎት እጅግ የቀረበ ነው። ለዚያም ይመስላል መጠነኛ ዝግጅቶችን እንኳን ያለ ዲጄዎቹ ማቅረብ አዘጋጆቹን የቸገረው። የዲጄዎች የሙዚቃ ምርጫና ግብዣ ከማህበረሰቡ የተቀዳ ነውና በተጠቀሰው ስልት የተቀነቀኑ ዜማዎችን ይመርጣሉ።
ሳምሶን በላይ የሙዚቃ አጫዋች /ዲጄ/ ነው። በትልልቅ ዝግጅቶች ላይ በሙያው አገልግሏል። የብሔረሰቦቻችን ሙዚቃ በተለያየ ቋንቋ ህብር እንዲፍጥሩ ተደርገው መሰራታችው ተወዳጅ እንዳደረጋቸው ይገልፃል። ሳምሶን ዘመናዊ ሙዚቃ ባህልን መሰረት አድርጎ በዜማና ቋንቋ ወህድ ሲቀርብ የሙዚቃ አፋቃሪው ጆሮ በቀላሉ መድረስ እንደሚችል ይናገራል።
«ውሎና አዳሬ አጠቃላይ ሕይወቴ ከሙዚቃ ጋር ነው» የሚለው ሳምሶን በዝግጅቶች ላይ በበዛ ታዳሚ የሚወደዱት መሰል ሙዚቃዎች መሆናችውን ያስረዳል። ለሙዚቃዎቹ መወደድ ምክንያት ደግሞ ቀለል ተደርገው ለአድማጭ እንዲመጥኑና ባህልን ሳይለቁ መሰራታቸው መሆኑን ይገልፃል። ሀገራዊ ምትን ያለቀቁ መሆናቸውም ተወዳጅነታቸው ከፍ ያደርገዋል።
በእርግጥ ሙዚቃ ተወራራሽና ድንበር ዘለል ነው። እዚህ ላይ የሚቀርብበት ስልት በቀላሉ ለማላመድና የራስ ለማድረግ ወሳኝነቱ አያጠያይቅም። እዚሁ በአገራችን ያለውን ሁኔታ ስንቃኝ ደግሞ፤ በአብሮነት መድረኮች፣ በባህላዊ ክዋኔዎች፣ በአውዳመትና ድግሶች ከየትኛውም የሙዚቃ ስልት በበለጠ ባህላዊ ዜማ ይበልጥ ተወዳጅነት አለው። ለዚህም ተመራጭነት ምክንያቱ በአንድ በኩል ከባህል ጋር ተከሽነው መቅረባቸው፤ በተጓዳኝ ሁሉን የማህበረሰብ ክፍል አሳታፊነታቸው ነው።
ሰው በባህሪው አንድ አይነት ነገር ሲደጋገምበት አይወድም፤ ወይም ለተመሳሳይ ገጽታ፣ ለአንድ ዓይነት ልማድና ለተደጋገመ ገጠመኝ ስልቹ ነው። ለዚህም ነው ስብጥርን መውደዱ። እናም የተለያየና አዲስ ነገር ብቅ ሲል ተወዳጅ መሆኑ አይቀርም። በዚህ መልክ በቀረበ አዲስ ስልት ህብረተሰባችንም ኪነ ጥበባዊ እድገቱን ያያል። አልፎም በአገሩ ውስጥ የሚኖረውን የወገኑን ገጽታ በጉልህ ይመለከታል። ይሄኔ ኪነጥበቡ ለባህሉ ባህሉ ደግሞ ለኪነጥበቡ እድገት የየራሳቸው ሚና ይጫወታሉ።
ኢትዮጵያዊ ባህሉን ይወዳል፤ ማንነቱን ያከብራል። አብሮነቱ በጋራ መኖሩ ጌጡ ነው። በራሱ ቀለም ተቀልሞ ለራሱ የሚቀርብለትን መምረጡ ለዚህ ነው። አብሮነቱ መጎልበቱ አንድነቱ መጠንከሩ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው ጥበብ መፈጠሩን ወዶታል። ሙዚቀኞቻችን የተለያየ ማህበረሰባዊ ገፅታን በሚያሳይ መልኩ ቋንቋና ዜማችንን አዋዝተው የሚያቀርቡበት ስልት ይበል የሚያሰኝ ነውና ተጠናክሮ ይቀጥል እንላለን።
አዲስ ዘመን ህዳር 30/2011
ተገኝ ብሩ