የሰው ልጅ በታሪኩ ውስጥ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማለፍ ከሚጓዝባቸው መንገዶች አንዱ ለውጥ ነው። ከሁሉም የላቀው ለውጥ፣ በራስ ላይ የሚካሄድ ለውጥም ነው። ምክንያቱም ለውጥ ከነበረው ወዳልነበረው፤ ካለው ወደተሻለው የመሸጋገሪያ ፍኖት በመሆኑ በጥንቃቄ ተይዞ የሚፈፀም ሂደት በመሆኑና የሚያዋጣና ተገቢ እውነት በመሆኑም ነው።
ለውጥ ከራስ ሲያልፍ የድርጅት፣አለፍም ሲል የማህበረሰብ አስተሳሰብ ፣ ከፍ ሲል የሃገር እየሆነ የሚሄድና ላለመመለስ የሚደርግን ዕድገትና ዕርምጃን የሚጠቁም አካሄድ ነው።
ጤናማ ሰው በግለ ባህሪው እንኳን፣ አንድ ዓይነት በልቶ፣ አንድ ዓይነት ለብሶ፣ አንድ ነገር ተናግሮ አያበቃም። በለውጥ ውስጥ ማለፍ ተፈጥሯዊ ግዴታው ነው። ልብ ብለን እንኳን ብናይ ሰው ሰላምታ ሲለዋወጥ የሰላምታ መለዋወጫ ቃላቱ በርካታ ናቸው። “ጤና ይስጥልኝ ፣ ደህና ነህ ወይ፣ ታዲያስ፤ ሁሉ በጎ ነው፤ አከራረምህስ፣ እንዴት ዋልክ፣ መዋያህን ሰላም ነህ/ነሽ፣ ቀንህ እንዴት ነው ወዘተ…” ይባባላል። ሌላው ቀርቶ በአንድ ቃል ላይ የሚሰማው የአነጋገር ቃና ለውጥ እንኳን በሰው ውስጥ ያለውን የለውጥና አዲስነት ፍላጎት ያሳየናል።
ለውጥ የፍላጎት ብቻ ሳይሆን የሰው ወይም የህዝብ ውስጣዊና ውጫዊ ፍላጎቶች ማደግ ወይ መጉደል ፣ ድምር ግፊት የሚያስከትለው ውጤት ነው።
ኢትዮጵያ በነባራዊ ሁኔታና በውስጣዊ ቀውስ ሂደት ውስጥ ስትናወጥ ቆይታ አምና መጋቢት ወር ላይ በዓይነቱ ልዩ በሆነና ከነበረው ወደ አልነበረው፤ ከተለመደው ወዳልተለመደው በሚያስኬድ መንገድ ላይ ራሷን አስገኝታለች። ይህ የተወለደ ለውጥ እያደር የሚጥለውን እየጣለ፣ የሚይዘውን እየያዘ ወደፊት ሲጓዝ ያልተጠበቁ መፈናቀሎች እዚህም እዚያም እያውገረገሩት የታሰበውን ያህል ሊጓዝ አልቻለም እንጂ አልተቋረጠም።
ይሁንናም የለውጡ ፈላጊ የተወሰኑ ሰዎች ሳይሆኑ ድምሩ የሃገር ሰው፣ መገፋቱ ያበሳጨው፣ ወደጠርዝ የተገፈተረው ህዝብ ፍላጎት በመሆኑ በትንሽቱ ብርሃንና ጭጋግም ውስጥ ለውጡን እየጠበቀ መጓዝ ይጠበቅበታል፤ እያደረገውም ነው።
ለውጡ እንዲጨናገፍ የሚፈልጉት ሃይላት ከተቀናበረ የቦንብ አደጋ እስከ ድንገተኛ መሳይ ግድያዎች ፣ዓይን እስካወጣ ለህዝብ ያሰቡ የሚመስል ፕሮፓጋንዳ የተቀላቀለባቸው ክፉ ትርክቶች ድረስ የሄደ መቀልበሻ ተጠቅመዋል፤ እየተጠቀሙም ነው። ይህም የፈለጉትን ውጤት ስላላመጣላቸው፤ መጠነ ሰፊ ጥቃት በተወሰኑ ዋና ዋና መሪዎች ላይ በማካሄድ የራሳቸውን ሰላም ያስጠበቀ የሚመስል ዕርምጃ ወሰዱ።
ሰዉ በኀዘን ማቅ እያለቀሰና በተሰበረ ልብ እህህ… ሲል የመወናጀያ ሃሳብ በመሰንዘር፣ ድርጊቱን የፈፀሙና ያስፈጸሙ የሚያስብል ትርክት ያለበት ዓይን ያወጣ መግለጫ መደስኮር ጀመሩ። መወናጀል ለማንም የማይረባ ቢሆንም ራሳቸውን የሰላም አለቃና የመረጋጋት ምንጭ አድርጎ ለማቅረብ በማስፈራሪያ ነጋሪት አጅበው ደለቁ። እና ብንሆን የምንመራው የሚል ትርጉም ያላቸው መግለጫዎች ማቅረብ ተያያዙ።
በታሪክ፣ ለክፋት የበሰለ ጭንቅላት የተጠየቀበት ጊዜ የለም፤ ክፉ ሰብዕና ያላቸው፣ መሪዎች በአጋጣሚ ስልጣን ላይ ይወጡና ከዚያ ላይ ላለመውረድ ምህረት የሌለው ዕርምጃ ይወስዳሉ። እንዲያውም “ትልልቅ አጥፊዎች ትልቅ ቦታ ይይዙና፣ ትላልቅ ጥፋት ይፈጽማሉ፤” የሚባለው ለዚህ ነው።
እነዚህን መሰል ሰዎች በያዙት ትልቅ ቦታ ላይ ሲቀመጡ ችግሮቻቸውን ወይም ችግር የሚመስላቸውን ነገር ሁሉ የሚፈቱት ምህረት በሌለው የጭካኔ መንገድ ነው። ይገድሉና ይወነጅላሉ፣ ወይም ያስሩና ይወነጅላሉ፤ ገድሎ ማሳበብን ደግሞ ማንም ይችለዋል። በ2ኛው የዓለም ጦርነት ወቅት፣ ሂትለር አይሁዶችን በመላው አውሮፓ ሲያስጨፈጭፍ ይገልጽ የነበረው “የጀርመን ህዝብ ጠላት” ወይም “ኃይለኛ ነጋዴዎች ናቸው” በማለት አልነበረም፤ ሚዛን አያነሳለትማ። ከዚያ ይልቅ የክርስቶስ ተቃዋሚዎችና የተረገሙ፣ ዘር ማንዘራቸው ጌታ ኢየሱስን የገደለ ነው ፤ እያለ ነበር የሚቀሰቅሰው።
ለውጥ ኢ-ፍትሐዊ ጨለማዎችን ለመግፈፍ ፍቱን መድሃኒት ነው። ርትዕ ያላቸው፣ ግልጽ ቀጥተኛና መልካም አካሄዶች በምድሪቱ ላይ በሁሉም መስክ እንዲሰፍኑ ይረዳልና። ኃላፊነት የሚሰማቸው ሰዎች ወደ አመራር እንዲመጡ ስለሚያግዝ፤ ተጠያቂነት እንዳለ የሚገነዘቡ የአገልጋይነት መርህ ያላቸው አለቆች ወደ አገልግሎቱ ይጎርፋሉ ስለዚህ ፤ ለውጥ አስፈላጊ ነው።
አንዳንድ ድርጊቶች ተገቢነት ያላቸው ቢመስሉም አግባባዊ ላይሆኑ ይችላሉ። በለውጥ ውስጥ መንገራገጭ እንዳለ ቢታመንም እንዳይቀለበስ መጣር ያለፈው ሰቆቃ ተመልሶ ወንበር እንዳይጨብጥና የመከራው ጊዜያት እንዳይመጡ ይረዳል።
የሰው ልጅ በሃገሩ ተስፋ ቆርጦ ስደት የሚያስከትለውን ሞት እንኳን ንቆ ወደ አንዱ ሃገር አልፌ፣ ቢያልፍልኝ እመርጣለሁ እያለ ነባራዊው ሁኔታ ከዚህ አይሻለኝም ብሎ መሰደድን ከመረጠ፣ ለውጥ ያስፈልጋል። በመከራ የተገኘች ልጅ ተምራና ደክማ ከተመረቀች በኋላ ሥራ ለመቀጠር ስትሄድ ዘርሽ ምንድነው ከተባለች፣ ለውጥ ያስፈልጋል። በተመረቀበት ትምህርት ከሚያገለግልበት ቦታ በስህተት ነው፤ የተቀጠርከው ተብሎ ከተገፋ፣ ወይ ሥራውን እንዳይሠራ ከተደረገ፣ ለውጥ ያስፈልጋል። ሃሳብ፤ ያቀረብከው፣ የእኛን ዘር በመጥላት ነው፤ ተብሎ ወደ ወህኒ ከተጋዘ፣ ለውጥ ያስፈልጋል። ሰበብ ተፈልጎ፣ የዓይንህ ቀለም አላማረኝምና ወደዚህ ሃገር እንድትገባ አልተፈቀደልህም ከተባለ፣ ለውጥ ያስፈልጋል። የተሰበሰብከው እኛን ጠልተህ ነው ተብሎ በቆመጥ በየጊዜው ከተደበደበና ማስፈራሪያ በተደጋጋሚ ዜጋው ከደረሰበት፣ ለውጥ ያስፈልጋል። ፍትሐዊ ውሳኔ በፍርድ ሸንጎዎች ማግኘት ካልተቻለ፣ ለውጥ ያስፈልጋል። የሀብት ድልድሉ ኢፍትሐዊነት ቅጥ አጥቶና መስመር ስቶ አንድ ወገን ሁልጊዜ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስድ ከሆነና የጨረታ አሸናፊ ከተደረገ፣ ለውጥ ያስፈልጋል። የድንበር ኬላዎች ለአንድ የተወሰነ ዘር ብቻ ተፈቅዶ ሌላውን ሁሉ እያገለለ የሀገርን የገቢ አቅም ሽባ ካደረገ፣ ለውጥ ያስፈልጋል።
ለውጡ እንዲመጣ ምክንያት የሆኑት ውስጣዊና ውጫዊ ሁኔታዎች፣ ሲመቻቹ የማይቀረው ለውጥ እንዲወለድ ማገዝ የተገባ ነው። ለማስቀረት ጥረት ማድረግ ግን አደጋ ያስከትላል፤ አሁን ያለው የለውጥ አካሄድና ዕድገት እንዳይጨናገፍም በትግል መጠበቅ እጅግ አስፈላጊ ነው። ለማስጨንገፍ ወይም የዕድገቱን ውጤት የራስ ድል ለማድረግ ያለፈው አሮጌ ሃሳብ አርበኞች ጥረት ማድረጋቸው የማይቀር ነው። ቀስ በቀስም ሸርሽረው ወደቀደመው ስቃይ ዜጋውን መመለስ ግባቸው ነውና።
ስለዚህ ሃገራችን ባለፈው አንድ ዓመት የተቀዳጀቻቸውን በየመስኩ የተገኙ ለውጦችን መደገፍ ሰላምን መደገፍ መሆኑ መታወቅ አለበት። ለውጡን መደገፍ ፍትህን መደገፍ ነው፤ ለውጡን ማጠናከር እኩልነታችንን ማጎልበት ነው።
አዲሱ ትውልድ የእነዚህን የአሮጌ አመለካከት እስረኞችና የ60ዎቹ ዓመተምህረት ርዕዮት አቀንቃኞች ትርክት ሰምቶ መደናገር የለበትም። እነዚህ አሮጌ ዘቦች፣ ያልተገነዘቡት ነገር ቢኖር የርዕዮቱ ጠንሳሾች፣ ራሳቸው፣ ማርክስ፣ ኤንግልስና ሌኒን እንኳን፣ ዳግም ከሞት ቢነሱ (አያምጣቸውና)፣ ህዝቡን ይቅርታ መጠየቃቸው የማይቀር ነው። ምክንያቱም የሠሩት ሥራ ለሰው ልጆች እልቂትና መንፈሳዊ ድርቀት ቁልፍ ምክንያት በመሆኑና ካለሙት ይልቅ ያጠፉት እጅግ ብዙ እጅ መሆኑን መገንዘብ አያቅታቸውምና። ይሄ፣ ብቻ አይደለም በእነርሱ ስም የተነሱት ሰዎች ሁሉ ከሰብዓዊ ፍጡርነት ወደሚያስፈራ እንስሳዊ አውሬነት ተለውጠው ካላጠፉ የማይተኙ ተኩላዎች እየሆኑ በመገኘታቸውም መፀፀታቸው አይቀርም። አንዳንድ አውሬ ለረሃቡ ማስታገሻ ከአደነ በኋላ ይተዋል፤ ክፉ አውሬ ግን አድኖ ብቻ አይተውም በአደን ላይ አደን ያደርግና የገደለውን በየጥሻው ይቀብርና ይረሳዋል፤ ከሚፈልገው በላይ ወስዶ ያልተፈለገ ጥፋት ይፈጽማል።
በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ፣ ናቡከደናጾር ማርኮ ያመጣቸውን የቤተ መቅደስ የከበሩ ዕቃዎችን፣ ከመማረኩም በላይ በጣኦት ፊት፤ አቃልሎ በግብር ማቢያ አዳራሾቹ ውስጥ በማሳየቱ የተቆጣው እግዚአብሔር “ማኔ ቴቄልፋሬስ” ብሎ ከወጣበት አወረደው፣ ከዙፋኑ ወደ ማንምነት አስኬደውና ለሰባት ዓመት እንደ እንስሳ ሣር እንዲግጥ፣ አደረገው። ለዚህ ምክንያቱ እብሪቱ ነው። የማን አህሎኝነት ትዕቢቱ ነው። መሪዎች በድርጊታቸው ጭካኔ ብቻ ሳይሆን በተልካሻውና ነውረኛ ሃሳባቸውም ከወንበራቸው ይወገዳሉ። አንድም በማስተዋል ለውጡን በውስጣቸው እስካላመጡ አለዚያም ለዋጭ እስኪታዘዝባቸው ድረስ በነበሩበት ይቆያሉ። ለውጥ ግን ወይ ከውስጥ አለበለዚያም ከውጭ መከሰቱ አይቀሬ ነው።
በኢትዮጵያ ያለፉትን 44 ዓመታት በስልጣን ላይ የቆዩት መሪዎች እግዚአብሔርን የማይፈሩ፣ ህዝብን የማያከብሩ፣ በጉልበታቸው የሚታመኑ፣ ገዳምን የሚደፍሩ፣ መነኮሳትን የሚያስነውሩ፣ የተገኘውን ጥሩና ጥሬ ሁሉ፣ ለእኔ የሚሉ፣ ይሉኝታ ቢሶች፣ ማህበራዊና መልካም ሃሳቦችን የሚያንኳስሱ፣ “የሌላ ዘር ነው” በሚሉት ሰው ሐሳብና ንብረት ላይ የጨከኑ፣ የህዝብን ዕንባ የዙፋናቸው መደላድል ያደረጉ ነበሩ። በህዝቡ ስም እየማሉ፣ ህዝብን በውሸት ተስፋ እያማለሉ፣ መልሰው ህዝቡን የሚያቆስሉ ነበሩ። ለዚህ ነው፤ ህዝብ የተንገሸገሸውና ለለውጥ ምክንያት የሆነው።
ለውጡን ናፍቆና መስዋእት ሆኖ ማምጣት አንዱ ነገር ሆኖ፣ ለውጡን ሊጠብቀው ካልቻለ፣ ለማያባራ መፈናቀልና ላልተለመደ ስደት መጋለጡ ብቻ አይደለም ፤ ክፉዎቹ ቀንበራቸውን በዘግናኝ ሁኔታ በመጫን ያሣሠበ ብቻ ሳይሆን “ሊያስብ ይችላል”፤ የተባለ ሁሉ ማረፊያው በትንሹ ቂሊንጦ ካለዚያም አድራሻው ቀልጦ ነው የሚቀረው። ምክንያቱም ለመግደል በቂ ምክንያት ስላገኙና ጠላት ስለሆነ ብቻ ሳይሆን የጠረጠሩት ሰው ደጋፊ አለመሆኑ ብቻ በራሱ “በቂ” ነው። የብዙ ንጹሐን ዜጎችም ደም ደመ-ከልብ የሆነው ለዚህ ነው። ክስ ካቀረቡበት ሰው ጥፋት ባያገኙም ከዘመዱ ይበደሩለታል።
ሴረኞቹ ፖለቲከኞች ባለፉት ሦስትና አራት አሰርት ዓመታት፣ የሚፈልጉትን ለማግኘት የማይፈለግ ነገር በማድረግ አሳይተውናል። ገድለው በሌላ ማሳበብ ፤ አፍርሰው በድንገት ነው በማለት ማስመሰል፤ አቃጥለው ሰበቡን በኤሌክትሪክ በማላከክ፣ አቁስለው ሆስፒታል በማሳከምና “በማስተዛዘን”፣ ክስ አቅርበው ወንጀል ፍለጋ በመማሰን ለረዥም ጊዜ በእስር በማማቀቅ፤ ተክነውበታል።
ታዲያ ይህንን ያወቀ ሰው፣ ሰው በዘሩ የሚሰፈርበት ያ-ጊዜ፣ ጨለምተኛ አስተሳሰብ የነገሠበት ያ-ዘመን፣ – ፍርሐት ያጠላበት ያ-የጨለማ ጊዜ፣ እንዳይመለስ መጠበቅና ተግቶ መቆም ይጠበቅበታል።
ለውጡ፣ በማያቋርጥ ወጀብ እየታጀበ ሲጓዝ የሚያመጣው ውጤት አለ፤ ለውጥ ሲቆም ነው መፍራት፤ ሲለዝብ ነው፤ መጠንቀቅ ያለብን፤ እንጂ ሲራመድማ መልካም ነው። አንድን ትልቅ ጎፈሬ፣ እያበጠርነው በቆየን ቁጥር የተሳሰረው እየለቀቀ፣ የተያያዘው እየተፍታታ፣ ጫፉ ላይ ያለው መንታነት እየተላቀቀ ይሄድ ይሄድና ማበጠሪያው ሲገባበት እንደልቡ ማለፍ ይጀምራል። ለውጥን እንዲህ ብናየው አሁን የለውጡ ጎፈሬ ክፉኛ እየተበጠረ ያለበት ዘመን ላይ ስላለን የሚነጨውና የሚነቀለው፣ የሚያመውና የሚቧጥጠው ነገር ይኖራል። እዚህና እዚያ ያሉት የጸጉሩ ያልተበጠረ ክፍል መንገራገጮች በጊዜ ውስጥ እየሰከኑና እየለዘቡ እንደሚሄዱ ሁሉ፣ ለውጡ እነርሱንም እየጎበኘና እየሰከነ ይሄዳል። ያኔም በምድሪቱ መረጋጋት ይሰፍናል።
ለለውጥ ስኬት ደንቃራዎች መኖራቸው የጉዞው ተገቢ አካል ነው ስንል፣ የሚያጋጥሙ እንቅፋቶች አሉ ማለታችን ነው፤ ግን አንድ ፀሐፊ እንዳለው፣ “ካልደፈረሰ አይጠራም” በሚል ብሂል ማደፍረስ ለውሃ እንጂ ለህዝብ አይሠራም። መደፍረስ ውሃውን በቆይታ ማጥራቱ እውነት ነው፤ ለህዝብ ግን ማደፍረስ፤ የከበረውን የሰውን ልጅ ነፍስ ይናጠቃልና አሳሳቢ ነው። የለውጡን እንቅስቃሴ የማይደግፉት ወገኖች እንቅፋቱንና ምሬቱን በመፍጠርና የተፈጠረውንም ጥቃቅን ችግር በማጉላት እርሱንም በፕሮፓጋንዳ በማጀብ የተካኑ ናቸው። ስለዚህ “የበላችው ያገሳታል ፣ በላይ በላዩ ያጎርሳታል“ እንዲሉ፤ በቅሬታ ላይ ቅሬታን በማከል ለውጡን በአላስፈላጊ ነውጥ እንዲደፈርስ ያደርጋሉ።
ነውጥና እሳት አንድ ነው፤ እንዳይፈጠር ሳይሆን መጣጣር፣ ከተፈጠረ በኋላ እንዴት ቢይዙት ይመረጣል በሚለው ላይ መምከር ብልህነት ነው። በብልሃት ያልተያዘ ለውጥ ለአደናቃፊዎች ጥሩ መሳሪያ ነው።
ቤተ-እምነቶች ይህንን ለውጥ በጽኑ መደገፍ አለባቸው። ይህን የምለው ከስሜት ተነስቼ ሳይሆን በእምነት አይቼ ነው። ምንም እንኳን እምነት እንደ አማኙ ደረጃ እና የእይታ አድማስ ልክ የሚታይ ቢሆንም ከትናንቱ ዛሬ፣ ከዛሬው ነገ የተሻለ እንደሚሆን ቅንጣት ታህል ጥርጣሬ የለኝም።
አንድ ሰው ወደ ነፃው ኑሮ ትመጣለህን? ብለው ሲጠይቁት ዛሬን ጭኜው ልምጣ ወይስ እንዴት ላድርግ ብሎ ሲላቸው፣ ያልገባቸው መስለው እኛ የምንፈልገው ለነገ ሰላም እንድትኖር ነው፤ ሲሉ መልሰውለታል። አንዳንዶች ካለፈው የዞረ ድምራቸው ጋር እየዞሩ ፤ በዘር ፖለቲካ የዛር አዙሪት ውስጥ ቆመው ስለ እኩልነት ሊያወሩ ይፈልጋሉ። ለነገሩ በደቡብ አፍሪካ የነበረው የአፓርታይድ ስርዓትም “ እኩልነት በልዩነት “ ነበረ ፤ የሚለው።
የነጭ ብቻ ትምህርት ቤት፣ የነጭ ብቻ ባቡር ትራንስፖርት ፣ የነጭ ብቻ ሆቴል፤ የነጭ ብቻ የመዋኛ ገንዳና የነጭ ብቻ የመኖሪያ ሰፈር ነበራቸው። በእዚያ ዝር ሲል የተገኘ ደቡብ አፍሪካዊ “ጥቁር“ እጣው መገደልና መታሰር ብቻ ነበረ። የሀገሪቱን ሀብት 85 ከመቶ መሬቱን፣ ባንኩን፣ እርሻውን፣ ሕንፃውን፣ ቴከኖሎጂውንና ዕውቀቱን ሁሉ ጨብጠው “እኩልነት በልዩነት” ነበረ የሚሉት።
ጥቁሩ፣ ደቡብ አፍሪካዊ የተሻለ ትምህርት ተከልክሎ፣ ጤና ጥበቃ ተከልክሎ፣ ብልጽግና ተከልክሎ፣ ብቻውን ክብሪት ክብሪት በሚያካክሉ ቤቶችና ቆሻሻ መጣያ በሚመስሉ አዳፋ መንደሮች (Shanty town or Ghettos ይባሉ ነበር) እየኖረ መብቱን ሲጠይቅ ደግሞ “ህግ ጥሰሃል፤ ህገ – መንግሥት ሸርሽረሃል” ተብሎ ይጋዝና ይገደል ነበረ።
የእኛውም ከዚህ ያልተለየ ነው፤ ልዩነቱ እዚህ ተመሳሳይ ትምህርት ቤት መማርና ሥራ ለመቀጠር ሲያመለክት ዘሩ/ሯ መቆጠሩ ነው። እነዚያ ነጮችና ጥቁሮች ሲሆኑ እኛ ደግሞ “ጠያይምና ጥቁር ልዩ ልዩዎች” ነን፤ ኢትዮጵያውያን ። በ”ልዩነት አንድነት” የሚል የዳቦ ስም ሰጥተው መቼም ግን አንድ እንዳንሆን አበክረው ሌት ተቀን ሲሠሩብን ኖረዋል።
አሁን ግን የመጣው ለውጥ ከመንደራዊነት ወጥተን የጋራ ሃገራዊ ራዕይ ዘርግተን በተሳካ መንገድ በእኩልነት ምዕራፍ ላይ እንድንጓዝ የሚያደርግ ዜጎች በሃገራቸው ጉዳይ ላይ እኩል መብትና ስልጣን እንዳላቸው ተገንዝበው በፍቅር የሚኖሩበትን አውድ ለመፍጠር የሚያስችል ጥረት እየተካሄደ ነው። ይህንን ጥረት ማገዝ ከሚከተሉት የብሶት ግጥሞችም ያድናል።
ስለዚህ ለውጥ ሲመጣ የያዙትን ያስጣላቸው፣ ሊያዝኑ ይችላሉ እንጂ፣ ያልያዙትን የጨበጡ፡ የራቃቸውን የቀረቡ፣ የተሸፈነው የተገለጠላቸው፣ ብዙዎች ግን በበለጠ ንቃት መብዛትና መደመር ይገባቸዋል።
እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲፈጠር፣ “ሰዉ ምን ሊያደርግ ይገባል?” የሚለውን ጥያቄ መመለስ የተገባ ይመስለኛል። በቅድሚያ “ጦር ከፈታው፣ ወሬ የፈታው” ይባላልና፤ ለሚወሩ ውዥንብራም አሉባልታዎችና የማህበራዊ ድረ- ገጽ ዘመቻዎች ጆሮ አለመስጠት፤ አለመስጠት ብቻ ሳይሆን ክፉ ሲያወሩ፣ ያወሩትን ክፉ አለመድገም ጨዋነት ነውና፤ በመተው መዝጋት ይገባል።
ክፉዎችንም መጽሐፍ ቅዱስ ሲገልጣቸው እንዲህ ይላቸዋል፤ “ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥ በትዕቢት የተነፉ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤(2ኛ ጢሞ 3፡ 4)”
ስለዚህ፣ የክፉዎች የድርጊት መሳሪያ አለመሆን “ከለማበት የተጋባበት” ይበልጣል፤ ይባላልና ራስን መጠበቅ መልካም ነው። ሐሰተኞች ናቸውና በሚያባብሉ “ማስረጃ የሌላቸው” መረጃዎችና፣ የብሶት ወሬዎች ያታልላሉ፤ ስለዚህ ነቅቶ በእነርሱ አድማ ላይ አለመሳተፍ፣ እውነት እንኳን የሆነ ችግር ሲያጋጥምም፣ ጠቃሚ ነው ? መልካምስ ነው ? ለሰላም እና መረጋጋት ይረዳል ወይ ብሎ፣ ከማዛመት መቆጠብም አርቆ አሳቢነት ነው።
በሀገራችን እየሆነ ያለው ሰላማዊ ለውጥ ዕርምጃውንና የጉዞ ምቱን ፣ ጠብቆ እንዲጓዝ ተገቢውን ድጋፍ ሳይዘገይም ሳይፈጥንም በማቅረብ አጋርነትን ማሳየት ከሁሉም ቅን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን አፍቃሪ ዜጎች ይጠበቃል።
በመጨረሻም ለውጡ የእራት ግብዣ አለመሆኑን በመገንዘብ፣ በለውጥ-ጠሎች ነውጥና ሸፍጥ አቅጣጫውን እንዲለውጥና በለውጡ ኃይሎች ላይ ህዝቡ ጥርጣሬ እንዲያድርበት የሚደረገውን ክፋት በትዕግስትና በማስተዋል በማክሸፍ ፣ በየጊዜው ለመልካም ሥራ እገዛችንን ማሳየት ብልህነት ነው፤ ቢያንስ ቢያንስ ከክፉዎች ጋር በሃሳብም በድርጊትም አለመተባበርና በጽሞና መቀመጥ አስተዋይነትም ነው።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ!!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሀምሌ 13/2011
አገልጋይ ዮናታን አክሊሉ